Thursday, February 6, 2014

ያለቦታው እና ጊዜው የሚንቋረር ጩኸት ♦ውህደት♦

  By: Yonatan Tesfaye

ለምንድነው የምንዋሃደው! እንዴትስ ነው የምንዋሃደው! ከማን ጋር ነው የምንዋሃደው! ትግሉስ ገብቶናል!

የመጀመሪያው ስህተት አብዛኛዎቹ የእንዋሃድ ጥያቄ አንሺዎች ችግር መዋሃዳቸው ጉልበት እንደሚሰጣቸው እንጂ ለምን አላማ ጉልበት እደሚያስፈልጋቸው አጥርተው አያውቁትም፡፡ ልክ ከዚህ በፊት እንደነበረው ተዋህዶ ኢህአዲግን በባሌም በቦሌም ማስወገድ እንጂ እንዴት እና በምን መልኩ መውረድ እንዳለበት የሚያስቀምጡት አንዳችም የጠራ መንገድ የላቸውም! ምርጫውን እያሰቡ ነው የምትሉ ከሆነ እናንተም ተሞኝታችኋል ማለት ነው! ሰላማዊ ትግል የሚባለው ገና ያልተገለፀላቸው ብዙዎች አሉ ህዝቡን ጭምር ማወናበድ ላይ ናቸው! አሁን ባለንበት ሰዓት ኢህአዲግ በፍትሃዊ ምርጫ ስልጣን ሊለቅ የሚችልበት የሞራል ዝግጅትም ሆነ ፍላገት የለውም፡፡ በዚህ ደረጃ ደግሞ ምርጫ ከኢህአዲግ ጋር መሰለፍ አጨብጫቢ ሆኖ ከማለፍ የዘለለ የሚፈይደው አንዳች የለም! ውህደት ተፈጥሮ እና ተቀቃዋሚዎች ሀይላቸው ባንድ ሆኖ ምርጫ አካሂደው ስልጣኑን መረከብ የሚችሉበት አቋም ቢኖራቸው እኳን ላለመገልበጡና ለፍትሃዊነቱ ደጀን የሚቆም የሰው ሀይል ከሌለ እና በተለይ በስነ ልቦና ረገድ ጠንካራ የሰላማዊ ትግል አቀላጣፊዎች ካልፈሩ አደጋው ይብስ ይከፋል! ተስፋ ሊያስቆርጥም ይችላል!

ሌላው እንዴት መዋሃድ እንደሚገባ ብዙዎቹ ምሁራኑ ጭምር በደፈናው የሚያልፉትና ማይደፍሩት ጉዳይ ነው፡፡ እንቁላል ቀስ በቀስ በእግሩ ይሄዳል እንደሚባለው አንድ ሆኖ ለመስራት እኮ መጀመሪያ አንድ ሊያደርግ የሚችል አቋም ላይ መድረስ የግድ ይላል! ያን ለማድረግ ደግሞ ነገሮች ደረጃ በደረጃ መጓዝ አለባቸው፡፡ መረዳዳት . . .መተጋገዝ . . .አብሮ መስራት . . .የጋራ መድረኮችና ውይይቶች ማዘጋጀት . . .በአባላት ደረጃ መቀራረብ መፍጠር ሌላም ሌላም . . .ከዚህ አንፃር አሁን ባለው ነባራዊ እዉነታ እንኳን ለመዋሃድ አብሮ ለመስራት እንኳን ረጅም ርቀት መሄድ የግድ ነው፡፡ ድልድይ ሳይሰሩ ወንዝ መሻገር አይቻልም! ደራሽ የመጣ ለት አጥረግርጎት ይሄዳልና! እናም ይህን ከግምት የማያስገቡ የተዋሃዱ እና የእንዋሃድ አባዜ የተጠናወታቸው ሰዎች ባጠቃላይ ካየነው ብስለት የጎደለው እና አርቆ ማየት የማያስችል አስተያየቶቻቸውን ደግመው ቢገመግሙ መልካም ነው፡፡


በብዙዎች የተባለው ሌላው ነገር ማን እና ማን ይዋሃዱ የሚለው ነው፡፡ ለምሳሌ ህወሓት ብቻውን ሀገሪቱን መምራት እንደማይችል ስለተረዳ ኦነግን ኢህዲን እና ሌሎችንም ግንባር አስፈጥሮ ሀገሪቷን መምራት የሚችልበት አቋም መያዝ ችሏል፡፡ አሁንም በዚህ ዘመን በጎሳ የተደራጁ ፓርቲዎች እንደ አሸን በመፍላታቸው እነሱኑ ብሔራዊ ለማድረግ እና ሀገር አቀፍ ትግል በጋራ ለመፍጠር ግንባር መፍጠር ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ ከዛ ውጪ ግን እንደ ሰማያዊና አንድነት ያሉ ፓርቲዎች ከመነሻቸውም ሀገራዊ በመሆናቸው የሚዋሃዱት ወይም የሚተባበሩት ድርጅት ሀገራዊ መሆን ሊኖርበት ግድ ይል ይሆናል አለዛ ደግሞ በጎሳ ተደራጀው ፓርቲ ራሱን በነዚህ ሀገራዊ ፓርቲዎች ውስጥ ማጠቃለል አለበት! ከመናሸውም የኢህአዲግን አይነት መዋቅር ያላቸው ክልላዊም ሆነ በጎሳ የተደራጁ ፓርቲዎች እና ግለሰቦች ቆም ብለው ሊያስቡት የሚገባ ነገር ቢኖር የግለሰብን ነፃነት እንደሚያስቀድሙ በፕሮግራማቸው አካተው በአደረጃጀት ግን አንድ አካባቢ ላይ መወሳናቸውን ነው! ይህ ጥያቄያቸውን ወይም ትግላቸውን የሚያጠበውና የሚያቀጭጨው መስሎ ይታየኛል!

ዋናው ሁሉም ሊረዳው የሚገባ ነገር ግን የምናደርገው ትግል ምን አይነት ነው የሚለው ነው! በምርጫ አሸንፎ ፓርላማ ለመግባት ከሆነ ተሳስተናል፡፡ ወይም የምንታገለውን አካል ገና አልተረዳነውም! ሰላማዊ ትግል ማለት በምርጫ ተወዳድሮ ስልጣን መያዝ አይደለም! ሰላማዊ ትግል በምርጫ መወዳደር እና ስልጣን የህዝብ የሚሆንበትን ወይም ሊሆን የሚችልበትን ፍትሃዊ ስርዓትን ለመፍጠር የሚደረግ ዘርፈ ብዙ ትግል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ደግሞ ኢትዮጵያ ዉስጥ ገና ያልተጀመረ የትግል አይነት ነው ብዬ ለመናገር እደፍራለሁ!

ለማንኛውም አንድነት ሀይል ነው! በጠንካራ መሰረት ላይ የቆመ አንድነት የሚጥለው ወጀብ አይኖርም!

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

No comments:

Post a Comment