Thursday, February 13, 2014

የመንግስት ጣልቃ ገብነት በሀይማኖት: የስብሃት ነጋ ምስክርነት


በሀይማኖት ጣልቃ ገብነት ጉዳይ በኢትዮጵያ ሙስሊም ማሕበረሰብና በኢህአዴግ መንግስት መካከል አለመግባባት መስፈኑ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መንግስት በሀይማኖታቸው ጣልቃ መግባቱ እንዲያቆም ሲጠይቁ መንግስትም የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ማሳሰሩ ይታወሳል። (ኮሚቴዎችን በማሳሰር የህዝብን ጥያቄዎች ማዳፈን ይቻል እንደሆነ እንጂ መመለስ ግን አይቻልም)።

መንግስት በሀይማኖት ጣልቃ የሚገባው በተለያዩ መንገዶች ሊሆን ይችላል። አንዱና ዋነኛው ግን የሀይማኖት መሪዎችን በመደለል የፖለቲካ መሳርያ እንዲሆኑ ማድረግና የፖለቲካ ካድሬዎች የሀይማኖት መሪዎች አድርጎ መሾም ነው።

የፖለቲካ ሹመት (ካድሬነትና አገልጋይነት) ሌላ የሀይማኖት መሪነት ሌላ። ፖለቲካና መንፈሳዊ ህይወት የተለያዩ ናቸው። የፖለቲካ ሹመት ከሆነ በገዢው ፓርቲ ሊመረጥ ይችላል። የሀይማኖት መሪ ግን በምእመናን ነው መመረጥ ያለበት። ስራውም ፖለቲካ ሳይሆን ሀይማኖታዊ ነው የሚሆነው። ሀይማኖታዊ መሪው በፖለቲካ ተፅዕኖ ስር መውደቅ የለበትም።


የኢህአዴግ መሪዎች ሁሉንም የሀይማኖት ተቋማትን ለመቆጣጠር የራሳቸው የፓርቲ አባላት የሀይማኖት መሪዎች አድርገው ይሾማሉ። ጓደኛዬ ናስሩዲን በፌስቡክ ገፁ እንዳስቀመጠው ከሆነ አቶ ስብሃት ነጋ እንዲህ ተናግረዋል:

“ቅድም የፌደራሉ መጅሊስ ምክትል ሰብሳቢው ሸህ ከድር እንዳለው የዱሮው እስልምና ሌላ ነው፡፡ እኔ ከድርን በፊት ጀምሮ ትግራይ ውስጥ አውቀዋለሁ፡፡ ምርጥ የሕወሓት ታጋይ ነበር፡፡ አብሮን ታግሏል፡፡ አሁን ደግሞ ሙስሊሙን እያገለገለ ነው፡፡ እስልምና እነዚህ የታሠሩት ሰዎች እንደሚሉት አይመስለኝም፡፡ እስልምና እነዚህ ሰዎች እንደሚያሳዩት ዓይነት እምነት ከሆነ እንደ እምነት አያስፈልግም፡፡ ፈፅሞ ሰዎቹ ለሀገር አይሆኑም፡፡”

ሼህ ከድር የሙስሊሞች ሀይማኖታዊ ተቋም የመጅሊስ ምክትል ሰብሳቢ ነው (ወይም ነበር)። ግን ሼህ ከድር የህወሓት ታጋይ ነበር። የህወሓት አባል ነው። ስለዚህ ሼህ ከድር የፖለቲካ መሪ እንጂ የሀይማኖት መሪ አይደለም። መጅሊስ የፖለቲካ ተቋም አይደለም። የፖለቲካ ሰው አይደለም የሚፈልገው። መጅሊስ የሀይማኖት ተቋም ነው። የሀይማኖት መሪ ይፈልጋል። እንደምናየው ግን የመጅሊስ አመራር አባላት የሀይማኖት መሪዎች ሳይሆኑ ፖለቲከኞች (እንዲሁም የጉሪላ ታጋዮች) ናቸው። እንዴት ይሆናል? ይሄ ተግባር ጥያቄ አያስነሳም? በዚህ መሰረት የሙስሊሞች ጥያቄ ትክክል ነው ማለት ነው።

ሙስሊሞቹ እንደ ምእመናን የሀይማኖት መሪ አያስፈልጋቸውም? "በሀይማኖታችን የፖለቲካ ካድሬዎች አያስፈልጉንም። የሀይማኖቱ እውቀት ያላቸውና በምእመናኑ እውቅና ያላቸው ሀይማኖተኞች እንዲመሩን እንፈልጋለን!" ብለው ቢጠይቁ አግባብነት የለውም? ከመቼ ጀምሮ ነው በማርክሲስታዊ አስተሳሰብ ያደገ የህወሓት ታጋይ ሀይማኖት ኖሮት የመጅሊስ ምክትል ሰብሳቢ የሚሆነው? ወይስ ሙስሊሞችን ለመቆጣጠር ነው የተፈለገው? ደግሞ የሀይማኖቱ ተከታዮች ሳይደግፉት?! የሀይማኖት መሪ'ኮ የምእመናኑ ድጋፍና እውቅና ያስፈልገዋል።

ሙስሊሞች ስለሀይማኖታቸው ሲጠይቂ ሌላ ስም ከመስጠት መጀመርያ መንግስት ከሀይማኖቱ እጁ ያንሳ። ካድሬዎቹን የሀይማኖት መሪዎች እያደረገ አይሹሙብን! ካድሬ በትምህርትቤት ይሾማል፣ በቤተክርስትያን ይሾማል፣ በመጅሊስ ይሾማል!??? ኧረ ተዉ ኢህአዴጎች! ፖለቲካና ሀይማኖት እንለይ!

ሁሉም ሃይማኖቶች ከፖለቲካ ነፃ የሆኑ የሀይማኖት መሪዎች ያስፈልጉዋቸዋል። የሀይማኖት ጉዳይ የመንግስት ጉዳይ ሳይሆን የምእመናኑ ጉዳይ ነውና።

ሙስሊሞች (ና ክርስትያኖች) ሆይ! መንግስት በሀይማኖታቹ ጣልቃ እንዲገባ የማትፈልጉ ከሆነ የመንግስትን በሀይማኖት ጣልቃ የመግባት ተግባሩ አጥብቃቹ ተቃወሙት። እየተቃወማችሁት ነው። ግን መፍትሔ የለም፣ ሰሚ የለም። ለጥያቅያቹ መልስ ከመስጠት ይልቅ መንግስት እያሰራቹ፣ እያሰቃያቹ ይገኛል። የመንግስት መፍትሔ ኮሚቴዎችን ማሳሰር ከሆነ በኢህአዴግ እምነት ሊኖራቹ አይገባም። እናም ኢህአዴግ መፍትሔ ሊያመጣላቹ እንደማይችል አረጋግጠዋል። ስለዚህ ምን ይደረግ? የሀይማኖት ጥያቄው ታፍኖ ይቅር?

የሀይማኖት ጥያቄማ መፍትሔ ይሻል። ምክንያቱም የሀይማኖት ጥያቄው ትክክለኛና አስፈላጊ ነው። ጥያቄው ሁላችን የምንደግፈው ነው። ጥያቄው ትክክል ከሆነ መልስ ያስፈልገዋል። መልስ የሚሰጥ አካል (መንግስት) ከሌለስ? መንግስት መልስ ሊሰጥ እንደማይችል ካረጋገጠልን ለህዝብ የሚቆረቆር፣ የህዝብን ጥያቄዎች መመለስ የሚችል፣ የሀይማኖት ችግሮች የሚፈታ፣ የሀይማኖት ነፃነት የሚፈቅድ፣ ሰብአዊ መብት የሚያከብር ዴሞክራሲያዊ መንግስት ያስፈልገናል ማለት ነው። ስለዚህ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ለመመስረት ጥረት እናድርግ። የምርጫ ድምፃችን የህዝብን ጥያቄዎች ሊመልሱ ለሚችሉ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲዎች እንስጥ። የህዝብን ጥያቄ መመለስ የሚያስፈራው ኢህአዴግ ከስልጣን (በዴሞክራሲያዊ መንገድ ወይ ምርጫ) እናውረደው። ሌላ ፓርቲን በመምረጥ ኢህአዴግን አውርደን ጥያቄያችንን የሚመልስልን ሌላ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ስልጣን እንዲይዝ እናድርግ። ከዛ የሀይማኖት ይሁን የሌላ ነፃነታችን ይከበርልናል። ካልተከበረ ትግላችን ይቀጥል።

በኣብርሃ ደስታ

No comments:

Post a Comment