Saturday, February 15, 2014

የቆሞ ቀርነት ፖለቲካ!

በመስከረም አበራ

ይህን ርዕስ ከዚህ በፊት አንስቸው ነበር፡፡ በወቅቱም “ቆሞ ቀርነት” የሚለውን ቃል አንድ ታሪካዊ ሁነት ላይ ብቻ በመመርኮዝ የፖለቲካ ትንታኔ የመስጠትን ስህተት ለማመላከት እንደሆነ ገልጨ ነበር፡፡ የቃሉ ትርጓሜ ለዚህ ፅሁፍም ተመሳሳይ እንደሆነ እየገለፅኩ ወደ ዋናው ሃሳቡ አልፋለሁ፡፡ ርዕሱን ደግሜ እንዳነሳው ያስገደደኝ አንድን ታሪካዊ ክስተትን ብቻ ተመርኩዞ፣ ያንኑም በቅጡ ሳያስተውሉ አደገኛ ማጠቃለያ የመስጠቱ ነገር እየበዛ በመምጣቱ ነው፡፡

የዘውዱ ዘመን ቆሞ ቀሮች!

በፊውዳሊዝም ፖለቲካዊ ዘይቤ የኖረው የሃገራችን ዘውዳዊ መንግስት የእድሜውን ርዝመት ያህል ሃገሪቱን ውጥንቅጥ ውስጥ ከቶ የኖረ ነው፡፡ ከዚህ ዘመን ውስጥ ደግሞ “ዘመነ መሳፍንት” ተብሎ የሚጠራው ከ 1769-1855 የቆየው ዘመን የሃገሪቱን ህልውና ፈተና ውስጥ ከቶ የነበረ የጦርነት እና የእልቂት ዘመን ነበር፡፡ የዘውዳዊ አገዛዙ ዘመን መደወሪያው ፊውዳሊዝም፣ ነገስታቱም ከቤተ-ክህነት ያልዘለለ ግንዛቤ የነበራቸው እንደመሆኑ በዘመኑ ስለጠፋው ጥፋት በዚህ ዘመን የንቃት ደረጃላይ ሆኖ መሪዎቹን ከመውቀስ ይልቅ በነበራቸው ውሱን ግንዛቤ ለሃገራቸው ላበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅና መስጠቱ ተሻይ ይመስለኛል፡፡ በተለይ የነገስታቱ የሃገር ፍቅር ከዙፋን አውርዶ እንደተራ ወታደር እስከመዋጋት የሚያደርስ ነበርና መወደስ አይበዛበትም፡፡

በአንፃሩ በዛሬ የንቃት ደረጃ ሲፈተሸ ጥፋት የሚባሉ በርካታ እንከኖች እንደነበሩባቸው የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ ይህ የሚያግባባውም ትናንትን በዛሬ ሚዛን መመዘኑ ትክክል ነው ተብሎ ከታሰበ ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ ‘በሞተ ስርዓት ላይ ከዚህ በላይ ጊዜ ማጥፋት አይገባም’ እንዲሉ ፕሮፌሰር መስፍን ነገስታቱን እነሱ ካለፉ ከስንት አመት በኋላ ወደ ጠረጴዛ የመጣውን የሰብአዊ መብት አከባበር ፍልስፍና እያነሱ እሱን በመተላለፍ ማብጠልጠል እልፍ ማይል ወደ ኋላ ተጉዞ ቆሞ መቅረት ይመስለኛል፡፡ አሁን አሁን ብቅ የሚሉ ጦማሪያን ደግሞ እጃቸውን የሚያፍታቱት እነዚህን ነገስታት በማብጠልጠል ነው፡፡ ነገሩ በአመዛኙ ከኢህአዴግ ወደ ስልጣን መምጣት ጋር ሃገሪቱን ከወረሳት የዘረኝነት አባዜ የሚነሳ ነው፡፡ ለዚህ ማመሳከሪያው የእነዚህ ጦማሪን ትችት ፍላፃ የሚወረወረው ከነሱ ብሄር ባልሆኑ ነገስታት ላይ ሲሆን ’ከእኛወገን’ የሚሏቸውን ነገስታት ደግሞ በፊውዳላዊ ስርአት ውስጥ ዲሞክራት፣ ብፁዕ እና ነብር በጥፊ የሚገድሉ ጀግኖች ለማድረግ መፋተራቸው ነው፡፡ ነገሩ ባስ ሲል ደግሞ የእኛ ሰፈሩ ባላምባራስ እንትና ከእንትን ምንጭ ማዞሪያ መለስ የተመለመሉ ወታደሮችን ብቻ ይዘው ጣልያንን ስላርበደበዱ የተራራማውን እና ቆላማውን ምድር ህዝብ ይዘው ካሸነፉት አፄ እንትና አንሰው ምክትል ጀግና መደረግ የለባቸውም እየተባለ ቁም ነገር እንደያዘ ሰው በምሬት ክርክር ይገጠማል፡፡ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ባልተነሳበት፣ የሰው ልጅን ገበያ አውጥቶ መሸጥ ሽምብራ እንደመሸጥ ነውር በሌለው ዘመን አፄ እንትና ባሪያ እንዲሸጥ ፈቅዶ ነበርና የነፃነት አባት ሳይሆን ሃገር ከሃዲ ነው የሚል ክርክር በዚችው መፅሄት ላይ ያነበብነው “ትንታኔ” ነው:: ለሃገራቸው ክብር ሲሉ ከሃገር ዳርቻ በእግር በፈረስ ተጉዘው በጣምራ ክንዳቸው ጠላትን ድል የመቱ ወንድማማቾችን ለመነጣጠል “አንኮበራዊ” እና “አክሱማዊ” አርበኞች የሚል ስራ-ፈት ሽንሸናም እንደ ደህና ነገር እየተወሳ ይገኛል፡፡ ለአንባቢ ቁምነገር እንደሚያቀብል ሰው ብዕር አንስተው እንደ እየሩሳሌም ቆነጃጅት ‘አክሱማዊያን እልፍ ገደሉ አንኮበሮች ግን ሺ ብቻ’ እያሉ ለሰፈራቸው ሰዎች ለመዝፈንም ይሞክራቸዋል፡፡ ይህ ሲባል የተረሳው (እና ገዛኽኝ ፀጋው የተባለው ፀሃፊ በዚሁ መፅሄት በደንብ ያስቀመጠው)ጉዳይ ‘አንኮበራዊውም’ ሆነ ‘አክሱማዊው’ ገዥ ያደረገውን ያደረገው ግዛቱን አስፋፍቶ ከተገዥዎቹ የሚሰበስበውን አመታዊ ግብር መጠን ለማሳደግ እንጂ ‘ከአንኮበራዊ’ እና ‘ከአክሱማዊ’ ማን ይጀግናል ለሚለው መልስ የሚሆን ነጥብ አስመዝግበው አልፈው፣ እኛ የልጅ ልጆቻቸው ደግሞ እንድንተነትነው አልነበረም፡፡



የቆሞ ቀር ፖለቲከኝነት አባዜያችን የሃገር ድንበር ከቀይ ባህር ማዶ ይሆን ዘንድ የተዋደቁ እንደ አሉላ አባነጋ አይነት ሃገር ወዳዶችን አስበውት በማያውቁት መልኩ የገድላቸውን አኩሪነት እና የጀግኖቹን ወገንተኝነት በተወለዱበት መንደር ብቻ ተወስኖ የሚቀር አስመስሎ ከማሰብ አልፎ እስከ መፃፍ እየተደረሰ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ቆሞቀርነት ብቻ ሳይሆን በአስፈሪ ሁኔታ እየተዋሃደን ያለው የዘረኝነት እና የመለያየት አባዜያችን ያመጣው ልክፍት ነው፡፡ ከዚህ በተዋጀ ሁኔታ ከታሰበ ግን አሉላም የሁላችንም ጀግና ናቸው፣ዶግአሊም ሆነ አድዋ የኢትዮጵያዊ ሁሉ ድል ነው፤አሉላ ቀርቶ ዘርአይደረስም ስለኢትዮጵያ የተጋደሉ የኢትዮጵያዊ ሁሉ ጀግና ናቸው፡፡

ከዚህ ባፈነገጠ መልኩ አሉላን የትግራዊያን ብቻ የጀግንነት ምልክት አድገው ሊያቀርቡ ለሚሞክሩ ተከራካሪዎች መቅረብ ያለባቸው ወሳኝ ጥቄዎች አሉ፡፡ እነዚህ የወንዝ ልጅ ነን ባዮች በጀግናው አሉላ አባነጋ ስም ተሰይሞ የነበረው ትምህርትቤት በመለስ ዜናዊ ስም ሲቀየር ምነው ይህ ተቆርቋሪነታቸው ለመለስ ሌላ ትምህርት ቤት ይሰራ እንጂ የመለስን ስም ለመስቀል የራስ አሉላ ስም መውረድ የለበትም ለማለት አላስቻላቸውም? ወይስ የአንድ ትግራዊ ስም በሌላ ትግራዊ ስም መተካቱ ችግር የለውም? እርግጥ በዘረኝነት አዙሪት ለተተበተበ ሰው ይህ ያሳምን ይሆናል ተገቢ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ ከወንድሞቻቸው ጋር ሲጋደሉ ለሞቱ የህወሃት ሰማዕታት ስንት ነዋይ የፈሰሰበት ሃውልት ሲሰራ የራስ አሉላ አፅም ያረፈበት ቦታ ይህ ነው የሚባል ምልክት የሌለው መሆኑ፣ ይህ ሳያንስ ምፅዋ ላይ ደርግ ያሰራው ሃውልታቸው ሲፈርስ ከአንኮበራዊያን ጋር ለማወዳደር ሲሆን የሚፈጥኑ የወንዝ ልጅ ነን ባዮች ተቆርቋሪነታቸው ምንም ያላናገራቸው ለምን ይሆን? እዚህ ላይ በዚህ ጉዳይ ላይ ድምፃቸውን ማሰማት ያለባቸው ከትግራይ የሆኑ ወገኖች ብቻ ናቸው ለማለት እንዳልሆነ ልብ ይባልልኝ፡፡ ምክንቱም እንደ አፄ ምኒሊክ፣አሉላአባነጋ፣ አብዲሳ አጋ፣ ሙሉጌታ ቡሊ(በስማአቸው ይጠራ የነበረው የሆለታው የጦር ትምህርት ቤት አሁን በሃየሎም አርአያ ስም ተቀይሯል)፣ በላይ ዘለቀ አይነት የሃገር ባለውለታዎች ስም ተገቢውን ክብር ማግኘት ያለማግኘት ጉዳይ ሁላችንንም የሚመለከት ነው፡፡ ለዚህ ወደ ሰዎቹ የትውል መንደር መሮጥ አያስፈልግም፤ቢያንስ ነጭ ወራሪን አንበርክከው ጥቁር አፍሪካዊ ወገኖቻችን ያላገኙትን ክብር በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ለተፈጠርን ሁሉ አጎናፅፈውናልና፡፡

በትግራዊነት እና አንኮበራዊነት ላይ በሚያጠነጥን ስንዝሮ ትንታኔ ፍቅር የወደቁ ተንታኞች ሌላው መለያ የፈለቁበትን ትግራዊነት ለማወደስ እና አንኮበራዊነት ብለው የሰየሙትን አካል ለማንኳሰስ ከአፄምኒልክ ዘመን አለፍ ማለት አለመቻላቸው ነው፡፡ በእነሱ መንገድ ተጉዘን በሚገባቸው ቋንቋ እንነጋገር ከተባለ ወደ ዘመነ መሳፍንት መጓዝ ግድ ይላል፡፡ ወደዛ ከተኬደ ደግሞ በዘመኑ አሻንጉሊት መንግስታትን እየሾሙ፣ የሃገሪቱን ህልውና ማጥ ውስጥ የከተተ የረዥም ዘመን መተላለቅን ያመጡ፣ በሃገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁነታ የማዕከላዊ መንግስትን አቅም ያደቀቀ የአካባቢ አለቆች ጉልበት መፈርጠምን እየኮተኮቱ ያሳድጉ የነበሩት ሚካኤል ስሁል ትግራዊ ናቸውና የአፄ ምኒልክ ስም የሚገረፍበት የቆሞቀርነት ብዕር ለበቅ በዚህ ሰው ላይም ሊወርድ ነው፡፡ ከዛ እልፍ እንበል ከተባለ ደግሞ የእንግሊዝን ጦር እየመሩ ወንድማቸውን አፄ ቴወድሮስን ያስገደሉት ትግራዊው አፄ ዮሃንስ የመሆናቸው እውነት አፍጥጦ ይመጣል፡፡ ይህን ብለን ሳንጨርስ ደግሞ አፄ ዮሃንስ ከዙፋን ወርደው እንደ ተራ ወታደር ስለሃገራቸው ሊፋለሙ መተማ መገኘታቸውን፣ በዛውም ውድ ህይወታቸውን ማጣታቸውን ታሪክ ያስረዳናል፡፡ ይህን በሰማንበት ጆሮ ደግሞ የመቀሌው ራስ ሃይለስላሴ ጉግሳን የባንዳነት ታሪክ ማድመጣችን አይቀርም፡፡ ይህ መሰሉ የታሪክ ዥጉርጉር የሚያስረዳው ሰዎች በወለዱበት መንደር ምክንያት ጀግናም ሆነ ባንዳ ሊሆኑ እንደማይችሉ ነው፡፡ ይህን የሚወስነው ከትውልድ መንደር፣ከቋንቋ፣ ዘር ውጭ የሆኑ ብዙ ምክንያቶች ቢኖርም የዚህ ፅሁፍ አላማ ይህን ማብራራት ስላል ሆነ ለጊዜ አልገባበትም፡፡ ይልቅ የታሪክን ግራ ቀኝ ሳናስተውል ልክ ነው ባሉት መንገድ በፍፁም ልባቸው ለሃገራቸው ነፃነት በተዋደቁ ዋኖቻችን ላይ ዘረኝነታችንን በብዕራችን ግንፍላት ለመግለፅ ስንንደረደር የምናስተው ብዙ ይሆናልና ይህን መሰል ከፈፋይ ብዕር ይዘን ልንፅፍ ባንነሳ ደግ ነው፡፡ ይህ ማለት ቀደምቶቻችን ምንም ስህተት አልሰሩም እያልኩ አይደለም፡፡ ይልቅስ ወደኋላ መለስ ብለን የዋኖቻችንን ስራ ስንገመግም በሚዛናዊ ጭንቅላት፣ ከዘረኝነት በተዋጀ ጨዋ ብዕር፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለትንታኔ የሚበቃ የእውቀት ስንቅ ይዘን መሆን አለበት ለማለት ነው፡፡

በአፄ ምኒልክ ዘመን ቆሞ የመቅረቱ ነገር የኦሮሞ ህዝብን ከኢትዮጵያ እንገነጥላለን ይሄ እንዳይሆን ከተፈለገ የአሮሞ ህዝብ ጥያቄ የተመለሰባት ኢትዮጵያ መመስረት አለባት(ጥያቄ የሌለው ኢትዮጵያዊ ይኖር ይሆን?) በሚሉ የኦሮሞ ብሄርተኛ ልሂቃን ዘንድም ይስተዋላል፡፡ እነዚህኞቹ ከሚኒልክ ዘመን በፊት የህዝብ ቁጥር ማሻቀብ በፈጠረው የእርሻ እና ግጦሽ መሬት መሰል የተፈጥሮ ሃብቶች እጥረት ወደ ሰሜን ራያ ድረስ የራቀ ጉዞ አደርገው እንደ ነበረ፣ ይህ ጉዞዋቸው ደግሞ የወይራ ዝንጣፊ የያዘች እርግብ የምትመራው፣ አንድም ሰው ሳይሞት የተደረገ መስፋፋት እንዳልሆነ ቢያውቁትም ደግመው ማሰብ አይፈልጉም፡፡ ለምን ቢባል ይህን ማመን የአፄ ሚኒልክን የተስፋፊነት እንቅስቃሴ አሁን በሚራገበው መጠን ለማራገብ አቅም ያሳጣል፡፡ነገሩ በመስፋፋት ውስጥ ያለው ደም መፋሰስም የኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አምሮቶች ያመጡት በማንኛውም ተስፋፊ ሊከናወን የሚችል ሁነት እንጅ ሰውን በዘሩ ማጥቃትን ኢላማ ያደረገ ክስተት አለመሆኑን ያረጋግጣል፡፡ይህ መሰሉ የመስፋፋት ግስጋሴ ደግሞ የምርጫ ሳጥን ተይዞ የነባሮቹ ህዝቦች ፈቃደኝነት እየተጠየቀ የማይሆን እንደሆነ ወደ መካከለኛ ዘመን የሃገራችን ታሪክ ተጉዞ፣ በአፍሪካ ደረጃ እንኳን በታሪክ መጠነሰፊ መስፋፋት ነበር የሚባልልትን የኦሮሞ ህዝብ የመስፋፈት ታሪክ በወጉ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ይህ ግን ዘረኝነትን የተከናነበ ቆሞቀር ፖለቲካዊ ትንታኔን ሰምቶ ስሜቱ እንደገፋው የሚከተለውን ጄሌ ቁጥር ይቀንሳልና በዘር ፖለቲካ አቀንቃኞች ዘንድ አይፈለግም፡፡ በመሆኑም የኦሮሞ ህዝብን እና ማዕከላዊውን መንግስት ግንኙነት ፖለቲካዊ ታሪክ በአፄ ምኒልክ የስልጣን ዘመን ጀምሮ የመጣ ነው በማለት እዛው ላይ ቆሞ መቅረቱ በብሄሩ ልሂቃን ዘንድ በብዛት ይስተዋላል፡፡ይህ እንግዲህ ከላይ የተጠቀሰውን በአፍሪካ ደረጃ ሳይቀር በስፋቱ እና በወሰደው ጊዜ ርስዝማኔ በታላቅነቱ የሚታወቀውን የኦሮሞ ህዝብ ወደ ሰሜን መስፋፋት አውቆ የረሳ፣ በጎንደሪያን ነገስታት ቤተመንግስት የኦሮምኛ ቋንቋ መግባቢያ እስከመሆን ደርሶ የነበረበትን ሃቅ የካደ ክርክር ነው፡፡ ታሪክን በዚህ መልኩ በሚፈልጉት መንገድ መተንተኑ በህዝብ ነፃነት ስም መከረኛ ስልጣን ላይ ቂብ ብሎ ተረኛ አምባገነን ለመሆን ነው፡፡ በእውነት ለህዝብ ነፃነት ነው ከተባለ ደግሞ ትግሉ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ታሪክ ሳይጣመም በአሳማኝ መንገድ መቅረብ አለበት፡፡

ከላይ በተወሳው መልክ በምኒልክ ዘመን ላይ ቆመው የሚቀሩ የኦሮሞ ብሄር ፖለቲካ ልሂቃን ከዚህ አለፍ የማለት ነገር በሚታይባቸው ሁኔታዎች ደግሞ ቀደም ሲል ቆመው የኖሩበትን ክርክር በሚጠናክር ሌላ ሁነት ላይ እመር ብሎ እዛ ላይም የጨው አምድ የመሆን ነገር ይታያል፡፡ ይህ ዘመን ደግሞ ወደ ኃ/ስላሴ ዘመን ያመራል፡፡ ይህኛው ክርክር በኃ/ስላሴ ዘመን በመንግስት ደረጃ በተያዘ እቅድ የኦሮሞ ህዝብ ከአንደኛ ደረጃ በላይ እንዳይማር መደረጉን፣ይህም በወቅቱ ከስርአቱ ማገር አንዱ የነበሩት ጀነራል ታደሰ ብሩ ኦሮሞ መሆናቸው ሳይታወቅ እንደተነገራቸው የሚያወሳው ክርክር ነው፡፡ ይህ አሳፋሪ እና መሆን ያልነበረበት ነገር ነው፡፡ ይህ ነገር እንደ በደል ለኦሮሞ ብሄርተኛ ልሂቃን የነፃነት ትግል ግብአት መሆኑም ከበቂ በላይ ነው፡፡ ይህ ሳይረሳ ነገሩ የተለገጠበት መንገድ የሚነግረን አንድ ትልቅ ጉዳይ በዛ ዘመን በትልቅ የመንግስት መንበር ላይ ለመሰየም ዘርን መጠየቅ እና ማወቅ እንደማያስፈልግ ነው፡፡ ለዚህ ማመሳከሪው በወታደራዊ ክንፉ ትልቅ ደረጃ ላይ የነበሩት ጀነራል ታደሰ የዘር ሃረግ ሳይመዘዘዝ በመቅረቱ ይህ ሚስጥር ስለተነገራቸው ነው፡፡ እነዚህን እውነታዎች ሳናጤን ዛሬ ላይ ቆመን እንትና የተገደለው፣ የተሰደደው የእንትን ተወላጅ በመሆኑ ነው እያልን በዘር ከረጢታችን ውስጥ ሆነን፣ የዘረኝነት መነፅር አጥልቀን የምንሰጠው ትንታኔ ትርጉም አልባ ይሆናል ፡፡ ወደዚህ አይነት ትንታኔ የሚመራንም አሁን አዲስ ታሪክ ለመስራት ካለመቻላችን የመጣ ስራፈትነታችን የሰጠን የተትረፈረፈ ጊዜ ውሃ እንድናላምጥ ስላደረገን ይመስለኛል፡፡

ወደዋናው ነገር ስመለስ የኦሮሞ ህዝብ ከአንደኛ ደረጃ በላይ እንዳይማር፣ ቋንቋውም እንዳይስፋፋ ተደርጎ ነበር የሚለው ክርክር በበቂ ማስረጃ እየተደገፈ ይቀርባል፡፡ እዚህ ላይአብሮ መነሳት ያለበት ጉዳይ ይህን የሚሉ ልሂቃን አሁን ባህልን የማስፋፋት፣ ትምህርትን ለሁሉም የማዳረሱ መብት ህገ-መንግስታዊ እና ሰብአዊ መብት በሆነበት ዘመን የድሮውን እያነሱ ቆሞ ከመቅረት ባለፈ የበፊቱ የትምህርት ክልከላ የጎዳውን ሰፊ የኦሮሞ ህዝብ ክፍተቱን በሚሞላ መልክ ትምህርት እንዲያገኝ የተለየ ጥረት ሲደርጉ አይስተዋልም፡፡ (በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆው የትግራይ ተወላጆች “ከዳስ ወደ ክላስ” በሚል ዘመቻ በክልላቸው ብዙ ለትምህርት ምቹ የሆኑ የመማሪያክፍሎችን ገንብተው ህፃናት በተሻለ ሁኔታ የሚማሩበትን መንገድ አመቻችተዋል፡፡) የኦሮምኛ ቋንቋ ሁን ተብሎ እንዳያድግ ተደርጓል ብሎ እስከ ዛሬ የሞተውን የዘውዳዊ ስርአት ከመውቀስ አሁን የብሄረሰቦች መብት ተረጋገጠበት በሚባለው ዘመን የተለያዩ መዝገበቃላትን እና የኪነጥበብ ስራዎቸን በቋንቋው በማዘጋጀት በፊት ነበረ ሚባለውን ክፍተት መሙላት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ቋንቋውን የማይናገርን የሃገር ልጅ የጎሪጥ ከማየት ይልቅ የወንድማማችነት ቅርርብ ፈጥሮ ቋንቋውን በፍላጎቱ እንዲማር ማድረግ ይሻላል፡፡ ይህን ለማድረግ ግን ችግር ላይ ቆሞ ከመቅረት ወደ መፍትሄ መንቀሳቀስን ይጠይቃል፡፡ የመፍትሄ እንቅስቃሴው ደግሞ የምኒልክን ስም የጠራ አቀንቃኝን በመርገም፣ ‘የእንትን ቢራን የምትጠጡ የኦሮሞ ህዝብን ደም እንደምትጠጡ ቁጠሩ’ በሚል ማንንም የማይጠቅም “የሳይበር” ትግል በማድረግ አይደለም፡፡ይህን የመሰለን ትልቅ የፖለቲካ ጥያቄ መልስ በቢራጠርሙስ ውስጥ መፈለግም ያስገምታል፡፡ \

የቀይ ሽብር ዘመን ቆሞቀሮች!

ቀይ ሽብር የተባለው የፈሪ ዱላ የአንድ ትውልድ ልበ-ብርሃኖች በአፈር እንዲያረጁ ያደረገ አሳዛኝ ብሄራዊ ኪሳራን ያመጣ ክስተት ነው፡፡ ጦሱም የሃገሪቱን ፖለቲካ ታሞ አይድን ያደረገ፣ በሃገራችን ፖለቲካ ከኮረንቲ እኩል አስፈሪ እንዲሆን ትልቅ ስንቅ የሆነ እና እስከዛሬ የማስደንበር አቅም ያለው ክፉ ጠባሳ ነው፡፡ ክስተቱ ዶ/ር መረራ በጥሩ አገላለፅ እንዳስቀመጡት ድንቁርና እና ስልጣን ሲገናኙ የተፈጠረ በመሆኑ ቀይሽብርን እያሰቡ ከመበርገግ ይልቅ ድንቁርና እና ስልጣን በሃገራችን ዳግመኛ እንዳይገናኙ መስራቱ ተሻይ ነው፡፡

የ 1997 ቆሞ ቀሮች!

የ1997 ምርጫን ተከትሎ የተከሰተው አሳዛኝ ሁነት የአብዛኛውን ለውጥ ፈላጊ ዜጋ ሃሞት ያፈሰሰ፣ በሃገሩ ፖለቲካ ተስፋ ቆርጦ በአውሮፓ ክለቦች የእግር ኳስ ስንክሳር ውስጥ እራሱን እንዲደብቅ ያደረገ ነው፡፡ ነገሩ በዕድል ለሚያምኑም የሃገራችንን አለመታደልም የነገረ ነው፡፡ ይህ ለውጥን ከልቡ አልሞ በነበረ ዜጋ የአእምሮ ጓዳ ቢመላለስ ጥፋት አይደለም፡፡ ክፋቱ ተስፋ መቁረጥ ማስከተሉ ነው፡፡ ነገር ግን ወደተስፋ መቁረጡ ከመንደርደራችን እና በወቅቱ ብዙ ሰርተው አጨራረሱ እንደ አጀማመሩ ያላማረላቸውን ሰዎች ከማብጠልጠላችን በፊት የ1997ቱ መነሳሳት እንዴት መጣ? የስንት ሰዎች የምን ያህል ጊዜ ጥረት ያንን መነቃቃት ፈጠረ? የእኔ ድርሻስ ምን ያህል ርቀት የተጓዘ ነበር? የሚለውን አብረን ማሰብ አለብን እንጅ ቴሌቪዥን ከፍተን ክርክር ማየታችንን፣ መስቀል አደባባይ ሄደን መሰለፋችንን ፣ ነጭ ቲ-ሸርት መግዛታችንን፣ ብር ማዋጣታችነን፣ ማኪያቶ ይዘን ስለነ እንትና መታሰር፣ የነ እንቶኔን መሰንጠቅ ማውራታችን የምንፈልገውን ዲሞክራሲዊ መንግስት ለመመስረት በቂ እንደሆነ ቆጥረን ተስፋ መቁረጥ ተገቢ አይደለም፡፡

ምክንቱም ቆመን ከቀረንበት 1997 ምርጫ በፊትም ሆነ በኋላ በህዝብ ደረጃ ያደረግነው አሰተዋፅኦ በቂ ሆኖ ተስፋ መቁረጥ ላይ አያደርስም፡፡ በወቅቱ የህዝብን ‘ድምፃችንን አዘርፋችሁ ፓርላማ አትግቡ’ ድምፅ ሰምተው፣ የገዥውን ፓርቲ መልከ-ብዙ መሰናክል (በአዲስ አበባ ዋና የገቢ ምንጭ የሚያስገኙ ድርጅቶችን በፌደራል ስር መደረጉ አንዱ መሰናክል ነበር) አጢነው ፓርላማ ባለመግባታቸው ወደ እስርቤት ለተጋዙ የተቃውሞ ፖለቲካ መሪዎች ደጋፊነኝ ባዩ ህዝብ ያሳየው አብሮነት እርዝመቱ እና ሙቀቱ ምን ያህል እድሜ ነበረው? እያደር የሚቀንሰው የቀደመ ፍቅራችንስ ለእስረኛ የተቃውሞ መሪዎች ጉልበት የመሆን አቅሙ ምን ያህል ነበር? በወቅቱ በድንገትም ሆነ የተቃውሞው አካል በመሆናቸው ህይወታቸውን ያጡ ወገኖችን ቤተሰቦች ይህን አወግዛለሁ ከሚለው የህብረተሰብ ክፍል የሚያገኙት አይዟችሁ ባይነትስ በቂ ይሆን? አሁንስ ቢሆን ‘የሃገሬ ህዝብ አሁን ካለው የተሻለ መንግስታዊ አስተዳደር የሚገባው ትልቅ ህዝብ ነው’ በማለታቸው እስርቤት የተወረወሩ የነፃነት ታጋዮች ጉዳይስ ምን ያህል ያሳስበናል? ይህ ሁሉ አሁን ማድረግ የምንችለው ጉዳይ እያለ በ1997 ላይ ቆመን መቅረት ትርጉም ሰጭ አይደለም፡፡ የነፃነት ትግል በ 1997 ቀረ ብሎ በተስፋ መቁረጥ ድንዛዜ ውስጥ መግባት ነፃነት ምን ያህል ዋጋ እንደሚስከፍል አለመረዳት ይመስላለልና ትግሉን በቅጡ ሳንጀምር እንዳለቀ መቁጠሩ አግባብ አይደለም፡፡ የነፃነትን ውድነት ለማወቅ እነ ማንዴላ፣ እነ ጋንዲ፣ እነ ሞርጋን ቸንጋራይ፣ ዛሬን አያድርገውና የጫካው ኢህአዴግ ለአላማቸው መሳካት መስዕዋት ያደረጉትን ነገር ብዛት የትግላቸውን መራራነት በውል ማጤን ያስፈልጋል፡፡

No comments:

Post a Comment