Thursday, October 8, 2015

ሥርዓታዊ ክሽፈት “Systemic Failure” (ይሄይስ አእምሮ)

“በሉ እናንተም ሂዱ እኛም ወደዚያው ነው፤ ዱሮም ምንገደኛ ፊትና ኋላ ነው፡፡”

“አፄ ምኒልክ ከልምድዎ አንዳንድ እያለ ቀረልዎ፤
አምናስ አለማያ ነበሩ፣ ዘንድሮን ወዴት ዋሉ፡፡” ዳዊት

“ከአባ ቁፋሮ እሸት ተበልቶለት” እንዲሉ እዚህና እዚያ ጥርዥ ብርዥ ከሚሉ እጅግ ጥቂት ለኅሊናቸው ያደሩ የሀገር አለኝታ ወገኖቻችን መካከል አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብቻ ብዙ ተለዩን፡፡ ነፍሳቸውን ይማርልን፤ ከስቃይ ወደስቃይ አያስገባብን፡፡

ፈረንጆች “When an old man dies, a big library is closed.” የሚሉት ምሣሌያዊ አባባል አላቸው፡፡ ሁላችንም የምንጋራው ነው – እናም “አንድ አንጋፋ ሰው ሲሞት አንድ (ትልቅ) ቤተ መጻሕፍት እንደተዘጋ” ቢቆጠር ለዚህ እውነት ሙሉጌታ ሉሌ ዓይነተኛ ምሣሌያችን ነው፡፡ ጋሽ ሙሌ ጠላትም ወዳጅም ሊክደው የማይቻለው ተንቀሳቃሽ ኢንሣይክሎፒዲያ ነበር፡፡ አንባቢ ብቻ አልነበረም፤ ያነበበውን የማይረሣና ባስፈለገ ጊዜ ሁሉ የሚጠቀምበትም ነበር፡፡ ለሀገሩና ለወገኑ የሠራውን ታሪክ ይዘክረው እንጂ እዚህ ዘርዝሬ መጨረስ አልችልም፡፡ አይሞከርምም፡፡ ለተወሰነ ጊዜ አብሬው ለመሥራት በመታደሌ ያን በማስታወስና እንደጀግና የብዕር ሰውነቱም የሁላችንም ሰብኣዊ ሀብት በመሆኑ እግዚአብሔር ነፍሱን እንዲምራት፣ ለቤተሰቡና ለወዳጅ ዘመዶቹም መጽናናትት እንዲልክልን አንድዬን እየለመንኩ ይህች መጣጥፍ ለርሱና ሰሞኑን በሞት ለተለዩን ውድ ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ ትሆንልኝ ዘንድ ክቡራን አንባቢዎቼን በታላቅ ትህትና እጠይቃለሁ፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታም በተለይ በስፖርቱ ቤተሰብ እጅግ ተወዳጅ የነበረውና ለእናት ሀገሩ ኢትዮጵያ በነበረው ሞልቶ የሚፈስ ፍቅር በብዙዎቻችን ዘንድ በስፋት የሚታወቀው አቶ አቤሴሎም ይህደጎ ከሙሌ ጋ የሰማዩን ሠረገላ ተጋርቶ በአንድ ወቅት ተለይቶናል፡፡ አቤን ነፍሱን ይማርልን፤ የሚወዳት ሀገሩ የእምዬ ኢትዮጵያ አምላክ ዋጋውን በሰማይ ቤት ይክፈልልን፡፡ የጀብዱ ሥራ ባለቤት የነበረው ኮሎኔል ባጫ ሁንዴንም የተነጠቅነው በዚሁ ሰሞን ነው፡፡ ሀገራችን ደህና ሰው አይበረክትላትም፡፡ ስንትና ስንት ሀገር ሻጭና ቸርቻሪ ወምበዴ እያለ እነዚህን እርሾዎች ወሰደብን፡፡ ከርሱ ጋር ማን ይታገላል? የሚገርመው አጋጣሚ ግን ወያኔዎች በዘርና በነገድ ሊለያዩን ሲሞክሩ አጅሬ ሞት ግን መማር አንፈልግም እንጂ ለመማር ዝግጁ ለሆንን ዜጎች የእነዚህን ሦስት ምርጥ ዜጎች ዘውጋዊ ማንነትና በአንዴ መጠራት ልብ ብለን አንድ ከማያደርጉን ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ነገሮች እንደሚበዙ መረዳት በተገባን ነበር፡፡ በፈጣሪ ዘንድ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ … ብሎ ነገር እንደሌለና ማዳላት የሰው ባሕርይ እንደሆነ ሞትም በኮታ የሚጠራ በሚመስል መልኩ ለማንም ሳያዳላ ከሁሉም በመውሰድ በአንድ ሰሞን የማይረሳንን ትምህርት ሰጥቶናል፡፡

የሕዝብ ሰው በኪነ ጥበቡም፣ በሥነ ጽሑፉም፣ በስፖርቱም፣ በወታደራዊ መስክም፣ ወዘተ. በመሆኑ በቅርቡ የተለየችንን ብርቅዬ የመድረክ ፈርጥ ሰብለ ተፈራንም ማስታወስ ይገባኛል፡፡ አንድ ታዋቂና ዝነኛ ሰው ሲለይ ከየቤተሰቡ አንድ ሰው እንደተለዬ ይቆጠራልና የእርሷም መለየት ብዙ ጉድለትን በየቤታችን እንደሚያስከትል የታመነ ነው፡፡ የሁሉንም ነፍስ ይማርልን፤ ይህን ሠራሽ/አልሠራሽ ብሎም አይጠይቅብን፡፡ የሕዝብ ሰዎች እንዲበዙልንና ከጠፋንበት ባድማ መሬት ፈልገው እንዲያወጡን ፈጣሪያችን ይዘዝልን፡፡

የኔ ሀዘን አንዳንዴ ቅጥ የለውምና ይቅርታችሁን፡፡ እናም በያዝነው ወር መጀመሪያ ገደማ በሕይወት እያለ በቁም ሞት የተለየንን የዴምሕቱን ሞላ አስገዶም ነፍስ ፈጣሪ እንዲምርልንና በአብርሃምና በያዕቆብ ነፍሳት አጠገብ እንዲያኖርልን እንጸልይለት – ወዶና ፈቅዶ እንዲያ አልሆነምና፡፡ በሥጋው የሞተ ትልቅ ዕዳ ተወጥቷልና ግልግል ነው፡፡ የሞላና የነሞላ ዓይነቶቹ ሞት ግን የትውልድ መጠቋቆሚያና የታሪክ መዘባበቻ ሆኖ መቅረትን ስለሚያስከትል፣ በዚያም ላይ ቀሪው ቤተሰባቸው በሀፍረት እየተሸማቀቀ አንገቱን ደፍቶ ለመኖር ስለሚገደድ ይህ ዓይነቱ ሞት እጅግ የሚያሰቅቅና ከሆድና ከምድራዊው የዘረኝነት አባዜ ጋር የሚቆራኝ ከፍተኛ ጉዳት አለው፡፡ ሰውን ያህል ትልቅ ፍጡር ውሻ ይመስል ደምና አጥንት እያነፈነፈ የመጨረሻ ነው ተብሎ በሚጠበቅ ወሳኝ ሰዓት ላይ ያመኑትን የዋሃን የትግል ጓኞቹን ከድቶ ወደጎሣዊ ጎራው ከተቀላቀለ ይህ ነገር ከሆድም በላይ ነውና በወዲያኛው ዓለምም በፈጣሪ ዘንድ ሳይቀር ትልቅ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ማንም ወገን ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡ ፈጣሪ የሰውን ልጅ ሲፈጥር ትግሬና አማራ ብሎ ሳይሆን በጎልዳፋው ግዕዜ “ንግበር (?) በአርአያነ ወበአምሳሊነ” ብሎ ከዐፈርና ከምራቅ አዋህዶ ሠራው እንጂ እንደወያኔዎች የደንቆሮዎች ዘፈን የሰው ግርድና አመሳሶ እንዲኖረው ጥቁርና ነጭ ወይም 11 ቁጥርና ዝናር ባገቴ አድርጎ አልነበረም – እነዚህ ቅጥልጥሎች ፍጹም ሰውኛ እንጂ መለኮታዊና ተፈጥሯዊ እንዳይደሉ ለመጠቆም ኮሌጅ መበጠስና ጥናትና ምርምር ማካሄድ አያስፈልግም፡፡ ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያውያንም በዘርና በጎሣ ተለያይተው ሞተው ከዚች ከዓለም የቆዳ ስፋት አኳያ የበሬ ግምባር ከማታክል መሬት የተገኙ የአዳምና የሔዋን ዘሮችን በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በነገድ ለመከፋፈል የተደረገው ከፍተኛ ወያኔዊ ጥረት በእጅጉ ያስደምማል፤ በዚህ ሸውራራ የወያኔ የዘር ቀመር አንዱን ለሞት ሌላውን ለሀብትና ለሹመት ማብቃት ከዘቀጠ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ የሚመነጭና የመጨረሻ ዕጣ ፋንታን ጨለማ የሚያለብስ የርኩሳን መናፍስት የተረገመ ተግባር ነው ፡፡ ይህን የወያኔ የክፋት መንገድ ተከትሎም ሕዝብን መካድና የትግልን መንፈስ ለመበረዝና ለመከለስ መሞከር ከሰውነት ደረጃ የሚያወጣና በቁም ነፍስ ይማር የሚያሰኝ ነውረኛ ድርጊት ነው፡፡ ነገን ለሚያውቅ ሰው አሣፋሪነቱ ወደር አይገኝለትም፤ ችግሩ የዚህ ብልሹ ቲያትር ተዋንያን ሆድ እንጂ ጭንቅላት ብሎ ነገር አልፈጠረባቸውም፤ የአባቶቻቸው የባንዳዎቹ ልጆች ከመሆናቸውም በተጨማሪ እከሌ ከእከሌ ሳይባል የውጪ ጠላቶቻችን ልዑካንና በቀደምት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን የጋራ ትግል ከሽፎ የነበረ ቆይቶና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በተለዬ ሥልት አንሠራርቶ የተከሰተ ኢትዮጵያን የመበታተን ግልጽ ሤራ ለማራመድ የተመረጡ ቅጥረኞች ናቸው፡፡ ቀን የሰጠው ቅል ድንጋይ እንደሚሰብር እነዚህም የባንዳ ልጆች ፈረንጆች የባረኩላቸውና ካለማሽን በዕውቅ የተሰናዳላቸው የክፍለ ዘመኑ ትልቅ ሎተሪ ወጥቶላቸው ለጊዜው ይሠሩትን አጥተው በአረመኔያዊ ድርጊቶቻቸው ውጤት ምክንያት በደስታ ሰክረው ይታያሉ፡፡ የተሰጣቸው ቀን ማለቁን ግን እንኳን እነሱ እኛም ያወቅን አንመስልም፡፡ ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን – ሃያታቸው አልቋል፤ ቁጥባቸው መንምኗል፤ የጀዛቸውን ሊያገኙ ዐውድማቸው ተለቅልቆ ሊበራዩ ጊዜው ደርሷል፡፡ ብሮባጋንዳ እንዳይመስልህ ወንድሜነህ፡፡ ዕድሜ ለምን ብቻ፡፡ “እንዲህ ጨሶ ጨሶ የነደደ እንደሆን፤ ያመዱ ማፍሰሻ ሥርፋው ወዴት ይሆን” ተብሎ በቁጪት የተቀነቀነው ዛሬ በ”ፈሪዎች” ዘመን ሣይሆን የፈጣሪን ፍርድ በማይቀጣጠቡበት የጥንት ዘመን ነው፡፡ Hence, TPLF cannot be an exception, though it is against all exceptions. As a matter of natural bent, nihilists like TPLF are always anti generalizations, including exceptions, taking into account the saying, “All generalizations have exceptions.”

ለማንኛውም በሞላ አስገዶም ፈለግ ለሚመሩ በሀገር ውስጥና በውጪ ላሉ ጭንጋፍ ዜጎቻችን ሁሉ ፈጣሪ ምሕረቱን ሰጥቷቸው ነፍሳቸውን ወደገነት እንዲያስገባላቸው እየተማጠንኩ ወደዋናው ርዕሴ ልግባ፡፡


ሥርዓታዊ መክሸፍ ምን ማለት ነው? ይህች መክሸፍ የምትባል ቃል ዱሮውንም ብትኖርም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም መጻሕፍት ጋር በተያያዘ እዚህም እዚያም በስፋት መነሣት ጀምራለች፡፡ ቃል ትርጎማ ውስጥ ባልገባ ደስ ይለኛል፡፡ ግና መክሸፍ አለመሣካት ነው ከተባለ አለመሣካት ራሱስ ምንድነው ? ለአብነት ጥይት ከሸፈ ሲባል በሌላ አገላለጽ “ቂም አለ” ለማለት ነው፤ “ቂም አለ” ሲባል የጥይቱን ካምሱር የጠበንጃው መዶሻ ተወርውሮ ቢመታውም ጥይቱ ደምብሾ ወይም እንደሰገሌው ጦርነት የንጉሥ ሚካኤል ጦር ጠበንጃዎች ጥይቱ በሻጥር በጎመን ዘር የተሞላ ኖሮ በሚፈለገው ፍጥገት አረሩ ከሙሻዙሩ ወጥቶ የተፈለገው የዒላማም ሆነ የጨበጣ ተኩስ ውጤት አልተገኘም ማለት ነው፡፡ ጥይቱ ተተኩሶ ወይም ባርቆ ዒላማን መሳት ወይም ወደ አሳቻ ሥፍራ ሄዶ አንድም ነገር ሳይመታ መቅረት መክሸፍ አንለውም – መሳት እንጂ፡- “አርሶ መራብና ተኩሶ መሳት፤ እያደር ይፋጃል እንደእግር እሳት” የሚባለውም ለዚህ ነው መሰለኝ፡፡

ከሸፈ ስንል እንግዲህ ከሞክሮ መሳት ባነሰ ደረጃ የሚገኝ አለመሣካት ይመስለኛል፡፡ እንደኔ ደግሞ መክሸፍ ከዚያም የሚያልፍ ነው፡፡ ለምሳሌ መቶ ነገሮችን በቀን ወይ በዓመት የሚያመርት አንድ ድርጅት በዕቅድ ዘመኑ ውስጥ ምርቱን ከመቶ ወደ አንድ ሺህ ለማሳደግ አልሞ ቢነሣና መቶ ሃምሳ ወይ ሁለት መቶ ብቻ ቢያመርት ዕቅዱን አላሣካም – ግን መንገዱን ጀምሯል፡፡ ከሽፏል ማለት የሚቻለን ግን አይመስለኝም፡፡ ለምን ቢባል ቢያንስ ከወትሮው ተሻለ እንጂ አንሶ አልተገኘምና፡፡ አሁንም እንደኔ ዕቅዱ ከሸፈ የሚባለው ምርቱ ከመቶው የቀድሞ ምርት ምንም ሳይጨምር ባለበት ሲቀጥል ነው፡፡ ይህ ድርጅት የነበረውንም የማምረት አቅም አጥቶ ወደ ዜሮ ምርት በመውረድ ለሠራተኛና ለመሳሰለው የደመወዝና የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ እየከፈለ በኪሣራ ከቀጠለስ? ይህን የመክሸፍ ሂደት በምንና እንዴት እንግለጸው? ከነበረው ነገር ላይ አዲስ ነገር መጨመሩ እንዳማረ የሚቀር ሆኖ ያለውን እያጣ ወደኪሣራ የሚነጉድ ድርጅት ወይ ሀገር ምን ሊባል ነው?

የእኛስ ጉዳይ? ሞክረን ከሸፍን ወይንስ ከመክሸፍም በታች ወረድን? የኛን መክሸፍ ለመግለጽ ቃል የምናገኝ አይመስለኝም፡፡ የቋንቋና የሕግ ውስንነቶች ብዙውን ጊዜ ያሳዝኑኛል፤ ያሳስቡኛልም፡፡ ያልነበረንን ጽንሰ ሃሳብ ለመግለጽ ወይም ያልነበረን ወንጀል ቅጣት ለመወሰን በሚያስቸግርበት ጊዜ አንዳንድ ሥራዎች ቀድመው ሊሠሩ ይገባል፡፡ አለበለዚያ ያደናግራሉ፡፡ ዐረብ ሀገር ጭንቅላት የሚያስቀላ ወንጀል ኢትዮጵያ ውስጥ ሦስት ወር ካስቀጣ እኛ ወይም እነሱ የዚህች ዓለም አካል አይደለንም ወይም ከሕግ አወጣጥ፣ አተረጓጎምና አፈጻጻም አኳያ መጠናት ያለበት ነገር አለ ማለት ነው – እንደምሳሌ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ከሰውነት ደረጃ ወርደን፣ ከቀሪዎቹ እንስሳት ደረጃም ዝቅ ብለን ተናጋሪ ግን የማያስቡና ለኅልውናቸው ደንታቢስ የሆኑ ፍጡራን ሆነን በምንገኝበት ሁኔታ ተራው ቃል – መክሸፍ – የሚገልጸን አይመስለኝም፡፡ ግዴላችሁም ሌላ ቃል እንፈልግ፡፡ ለጊዜው ግን ምርጫ ስለሌለኝ ይህንኑ ልጠቀም፡፡

የማይጠራጠሩት ሥርዓታዊ ክሽፈት ገጥሞናል፡፡ የተበላሸነው ከአናት ነው ለማለት ነው፡፡ አናት ሲበላሽ ደግሞ ግርጌም ይበላሻል፡፡ ግርጌም ብቻ ሣይሆን ጎኖችም አይቀርላቸውም – ባጭሩ ተያይዞ መምሸክ ነው፡፡ ሀገርና ቤተሰብ አንዳቸው በአንዳቸው ይመሰላሉ፡፡ ቤተሰብ በልማድ በአባት ይመራል – ቀጥሎ በእናት፡፡ አባትና እናት በፍቅርና በመተሳሰብ ቤተሰባቸውን ካስተዳደሩ ጥሩ ልጆችን የማፍራትና ጥሩ ማኅበረሰብን የመገንባት ዕድላቸው በጣም የጎላ ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ከሆነ ደግሞ ያልዘሩት አይበቅልምና በየትኛውም የአመራርና የአስተዳደር ቦታ የምናገኛቸውን ዜጎች ጨምሮ አብዛኛው የኅብረተሰቡ አባል እንደነዱሽና ኃላፊነት የማይሰማው ይሆናል – በለዘበ አንደበት ስንገልጸው፡፡ አንድን ቤተሰብ ጨዋና ገምቢ የማኅበረሰብ አካል ሊያደርጉት ከሚችሉት ማኅበራዊና ባህላዊ የመንፈስ ሀብቶች መካከል ደግሞ ሃይማኖትና የሞራል ዕሤቶች በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን የግንኙነት ገመዶች የሚበጣጥስ ትውልድ ከመጣና ሥልጣኑን ከተረከበ ደግሞ አዲዮስ ያቺ ሀገር፡፡

እኛን የገጠመን እንግዲህ ይህ ነው፡፡ እርግጥ ነው – ይህ ክስተት በአንድ ወይ በሁለት ዓመት ውስጥ ተረግዞና ተወልዶ አድጎም ለአቅመ-ጥፋት አይደርስም፡፡ ጊዜ ይወስዳል፤ የሂደት ውጤትም ነው፡፡ የኛ የጥፋት ፅነስ መቼ እንደተረገዘና መቼስ ተወልዶ ከምንጊዜው ለዚህ እንዳበቃን አጥኚዎች ሊነግሩን ይችላሉ፡፡ ግን አሠርት ዓመታትን የሚፈጅ፣ ቀድሞ ውስጥ ውስጡን እየቆዬ ግን በሂደት የአባቱን ኮቴ እየለካ አባቱን አንደሚፎካከርና ጠያፍ ተግባር እንደሚያከናውን የዝንጀሮ ልጅ ዓይነት ጥንካሬውን ሲያረጋግጥ ለርሱ ዓላማ ስኬት የማይመቹትን ነባር ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ተቋማት የሚደረማምስ ማኅበረሰብኣዊ ነቀርሣ ነው፡፡ አይሲስን ተመልከቱ፤ ታሊባንን ተመልከቱ፤ ቦኮሃራምን ተመልከቱ፤ አልሻባብን ተመልከቱ፤ … ወያኔም ከነዚህ አጥፊ የዓለም ሕዝብ ጠንቆች አይለይም፤ እንዲያውም በጭካኔ ደረጃው ከነሱ ይብሳል፡፡ ፀረ-ሕዝብ ነው፤ ፀረ-ታሪክ ነው፤ ፀረ-ሃይማኖት ነው፤ ፀረ-ባህልና ትውፊት ነው፤ ፀረ-ዐማራ ነው፡፡ ይህ ሥርዓታዊ ብልሽት በመንግሥት መልክ በሕዝብ ቤተ መንግሥት ለ25 ዓመታት ተቀምጦ የሠራውን የጥፋት ሤራ መዘርዘር ለቀባሪ ማርዳት ነው፡፡ ግን ለትውስታ ያህል በመጠኑ መነካካት ከመነሻችን ጋር ስለሚገናኝ ተገቢ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግና በሌላ ጉዳይ ትንሽ ዕረፍት ቢጤ እናድርግ፡፡

በዚያን ሰሞን የመስፍኔን መጽሐፍ ሳነብ ብዙ የተደበላለቀ ስሜት ተሰማኝና በወቅቱ “ልናገረው ወይንስ አልናገረው? መስፍኔን አስቀይመው ይሆን? በዚህ ሃሳብን በነፃነት መግለጽ እንደነውር በሚቀጠርበት፣ ‹ለትልቅ ሰው መልስ አይሰጥም!› እየተባለ ታናሽ በታላቅ በሚገሰጽበት ማኅበረሰብ ውስጥ የሚሰማኝን ብናገር ከመሰደብና ከመነቀፍ ውጪ ማን ዳምጠኛል?” በሚል ስዋልል ከርሜ ዛሬ ላይ ደረስኩ – አሁን ግን በቁም መወቃቀስ እንደሚሻል አመንኩና ሳልቀድመው ወይም ሳይቀድመኝ መተንፈስን ወደድኩ፡፡ መጽሐፉን የውሻ ጆሮ አስመስዬ በየገጹ ጠምልዬ ጠምልዬ እንዳኖርኩት አሁንም አጠገቤ አለ፡፡ በዚያኑ ሰሞንም አንድ ሁለት ይሁኑ ሦስት ያህል ወጣትና ሽማግሌ ሃያስያንም በመጽሐፉ ዙሪያ የተሰማቸውን አስነብበዋል፡፡ ብዙዎቹን አንብቤያቸዋለሁ፡፡

በቅድሚያ ግን መስፍኔን ለመተቸት የሚያበቃኝ ምንም ዓይነት የሞራልም ሆነ የትምህርት ደረጃ እንደሌለኝ ከወዲሁ መናዘዝ እፈልጋለሁ፡፡ መስፍኔ ከወጣትነት እስከሽምግልና ዕድሜው ለዚህች ሀገር ቆላ ደጋ ሲንከራተትና አሣሩን ሲበላ የቆዬ፣ በየሚያጋጥሙን ጭራቅ መንገሥታትም እየተጎሸመ መከራና ስቃይ ሲወርድበት የኖረ በሣይንሳዊ የክሎኒንግ ጥበብም ይሁን በቡድሂዝም የሪኢንካርኔሽን (ዳግም ልደት) መንፈሣዊ የነፍስ ዑደት ሀገሩ ደግማ ልታገኘው የሚገባት አንደኛ ደረጃ ዜጋ መሆኑን አምናለሁ – ዜጎች በደረጃ ከተቀመጡ፡፡ መስፍኔ ደፋር፣ ሃሳቡን በሀፍረትም ይሁን በፍርሀት ደብቆ የማያስቀርና የሚያምንበትን የሚናገር/የሚጽፍ ሰው ነው – የተባለውንና የሚባለውን በድጋሚ ለማስቀመጥ ያህል ነው፡፡ ዕድሜ ልኩን ለዚች ሀገር ደክሟል፤ ለፍቷል፡፡ ውለታ መመለስ የማትችለዋና የማትፈልገዋ ኢትዮጵያ በዚህ ድንቅ ዜጋዋ የእርጅና ዘመን እንኳን የኅሊናና የአካል ዕረፍት እንዳትሰጠው የተጣባት ሾተላይ ፋታ አልሰጥ ብሏት የጎሪጥ እያየች በወረሩዋት መዥገሮች አማካኝነት በክፉ ዐይን እያየቺው ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ እንደሚባልላት ሣትሆን እጅግ ያልታደለች ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ እንደሀገር ብትበጅልን/ብትሠራልን ኖሮ መስፍኔ በአሁኑ ወቅት በግሩም ሁኔታ የሚጦርበት፣ ሙሉጌታ ሉሌም በሀገሩ ምድር እየተዘዋወረ ውብ ታሪኳን የሚጎበኝበት ጊዜ በሆነ ነበር፡፡ ሁሉም አንጋፋዎቻችን ግን ተገፍተው ወደዳር በመውጣት ለአልባሌ ኑሮ (ይበልጥ ደግሞ ለኅሊናዊ ጉስቁልና)ና ለመንፈስ ጭንቀት ተዳርገዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ትውልዳዊ የሚመስል እርግማን በቶሎ ካልተቋጨ ከአሁኑ የወደፊቱ ያሳስባል፡፡ ስለሆነም ፈጥሮ የማይረሳው የዓለም መድሕን የመከራችንን ደብዳቤ ቀድዶ እንዲጥልልን ከክፋት ተቆጥበንና በፍቅር ተሳስረን እንጸልይ፤ ጉድለቱ ከኛም ነውና፡፡

ወደ መጽሐፉ፡፡ “አዳፍኔ – ፍርሀትና መክሸፍ” በጠቅላላው 280 ገፆች ያሉት በ2007 ዓ.ም የታተመ የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን ታሪካዊ መክሸፍ በግልጽ ቋንቋ የሚያትት የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ኢ-ልቦለድ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉን ማንበብ የብዙዎቹን ችግሮቻችንን መንስኤና ወደ መፍትሔውም እንድናመራ የሚጠቁሙንን ነጥቦች እንድናውቅ ይረዳናል፡፡

ከፍ ሲል እንደጠቆምኩት በዚህ መጽሐፍ ላይ የተሰጡ ትችቶችን ከሞላ ጎደል ሁሉንም አንብቤያለሁ – ጊዜው ቆየት ቢልም፡፡ አንዳንዶቹ ቁጣ ያዘሉ ናቸው – ከአስተማሪነታቸው ይልቅ የስሜት መጎፍነንን ያሳብቃሉ፡፡ የኔ አጭር አስተያየት ከአንዳንዶቹ ጋር ቢመሳሰል ቀድሞም የታዘብኩትና ልጽፈው ያሰብኩት እንጂ ኮርጄ እንዳልሆነ በትህትና መግለጥ እፈልገለሁ፡፡

እውነቱን ለመናገር መስፍኔ ይህን መጽሐፍ በጣም በተጣደፈ ሁኔታ ያሣተመው ይመስላል፡፡ ወጣቱን ትውልድ ለመቅረጽ ከመጀመሪያው የ“ብፁዕ” ዜጋነት ተርታ ከሚገኝ አንድ ምሁር ይህን መሰል የአርትዖት ችግር ያለበት መጽሐፍ አልጠበቅሁም፡፡ መሰላቸትና የዕድሜ ነገር ከሆነም ለሌሎች ሰዎች ማሳየትና ተገቢውን የኅትመት ጥራት እንዲያገኝ ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ መጽሐፍ ኗሪ ቅርስ ነው፡፡ ደጋግሞ በማሳተም ሂደት ስህተቶችን ማረምና ማስተካከል የሚቻል ቢሆንም የመጀመሪያውም ኅትመት ቆንጆ ሆኖ የመውጣት መብቱን ማሳጣት ባልተገባ ነበር፡፡ እንኳንስ ይህን የመሰለ ትልቅ ሀገራዊ ቁም ነገር የያዘ መጽሐፍ ተራ ደብዳቤና አሁን የምጽፈውን የመሰለ ተራ መጣጥፍን እንኳ በአግባቡ ማሰናዳት ተገቢ ነው፤ የአርትዖትን ችግር ማስወገድ አንባቢን ከማክበርና የሙያውን ሥነ ምግባር ከመጠበቅ አኳያም የሚደገፍ ገምቢ ተግባር ነው፡፡ ከዚህ ነጥብ አንጻር ብዙ ህፀፆችን ታዝቤያለሁ፡፡ መጽሐፉ ለዳግመኛ ኅትመት ቢታሰብና ደህና ቀን ቢመጣ በአርትዖት ረገድ እኔም ያቅሜን አስተዋፅዖ ለማድረግ ቃል እገባለሁ፡፡ “ያለውን የወረወረ ፈሪ አይባልም”፡፡ አቀራረብም ከሚቀርበው ነገር ባልተናነሰ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል – “ከፍትፍቱ ፊቱ” እንል የለም?

ችግሮቹ ባጭሩ፡- የሞክሼ ሆሄያት ግድፈት አይነሣ፡፡ ቢቻል እሱንም ማስተካከል ቢሞከር የጽሑፍን ቅርስ ከማስተላለፍ አንፃር ደግ ነበር፡፡ ምክንያቱም የአንድ ፕሮፌሰር ጽሑፍ ለተቀባዩ ትውልድ እንደወረደ በጽድቅነቱ ስለሚሠርጽ እዚያ መጽሐፍ ውስጥ እንደተጻፈው ነው ወጣቱ የሚጽፈው፡፡ ምሳሌ፡- ንጉሱ፣ ሰራዊቱ፣ ምህረት፣ ፅሁፍ፣ … ተብሎ ቢጻፍ ምንም እንኳን መግባባቱ ቢኖርም የተለመደው አጻጻፍ ግን ንጉሡ፣ ሠራዊቱ፣ ምሕረት፣ ጽሑፍ፣ … በመሆኑ የጽሑፋችን ማለትም የአጻጻፋችን ታሪክ በቅጡ አልተላለፈም፡፡ ከተገቢው የቃላት ብዜት አንጻርም መምህራኖች፣ ቀሳውስቶች፣ ቃላቶች፣… እያልን ብንጽፍ ወጣቱ ይሄ አጻጻፍ ወይ አነጋገር ልክ ይመስለውና ይከተለዋል – መሆን የሚገባው ግን መምህራን/ራት(መምህሮች)፣ ቀሳውስት/ቄሶች፣ ቃላት/ቃሎች … ነው፡፡ ይህን ችግር በዚህ መጽሐፍ ለማየት መሞከር ቅንጦት ነው፡፡ በእውነት በሩጫ የተሠራ የሚመስልና የችግሮቹ መንስኤም ሊገባኝ ያልቻለ መጽሐፍ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

የፊደላት ግድፈት በፈረንጆቹ (spelling error) የሚሉት በብዛት ይስተዋላል፤ የ“ፎንት” (የሆሄ ቅርጽና መጠን)ም አለመላው የመዘበራረቅ ነገር ይስተዋላል፤ የሥርዓተ ነጥብ ችግርም አለ፡፡ ገጽ 3 ላይ “ዕዳውን የሚከፍል ትውልድ አ[እ]ስቲመጣ…” የሚለውን ጨምራችሁ ውስጡን ስትገቡበት ብዙ የአርተዖት ችግሮች አሉ፡፡ ከመጽሐፉ ምሳሌ በማምጣት አንባቢን ላሰለች አልፈልግም፡፡ መጽሐፉን በማንበብ የምጠቃቅሳቸውን ስህተቶች ማጤን ይቻላል – ረዳቶችን በማፈላለግ አለመሳሳት እየተቻለ ለምን ይህን ያህል የጎላ ስህተት ተፈጠረ እያልኩኝ ነው እንጂ ሰው አይሳሳት የሚል አቋም ኖሮኝ እንዳልሆነ ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡
የሃሳብ መደጋገም በስፋት ይታያል፡፡ ለምሳሌ ስለአቢቹ አንድ ሁለት ቦታዎች ያህል አንቀጹ እንዳለ ተደግሞ ተጽፏል፡፡ ሌሎችም አሉ – እንዳሉ በ “ኮፒ/ፔስት” የተደጋገሙ ሃሳቦች አልፎ አልፎ አሉ፡፡

ማውጫው ላይ ያልተጠቀሰ በውስጥ ገጽ ገን የተገለጸ የአንድ ሰው አስተያየት አለ – ገጽ 202 የሚገኘው የክፍሉ ሁሴን ትችት፡፡ አሁንም በማውጫው ትችት አንድ፣ ትችት ሁለት ከተባለ በኋላ ትችት ሦስት ሳይኖር ትችት አራት ነው የቀጠለው – ተችት አምስትም አልተጠቆመም፡፡ ገጽ 5 ማውጫው ላይ በግርጌ አካባቢ “ERROR! BOOKMARK NOT DEFINED.” የሚል ምንነቱ የማይታወቅ ጽሑፍ አለ፡፡ ምንድነው? ምናልባት የአርታዒ አስተያየት ይሆን? ከቋንቋ አጠቃቀም አንፃርም ግዴለሽነትን ታዝቤያለሁ – ለምሣሌ አንድ ቦታ “አንቀጽ” ማለት እየተቻለ የቃል ውይይት(colloquial) ይመስል “ፓራግራፍ” እየተባለ ተጽፏል፡፡ አልገባኝም፡፡

ከገጽ 165 ጀምሮ መስፍኔ በቀደመው መጽሐፉ ላይ የቀረቡ ትችቶችን እንዳሉ አስቀምጧል- የደጋፊም የገሳጭም፡፡ የደገፉትን የሚያወድስበት የነቀፉትን የሚኮንንበት የመጽሐፉ ክፍልም አለው፡፡ እዚህ ላይ ነው የኔም ስሜት የጠየመው፡፡

መስፍኔ ዐዋቂ ነው፡፡ የማኅበረሰባችን ዋልታና አርአያሰብ (icon) ነው – በብዙ ነገር፡፡ እዚች አካባቢ ባነበብኩለት የአታካራ እሰጥ አገባ ግን አልተደሰትኩለትም – እኔን ማስደሰት የሚያስደስተው ከሆነ፡፡ መስፍኔ ከልጆች ጋር እንካስላንትያ መግባት አልነበረበትም፡፡ ማስተማር ሲገባው እንደልጆች ሆኖብኛል፡፡ ዕድሜና ዕውቀት ጥበብን ያላብሳሉ፡፡ ጥበብ ደግሞ ከሀሙራቢያዊ የጥርስ ለጥርስ “ህገ -አራዊት” አውጥታ ወደ ኅሊናዊ የማመዛዘንና በአስተዋይነት የመራመድ ምህዋር ታስገባለች፡፡

እዚህ ላይ ታዲያ መስፍኔን ምን እንደበላብኝ ባፈላልግ አጣሁት፡፡ በሚዲያ ሲጠቅሳት የሰማሁለት እልኸኝነቱና ቁጡው ባሕርይው ገዝፎ ወጣና መስፈኔን ደበቁት – ንባን ቀጥዬ ብዙ ብጠብቀውም በስተርጅና ከሸፈተበት ኢትዮጵያዊ የመበቃቀል ጫካ ሊወጣልኝ አልቻልኩም፤ እኔስ ማን ነኝና! ንድድ አይለኝ መሰላችሁ? አንደበትና ዕድሜ ሲዋዋጡ ደስ ይላል፤ ያኔ አፈንጋጭን የሚያርምና ወደመስመር የሚያስገባ የተባ ብዕር ይወለዳል – ትውልድን የሚቀርጽ፣ የመነቋቆርን አዙሪት በጣጥሶ የሚጥልና አቅል የሚያስገዛ ታጋሽና አስተዋይ ብዕር፡፡

አንድ ወቅት እንዲህ ሆነ አሉ፡፡ በደርግ ጊዜ ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ከአንድ አሜሪካዊ ፈረንጅ ጓደኛው ጋር በአዲስ አበባ ውስጥ አንደኛው ቡና ቤት ይዝናናሉ፡፡ ሀበሻው ፈረንጁነን ፡- “የኢትዮጵያ መንግሥት ‹ኢምፔሪያሊዝም ይውደም! የአሜሪካን ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም በጠንካራው ክንዳችን ተገርስሶ በምትኩ ዓለማቀፋዊ ወዛደራዊነት ይገነባል!› እያለ በየአደባባዩ በግልጽ ሲፎክር አሜሪካ እንዴት አስችሏት ዝም አለች?” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ፈረንጁም “አየ ሞኜ፣ አሁን አንድ ሕጻን መጥቶ ‹እናትህ እንዲህ ትሁንልህ! እከካም፣ አህያ..› ብሎ ቢሰድብህ ከርሱ ጋር ቦክስ ትገጥማለህን?ስትገጥምስ ብትገኝ ሰው አይስቅብህም?” አለው ይባላል፡፡

መስፍኔ መናደድህ ጥሩ ነው፤ አንተ ራስህም “ተናደዱ፤ ካልተናደዳችሁ ትርጉም ያለው ሥራ አትሠሩም” የሚል ቃና ያለው መልእክት ስታስተላልፍ የሰማሁህ ወይም ያነበብኩህ መሰለኝ፡፡ ስንናደድ ግን ገደብ ሊኖረን አይገባምን? እስኪ ዐይንህን ጨፈን አድርገህ ከአንድ ውራጅ አድናቂህ አንደበት የፈለቀችን ይህችን አስተያየት በጥሞና አሰላስላት፡፡ እቀጥላለሁ… መክሸፋችን ዙሪያገባውን መሆኑንም ዐውጃለሁ፡፡ ስንከባበር እንደማመጣለን፤ ስንደማመጥም መከባበራችን በሂደት ይከሰታል – ያኔ መግባባት ይፈጠራል፡፡ እንደሚባለውም ያኔ ባለመስማማታችን ራሱ ልንግባባና በልዩነቶቻችን ሣይቀር የጋራ ተጠቃሚዎች ልንሆን እንችላለን፡፡

መስፍኔ ታምራት ነገራንና ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን የወረፈበት መንገድ ቢለወጥልኝ በወደድኩ፡፡ ይህን የምለው እነዚህ ወገኖች መስፍኔን አላስከፉትም ለማለት ፈልጌ ሣይሆን “ልጆቹን” ሊያስተምር የሚችል የተለዬ አቀራረብ ከመስፍኔ እጠብቅ ሰለነበረ ነው፡፡ እንደነሱው እንደልጆቹ ስሜታዊና አንጓጣጭ መሆን ይቻላል – ስሜታዊና አንጓጣጭ ሆነው ባልተገባ መንገድ አቃቂር ሰጥተው ከሆነ፡፡ ነገር ግን መማማር የሌለበት እንዲሁ የመደናቆር ዐውድ ይፈጠርና ሲካሰሱና ሲወነጃጀሉ መኖር ነው፡፡ ለምሳሌ ዲ. ዳንኤል ክብረት መጠራት በሚፈልግበት ስም መጨቃጨቅ ተገቢ አይመስለኝም – ሲፈልግ ‹ሊቀ ጳጳስ› ብላችሁ ጥሩኝ ቢል የመጥራትና ያለመጥራት መብቱ የጠሪው ሆኖ ሣለ ስለመጽሐፍ ትችት መልስ ለመስጠት ያ የግል ጉዳይ ከዚህኛው የትችት ጉዳይ ጋር ተጣልፎ ዒላማን በሳተ መንገድ ሰውን ለማነወር እንደግብኣት መገልገል ተገቢ አይመስለኝም፤ እንደዚያ ከሆነ “እንዴት አደራችሁ?” ለሚለው የሰላምታ ጥያቄ መልሱ “ተልባ እየዘራን ነው” ሊሆን ነው፡፡ ስለስብዕናዎች መነታረክና መወዛገብ ከዋናው አጀንዳ የሚያስወጣ ይመስለኛል፡፡ ስለአፍንጫ እየተነጋገሩ “እግርህ ወልጋዳ ነው” ቢባል የየጁ ደብተራ ሠራው የተባለውን የጎደለ ቅኔን የማሟያ ታሪካዊ ቀረርቶ እንደመድገም ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ከትልቅ እስከ ትንሽ – ከልሂቅ እስከ ደቂቅ – የሚጎድለን ብዙ ነገር አለ፡፡ መቼ እንደምንስተካከል አይገባኝም፡፡ ወደ ቁጣና ወደንዴት የሚሮጡ የአንጎላችንን ክፍሎች ፈጣሪ እንዲገርዝልን እንጸልይ፡፡

ስለ “ልጆቹ” አለመማርም (“ስለማይምነታቸው”) ብዙ ብሏል – መስፍኔ፡፡ ከንዴት ንግግር ብዙም አሳልፌ እንዲገባኝ አልፈለግሁም፡፡ እነዚህ ሰዎች ከፋም ለማም በንባብም ይሁን በትምህርት ገበታ ዕውቀት ሸምተዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ይነስም ይብዛም ሙያ አላቸው፡፡ በዚያም ምክንያት አረረም መረረም በሙያቸው ሀገራቸውንና የሚገኙበትን ትውልድ እያገለገሉ ይገኛሉ – በግልቡ የትምህርት ሥርዓት ጨርሰው የግልብ ዕውቀት ባለቤት መሆናቸውም እነሱን የሚያስወቅስ ሣይሆን መስፍኔንና እኔን ጎምቱውን ዜጋና እኛን ያፈራው የከሸፈ ሥርዓት በኃላፊነት የሚያስጠየቅ ነው – ጠያቂ ካለ፤ ራሳችንም ተዋናይ በሆንበት የትውልድ ኪሣራ ትውልዱን ብቻ መውቀስ የትም የሚያደርስ አይመስለኝም – ጲላጦስ እጁን በመታጠቡ ከኃጢኣቱ እንዳልነፃ ተምረናልና፡፡ ሲያጠፉ መምከርና መገሰጽ የአባት ወግ ሆኖ ሳለ ታናናሾችን በአሽሙርና በአግቦ ለሌሎች አሽሙረኞችና አግቦኞች አሳልፎ መስጠት ተገቢ አልመሰለኝም፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ አልታደልንም፡፡ መማማር መቼ ይጀመር? እነሱ ከኛ ከታላላቆች ምን ይማሩ? አሽሙርን? ምፀትን? ሽሙጥን? እኮ ምን? … በዚህስ በውነት ከፍቶኛል፡፡ አሁንም እንዲህ ስል “ልጆቹ” የሠሩት ትክክል ነው እያልኩ አይደለም፤ ሁሉም መታረም ባለበት ይታረም ነው የኔ አብባል፡፡ ለማንኛችንም እኔን መሰል ተራ ዜጎች የሚጠቅመንን አንድ ምክር ልጠቁም – ስህተትን ለማረም ቅድመ ሁኔታው ቀናነትና የአንጎልን በር በ“ዕወቅት ይበቃኛል” የደናቁርት ጓጉንቸር ጠርቅሞ አለመዝጋት ነው፤ በቃ፡፡ የመማሪያ ቀን መቼ ናት? ብለን ደግሞ እንጠይቅ፡፡ አንድ ሰው ተፀንሶ፣ ተወልዶና አድጎ ይቺን ምድር እስኪሰናበት ያለው ጊዜ ሁሉ ላደለው መማሪያ ነው – በጥናቶች መሠረት ማሕጸን ውስጥ እያለም ጭምር ማለቴ ነው፡፡ ዕውቀት በቅቶት የሞተ ሰው ደግሞ የለም፡፡ ይበልጥ ያወቅን በመሰለን ቁጥር ይበልጥ ያላወቅን ያህል ካልተሰማን ደደብን እንጂ አላወቅንም፡፡ ጊዜ ካገኘሁ መስፍኔ ስለሚያራምዳቸው የማልወድለት አንድ ሁለት አቋሞቹም ትንሽ መተንፈሴ አይቀርም፡፡ ከዚያ በፊት ግን ከፍ ሲል በይደር ባቆየነው የሥርዓታዊ ብልሽት/መክሸፍ ዙሪያ ትንሽ ዕረፍት እናድር፡፡

ሥርዓታዊ ክሽፈት በለዬለት መልኩ ከገጠመን ሩብ ምዕተ ዓመት ሆነ፡፡ መንግሥት የለንም፡፡ እንደነገሩም ቢሆን ቀደም ሲል የነበሩን መንግሥታዊ ሥርዓቶች ቀስ በቀስ እየበሰበሱና እየበከቱ መጥተው በግንቦት 20 ቀን 1983 ዓመተ ፍዳ ላይ ለይቶላቸው ግብኣተ መሬታቸው ተፈጸመ፡፡ ሁላችንም እንደምንረዳው የመንግሥቶቻችን ወረደ መቃብር የተከናወነው በ83 ይሁን እንጂ ህመማቸውና ጣረሞታቸው የጀመረው ግን ከዚያን ጊዜ በፊት ነው፡፡ የህመማቸው ዋና መንስኤ ብዙዎቻችን አዘውትረን እንደምናወሳው የኛ የኢትዮጵያውያን ግላዊ የሥልጣንና የሀብት እንዲሁም የዝና ወዳድነት ጠባይ ሲሆን ከዋናነት የማይተናነሰው የታሪካዊ ጠላቶቻችን ሤራ ደግሞ ሌላኛው ነው፡፡ ይሄ መከረኛ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖትና አሁን አድፍጦ የአብቅቴውን ኮከብ እየቆጠረ ያለው “ዐማራነት” ባመጡባት ተዝቅ የማያልቅ ዕዳ ኢትዮጵያችን የመከራ ገፈት ቀማሽ ሆና መቅረቷ የተደበቀ አይደለም፡፡ ዐማራነቱን የማያውቀው ዐማራ የራሱን ነገዳዊ ማንነት ከኢትዮጵያዊነት ጋር – ምናልባትም ሲያቀብጠው – ጨፍልቆ ፍዳውን ማየት ከጀመረበት በተለይ ደግሞ ከጣሊያን ወረራ ወዲህ እሱንና ለአንድነት ጽናት ዋና አብነት እንደሆነ በጠላቶቻችን ዘንድ የሚታመንበትን የኦርቶዶክስን ሃይማኖት ከምድረ ኢትዮጵያ ለማጥፋት እነስም አይጠሬ ያልፈነቀሉት ደንጊያ የለም፤ በመጨረሻው ግን የሥነ ልቦና ቁስላቸው እንደቂጥኝ ውርዴ ከዘር ወደ ዘር ተላልፎ አንጎላቸው ውስጥ እያመረቀዘ በበቀልና በጥላቻ አብደው የሚኖሩ የቀድሞ ባንዳዎች ልጆች በግላጭ ተገኙና ሁለቱንም የኢትዮጵያ ባለውለታዎች ድራሻቸውን ማጥፋተ ቻሉ – ለጊዜው፡፡ ይሁንና የተነሣ ይወድቃል፤ የወደቀም ይነሣልና የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ሁሉም የየመክሊቱን አያጣም፡፡ There is a time for hibernation as there is time for aestivation. ላፎንቴ የተባለ የፈረንሣይ ጸሐፊና ባለቅኔ ተናግሮታል እንደተባለው “Patience and passage of time do more than strength and fury.” እኛም “የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም” እንላለንና የኩበት ዘመን አልፎ የወርቅ ዘመን ሲብት የመገፋታችንን ያህል እንካሣለን፡፡ ስንዴ ካልተዘራ አይበቅልም፤ ካልበቀለም አያፈራም፤ ካላፈራም ኃይለ-ሰብዕን አያፀናም፡፡ እናም የታሪክን ፍርድ በኩራት የምንመሰክርበት ዘመን አፍታ ሳይቆይ ይመጣል – ቃል ነውና፡፡ ቃሉም የነበረና ያለ የሚኖርም ነው፡፡ ግን ግን ከበቀልና ከተመሳሳይ የጥላቻና የመጨራረስ አዙሪት እንዳንገባ ሁላችንም እንጠንቀቅ፡፡ አንጎል እንጂ ጠበንጃ የማይሠራበት የዕውቀትና የማስተዋል ዘመን እንዲብልን ከጉልበት ይልቅ ለአስተሳሰብ ዕድገት ቅድሚያ እንስጥ፡፡ በቀል ሁልጊዜ የሚወልደው የተሻሻለ በቀልን ነው፡፡ የተሻሻለ በቀል ደግሞ የከፋ በቀል ማለት ነውና ከአዙሪቱ መውጣት ይከብዳል ብቻ ሣይሆን ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ቀን ሰጠኝ ብሎ ቂም በያዙበት ላይ ጥቃት ማድረስ ወያኔን መሆን ነው፤ ወያኔን መሆን ማለት ከእንስሳነትም መውረድ ነው፡፡ እንስሳት እንኳን የቋጠሩትን ቂም ረስተው ከሰው ጋርም ሆነ ከመሰሎቻቸው ጋር በፍቅር ይኖራሉ፡፡ ወያኔዎች ግን የጣሊያን ጊዜውን በአባቶቻቸው ላይ በአርበኞች እንደደረሰ የሚነገረውን የውርደት ማቅ እስካሁኒቷ ደቂቃ ድረስ ሣይረሱ በተለይ ዐማሮችን እንደባብ እየቀጠቀጡ ይገኛሉ፡፡ ምድረ ዐማራም ያልጠበቀቺው የቂም ቋጠሮ ቁልል እየተፈታ ሲለበልባትና ዘር ማንዘሯን እያነፈነፈ ሲጨፈጭፋት ከኢትዮጵያዊነት ውጪ ያዘጋጀችው የዘር ከረጪት የላትምና ይሄውና ጊዜ እስኪያቃናት በክልሶቹ በነሣሞራ የኑስ አከርካሪዋ ተሰባብሮ ኤሎሄ እያለች ትገኛለች፡፡ “አርቀን የቀበርነውን ዐማራ ለምን ለቦርድ አባልነት ትመርጣላችሁ!” የሚል የጦር ኤታ ማዦር ሹም የሚገኘውና በዚህም አስነዋሪና ከአንድ የጦር “ጄኔራል” የማይጠበቅ ንግግሩ ከመከሰስ ይልቅ የሚሸለምባት ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ መሆንዋን ዛሬ ባይቻል ነገ በድንቃ ድንቅ ነገሮች ማስፈሪያ መዝገብ (ጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ) እንደሚመዘገብ በበኩሌ አልጠራጠርም፡፡ ይለፍ እንጂ ሲያልፍ የምናወራው ብዙ ዝግንትል ታሪክ አለን – በአሣፋሪነቱ ወደር የማይገኝለት፡፡

ሥርዓታዊ ክሽፈቱ በብዙ ምናልባትም በሁሉም መስኮች እየታዬ ነው፡፡ ሃይማኖቱ ከቁንጮው ጀምሮ ሞቷል፡፡ ከዘርና ከነገድ ወይ ከቋንቋ አታያይዙት፡፡ የትኛውም የሃይማኖት አባት ለሥጋ ፈቃድ ተሸንፎ የኅሊናን ሚዛን ሰባብሮ ጥሏል፡፡ ያልጣለው አንድ ነገርን ብቻ ነው፤ እሱም አለባበስና መስቀል አያያዝን ነው፡፡ ጸሎቱ ሙሉውን ሌሊትና ሙሉውን ቀን ሲዥጎደጎድ ያድራል፤ ይውላልም፡፡ ግን ሁሉም ከንቱ ነው፡፡ ማንኛውም ምህላም ሆነ ጸሎት መንበረ ፀባዖት ሊደርስ ይቅርና ኢትዮጵያዊው “ወጣት ሣይንቲስት” ከየምናምኑ ለቃቅሞ የሠራት ሚጢጢዬ አውሮፕላን ለመብረር ያደረገችውን ሙከራ ያህል እንኳን ወደሰማይ አይወጣም፡፡ ማንን እናታልላለን? በእውኑ በጸሎት እርዝመትና በቅርጻዊ ክርስትና እግዚአብሔርን ማሞኘት ይቻላልን? ማንኛውንም የክርስትና ሃይማኖት ግንድና ቅርንጫፍ ተመልከቱ፤ ሁሉም መሣቂያ ናቸው፡፡ ዲያቆኑን፣ ቄሱን፣ ደብተራውን፣ ዘማሪውን፣ ሰባኪውን፣ ጳጳሱን፣ ኤጲስ ቆጶሱን፣ ሊቀ ጳጳሱን፣ ሊቀ ማዕምሩን፣ ሼሁን፣ ፓስተሩን፣ ምዕመኑን ሣይቀር ተመልከቱ፡፡ ከሞላ ጎደል ሁሉም ሃይማኖትን እንደሸቀጥ ቆጥረዋታል፡፡ “ጧት ተመርቶ ከሰዓት መርካቶ” ሲባል የሰማነው ለላቭሊ ብስኩት ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ለሃይማኖት ሆኗል፡፡ ጧት ከአንዱ ቅርንጫፍ ትገነጠልና ከሰዓት በኋላ የራስህን ሃይማኖት ወይም “ቸርች” የሚሉትን ዘመነኛ ፈሊጥ (እንደታምራት ላይኔ) ታቋቁመና ይህን የፈረደበትን በኑሮ ጭንቀት ምክንያት ይገባበትን ያጣ ምዕመን ናላውን እያዞርክ ትቦጠቡጠዋለህ፤ ገንዘቡንም፣ ሚስቱንም፣ ቆነጃጅት ልጆቹንም እየቀማህ በማማገጥ “ክርስቶስንም ሴቶች ያገለግሉት ነበር” እያልክ ኑሮህን ታዘምናለህ፤ ብትከሰስና ብትወቀስ ከሰሞነኛ ወሬነት ሳያልፍ በ“ሃይማኖተ አበው” ጉድህ ተሸፍኖልህ መደበኛ የስብከት ወይም የዘማሪነት ሥራህን ትቀጥላለህ – ምክንቱም ክሽፈቱ ከአናት ነውና፡፡ ኃጢኣት የዘመናችን የጽድቅ መንገድ ሆናለች፡፡ እግዚአብሔር ተረስቶ ገንዘብ እየተመለከ ነው፡፡ የኖኅና የሎጥ ዘመን የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ነው የምንገኘው፡፡ ቢያወሩት አያልቅም ወዳጄ፡፡ ግን አትወነባበድ፡፡ በምታምነው ረግተህ ጊዜውን ጠብቀው፡፡ ከአናት ሥርዓታዊ መክሸፍ እንደገጠመን ተረዳና በነፈሰው ዐውሎ ንፋስ ሁሉ ላለመወሰድ ራስህን ከመጥፎ ነገር አቅበህ ኑር፡፡

ቤተ መንግሥት ግባ – ዳሩ ማን ያስገባሃል እንጂ፡፡ የተያዘው በከሸፉ ዜጎች ነው፡፡ በዘረኝነት በታወሩ፣ በማይምነት ጥቁር ካባ በተጀቦኑ፣ በሆዳምነት የጅብ ቆዳ በተለበጡ፣ በጥጋብ ሞራ መላ ሰውነታቸውን በተሸፈኑ መናኛ ሰዎች ቤተ መንግሥቱ ተቀስፎ ተይዟል፡፡ ርቦህ ብትጮህ በጥጋብ ይመነዘራል፤ ተጨቁነህ ብትጮህ የነፃነት መብዛት እንዳናፈለህ ይደሰኮርልሃል፤ በሽታ ተጠናውቶህ በጣር ስታቃስት የልማቱ ተቋዳሽ ሆነህ በጥጋብ ቁንጣን እንደተበገርህ ይወራልሃል፤ መብራትና ውኃ አትተህ በዳፍንት ስትርመጠመትና በውኃ ጥም ስታልቅ ሀገርህ ካደጉ ሀገሮች ተርታ ልትሠለፍ ሣምንታትና ቀናት ብቻ እንደቀሯት ይሰበክልሃል፤ በኑሮ ውድነት እየተጠበስክ እሪ ብትል በምቾት እየተናጥህ ድሎት እንደሰለቸህ ይነገርልሃል፤ በማይምነት ደዌ ተለክፈህ ወደ አዘቅት የሚያዳፉህን ትርዒት ገልብጠው ወደጨረቃ እየመጠቅህ እንደሆነ ያናፉልሃል፣ በዘረኝነት ጨንገር እየተገረፍክ ያለህበትን የአድልዖ ሥርዓት ከምናባዊው የመንግሥተ ሰማይ የኤደን ገነት ጋር አስተካክለው በተጨፈን ላሞኝህ ለራስህ ይሰብኩልሃል፣ … ሥርዓታዊ መክሸፍ ከዚህ በላይ የለም፡፡ በውሸት ተገንብቶ በውሸት የበከተ ሕንፃ ውስጥ የሚኖር የገለማ ሥርዓት ሊወልድ የሚችለው እርሱን መሰል ፍጡር ነው፡፡ ስለሆነም በየምትሄድበት መሥሪያ ቤት የሚገኘው የበሰበሰውና የከሸፈው ሥርዓት ወኪሎች ከሞላ ጎደል ሁሉም እርሱን ይመስላሉ፡፡ ከእባብ ዕንቁላል እርግብ አይጠበቅም፡፡ ሽንት ቤት ተቀምጦ ደግሞ ፈስ ገማኝ አይባልም – ተከተል አለቃህን፣ ምታ ነጋሪትህን፡፡ አዲዮስ ሥርዓት፡፡ አዲዮስ ሀገር፡፡ የበላ ሮጠ፤ የሮጠም አመለጠ፡፡

በትምህርቱ ዘርፍ ግባ፡፡ የአባታቸውን የአቶ ሴክተር ሪቪውን ኹዳድ የሚከተሉ የባንዳ ልጆች ማንም ተምሮ ቁም ነገር እንዲሠራና ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ስብዕና እንዲላበስ አይፈልጉም፡፡ ስሙን መጻፍ የሚችል ትውልድ መፈጠሩ ራሱ ያናድዳቸዋል፡፡ ስለሆነም ብልሽቱና ክሽፈቱ ሥር ነቀል እንዲሆን የማይበጥሱት ቅጠል፣ የማይምሱትም ጉድጓድ የለም፡፡ እመነኝ – እኔም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ መምህር ነበርኩና የምለው ነገር ከማንኛውም እውነት በላይ የሚዘገንን ሀገራዊ ክስተት ነው፡፡ ስማቸውን የማይጽፉ ተማሪዎች በተለያዩ የሙያ መስኮች በመጀመሪያና በሁለተኛ እንዲሁም በሦስተኛ ደረጃ የዲግሪ መርሐ ግብሮች በ“ማዕረግ እየተመረቁ” የሥራውን ዓለም በማጥለቅለቅ ላይ ናቸው፡፡ የሚገርምህ አለማወቃቸው የማያሳፍራቸውና ባለማወቃቸውም ከመኩራት አልፈው የማይቆጩ የትውልድ ፍሬዎች እየመጡ ነው፡፡ ነገን ፍራልኝ፡፡ የወያኔዎቹ ልጆች ራሳቸው በድንቁርና እየገፉ በሀብት ግን እየወፈሩ በሕዝብ ደም እንደመዥገር እያበጡ ገና ከአሁኑ ሊፈርጡ ደርሰዋል፤ ቻይናም ይማሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የወላጆቻቸው ድንቁርና ተዛምቶባቸው እነሱም በጭቅላነታው አሥረሽ ምቺውን ለመዱና በኢክዝኪዩቲቭና በራቭ “መኪኖቻቸው” የከተማዋን ዳንስ ቤትና ቆነጃጅት ሲያዳርሱ ነው የሚያድሩት፡፡

በግል ት/ቤቶች ከሚማሩ ተማሪዎች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የወያኔ ልጆች እንደሆኑ ይነገራል፡፡ እንዲህም ሆኖ ትምህርት የማይገባቸውና በጧቱ በየዝጉብኝው የሚልከሰከሱ የመጥረቢያ ልጅ መዘለፊያ ሆነዋል፡፡ ያልተለፋበት ሀብት በደናቁርት እጅ ሲገባ አባትም እናትም ልጅም ሁሉም ተያይዘው የጥፋትን መንገድ ይከተላሉ እንጂ ወደጥበብና ማስተዋል አምባ የሚያቀኑት በጣም ጥቂት ናቸው – ጭራሽ የሉም እንዳይባል ያህል ብቻ፡፡ ስለዚህ በትምህርቱ ዘርፍ ተስፋ አይኑርህ – ከጥቂት ግላዊ ጥረቶች በስተቀር የትምህርት ነገር ሞቶ ተቀብሯል፡፡ እርግጥ ነው – ወረቀት በሽበሽ ነው፡፡ ከአንድም ሶስትና አራት የታቀፈ ልታገኝ ትችላለህ፡፡ ዕድሜ ለፎርጅድ፣ ዕድሜ ለወሸከሬው የትምህርት ሥርዓት፣ ዕድሜ ለገንዘብህ በዚህ የማስመሰል ዘመን ዲግሪና ዲፕሎማ እንደመያዝ ቀላል ነገር የለም – ልክ እንደመንጃ ፈቃድ እቤትህ በፖስታ ታሽጎ ሊደርስህ ይችላል፡፡ የምትፈልገውን ተናግረህ በገንዘብህ በእጅ እየሄድህ ማስፈጸም እንጂ ለምን ብለህ መጠየቅ ፋራነት ነው፤ የሚጠይቅህ “ባላገር”ም የለም፡፡ “እሹ ታገኛላችሁ፣ አንኳኩ ይከፈትላችኋል” የሚለው መጽሐፍ ቅዱሣዊ አስተምህሮ ተለውጦ የወያኔን ቤት ማንኳኳት ባህል ሆኗል፡፡ ከዚህ በላይ ሥርዓታዊ መክሸፍ የለም፡፡

ወደሐኪም ቤቶች ጎራ በል፡፡ ከካርድ ጀምሮ ባልተወለደ አንጀት ይሞሸልቁሃል፡፡ አንዳንድ ቦታ ለካርድ ብቻ ከአንድ ሺህ የኢትዮ. ብር በላይ ለመክፈል ትገደዳለህ፡፡ ክኒን ከጨመርክ ቆጠራው በመቶዎች ሣይሆን በሺዎች ነው፡፡ ሞራልና ሃይማኖት በገንዘብ ስለተለወጡ ሐኪሙም፣ ቀጣሪውም ዐይናቸውን የሚበለጥጡት ኪስህ ላይ ነው – ያንተ መሞትና መዳን ሁለተኛ ጉዳይ ነው፡፡ በመኪናው እየሮጠ ገብቶ በትንሽ የቀዶ ህክምና ሰበብ ሕይወቱን ያጣና ዘመዶቹ መጥተው 20 ሺህ ብር አካባቢ ከፍለው – ማለትም የልጃቸውን ሬሣ ገዝተው – የሄዱበትን ታሪክ በግሌ ዐውቃለሁ፡፡ እያንዳንዱ የግል ሐኪም ቤት ቄራ ነው፡፡ በሰላ ቢላዎ አንተንም ጥሪትህንም አርዶ ባዶህን ያስቀርሃል፡፡ ለተራ አለርጂክ ብትገባ የማይታዘዝልህ የምርመራ ዓይነት የለም – የሚያቆማቸው ያንተ ቤት ተሸጦ በረንዳ አዳሪነትህ ወይም በቃኝ ብለህ ወደሚቀርብህ ጠበል መጓዝህ ብቻ ነው ወንድሜ፤ ወለም ብሎህ ስትሄድ አክታ እንድትመረመር ብትመረመር ምን ትላለህ? ለብጉንጅ ሕክምና ሄደህ ወንዱን ልጅ የእርግዝና ምርመራ እንድታደርግ በስህተት ብትታዘዝ ምን ታደርጋለህ? ለህመም ማስታገሻ አንድ መርፌ ብትወጋ የወር ደሞዝህን አስረክበህ ትወጣለህ፡፡ ዘመናዊ ምርመራማ አትሞክረውም፡፡ በአንድ የግል ክሊኒክ ወይ ሆስፒታል ከምታድር መታመምህ ከፋ እንጂ በአንድ እግር ሼራተን ብታድር በጣም ይረክስልሃል፡፡ ባለቤትህ እንድትወልድ ወዳንዱ የግል ጤና ተቋም ብትሄድ ሕጻኑንም እነሱ የሰጡህና ማሳደጊያም የሚቆርጡልህ ይመስል የሚያስከፍሉህ በአሥር ሺዎች ነው – ፎጣ ዘርግቶና እትብት መቁረጫ መቀስ ይዞ ለመጠበቅ ነው እንግዲህ ይህ ሁሉ ክፍያ፡፡ ጉድ ሆነንልሃል፡፡ ቦሃ ላይ ቆረቆር እንዲሉ የሀኪሞቹ የችሎታ ማነስ ችግር ደግሞ ለወሬ አይበቃም፤ ደም ሲያይ የሚሸሽ የህክምና ዶክተር ሞልቷል አሉ፡፡ የዱሮው ረዳት ጤና መኮንን ከአሁኑ እስፔሻሊስት ዶክተር በስንት ጣሙ፤ በስመ ህክምና በቅጡ ባልተማሩ ሀኪሞች ምክንያት እየተረፈረፈ ያለው ሕዝብ ብዙ ነው፡፡ በዚህና በተጓዳኛ ምክንያቶች የተነሣ ጠንቋይ ቤቶችና መጣፍ ገላጮች ሰው በሰው ሆነዋል፤ የዋሁ ደግሞ ጠበሎችን የሙጥኝ ብሎ ጠጠር ቢወረወር ማረፊያ የላቸውም – የሚገርመው ከጤነኛው በሽተኛው መብዛቱ ነው፤ ዕድሜ ለወያኔ ቢያንስ የጨጓራ በሽተኛ ያልሆነ ሰው አታገኝም – ደም ግፊትና ስኳርማ እንደደርግና ወያኔ ወታደራዊ የመኮንንነት ማዕረግ ሹመት በ“ከዚህ መልስ” የተረጨ ነው የሚመስል፡፡

ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እግር ጥሎህ ብትሄድ የታወቀ ሰው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ቅድሥት ሥላሤ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ ያለህ ይመስልሃል፡፡ ጤነኛ ሆኖ እቤቱ የቀረ ሰው ያለ አይመስልህም፡፡ በአንጻራዊ አነጋገር የመንግሥት ተብዬዎቹ ሆስፒታሎችና የጤና ኬላዎች በዋጋ ርካሽ ናቸው፡፡ ጥራታቸው ግን ዜሮ ነው፡፡ “እኔ እኮ አይደለሁም ጭንሽን እንድትከፍቺ ያደረግሁሽ …” የምትልን “የጨዋነት ሥነ ምግባር” የተላበሰች አዋላጅን ጨምሮ ያልታዘዘለትን ታማሚ ሰው በስህተትና በግዴለሽነት መርፌ በመውጋት ነፍስ የሚያጠፉ ሀኪሞችና ነርሶች በተለይ በመንግሥት የጤና ተቋማት እንደሚበዙ ይነገራል፡፡ የሙያ ሥነ ምግባር ይቅርና የሙያ ችሎታ እጅግ የወረደ መሆኑ ተወርቶ ተወርቶ ያለቀ ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉም ዜሮ ዜሮ፡፡ ተቋማቱም ዜሮ፣ “መንግሥት”ም ዜሮ፣ ሕዝቡም ዜሮ፡፡ ሁሉም ዜሮና የዜሮ ድምር ሆኖ ዐረፈው፡፡ ሀገር እንዲህ መቀለጃ ሆነች፤ ከዚህ በላይ ሥርዓታዊ ክሽፈት የለም፡፡

የግል ህክምና ጣቢያዎች ውድ ቢሆኑም የሰው ደም መጣጮች የሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣኖችና ሀብታም ነጋዴዎች ስላሉ ገቢያቸው አይቀንስም፡፡ የኛን ገንዘብ ይጭነቀው እንጂ እኔ ወደዘብር ገብርኤል ጠበል ስሄድ ነጋዴውንና ባለሥልጣኑን ወደ ቅዱስ ገብርኤልና ሃያት ሆስፒታሎች እልካለሁ – እንዲያውም ከአነስተኛ ሀብታሞችና ድሃ ታካሚዎች የውስጥ ዕቃ በኅቡዕ እየተዘረፈ ሀብታሞችና ባለሥልጣኖች እንደሚተከልላቸውና የተዘረፈባቸው ሰዎች እንደሚሞቱ ከአንድ ሁነኛ ምንጭ አረጋግጫለሁ (አሁን አልናገርም)፡፡ በጥቅሉ ግን በአሁኑ ወቅት ሰው እንዴት እንደተጨካከነ ብታይ በተረት ተረት የሰማኸው የዱሮው ኢትዮጵዊነት ይናፍቅሃል፡፡ ከላይ ሥርዓቱ የተበጀበት ጅማትና ቆዳ አንዴውኑ ከጅብና ከዓሣማ ስለሆነ ሁሉም ቦታ የምትሰማው ድምፅ የምግብ ማላመጥ ነው፡፡ ኅሊና ጠፍቶ ሆድ ነግሦኣል፡፡ (በነገራችን ላይ የዘንድሮው ሞት በጣም አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡ ታምሞ መሞት ብርቅ እየሆነ ነው፡፡ ትናንት አብሮህ ያመሸው ጓደኛህ ሌሊቱን ሞቶ በማግሥቱ ቀብር ልትጠራ ትችላለህ፡፡ የቅስፈት ዘመን ሆነ፡፡ ለንስሃ ሞት መብቃትም ዱሮ ቀረ፡፡ የሚገርም የጥድፊያ ዘመን! ኑሮው ሩጫ፣ ተቀምጠህም ሩጫ፣ ተኝተህም ሩጫ፣ በእውንህም በህልምህም ሩጫ፣ ሞትህም ሩጫ፡፡ ከዚህ ይሠውርህ ወንድሜ! ከዚህ ይሠውርሽ እህቴ!) ብቻ ሥርዓታዊ ክሽፈቱን ከዚህ ከፍ ሲል ከጠቀስኩልህ የህክምና ሁኔታ አንጻርም እንድትመለከተው ልጠቁምህ እፈልጋለሁ፡፡

ወደ ንግዱ ገባ በልና ፈትሽ፡፡ ዛሬ መናጢ ድሃ የነበረው ሰው ዛሬ ማታ እጅግ ቢዘገይ ነገ ጧት የናጠጠ ሀብታም ሆኖ በዐይኑ ቂጥ ቢያይህ አትከፋ – ሥርዓታዊ ክሽፈቱ የፈጠረው ኳሻርኳራዊ የዕድገት ነጸብራቅ ነው፡፡ ዋናው ኅሊናን የማሣመኑ ነገር ነው፤ በዚህ አትቅና፡፡ የምትቀና ከሆነ ደግሞ በዘርህ ወይም ጤፍ የሚቆላ ምላስ ካለህ በተመቸህ መንገድ የተግማማው ሥርዓት ጋ ጠጋ በልና የድርሻህን ነጨት አድርገህ ዘወር በል – ዕድለል ከቀናህ ያልፍልሃል የዐይንህ ቀለም ካስጠላቸውም ሰዎች የሆኑትን ትሆናለህ፡፡ የሆነው ቢሆን ግን በዘረኝነት ልክፍት ካልታወርህና እንደቢጠቴዎችህን ህግንና ሥርዓትን እየጣስህ በንግድ ስም ካልዘረፍህ ከድህነት አትወጣም፡፡ ወደንግድ ማዕከልህ ስትሄድ ኅሊናህን ቤትህ ውስጥ አስቀምጠህ መሆን አለበት፡፡ በንግድ ዋጋና ሚዛን ላይ ማጭበርበሩ እንዳለ ሆኖ ጥራትን አፈር ደቼ በማብላት የሚታፈሰው ትርፍ ቁጥር አይገልጸውም፡፡ ከዚህ አንጻር የምንበላው ዘይትና ቅቤ የትና ማን እንደሚሠራው እኛ ከመገመት ውጪ እውነቱን የሚያውቀው አንድዬ ብቻ ነው፡፡ አለማለቃችንም የርሱው ዕርዳታ ታክሎበት እንጂ እንደነጋዴዎቻችን ስግብግብነት ቢሆን ኖሮ አንድ ክረምትም አንዘልቅም ነበር፡፡ ሥጋው ከምን እንደተሠራ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ሆኖ አንድ ኪሎ ተብሎ የሚሰጥህ አኞ ሥጋ ከግማሽ እልፍ ቢል ነው፤ በሚዛን ወይም በሜትርም ይለካ፣ በሊትርና በጣሣም ይሠፈር ፣ በክንድም ይመተር እቤት ስትገባ ግን ተሸቅቦ ታገኘዋለህ፡፡ ጓደኛ ጓደኛን፣ ወንድም እህቱን፣ ልጅ አባቱን፣ እናት ልጇን፣… በሚያምት እየማሉ ጭምር በንግድ ስም በስፋት የሚያጭበረብሩባት ብቸኛዋ የአፍሪካ ሀገር ኢትዮጵያ ትመስለኛለች፡፡ ይህን ለመቆጣጠር የተመደበ የይስሙላና እስትንፋሱ በሙስና የሚንቀሳቀስ ተቋም ሊኖር ቢችልም በእውነቱ ግን በያገባኛል ሀገራዊና ሕዝባዊ ወገንተኝነት ስሜት ከመስመር የወጣ የንግድ እንቅስቃሴን ተከታትሎ የሚያስካክል አካል የለም፡፡ ሥርዓታዊ ክሽፈት ከዚህ የበለጠ ካለ ንገሩኝ፡፡

በንግዱ ውስጥ ህግን ጠብቀህ ልነግድ ብትል አንድ ጀምበር አትቆይም፤ ከሳስረህ ዕዳ በዕዳ ሆነህ ወደ በረንዳ ትጣላለህ ወይም እንደአንዳንድ ዜጎች የሦስት ብር ገመድህን ገዝተህ ወደሚቀርብህ ዛፍ ትሄድና ትንጠለጠላለህ – ይህንንስ ለጠላትህም አይስጠው ልጄ፡፡ ነጋዴው መንግሥት ተብዬውንና ሕዝብን እያጭበረበረ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ይከብራል፡፡ ዕቃን ማስወደድ አሁን አሁን በሴከንዶች ውስጥ የሚከሰትና በአንድ ኣዳር ሰዎችን ወደ ሀብቱ ጫፍ የሚያስወነጭፍ ልዩ ቢዝነስ ሆኗል፡፡ የአንዳንድ ሰዎችን የገንዘብ አወጣጥ ስትመለከት- በድግስና በቤት አሠራር ወይም በሚገዙት ዕቃ ሲታዩ – ገንዘቡን ከዛፍ የሚሸመጥጡት ወይም የገንዘብ ማተሚያ ማሽን ያላቸው ነው የሚመስሉት፡፡ እኔማ ይገርምሃል በአንዳንድ ፅዱና ቅንጡ የከተማችን ክፍሎች ስሄድ ግማቱ አላሳልፍህ እያለኝ እቸገራለሁ፡፡ በውስጡ ያለው የሙስናና የተበላሸ አሠራር ስለሚሸተኝም እንደሆነ እንጃ ግን በነዚያ መንደሮች ሳልፍ ጥምባት ክርፋቱ አያስኬደኝም፡፡ እንዲህ ያለ ምናባዊ የግማትና ክርፋት ስሜት የማይሰማኝ እውነተኛ መጥፎ ቁሣዊ ሽታ ባለባቸው የቁጭራ ሠፈሮች አካባቢ ሳልፍ ነው፡፡ በነዚያ አካባቢዎች ሊከረፋ የሚችል የሰው ደምና ወዝ እምብዛም ስለሌለባቸውና ንጹሓን ዜጎች፣ ምንዱባን የእምዬ ከርታታ ልጆች በመሆናቸው ከአፍንጫ አልፎ አንጎሌን ሊበክል የሚችል መጥፎ ጠረን አላገኝባቸውም፡፡ የነጋዴውን ነገር ግን አታንሱት፤ በፈርንሣይ ኮሎኝ ሽቱ ቢታጠብም ግማቱ አጠገቡ አያደርሳችሁም፡፡ ተግባራቸው በርግጥም የክፉ ክፉ ነው፡፡ ስለሀገርና ስለሕዝብ ማሰብ አቁመዋል፡፡ ለሠራተኞቻቸው እንኳ ከውሻና ድመቶቻው ያነሰ ነው የሚጨነቁላቸው፡፡

የመቶ ብሩን ዕቃ በስልክ እየተመሣጠሩ በአንዴ ሁለትና ሦስት ሺህ ብር ሲያደርሱት ስታይ የአንዲት ሀገር ዜግነትህን ስሜት ጎማምደው ይጥሉብህና ራስህን እንደመፃተኛ እንድትቆጥር ያደርጉሃል፡፡ ዜጋ ለዜጋ ካልተሳሰበ ደግሞ የአንድ ሀገር ሰው መሆን ትርጉሙ እምን ላይ ነው? ችግር ሲመጣ ግን ቀድሞ የሚደርሰው ድሃው ነው፤ መንግሥት ተብዬው የወያኔ ጉጅሌም ወገናዊነቱ ለሀብታሞቹ ነው፤ ሀብታሞቹም አሁንም ማንም እንደሚያውቀው የአንበሣውን ድርሻ የሚወስዱት ሰሜነኞቹ ወንድምና እህቶቻችን ናቸው፡፡ ባድመ ላይ የተረፈረፈው ዜጋ የትኛው ነው? ግሩም ዓለም! ግሩም የጋራ ሀገር፤ ቢያወሩት አያልቅም ጎበዝ፡፡

ማኅበረሰቡን ጓዳ ጎድጓዳውን ገብተህ ብትቃኝ ዋናው የክሽፈቱ አቀንቃኝ ሆኖልሃል፡፡ ሀዘኑ ቁጩ፣ ልቅሶው ቁጩ፣ ዝምድናና ጓደኝነቱ ቁጩና ከጥቅም ጋር የተገናኘ፣ ድግምቱ ትብታቡ ደንቃራው፣ መተቱ፣ መጠላለፉ፣… ልዩ ነው፡፡ ተስፋ ያስቆርጥሃል፡፡ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሠላሣ ሃይማኖት ብታገኝና ሁሏም የጎሪጥ ስትተያይ ብትታዘብ የስምንተኛውን ሺህ መድረስ እያስታወስህ የዐርባ ቀን ዕድልህን ከመራገም ውጪ ሌላ አማራጭ የለህም፡፡ ፍቅር ታጥባ ገደል መግባቷን ስትረዳና ትዳርም ፍቅረኛነትም “የፉጌ” መሆኑን ስትገነዘብ ራስህን ይዘህ በምሬት ትጮሃለህ – ጩኸት አንዳች መፍትሔ ይሰጥህ ይመስል፡፡ ወንድማለም ዕንባ ደግሞ ዱሮ ቀረ፡፡ በቀደም ለት እንዲህ ሆነልህ፡- እንዲህ – አንድ ሽማግሌ የግቢያቸውን ቤቶች ተቀራምተው ከሚኖሩ የገዛ ልጆቻው ጋር ይኖራሉ፡፡ ሚስትና ተንከባካቢ የላቸውም፡፡

ይርባቸውና አንዲቷን ልጃቸውን ጠርተው “ራበኝ ልጄ፤ እባክሽን የምቀምሰው ነገር ስጪኝ” ይሏታል፡፡ “በገንዘብህ ገዝተህ አትበላም!” ትላቸውና ጥላቸው ወደ ጉዳይዋ ትሄዳለች፡፡ የሠፈር ልጅ አስጠርተው ወደሱቅ በመላክ ሙዝ አስገዝተው ወስፋቸውን ይሸነግላሉ፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ግን ወዲያው ይሞታሉ፡፡ ልጆችና ጎረቤቶች ይሰበሰቡና የቀብሩ ሰዓትና ቦታ ይወሰናል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከልጆቻቸው አንድም ሰው የሚያለቅስ ይጠፋና የውሻ ሬሣ ያስቀመጡ ያህል ሁሉም ዝም ዝም ይላል፡፡ ቀብሩ እንደተፈጸመ በልዩ ልዩ ሱሶች ተጠምደው ከሰውነት ተራ የወጡት ልጆቻቸው ጫታቸውን በየጉያቸው እየወተፉ ወደየክፍላቸው ይገባሉ – ልክ ከቀብር መልስ፤ ራሱ ጉድ እየተባለለት የሚገኘው ቀባሪና መንደርተኛም አገጩን በመዳፉ ይዞ ጉድ አለ፡፡ በየቦታው የምንታዘበው የልቅሶና የሀዘን አጋጣሚ እንደዱሮው ከአንጀት ሣይሆን ዛሬ ዛሬ ከውርስ ጋር በተገናኘና ከአንገት በላይም ነው፡፡ ኧረ እናት አባቱንም ለሀብት ብሎ የሚገድል ሞልቷል! በወሲብ ረገድም እዚህ የማይወራ ስንትና ስንት አስጸያፊ ድርጊት እየሰማን ነው – ማውራት የሚቀፍ፡፡ … የደረስንበት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዝቅጠት ተነግሮም ሆነ ተጽፎ አያልቅም፡፡ ምን ይብጀን?

አሁን ደግሞ የት እንግባ? … የትም ግባ ያው ነው እባክህን፡፡ ሥርዓታዊ ክሽፈቱ ያልዳሰሰው ቦታና አካባቢ የለም፡፡ በመጀመሪያ ግን የተመታውና ከኅልውና ውጪ የሆነው ሰው መሆን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሰው አትቆጠርም፡፡ ሰውነትህ ከተመታ ደግሞ እንደእንስሳ ያገኘኸውን እያመነዠክህ ከመኖር ውጪ አትተሳሰብም፤ አትተዛዘንም፤ አትረዳዳም፤ በስሜት ቋንቋም አትግባባም፡፡ ወደዐውሬነት ተለውጠሃልና፡፡ ዐውሬ ደግሞ ሆዱ እንዳይጎድል ሲብስበት እርስ በርሱም ቢሆን እየተበላላ

ነፍሱን አውሎ ያሳድራል እንጂ የአእምሮ ብስለት አይጠበቅበትም፡፡ ወይ ጉዳችን!

ከፍ ሲል ወዳንጠለጠልኳት የመስፍኔ ጉዳይ ልግባና ጽሑፌን ከመጀመሬ በፊት ልጨርሰው፡፡

መስፍኔ እንዲያ ሲል ፍርሀቱ ይገባኛል፡፡ ፍርሀቱን እጋራለሁ፡፡ ግን መስፍንዬ ያበዛዋል፡፡ ሰዎች እንደሚሉት በሚስቱ ትግሬነት እንዲያ ይላል ብዬ ማመን ደግሞ አልፈልግም፤ እርሱን በዚህ ማማት ከንቱነት ይመስለኛልና፡፡

“ትገሬዎች በወያኔ አልተጠቀሙም”፡፡ ይህች የመስፍኔ አቋም በጣም ገራገርና በብድር የምታስቅ ናት – አሁን ይስቀውና ያገጠው የሌለው፡፡ ምን ማለት ነው? እንዲህ ማለቱስ ማንን ይጠቅማል? ማንንስ ይጎዳል? ከተፈለገ እኮ ወደዚያ ጥያቄ መግባት ላያስፈልግ ይችላል፡፡ በእውነት አንገትን አርዶ መግደልና በሀሰት እውነትን ሸፋፍኖ ሰውን በከንቱ ለማስደሰት መሞከር ሁለቱም አንድ ናቸው፡፡ መስፍኔ እርግጠኛ ነኝ – የፍቅር እስከ መቃብሩ ካሣ ዳምጤ አሽከር የነበረው ሰውዬ ዘመነኛው ካሣ ስሙን ሊለውጥለት ሲሞክር ከወያኔዎች በጣም የሚሻለው (ሰጠኝ መርቆ/ፈረጃ?) “አይ፣ ገቶች፣ ሶቹ ማቁኝ በፈረጃ ሲለሆኔ አሁኒ ዕዝራ ቢል ይስቁብኛል” ያለው ወዶ እንዳልነበር የሚያስታውሰው ይመስለኛል፡፡ ያለማንነት ማንነት መስጠት ለትዝብት እንደሚዳርግ ማወቅ ይገባል፡፡ “ለምን ይዋሻል?” የሚለው የሠይፉ ፋንታሁን ፕሮግራም አሁን አለ ይሆን?

“የተከበሩ ዶክተር፣ ወንድን ልጅ ወደሴትነት ለውጦ አርግዞ እንዲወልድ ማድረግ ይቻላል ወይ?” ብሎ አንድ ወቅት አንድ ጋዜጠኛ የሕክምና ባለሙያውን ይጠይቃል – ቀደም ካለ ታይም ወይም ሌላ መጽሔት ላይ ያነበብኩት እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ “እርግጥ ነው ይቻላል፤ ግን ‹አስፈላጊነቱ ምን ያህል ነው› የሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት አለበት፡፡” ነበር ያለው ዶክተሩ ሲመልስ፡፡ እውነት ነው – ሴቶች ድንገት ተነስተው “ከእንግዲህ ወዲያ ልጅ አንወልድም!” ብለው ማኒፌስቶ(መጋለጫ) ቢያወጡ ልክ ነው ወንድን ፆታውን ቀያይሮ እንዲወልድ ማድረግ ይቻል ይሆናል፡፡… እንዲህ ዙሪያ ጥምጥም የምሄደው “ትግሬዎች በዚህ ሥርዓት አልተጠቀሙም!” ብሎ ትከሻን እየሰበቁ ወገብን እያረገረጉ መከራከር ጥቅሙ ምንድነው? የሚለው ነገር ግራ ስለሚያጋባኝ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ የነኦባማ “አትጠይቅ/አትናገር” የምትለዋ መመሪያ ለኛ የዘረኝነት ዘመናዊ ደዌ በምትስማማ መልክ ተገልብጣ ወደኛ ብትመጣና ብንጠቀምባት ደስ ይለኛል – do not ask, do not tell. እንጂ አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር የሚለው በወያኔ “ትግሬ አልጠተቀመም”ም ሆነ መስፍኔና መሰሎቹ የሚያንቀራብጡት ይሄው የሞኝነት የመከራከሪያ ነጥብ ጉንጭ አልፋ እንጂ ውኃ የሚያነሣ አይደለም፡፡ ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ፡፡ እንዲህ ብሎ መናገር በራሱ ፈረንጆቹ adding an insult to injury እንደሚሉት ነው፡፡ መንግጎ ማባስ፡፡ አንዱን ያስደሰቱ መስሎ በሌላው ቁስል ሚጥሚጣና ጨው መነስነስ – ያገጠጠ ደረቅ እንጨትም ያለአንዳች ርህራሄ መሰካት፡፡

እንግዲያውስ የተጠቀመው በማይምነት ዶፍ ተመትቶ ሀሁን እንኳን ሳያውቅ በየደረሰበት እንዲጨፈጨፍ በወያኔና ጀሌዎቹ ክተት የታወጀበት ዐማራው ይሆን? (“ሞረሾች” እንዳይቀየሙኝ እንጂ መስፍኔ “ዐማራው የለም “ የሚለውን አቋሙን በተወሰነ ደረጃ ስለምጋራው ያን አሁንና ለጊዜው አልነካበትም!) በመርፌና በክትባት መልክ አምካኝ መድሓኒት እየተሰጠው ያለቀው፣ ኤች አይ ቪ የያዘው የወያኔ ጭፍራ ከያለበት በወረንጦ እየተለቀመ ዐማራው ወደሚኖርባቸው ክልሎች እንዲላክና በሥውር በታወጀ ጦርነት እንዲያልቅ የተፈረደበት ዐማራ ይሆን የተጠቀመው? ከግንቦት ወር 1983 ዓመተ ፍዳ ወዲህ ከየመሥሪያ ቤቱ በመብራት እየተፈለገ ተለቅሞ ከሥራ እንዲፈናቀል፣ በየሰበብ አስባቡ እሥር ቤት እንዲታጎር፣ እንዲገረፍና እንዲጋዝ፣ ካለፍርድ በድብቅ እንዲረሸንና በድኑ በየጉድባው እንዲጣል የተደረገው ዐማራ ይሆን የተጠቀመው? (አደራ ዐማራ ነን የምትሉ ሰዎች የምለውን ሁሉ ለጸሎታችሁ ማድመቂያ እንጂ ለበቀላችሁ ማጎልበቻ እንዳታደርት በሞተ ዘመዳችሁ አጥንት ይዣችኋለሁ፡፡ በቀል የእግዚአብሔር ናትና ለርሱ ተውት፡፡ በቀል ለመለስ የመንፈስ ዘመዶች ለሩዋንዳዎቹ ሁቱና ቱሲም አልበጀም፡፡ በቀል የሰይጣን ቀኝ እጅ ናት – ይቅር ባይነትና ምሕረት ግን የእግዚአብሔር ነው፡፡ የበደል ሰምበር የሚጠፋው በበቀልና በነገር ቁርሾ ሳይሆን በይቅርታና በፍቅር መስፈን ነው፡፡ አሁን የምለውን የምለው እውነቱ ተደብቆ ለምን በውሸት እንደለላለን ከሚል ነው፡፡ ባይቆጭ ያንገበግብ፤ በሚስቴ በኩል ቢሆንም እኮ “ዐማራ” ነኝ! ለነገሩ እንደኔው በሚስቱ ዐማራ የነበረው መለስስ መች ራራላቸው? ወይ ዕድላቸው! በምን ቀን ተፈጥረው ይሆን?)

ውድ መስፍኔ ዐማራውን እንተወው፡፡ አዲስ አበባን ዞረህ ዐይተሃታል ለመሆኑ? ሀብቷን፣ መሬቷን፣ የጥቅማጥቅም ቦታዋን፣ ሥልጣኗን፣ … ማን ነው ለብቻው የተቆጣጠራት? ትግሬ አልተጠቀመም ነው የምትለኝ? አራዶች ቢሆኑ “ሄይ! ፕሮፍ አይሰማም ባክዎን!” ይሉህ ነበር፡፡ ቅጽሎችን እንዳስፈላጊነቱ መጠቀምም የወግ ነው፡፡ “ሁሉም ትግሬ ተጠቃሚ አይደለም” ቢባል ጥሩ ማምለጫና እውነትም ነው፡፡ በተረፈ ዐይን አይቶ ልብ ይፈርዳልና ይህን ነገር መስፍኔ ቢቻልህ ይቅርታ ጠይቀህ አቋምህን ለማስተካከል ሞክር – ይህን የምትለው ለምንም ዓላማ ይሁን ግን በደል ነው፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ይቅር የማይለው ትልቅ በደል፡፡ ስሜትም አይሰጥም፡፡

የት ነው እየኖርን ያለነው? አንዳንዴ እደነግጣለሁ፡፡ ሰዎች የሚናገሩት እውነት ይሆን እንዴ? እልና ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ ሰዎች ለአንድ እውነት ያለን ግንዛቤም ያስገርመኛል፡፡ እኔ ለምሳሌ በዚህ መጣጥፍ ውስጥ የምለው ሁሉ ለኔ እውነት ነው፡፡ ለአንዳንዱ ደግሞ ነጭ ውሸት ሊሆን ይችላል፡፡ ለሌሎች ደግሞ ግነት የበዛበት ግን መጠነኛ የሆነ መነሻ እውነት ያለው እንደሆነ አምኖ ሊቀበል ይችላል፡፡ ግን ግን እውነት ምንድናት? መኖሪያዋስ የት ነው? የኔ? ያንተ? የርሷ? ወይንስ የነሱ? ለመሆኑ ዲዮጋን አልሞተ ይሆን?

እውነት የፈለገችውን ትምሰል ኢትዮጵያ ውስጥ የምኖርና ስለዘመኑ መቅሰፍታዊ የአፓርታይድ አገዛዝ ብዙ ነገር ዐውቃለሁ ብዬ አፌን ሞልቼ የምናገር ሰው በዚህ ዘመን “ትግሬ አልተጠቀመም” ሲባል ብሰማ በትንሹ አድርባይነት ሲሆን ከፍ ሲል ደግሞ ድንቁርና ነው፡፡ ድንቁርና ደግሞ የፊደል ገበታን ከመለየትና ካለመለየት ጋር ግዳዊ ግንኙነት የለውም፡፡ ድንቁርናን ከማይምነት ካመሳሰልነው ማይምነትንም ካለማወቅ ጋር ካቆራኘነው አንድን ነገር የማወቅና ያለማወቅ ጉዳይ ከማወቅና ካለማወቅ ጋር ብቻ እንጂ በግድ ከዲግሪና ከሠርቲፊኬት ጋር ሊያያዝ አይችልም፡፡ ስለሆነም እኔን መሰሎች በፊደል ላይ የሸፈትን ምሥኪን ወገኖች ከምንሰማው ሣይሆን ከምናየውና ከሚደርስብን መሪር እውነታ ተነስተን የማተባችንን – ሃቁን ብንናገር ሊፈረድብን አይገባም ባይ ነኝ፡፡ እናም መላዋ ኢትዮጵያ በወያኔ ጀሌ እግር ተወርች ተቀፍዳ ሀገርና ወገን በዋይታ እየነፈረቀና በአድልዖ ከእናቱ ሞሰብ እየተገለለ ባለበት ሁኔታ “ትግሬ አልተጠቀመም” የሚሉት ሥልት አልባ ዘፈን የዓዞ ዕንባ አንቢዎች የሚያቀነቅኑት የጆሮ ታምቡርን የሚጠልዝ የሰካራም ዘፈን እንጂ ሊቀበሉት የሚቻል ሚዛን የሚደፋ ነገር አይደለም፡፡ እውነት ነው እውነት ትጎመዝዛለች፤ ትመራለችም – ይህን በሚገባ እረዳለሁ፡፡ ግን ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ ስንት ቀን በዚህች ምድር እንደምቆይ አላውቅም፡፡ ስለዚህም ዋሽቼ ራሴንም ሆነ ሌሎችን ላግባባና ላባብል አልሞክርም፡፡ የዶሮ ማታ ዘመን አለፈ፤ መተሬም ይሁን ኮሶ ስኳር እያላሱም ቢሆን መጨለጥ ነው፡፡ ደግሞስ ለየትኛው ዓለም ብለን እንዋሻለን? ብዙዎቻችን አልገባንም እንጂ አልቋል እኮ፡፡ ምኑ ነው ያለቀው? ዓለምን በምናብህ ቃኛት፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ ቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት የሚገኘውን “የትግራይ አየር መንገድ” ተመልከት፡፡ ጆሮ ያለው ሰው ይስማ፡፡ የተማረ የሌላ ነገድ ሰው ጠፍቶ ሣይሆን እነዚህ የመርገምት ልጆች ሁሉንም ነገር መቆጣጠር ስለሚፈልጉ ይህ ዝነኛ አየር መንገድ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ በትግራይ ሰዎች እጅ ነው፡፡ ከዘበኛ እስከ ዋና ሹም ወያኔ ነው፡፡ የሚገርመው በዚህ አየር መንገድም ሆነ በሌሎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚመደቡ ተጋሩ ቢቻል የተማሩ ቢሆኑ የሚመረጥ ሲሆን የተማረ ከሌለ ማይሙ እንደወረደ ከትግራይ ተጠርቶ ይመደባል፡፡ ሥራውም በዚያው ልክ ብልሽትሽቱ ይወጣል፡፡ መስፍኔም ሆነ ሌላ ሰው ከስሜት ሕዋሳቴ አይበልጡም፡፡ ስለሆነም እነግራቸዋለሁ፡፡ ቦሌንና አካባቢውን የአቪየሽን ሴክተር አንድ አላችሁ አይደል? “የትግራይ አየር ኃይል”ንም አትርሱ! ድፍን ንፍጣም ወያኔ የሚጋግርና የሚያቦካውን የኢትዮጵያን ምርጥ ምርጥ ተቋማትንም በእግረ መንገድ አስቡ፡፡ ወያኔዎች ለምን ሥልጣን ያዙ የሚል ቅሬታ በጭራሽ የለኝም፡፡ ችግሬ በማይም ድፍረታቸው ሀገር አጠፉ፣ ዘረኝነቱ ቅጥ አጣ፣ በሌሎች ነገዶች በተለይም ዐማራ በሚባለው የእግዜር ምሥኪን ፍጡር ላይ የጭካኔ ብትራው በዛ፣ ወዘተ. የሚል ነው፡፡ እንጂ ሀገር በፍትሃዊ መንገድና በዕውቀትና በጥበብ ማስተዳደር ቢችሉማ ኖሮ ምን አሳጣኝ ብዬ እንቅልፌን ትቼ በደረቅ ሌሊት ስጨነቁር እገኛለሁ?(9፡05)

ንግዱን ማን ነው የተቆጣጠረው? ማን ነው ካለቫት የሚነግደው? ማን ነው በከፍተኛ የቤት ኪራይ ሰበብ እየተፈናቀለ ለስደትና ራስን ለማጥፋት ፈተና የሚዳረገው? ማነው በመንግሥት ውስጥ በሚገኝ ሌላ ሥውርና ነፃ መንግሥት እየተጠቀመ ሌላውን ግን እየበደለ ያለው? አቶ ዳዊት ብሎ ብሎ “ትግራይ እንደሌሎች ክልሎች አልተጠቀመችም” ብሎ በድፍረት መናገሩ ምን ለማለት ነው? የትኛውን ክልል ተዟዙሮ ጎብኝቷል? አሁን ይሄ በውነት ያቀባብራል? በአድሏዊው የወያኔ ብልሹ ሥርዓት ሸወርራ አገዛዝ ምክንያት (በተለይ የተማረ) ሰውም ልማትም ሣይኖራቸው ባድማ ሆነው ዐይጥ መፈንጪያ የሆኑትን የዐማራ ክልል ከተሞችን ዞር ዞር ብሎ ጎብኝቶ ይሆን? የትግራይንስ ት/ቤቶችና ሆስፒታሎች፣ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች የትኛው ክልል አስገብቶ ሊያስቆጥራቸው ነው? ይሄ ይሉኝታ የሚሉት ነገር ከወያኔ ውድብ ሲወጡም አይለቅም ልበል? ምን ዓይነት መረገም ነው! ደግሞስ የትግራይ ንግድ ቤቶች በዐማርኛ ማስታወቂያ ቢለጥፉና ወጣቶች ዐማርኛ ዘፈን ቢያዳምጡ ጥፋቱና ጉዳቱ ምኑ ላይ ነው? ባይሆን እንደ አንድ ትልቅ ሰውና የሀገር ሽማግሌ “የናንተንም ባህላ ቋንቋ አትርሱ፤ የጋራውንም ተከባክባችሁ ያዙ” ይባላል እንጂ እንዴት የወል ቅርስን በመጠቀማቸው ሊወቀሱ ይገባቸዋል? (ይህን ያዙልኝ – ቀድመው ይጠሉሻል፤ በኋላ ግን አንቺን በመጥላታቸው ይጸጸቱብሻል፤ ሊያገኙሽ ቢመኙም አይቻላቸውም! ኦሮምኛ እንዲህ ያለ ግሩም ተረት አለው -“ይሆናል ቢሉን አህያ አረድን፤ አይሆንም ቢሉን ጠራርገን ጣልን፤ እንዴ፣ ይሆን ነበር እኮ (ለምን ጣላችሁት) ቢሉንና ወደጣልንበት ብንሄድ አጣነው”፤ ይህም ይሆናል!!)

መከላከያን በሙሉ የተቆጣጠረው ማን ነው? የኔ ጓደኛ በዐማራነቱ ብቻ – ሊያውም ዐማራነቱን ያሳወቁት እነሱው ራሳቸው ናቸው – ከገቡ ጀምሮ በእንትንነት መደብ እየሠራ ሲገኝ ጓደኞቹ ትግሬዎች ግን ዛሬ በንግድና በጦሩ ውስጥ ቢጠሯቸው የማይሰሙ ቀጭን ጌቶችና የመሀል አገሩን ሰው የሚያሽቆጠቁጡ የጦርና የሲቪል ባለሥልጣኖች ናቸው፡፡ አንወሻሻ! የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከታች እስከላይ ማን ነው የሚዘባነንባቸው? ምድረ ማይም ወያኔ አይደለም እንዴ በሌላው ላይ ነግሦ ያለ? የሀገሪቱን ሀብትና መሬት እንደልቡ የሚፈነጥዝበት ትግሬ መሆኑ ቀረ እንዴ? ለመጽናኛነት ከጠቀመ – አላውቅም – አንዳንድ የመሀል አገሩ ዓይነት ይሉኝታና ሀፍረት የያዛቸው ትግሬዎች እንደኛው መሰቃየትን መርጠው በእውነተኛ ገቢያቸው እየኖሩ እንደኛው የሚሰቃዩ አሉ፡፡ በየዕድሩና በየሠፈራችን የምናውቃቸው ከደሙ ንጹሕ የሆኑና በነገይቷ ኢትዮጵያ ተገቢ ሥፍራቸውን የማያጡ ትግሬዎች መኖራቸው የሚዘነጋ አይደለም – ይህም የሆነው በራሳቸው ፈቃድና ከወያኔ ይሁንታ ውጪ እንጂ ማንም ከልክሏቸው አይደለም፤ የፈቃድ ፆም እየፆሙ ነው፡፡ ትልቅ ዋጋ አላቸው፡፡ የአባትህ አገር ሲወረር አብረህ ውረር ቢሉ እኛም አንተርፍም ነበር፡፡

በነገራችን ላይ የልብ ወዳጄ የኢትዮሚዲያው አብርሃ በላይ ትግሬነቱን ቢጠቀምበት ኖሮ – ለሰው እንኳን ሳያውስ “በከንቱ አከሰረው” እንጂ – የቁጩ ሣይሆን የኮራ የደራ እውነተኛ የወያኔ ሚኒስትር መሆን ይችል ነበር፡፡ የሥጋ ፍትወት ፈታኝ ነው፡፡ ይህን ፈተና የሚያልፍ ግን ብፁዕ ነው፡፡

መስፍኔን የምወቅስበት ብዙ ነገሮች ነሩኝ፡፡ ለምሳሌ በትጥቅ ትግል ላይ ስላላው አሉታዊ አቋም፣ በውጪ ስለሚታገሉ የተቃውሞ ኃይላት ዙሪያ የሚከተለው የማጥላላትና የማንኪያኪያስ “ዘመቻ”፣ በምሁራን ላይ ስላለው የንቀት ግምትና ይህን ግምቱን ስለሚገልጽበት አንቋሻሽ የቋንቋ አጠቃቀም(ለምሳሌ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴን በምን ሁኔታ እንደገለጸው ከዚሁ የክሽፈት መጽሐፍ መመልከት በቂ ነው)፣ እንደጋሼ ፀጋዬ ገ/መድኅን ሁሉ በወጣቱ ላይ ስላለው አነስኛ ግምትና ስለመሳሰለው ጠቃሚና ለሌሎችም ተመሳሳይ ስሜት ላላቸው ዕውቅ ሰዎቻችን ትምህርት ይሰጣሉ ብዬ ያሰብኳቸውን አንዳንድ ነጥቦች እያነሳሁ መጣል አምሮኝ ነበር፡፡(በድፍረት ከታወሩ አይቀር እንዲህ ነው፤ “ትምህርት ይሰጣሉ ብዬ ያሰብኳቸውን” አልኩ ልበል?) ግን ጊዜው የሩጫ ሆነና እናንተን አንባቢያንን ማሰልቸት ይሆንብኛል ብዬ በመሥጋት ተውኩት፡፡

ለማጠቃለል ያህል ከመሬት ተነስተህ “በዚህ ሥርዓት ትግሬ አልተጠቀመም” ማለት አንድም ቀደም ሲል እንዳልኩት – አሁንም እደግመዋለሁ – የለዬለት አድርባይነት ነው፣ አንድም እያወቁም ይሁን ሳያውቁ ወያኔን ለማስቀየም የማይጠቅም ጅራፍ ማንጓት ነው ( ውሸት መሆኗን ልቦናቸው ቢያውቅም ወያኔዎች ሰዎች እንዲህ ሲሉባቸው አይወዱም፤ ምክንያታቸው ደግሞ ግልጽ ነው – ያም ትግሬንና ሌላውን ማጣላት ስለሚፈልጉ ነው፡፡ … ምቹ ሁኔታ ይፈጠር እንጂ ደግሞ ትግሬና ሌላው ዜጋ እጅና ጓንት መሆኑን በሕወሓት ውድቀት ማግሥት ወያኔዎች የሚገነዘቡበት ጊዜ ሩቅ አይደለም – የኢትዮጵያውያን ለሺዎች ዓመታት በዘለቀ የአብሮነት ኑሯቸው በችግርና በደስታ ጊዜ የሚያሣዩት የተለዋዋጭነት ባሕርይና(resilience) የአንድነት መንፈስ በ25 ወይ በ40 የግፍና የመከራ ዓመታት ውስጥ ተበጣጥሶ የሚወድቅ የዕቃ’ቃ ጨዋታ ክርና ሲባጎ እንዳልሆነ ለነዚህ የርኩሳን መናፍስት አጋሰሶች የምናሳይበትና ደስታ ማለት ገመቹ፣ ገመቹ ማለትም ሐጎስ መሆናቸውን የምናስመሰክርበት የነፃነት ጊዜ በጣም ቅርብ ነው፡፡) በተረፈ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን፣ የልማት አውታሮችን፣ የዕቃና የአግልግሎት አቅርቦቶችን፣ የትምህርት ተቋማትን፣ የማዕድን ምንጮችን፣ የመሬት ይዞታዎችን፣ ስንቱ ተዘርዝሮ … ይህን ሁሉ ጉድ በማይም ጭፍሮቹ ቁጥጥር ሥር አውሎ ሀገሪቱንና ሕዝቧን እንደትኋን እየመጠመጠ የሚገኝን ሕወሓት የተባለ መዥገር አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ውስጥ በተጎለተ ደሳለኝ በሚባል የቀድሞ አህያቸው ስም የሚጠራ ኮንዶም ግለሰብ አማካይነት ሁሉን ነገር ለፈለጉት ትግሬና ሆዳም አንጋች እያደሉ ባሉበት ሁኔታ ትግሬ አልተጠቀመም ማለት የጤንነት ምርመራ የሚያሻው፣ ከሃይማታዊ የጸበል አገልግሎትም አንጻር ለሰባት ዓመት የሸንኮራ ዮሐንስን ጠበል የሚሻ በሽታ ነው፡፡

የምለው ሁሉ የዐዋጁን በጆሮ እንደሆነ ዐውቃለሁ፡፡ ለጊዜው አዲስ ነገር የለም፡፡ አዲስ ነገር የሚኖረው አሮጌው በአዲስ ሲተካ ነው፡፡ ያም ሂደት ከተጀመረ ቆዬ፡፡ ምክንያቱም በእያንዳንዱ አሮጌ ውስጥ የሚጸነስ አዲስ ነገር መኖሩ የተረጋገጠ ነውና – Nemesis፡፡ ከዋሻው መጨረሻ ጭላንጭል ይታየኛል፡፡ … ይህች ተናግራ የምታናግር ሀገር ዝም ካሏት ብዙ ታስወሻክታለችና ቢበቃኝስ፡፡ መልካም አዲስ ዓመት አላልኳችሁም ልበል? አዎ፣ ገና እኮ መንፈሱ አለ – “እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ”፡፡

Yiheyisaemro@gmail.com

No comments:

Post a Comment