Saturday, February 15, 2014
የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በኢትዮጵያ!
በቅዱስ ዬሃንስ
የወያኔ መንግስት በትልቁ ከሚታማባቸው ነገሮች አንዱ ደካማ የሰብዓዊ መብት አያያዙ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ የተስማማባቸውን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማክበር የተሰማማች ብትሆንም በአሁኑ ጊዜ በአለም ላይ የከፋ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ካለባቸው ሀገራት አንዷ ነች፡፡ ለዚህም ሂውማን ራይትስዎችና አምነስቲ ኢንተርናሽናልን የመሳሰሉ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሪፖርት ባወጡ ቁጥር በመልስ ምት የሚሰነብተውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን መመልከት በቂ ነው፡፡ ለነገሩ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማወቅ የነዚህን ተቋማት ሪፖርት መጠበቅ አያስፈልገንም፡ ፡ እኛው ራሳችን የነገሩ አካል ነንና፡፡ ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን የተንሻፈፉ የህግ አንቀፆች እየተጠቀሱብን ወህኒ እንወርዳለን፡፡ ለዚህ ደግሞ እስር ቤቶችን ሁሌም ቢሆን ከፖለቲካ እስረኞች ነፃ ሆነው አለማወቃቸው አንዱ ማሳያ ነው፡ ፡ እንደለየለት የሶሻሊስት ሀገር ዜጎችም የተዋጠ ጥሬ ሳይቀር ነገራችን ሁሉ ለቤተ-መንግስት ፍጆታ ይውላል፡፡ ዜጐች እኩልነት በሚሸረሸሩ ህጐች የተነሳ ንብረት የማፍራት መብታቸው እየተገደበ ይገኛል፡፡
በተለይ አሁን አሁን ፓርቲው ከያዘው ልማታዊ መንግስት መንገድ ጋር የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ እየሰፋ መጥቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የልማታዊ መንግስት እሳቤ ከሰብዓዊ መብት በፊት ለፓርቲ መደላደልና ለኢኮኖሚ እድገት ቅድሚያ ስለሚሰጥ ነው፡፡ ፓርቲው እንደ አርአያ እየመዘዘው ያለው የምስራቁ አለም በሰብዓዊ መብት አያያዝ የተመሰገነ አይደለም፡ ፡ መቼም የኢህአዴግ የዘንድሮ ‹‹ሮልሞዴል›› ቻይናም እንደ ኢኮኖሚ እድገቷ በሰብዓዊ መብት አያያዟ ምሳሌ ልትሆን የምትችል አይደለችም፡፡
ከነዚህ ሁሉ በተጨማሪ የኢህአዴግ አስተዳደር በብዙ መስኮች ‹‹ከዴሞክራሲያዊነት የፀዳ›› ነው፡፡ በአገራችን ማዕከላዊና ቃሊቲም ይመሰክራሉ፡፡ በሚያስጠልሏቸው ጋዜጠኞች ብዛት፡ ፡ መቼስ እኛ ኢትዮጵያውያን ከሙያዎች ሁሉ የጋዜጠኝነት ሀሁ እምቢ ብሎን ነው ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ የሆነ መሪዎቻችን እምቢ ያላቸው ነገር ቢኖር ነው እንጂ፡፡ ኢትዮጵያዊ ሁሉ መልካም አስተዳደር ብሎ ነገር እንደናፈቀው ነው፡፡ ሲቪል ሰርቪሱ በጌታና ሎሌ (Patron-client) ግንኙነት በተዋቀረበት፣ ብቃት ሳይሆን ‹‹ኢ-ጠያቂነት›› ዋና መስፈርት በሆነበት ሁኔታ መልካም አስተዳደርን መጠበቅም ጅልነት ነው፡፡ ሹሞቻችን ‹‹በአቦ-ሰጡኝ›› ይመሩናል፡፡ ያደናግሩናል ቢባል ይቀላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ አንድ ያስፈገገችኝን ቀልድ ሰማሁ፡፡ ነገሩ ቀልድ ተባለ እንጂ ሺ ጊዜ እየሆነ ያለ ነገር ነው፡፡ ከክልሎቻችን የአንዱ ፕሬዘዳንት የሆኑ ሰው ናቸው አሉ፡፡ ያው በታማኝነት መስፈርት ነበርና የተሾሙት የሚያስተዳድሩት ክልል ህዝብ በብቃታቸው ፍፁም ደስተኛ አልነበረም አሉ፡ ፡ እና በቅርቡ በፌደራሉ መንግስት ሌላ ስልጣን ተሰጥቷቸው ፕሬዝዳንትነታቸውን ይለቃሉ፡ ፡ በፕሬዝዳንትነት የቆዩት ለአስር አመታት ነው፡ ፡ ታዲያ ሲወርዱ ምን ቢሉ ጥሩ ነው?›› አይ… እ ለትንሽ ስራዋን ልለምዳት ስል›› አምስት፣ ስድስት፣ ሰባት….
እንግዲህ ዴሞክራሲ ወዴት አለ? እንግዲህ በኛ መዝገበ ቃላት ዴሞክራሲ ማለት እስካሁን ያየናቸው መርሆዎች መከበር ማለት ነው፡፡ ሹሞቻችን ደግሞ የሆነ ያልታተመ የዴሞክራሲ መፍቻ ያላቸው ይመስላል፡፡ አልገባንም ወይም አልተግባባንም፡፡ አንድ ልብ ያልሆነ መንግስትና ህዝብ ፍሬ አያፈራም፡፡ ወይ የናንተው ይግባን ወይ ደግሞ የኛን ተረዱ፡፡
የሰብአዊ መብት ጥሰት ይቁም!
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment