በማስረሻ ማሞ (አምስተርዳም)
የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሞራል መሠረት እና ብቃት በሌላቸው ፖለቲከኞች እጅ ከወደቀ ሰንብቷል። ይህ የሰነበተ እውነታ በአሁን ሰዓት ከዝቅጠትም በታች እየኾነ ነው። ለኢትዮጵያ የሚያዋጣት ብሔርን መሠረት ያደረገ ፖለቲካዊ ርዕዮት ነው የሚለው የፖሊቲካል ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ሁሉን አቀፍ ፍትህ የተንሰራፋበት ቢኾን ምናልባት አዋጪ ሊኾን ይችላል የሚል ግምት ማስቀመጥ ይቻል ነበር። ነገር ገን ስትራቴጂው ወረቀት ላይ ሌላ መልክ የያዘ፤ ምድር ላይ ደሞ ሌላ ትርክት የዋጠው ነው። ከጅምሩ ፍትሃዊነቱ አጠራጣሪ ስለኾነ ስትራቴጂው ለማፋጀት ያለመና እርስ በርስ በጥርጣሬ ከመተያየት የማያመልጡ የብሄር ፖለቲከኞችን እየፈለፈለ ይገኛል። ለዚህም ነው ከሁለት ዐሥርተ ዓመታት በፊት “በትምክህት” ፍረጃ የተጸነሰው ሕዝብን የማቃለል ጅምር ወደ ለሃጭ ተዋስዖ ያደገው።
የብአዴን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አለምነው መኮንን ይህን የለሃጭ ተዋስዖ ከየት አመጡት? የሚለው ጥያቄ በእኔ እምነት ወሳኝ ጥያቄ ነው። ብዙዎች እንደሚያምኑት ብአዴን እንደ ፓርቲ የራሱ የኾነ ነጻነት እና እምነት ያለው ፓርቲ አይደለም፤ አሻንጉሊት እና አስፈጻሚ፤ ከሕወሃት የሚወርድለትን ትዕዛዝ እና ፖለቲካዊ ትንተና ለማስተላለፍ የሚያገልግል “ትቦ/ቧንቧ ፓርቲ” ነው። ከአራቱ የኢሕአዴግ ፓርቲዎች ውስጥ ራሱን ሥልጣን እንደሚጋራና 22 ሚልዮን ሕዝብ እንደሚወክል ድርጅት ፖለቲካዊ ስሌት ውስጥ አስገብቶ የሚንቀሳቀስ ፓርቲም አይደለም። “የአማራውን” ሕዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችል ምንም ዐይነት ተነሳሽነትም የለውም። ይህን እውነታ በግልጽ ለመረዳት የፓርቲውን ቁልፍ ሰዎች ማንነት ማየት ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ። አንድ የብሔር ፓርቲ የአባልነት መመዘኛ መስፈርቱ ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ ቀድመን እናንሳ። በደም እና በዘር ከዚያ ብሔር የተገኘ ሰው ብቻ ነው የፓርቲው አባል መኾን ያለበት? ወይስ በምርጫም የዚያ ብሔር አባል ነኝ ማለትን ያካትታል?
የሚያካትት ከኾነ በብሔር የመደራጀት ትርጉም ለምን ያስፈልጋል የሚለውን ጥያቄ ማንሳታችን አይቀርም። ይህን ጉዳይ ማንሳት የፈለግኹት የመንግሥት ቁልፍ ሰው ናቸው ተብለው የሚነግርላቸውን አቶ በረከትን እንደምሳሌ ለመመልከት ነው። አቶ በረከት በደም ከአማራው ጋራ የሚያስተሳስራቸው አንዳችም ነገር የለም። ነገር ግን የአማራው ጉዳይ የእኔ ነው ብሎ በተቀመጠው ፓርቲ ላይ ቁልፍ ቦታ አላቸው። የብአዴን አመራሮችም ኾኑ አባላት አቶ በረከት ከዚህ ፓርቲ ራሳቸውን እንዲያወጡ መጠየቅ አለባቸው፤ ቡግና ውስጥ ተወልዶ ማደግ አማራነትን ያቀዳጃልና እኔም አማራ ነኝ የሚል አቋም ካላቸው፤ ቀድመህ ለተገኘህበት የብሔር ማንነት ቅድሚያ ስጥ ከሚለው የራሳቸውና የተከታይ ካድሬዎቻቸው ትንተና ጋራ ስለሚጋጭ የሚያዋጣ አካሄድ አይኾንም። እንደ በረከት ዐይነት “የአማራነት ልብስን ቀደው ያሰፉ” ሰዎች ለአማራው ሕዝብ ቆመናል ብለው ከሚያስቡ ሰዎች ጋራ በአንድ ጠረጴዛ ላይ መቀመጣቸው መዘዙ ብዙ ነው። በዋነኛነት ሌሎችን ነጻነት ያሳጣቸዋል። ነጻነት የሌለው ሰው ደግሞ ከራሱ የሚናገረው ነገር የለውም።
አቶ በረከት ከጫካ ጀምረው የሕወሓት ዋነኛ ሐሳብ አስተግባሪ ናቸው። አማራ ትምክህተኛ እና ነፍጠኛ ነው የሚል የፖለቲካ መሣርያ ይዘው መሥራት የጀመሩት ዛሬ አይደለም። አማራው እንደ ሕዝብ ትምክህት አለበት ወይ የሚለው ሐሳብ በራሱ ሕዝብን በአንድ ቅርጫት ውስጥ አስገብቶ እንደመፍረድ ስለሚቆጠር ሐልዮቱ በራሱ ወኃ የሚያነሳ ጭብጥ የለውም። የአማራውን ልሂቅ ስህተት እና ተግባር ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋራ ጭቆናን ሲካፈል ለኖረ ሕዝብ ማሸከምም የወጣለት ኢ-ፍትሃዊነት ነው። የትኛውም አማራ፤ የትኛውም ትግሬ፣ የትኛውም ኦሮሞ፣ የትኛውም ጉራጌ፣ የትኛውም ወላይታ . . .እና ሌሎችም ብሔሮች የጨቋኝ አገዛዝ ሰለባዎች ነበሩ፤ እንደ ሕዝብ። አሁንም ናቸው። አማራ እንደ ሕዝብ የተለየ ያገኘው ጥቅም አለ ብዬ አላስብም። ስለዚህ አማራውም እንደ ሕዝብ በብሔር መብቱን ያስጠብቅ የሚል መነሻ ይዘን ከመጣን ስድብን ተሸክሞ የሚዘልቅበት ምንም ዐይነት ምድራዊ ምክንያት ሊኖር አይችልም።
የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣናት አማራውን ወክለናል ብለው በሚንቀሳቀሱ አመራሮች ላይ ለምን “ትምክህተኛ”፣ “ነፍጠኛ” እና “ለሃጫም” የሚሉ ቃላቶችን በአፋቸው ላይ ማስቀመጥ መረጡ? በኦሮሞው ላይ “ጠባብ” እና “ሁሉም ሲፋቅ ኦነግ ነው” የሚለውን ፍረጃ እና ስድብ ማሸከምስ ፈለጉ? ይህን ፍረጃ እና ስድብ የመረጡበት ምክንያት አንድና አንድ ብቻ ነው። የሁለቱ ብሔሮች ጥንካሬ የሥልጣን መሠረታቸውን ስለሚያናጋ ነው። ራሳቸው ቀይደው ባመጡት የብሔር ፖለቲካ አደረጃጀት ኦሮሞው እና አማራው ባላቸው የሕዝብ ብዛት ብቻ የሥልጣን ተቀናቃኝ በመኾን ወደፊት የሥልጣን ርካብ ላይ እንደ ሕወሓት ያለው ድርጅት እንዳይወጣ እንደሚያደርገው ጠንቅቀው ያውቃሉ። ስለዚህም “እኔ ትምክህተኛም፤ ጠባብም አይደለሁም” የሚለውን ፍረጃ መልስ እስኪሰጡበት ድረስ ሥልጣናቸውን ማራዘም ይፈልጋሉ። ሕወሃት ለሌሎቹ የኢትዮጵያ ብሔሮች ቀርቶ ሕዝባዊ መሠረት አለኝ ለሚለው የትግራይ ማኅበረሰብም የማይገደው መኾኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል። (ለዚህ የአብርሃ ደስታን ሪፖርቶች መከታተል ብቻ በቂ ነው)።
ብዙ የነቁ የትግራይ ልጆች እና ራሳቸውን ከአረና ጎን አሰልፈው የሕወሃትን አምባገነናዊ አስተዳደር ለሚታገሉ ሰዎች የሚያወጣላቸው ስም አማራውን እና ኦሮሞውን ከፈረጁበት ጋራ ተመሳሳይ ነው። አሁንም አዲሱ “የትምክህት ለሃጭ” ተዋስዖ በገዛ ልጁ አባቱን ማሰደብ ዐይነት ነው። ይህ አዲስ ነገር አይደለም። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ይህንኑ ተመሳሳይ ድርጊት ፈጽመዋል። ይህ ሕዝብን የማቃለል እና በእሳት ላይ ቤንዚን የማርከፍከፍ ተግባር ተጸንሶ የሚያድገው በሕውሓት ሴል ውስጥ አይደለም ብሎ ማንም አይጠረጥርም።
በ97 ምርጫ ገዢው ፓርቲ ከተቃዋሚ ፓርቲ በኩል ያለው ጫና እየበረታበት ሲመጣ እና በፖሊሲ ክርክሮች ላይ ሕዝቡ የበለጠ ድምጹን ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ሊሰጥ ወደሚችልበት ኹኔታ ባዘነበለበት ወቀት “ኢንተርሃምዌይ” የምትለዋን ቃል ከአለቃቸው ተቀብለው በቴሌቪዥን መስኮት መጥተው የነገሩን አማራውን እወክላለሁ ብለው የተቀመጡት አቶ አዲሱ ለገሰ ነበሩ። ከራሱ አፍልቆ ያመነበትን ነገር በራሱ ቋንቋ የሚናገር አንድም ባለሥልጣን እንደሌለን እናውቃለን። አቶ መለስ ቃላቶችን ይፈበርካሉ፤ እነዚያን የተፈበረኩ ቃላት በዙሪያቸው ኅሊና እና ሆዳቸውን የሸጡ ባለሥልጣናት እንደ ዐየር ባየር ነጋዴ አውጥተው እንደ በቀቀን ሲጮኹብን ይውላሉ።
እጅግ በጣም አስገራሚው ነገር ኢሕአዴግ ውስጥ ካሉት አራት ድርጅቶች መካከል በአመራር ደረጃ ለወከሉት ሕዝብ ባለመቆርቆር ብአዴኖችን የሚተካከላቸው አለመገኘቱ ነው። በታምራት ላይኔ ተጀምሮ፣ በአዲሱ ለገሰ ተባብሶ፣ በአለምነው መኮንን የዝቅጠት ደረጃ ላይ ደርሷል። ምንም እንኳ “የዘር ምርጥ፤ ወይም ንጹህ ዘር” የሚባል ጽንሰ ሐሳብ በዚህ ዓለም ላይ ባይኖርም፤ (አለ ብለው የሚያስቡ ካሉ፤ እንደ ሂትለር ዐይነት በሽታ የተጠናወጣቸው ይመስለኛል) አንዳንዶች የእነሱን ዘር ከሌላው ዘር የተለየ እና የተሻለ አድርገው ለማሳየት ሲታትሩ እየተመለከትን ነው። እያንዳንዱ የሰው ልጅ ሲፈጠር እኩል ነው የሚለውን ዋናና መሠረታዊ ጉዳይ ኾነ ብለው ለመሸሽ ፖለቲካዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ “ማንነት እንዲህ ነው፤ እንዲያ ነው” በሚል ጉንጭ አልፋ ክርክር ውስጥ የሚገቡ ሰዎችም ሞልተዋል። እነዚህ በፖሊቲካ መጫዎች ሜዳው ታስቦ እና ተሰልቶ ከተቀመጠላቸው ተዋስዖ ውጪ አዲስ ተዋስዖ መፍጠር ያቃታቸው ናቸው። ቀጣይቱ ኢትዮጵያ አዲስ ተዋስዖ ያስፈልጋታል። ሁሉም የሰው ልጆች በመጀመርያ እኩል ናቸው በሚል መሠረታዊ ኀልዮት ላይ የሚያጠነጥን ተዋስዖ።
የለሃጭ ተዋስዖው በሁለት ወገን ራሳቸውን የቀየዱ ልጋጋም ተፋላሚዎችን እያሳየን ነው። “ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር ይሻላል” ወደሚል መፈክረኛነት መሻገር አርቆ አሳቢነትን የሚያሳይ እንዳልኾነ ግልጽ ነው። ምክንያታዊ ከኾኑ ምልከታዎች ወጥተን የስድብ ጅራፍ የምናጮህ ትውልዶች መኾናችንም አሳዛኝ እውነታችን ኾኗል። አማራው እንደ ሕዝብ እየተሰደበ ነው የሚለው ነገር የሚያስቆጣን እና የሚያንገበግበን ከአማራ ስለተወለድን ብቻ ከኾነ ፍትሃዊ የመኾን ዕድላችን ይመነምናል። ይህ ማለት ግን መሰደብን አሜን ብላችሁ ተቀበሉ እና እለፉት ከሚል እሳቤ ጋራ ፈጽሞ አይገናኝም። ግለሰቦችም ኾኑ ብሔሮች በማንኛውም ኹኔታ መሰደባቸውን መቃወም እና መታገል ነው ዋናው እና ትልቁ ቁም ነገር።
በሌላ በኩል ሌላው ብሔር ሲሰደብ ወገባቸውን ታጥቀው የሚመጡ ሰዎች አማራውም እንደ ሕዝብ ሊሰደብ አይገባውም ብለው ከጎኑ ካልቆሙ፤ ለብሔር እንቆረቆራለን የሚሉት ጊዜያዊ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ትርፋቸውን ለማስጠበቅ ብቻ እንደኾነ ያሳብቅባቸዋል። ይህ ደግሞ እንደ አገርም ኾነ እንደ ማሕበረሰብ ዘላቂ የኾን ትርፍ የምናካብትበት ጉዳይ አይኾንም።
ለብሔር/ለጎሳ ፖለቲካ ቅድሚያ ሰጥተው የክርክር ሰይፋቸውን የሚመዙ ሰዎች አሁን አማራ በሚባለው ብሔር ላይ የተቃጣውን ስድብ ሲቃወሙት ካላየን፤ የሚከተሉት ፖለቲካዊ ርዕዮት ሚዛን የሚደፋ ነው ብለን እንድናስብ አያደርጉንም።
በእኔ እምነት አቶ አለምነው መኮንን የፈጸሙት ነገር ወንጀል ነው። ያውም ትልቅ ወንጀል። ጉዳዩ በግምገማ ወይም ከሥራ ኀላፊነታቸው ዝቅ በማድረግ ብቻ የሚታለፍም አይደለም። የሚመራውን ሕዝብ በዚህ ደረጃ አሳንሶ እና አዋርዶ የሚመለከት መሪ ፓርቲውንም ኾነ አገሩን አይጠቅምም። የፌዴራል መንግሥቱ የክልል መንግሥታት እና ባለ ሥልጣናት የህዝብን ክብር እና ስም የሚያጎድፍ ተግባር ሲፈጽሙ ነገሩን የሚዳኝበት የራሱ የኾነ ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ አለው። በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት ርምጃ የመውሰድ የሞራል ብቃትም ኾነ መሠረት የለውም የሚል መከራከርያ ሊነሳ እንደሚችል እገምታለሁ። ይህ መከራከርያ እና ግምት ትክክል ነው ብዬም አምናለሁ። ይህ ዐይነቱ በሕዝብ ላይ ቁጣ ሊያስነሳ የሚችል ድርጊት ከወዲሁ በራሱ በፌዴራል መንግሥቱ መልስ የማያገኝ ከኾነ፤ ራሱን በጊዜ ሂደት ከስሩ መንግሎ ሊጥለው እንደማይችል ምንም ማረጋገጫ አይሰጠንም። ይህ ሐሳብ ራሳቸውን በተቃዋሚ ጎራ ላሰለፉ ዜጎች ‘የዋህና የኢትዮጵያን መንግሥት ተፈጥሯዊ ማንነት ካለማወቅ የመነጨ’ ሊመስላቸው ይችላል። ለጊዜው መልሴ ይምሰላችው ግድ የለም የሚል ይኾናል። ነገር ግን በበሰበሰ አሠራሩም ቢኾን ይህን ጉዳይ ችላ ማለት አያዋጣውም ባይ ነኝ። ባለሥልጣናቴ ሙስና ሲሠሩ አገኘኋቸው ብሎ ዘብጥያ ካወረደ፤ አቶ አለምነህን የማያወርድበት ምንም ምክንያት ሊኖር አይችልም ከሚል መነሻም ነው።
በመጨረሻ፦ የአቶ አለምነው ንግግር ማንንም ሰው የኾነ ሰው ሁሉ ምን ያህል ሊያስቆጣ እንደሚችል ለማሳየት ንግግሩን በሌሎች ብሔሮች ገልብጬ ማየት ፈለግሁ። ይህን ማድረግ የፈለግኹት ለብሔር ማንነት ቅድሚያ የሚሰጡ ሰዎች ዝምታ ምን ያህል አግባብ እንዳልነበረ ለማሳየት ነው።
አቶ አለምነው እንዲህ ነበር ያሉት። “አማራው በባዶ እግሩ እየሄደ፤ ነገሩ መርዝ ነው፤ ይህንን የትምክህት ለሃጩን ካላራገፈ በአንድነት አብሮ መኖር አይችልም!”
ይህንኑ ንግግር የሕወሃት ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲህ ብለው አቀረቡት ብለን እናስብ “ትግሬ በሰቆጣ እየሄደ፤ ነገሩ መርዝ ነው፤ የእብሪት ለሃጩን ካላራገፈ በአንድነት አብሮ መኖር አይችልም!”
እንደገና ይህንኑ ንግግር የኦህዴዱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሲያቀርቡት “ኦሮሞ በቦት ጫማ እየሄደ ነገሩ መርዝ ነው፤ የመገንጠል ለሃጩን ካላራገፈ በአንድነት አብሮ መኖር አይችልም!” ቢሉ ምላሾቻችን ምንድን ነው የሚኾኑት? የለሃጭ ተዋስዖ ምናልባትም ልጋግ ኾኖ ሁላችንንም ጠራርጎ እንዳያጠፋን ያሰጋል። ሁላችንም ከጊዜያዊ ጥቅማችን በላይ ለሰው ልጆች እኩልነት እኩል እንቁም።
No comments:
Post a Comment