ዛሬ በደረስንበት 21ኛው ክፍለዘመን በአለማችን የሚገኘው ሕዝብ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቹ በተከበሩበት ሁኔታ መመራት ይሻል፡፡ በዚህ ዘመን አምባገነን መሪዎችና መንግስታት በየትኛውም መስፈርት ስልጣን ላይ የመቆየት እድል የላቸውም፡፡ በዚህ ረገድ በቅርብ አመታት ውስጥ የማይደፈሩና እንደ ፈርኦን ይመለኩ የነበሩ አምባገነን መንግስታት በህዝባዊ ማዕበል ተጥለቅልቀውና ተንጠው መቀመቅ ሲወርዱ የአለም ህዝብ ሁሉ አስተውሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት የዲሞክራሲና የነፃነት ጥየቄ ከዳቦ ጥያቄ ይበልጥ አንገብጋቢ እየሆነ መጥቷል፡፡
የአለማችን አንድ አካል የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ የዘመናት የስልጣኔ ጉዞዋ የምድራችን ቁንጮ የታሪክ ባለቤት ያደርጋታል፡፡ በየዘመናቱ የተነሱ ገዢዎቻችን ሲጭኑብን የቆዩት የአገዛዝ ቀንበር ወገባችንን ቢያጎብጠውም የኢትዮጵያ አንድነትና ሉኣላዊነት ፍፁም ሳይሸራረፍ ተጠብቆ ዘመን እንዲሻገርና ለትውልድ እንዲተላለፍ የማይሻ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡
ወታደራዊው ደርግ ከሥልጣን በተወገደ ማግስት ዲሞክራሲና ነፃነት የሰፈነበት የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩባትን ኢትዮጵያ ለማየት ያልጓጓ ኢትዮጵያዊ አልነበረም፡፡ ህልማችን በእውነት ሳይፈታ ቀረ፣ ተስፋ ያደረግነው ነገር ከዓመት ዓመት እየጨለመ መጣ፡፡ ኢህአዴግ ባለፉት 23 ዓመታት የምኒሊክን ቤተመንግስት ቢቆጣጠርም የአገርን ህልውና ከመጠበቅና የህዝብ እንባን ከማበስ ይልቅ ዜጎችን መውጪያ መግቢያእያሳጣና የመከራን ገፈት እያስጨለጠ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡ ስደቱ፣ እንግልቱ፣ ግርፋቱ፣ እስራቱ፣ ግድያው፣ አፈናው፣ ስቃዩ ከመቀነስ ይልቅ በየጊዜው እየከፋ ይገኛል፡፡ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ይህን ቀንበር ለመስበር እንደ መርፌ ቀዳዳ በጠበበው የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ እየተንቀሳቀሰ በመላው አገሪቱ ህዝብን ለትግል እያሰለፈ ይገኛል፡፡
ይህን እልህ አስጨራሽ ትግል ለመምራት ትልቁ የስልጣን አካል የሆነው ይህ ጠቅላላ ጉባኤ ታህሳስ 19 እና 20 / 2006 ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት ባደረገው ከፍተኛ ስብሰባ አያሌ አገራዊ ጉዳዮችን በማንሳት ተወያይቷል፡፡ የፓርቲውን ምክር ቤት ፣ የሥራ አስፈፃሚና የኦዲት ኮሚሽንን ሪፖርት በማድመጥ ጠንካራ ውይይት አካሂዷል፡፡
በመጨረሻም የአገልግሎት ዘመናቸውን ባጠናቀቁት የፓርቲው ፕሬዚደንት የተከበሩ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ምትክ የተከበሩ ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራውን ፍፁም ግልፅና ዲሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ ተክቷል፡፡ የፓርቲውን ብሔራዊ ምክር ቤት እና የኦዲት ኮሚሽን አባላትንም በመምረጥ ጉባኤው ተጠናቋል፡፡
አባላቱ በጉባኤው ማጠናቀቂያ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የሚከተለውን የአቋም መግለጫና ውሳኔ በማሳለፍ ተጠናቋል፡፡
1ኛ. ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በአገሪቱ የሚደረገውን የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ለማኮላሸት ነጋ ጠባ የሚያጠነጠነው እኩይ ሴራ የህዝቡን ስሜት ወደ ሌላ አቅጣጫ እና ጥግ እየገፋው ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ፓርቲያችን አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በጀመረው የሰላማዊ ትግል ጉዞ የኢትዮጵያን ህዝብ የስልጣን ባለመብት ለማድረግ እስከመጨረሻው እንጥፍጣፊ በጥብቅ መታገል እንደሚኖርበት ይታመናል፡፡ በመሆኑም እኛ ከመላው አገሪቱ በዚህ ጉባኤ ላይ የታደምን የፓርቲ አባላትና አመራሮች ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ ለሰላማዊ ትግሉ ቁርጠኛ መሆናችንን እናረጋግጣለን፡፡
2ኛ. አምባገነኑ የኢህአዴግ መንግስት የፓርቲያችንን እንቅስቃሴዎች እግር በእግር እየተከታተለና በሀሰት ውንጀላ በማጠልሸት በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳናገኝ ጠቅልሎ በያዘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሰፊ የሆነ አፍራሽ ተልዕኮን እያስተጋባ ይገኛል፡፡ይህ ጉዳይ ህገ መንግስቱ ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ያመቻቸውን መንገድ ሙሉ ለሙሉ የሚጠቅም ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አገር እየመራሁኝ ነው የሚለው ኢህአዴግ ፓርቲያችንን ከሽብር ድርጊት ከአሸባሪዎች ጋር ለማቆራኘት የሚያደርገውን እኩይ ሴራ አጥብቀን እናወግዛለን፡፡
3ኛ. በዚህ ልዩ ጉባኤ ወቅት በአካል በመቅረብ በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ካድሬዎችና ታጣቂዎች በሰሜን ጎንደር ዳባት ወረዳ አርቡር ቀበሌ ነዋሪ የሆነችው የ 8 ዓመቷ ህፃን ስለእናት ማስረሻ ጥላሁን የደረሰባትን እጅግ ዘግናኝና ሰቅጣጭ የአካል ጉዳትአሳይታለች፣ ሁኔታው የጉባኤውን አባላት ክፉኛ ያስቆጣ ሆኗል፡፡ አባቷን እና የቤት እንስሳትን በጥይት ገድለው ህፃን ስለእናትን በጥይት አረር እጇን የቆረጡ እኝህ እኩያን ወንጀለኞች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን፡፡
4ኛ. የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የአመራር ዘመን አገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ እጅግ የተዋረደችበትና ሉኣላዊነቷ የተደፈረበት ወቅት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ዜጎች የከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰት ይደርስባቸዋል፣ይታሰራሉ፣ ይደበደባሉ፣ ይገደላሉ፣ ይሰደዳሉ ወዘተርፈ፡፡
ለስደት በተዳረጉባቸው አገራትም ዜጎቻችን በግፍ ሲገደሉና ሲደበደቡ እያን ነው፡፡ በቅርቡ በሳውዲ አረቢያና ሰሞኑን ደግሞ በደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሰው ሞትና ስቃይ የእያንዳንዳችንን ልብ የሰበረ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ተጠያቂው ኢህአዴግ ነው፡፡
በመሆኑም ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በመላው ዓለም እንደ ወንዝ ዳር አሸዋ ተበትነው ለሚንገላቱ ዜጎች ጉዳይ በአፅንኦት እየተከታተለ እንዲታደግና የመንግስትነት ግዴታውን ባግባቡ እንዲወጣ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡
5ኛ. በአሁኑ ወቅት የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ጥቂት ሹማምንት እጆቻቸውን እያስረዘሙ የአገርን ሀብት እየዘረፉ ናቸው፣ ሥርዓቱ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ በሙስና የተጨማለቀ መሆኑን እየተጋለጠ ነው፡፡ ዜጎች ዛሬ የዕለት ጉርሳቸውን አጥተው ሲራቡና ሲጠሙ፣ወጣቶች የሥራ ዕድል ተነፍጓቸው በአሳፋሪ ሁኔታ ከአገር ሲሰደዱ፣ የኑሮ ውድነቱ ትውልዱን ግራ እያጋባ ነው፣ ህዝቡ ፍትህና መልካም አስተዳደር በማጣት ነጋ ጠባ የዜግነቱ ጉዳይ ጥያቄ በፈጠረበት ሁኔታ የነገዋን ኃያልና የበለፀገች ኢትዮጵያን አይደለም ማየት ይቅርና የህልውናዋ ጉዳይም አጣብቂኝ ውስጥ የገባበት ሰዓት ላይ ደርሰናል፡፡ በአገሪቱም አስከፊ ብሔራዊ ቀውስ ይፈጠራል ብለን እንሰጋለን፡፡
ከዚህ አንፃር ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብሔራዊ መግባባትን የሚያሰፍን መድረክ እንዲያዘጋጅ አበክረን እንጠይቃለን፡፡
6ኛ. ኢቴቪ የኢትዮጵያ ሕዝብ ልሳንነቱን እርግፍ አድርጎ በመተው የገዢው ፓርቲ አገልጋይ መሆኑን የትኛውም ኢትዮጵዊ የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት ፕሮግራም ላይ በመላው አገሪቱ ሰላማዊ ሰልፍ እና ስብሰባዎችን በጠራበት ወቅት ኢቴቪ ጅሃዳዊ ሃረካት ፊልምን አቀናብሮ ፓርቲያችንን ከአሸባሪዎች ተርታ ሲፈርጀው ቆይቷል፡፡ ሌላው ቀርቶ ጉባኤያችንን ባከናወንበት ታህሳስ 19 ምሽት ኢቴቪ ያንኑ ፊልም በድጋሚ በማቅረብ አንድነት ፓርቲ በደሴ፣ በጎንደር፣ በአርባምንጭ፣ በጂንካ፣ በባህርዳር ወዘተ ካደረጋቸው ሰላማዊ ሰልፎችና በፓርላማ የፓርቲያችን ብቸኛው ተወካይ ስለ ፀረ ሽብር ህጉ አፋኝነት ያነሱትን ሀሳብ ከሽብር ጋር በማያያዝ ከንቱ ዲስኩር ሲያቀርብ ተመልክተናል፡፡ ኢቴቪ የአንድ ድርጅት መሆኑ አብቅቶ የኢትዮጵያን ሕዝብ ዋይታና ብሶት የሚያስተጋባ ግዙፍ የብዙሃን መገናኛ ድርጅት እንዲሆን አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡
7ኛ. ፓርቲያችን አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ከተመሠረተበት ዕለት ጀምሮ ከኢህአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ ጋር በብርቱ እየተናነቀ መሪዎቹ እየታሰሩበትና እየተደበደቡበት መዋቅሩን በመላው አገሪቱ ዘርግቶ አመርቂ የትግል ውጤት እያመጣ ቢሆንም የኢትዮጵያን ሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ የሚቀረው ጉዞ እጅግ ረጅም ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ፓርቲያችን ይህ ታላቅ ጉባኤ የወሰናቸውን ውሳኔዎችና መርሃ ግብሮች በአግባቡ እየተወጣ ታሪክ ይሰራ ዘንድ አጥብቀን እናስገነዝባለን፡፡
በቀጣይ ዓመታት ፓርቲውን በበላይነት እንዲመሩ የተመረጡ አመራሮች ከመቼውም ግዜ በበለጠ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ከአደራ ጭምር እናሳስባለን፡፡
No comments:
Post a Comment