Sunday, February 23, 2014

ፍርድ ቤቶች ፍርድ ቤት ይቅረቡ!

ሥራቸውን በአግባቡና በትክክል የሚያከናውኑ ፍርድ ቤቶች የሕዝብ አለኝታዎች፣ የዜጐች ኩራትና መተማመኛ ናቸው፡፡ በአንፃሩ ፍርድ ቤቶች ሥራቸውን በሕግና በታማኝነት የማይሠሩ ከሆነ ደግሞ የሕዝብ ሞራል እንዲወድቅ ሐሞቱም  እንዲፈስ ያደርጋሉ፡፡ ተስፋ ያስቆርጣሉ፡፡ 

በኢትዮጵያ በትክክል ሥራውን የሚሠራ ዳኛ የለም አንልም፡፡ ተገቢ ፍርድና ውሳኔ የሚሰጥ ችሎት በጭራሽ የለምም አንልም፤ አሉ፡፡ ምሥጋናም ይገባቸዋል፡፡ አጠቃላዩ ሁኔታ ሲታይ ግን ፍርድ ቤቶች ሥራቸውን እየሠሩ አይደለም፡፡ ሕግን እያስከበሩ አይደለም፡፡

ፍርድ ቤቶች ራሳቸው ፍርድ ቤት ይቅረቡ የሚያሰኝ ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን፡፡ በየትኛው በፍርድ ቤትና በየትኛው ችሎት ትክክለኛ ውሳኔ ይሰጣል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እጅግ አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡

በፍርድ ቤቶች ዙሪያ አራት ዓበይት ችግሮች ይታያሉ፡፡

ችግር አንድ - ሙስና

ፍርድ ቤቶች ከማንኛውም ተቋም በላይ ከሙስና የፀዱ እንዲሆኑ ይጠበቃሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱንና ሕጐችን የመተርጐም ኃላፊነት የተሰጣቸው ናቸውና፡፡ እነሱ ራሳቸው በሙስና ሊዘፈቁ ሳይሆን፣ በሙሰኞች ላይ በቀጥታ በመወሰን ሙስና እንዲጠፋ ለማድረግ ትልቅ ሚና እንዲጫወቱ ይጠበቃል፡፡

ግን! ነገር ግን! ራሳቸው የሙስና ሰለባ እየሆኑ ናቸው፡፡ ጉቦ በመብዛቱ በጥቅማ ጥቅም ቀጠሮ ማራዘም፣ ፋይል መዝጋትና ፍርድ ማዛባት በከፍተኛ ደረጃ እየታየ ነው፡፡ አሳሳቢና አስጊም እየሆነ ነው፡፡


ችግር ሁለት - አቅም ማነስ

በፍርድ ቤቶች ዙሪያ የአቅም ማነስ እየታየ ነው፡፡ ጉቦ በመቀበልና በጥቅም በመደለል ሳይሆን፣ በክፋትና በተንኮል ሳይሆን፣ በሀቅ ለመሥራት እየፈለጉም በአቅምና በብቃት ማነስ ምክንያት ፍትሕና ፍርድ ሲዛባ ይስተዋላል፡፡

በፍትሕ ቦታ ላይ መቀመጥና የዳኝነትን ኃላፊነት መቀበል ከፍተኛ ብቃት ይጠይቃል፡፡ ዳኝነት የ‹‹እርስዎም ይሞክሩት›› ቦታ አይደለም፡፡ ነገር ግን በብስለት ማጣት፣ በአቅም ማነስና አለመኖር ምክንያት ፍትሕ እየተዛባ ዜጐች እየተጐዱ ናቸው፡፡ ሕዝቡ በፍትሕ አካላት ላይ እምነቱ በመቀነስ ላይ ይገኛል፡፡

ችግር ሦስት - ጣልቃ ገብነት

በማንኛውም ፍትሐዊ ሥርዓትና በአገራችንም ሕገ መንግሥት ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚው ነፃ ሆነው የሚንቀሳቀሱና ከሕግ ውጭ ጣልቃ ገብነትን የማይቀበሉ ናቸው፡፡

ነገር ግን በአገራችን ፍርድ ቤቶች የአስፈጻሚው አካል ጣልቃ ገብነት ይታያል፡፡ በድብቅ በስልክ፣ በግል ግንኙነትና በተለያዩ ዘዴዎች ዳኞችና ፍርድ ቤቶች እንዴት ብለው መፍረድ እንዳለባቸው ጫና ይደረግባቸዋል፡፡

ያን ፋይል ዝጉ፣ ይኼንን ለዚህ ፍረዱ፣ ያኛውን ነፃ ልቀቁ፣ እዚያ ላይ ጠበቅ በሉ የሚል ጣልቃ ገብነት እየተስተዋለ ነው፡፡

ይህ ዓይነቱ ድርጊት በፍትሕ አካላትና በዳኞች ላይ ሥጋትና ፍርኃት እያስከተለ፣ ነፃና ደፋር ሆነው እንዳይፈርዱ እያደናቀፈ ነው፡፡ የሚፈራ ፍርድ ቤት ፍትሕ ሊሰጥ አይችልም፡፡

በተለይ በአገራችን ሁኔታ ፍርድ ቤቶች ላይ ጫና የሚፈጠረው በአስፈሪ ባለሥልጣናት ብቻ ሳይሆን የሚያስፈራሩ ግለሰቦችም እየተጨመሩበት ነው፡፡

ችግር አራት - መፍትሔ ሰጪ አካል ጠፋ

ችግሮች መፍትሔ የላቸውም ማለት አይደለም፡፡ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የሚታይ ችግርን ለመፍታት ከተፈለገና ከተቆረጠ መፍትሔ ይገኝለታል፡፡

የፍርድ ቤቶች ችግርም የማይፈታ አይደለም፡፡ ጉቦኛን መቅጣትና ማስወገድ ይቻላል፡፡ አቅምን ማሳደግና መጨመር ይቻላል፡፡ ጣልቃ ገብነትን ማስቆምና ጣልቃ የሚገባን መቅጣት ይቻላል፡፡ ይህ ግን በዘፈቀደ የሚደረግ ሳይሆን በሕጋዊ አካል አማካይነት ነው፡፡

ፓርላማ የድርሻውን ቢጫወት፣ መንግሥትም ኃላፊነቱን በትክክል ቢወጣ፣ የፍትሕ አካላትና የአመራር አካላት ጠንካራ ቢሆኑ፣ ፍርድ ቤቶቻችን ከዚህ ሁሉ ችግር በተገላገሉ ነበር፡፡

ግን ነገር ግን ዕርምጃ የሚወስድ አካል የለም፡፡ ቆራጥ አካልና ቆራጥ አቋም አልተገኘም፡፡ መፍትሔው ዝም ስለሆነ ችግሩ እየተባባሰ ነው፡፡

መፍትሔ የሚሰጥና የሚያስተካክል አካል በመጥፋቱና ችግሩ እየተባባሰ ስለመጣ፣ ፍርድ ቤቶችን ከሰን ፍርድ ቤት እንውሰዳቸው ወይ? ፍርድ ቤቶች ፍርድ ቤት ይቅረቡ ወይ?

ፍርድ ቤት ከቀረቡም እነሱ ዘንድ ያለው ችግር የሚቀርቡበት ፍርድ ቤትም ይኖራልና ለመፍትሔው የሚመለከተው አካል አስቸኳይ ዕርምጃ እንዲወስድ ማድረግ የግድ ይሆናል፡፡

ፍርድ ቤቶች ከጉቦ ይፅዱ፣ ከሙስና ይራቁ፣ አቅማቸው ይጠናከር በእነሱ ላይ የሚደረገው ጣልቃ ገብነት ይቁም፡፡ ፓርላማና መንግሥት በልዩ ትኩረት ልዩና አስቸኳይ ዕርምጃ ይውሰዱ! አሁኑኑ!        

ምንጭ፡ ሪፖርተር ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment