Saturday, November 23, 2013

የፌደራል ፖሊሶች ሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ ፊት ለፊት የተቃዉሞ ስልፍ የወጡ ኢትዮጵያዉያንን ደበደበ

ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ በወንድሞቻቸዉና በእህቶቻቸዉ ላይ እየደረሰ ያለዉ በደልና ሰቆቃ አንገብግቧቸዉ ቁጣቸዉን ለመግለጽና የሳዑዲን መንግስት ለመቃወም በሳውድ አረቢያ ኢምባሲ ፊት ለፊት ተቃውሞዋቸውን ለመግለጽ የወጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ህጻን’ ወጣትና ሽማግሌ ሳይባል በፌደራል ፖሊሶች እንደተደበደቡ ከአዲስ አበባ የደረሰን ዜና አስረዳ። በዚህ የሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ከተደበደቡት ሰዎች ሌላ የሰማያዊ ፓርቲና የአንድነት ፓርቲ አመራሮችና አባላት መታሰራቸዉ ታዉቋል። በዚህ ወያኔ እመራዋለሁ የሚለዉን ህዝብ እንደ ጠላት ቆጥሮ ባጠቃበት አጋጣሚ ከ100 በላይ ሰዎች የታሰሩ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪና በየክልሉ የሚኖረዉ ህዝብ በወያኔና በሳዑዲ መንግስት ላይ ቁጣዉንና ተቃዉሞዉን እየገለጸ መሆኑ ታዉቋል።

የሰማያዊ ፓርቲ መሪዎች፤ አባላትና ደጋፊዎች ከፓርቲዉ ጽ/ቤት ተነስተው ወደ ሰላማዊ ሰልፉ ቦታ ሲሄዱ 4 ኪሎ የኦሮሚያ ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ጎን በሚገኘው ወታደራዊ ገራዥ መታሰራቸውን የታወቀ ሲሆን ከመታሰራው ቀደም ብሎ ከፖሊስ ጋር እንሂድ አትሄዱም በሚል ጭቅጭቅ ላይ እንደነበሩ ተሰምቷል። ሌሎች የፓርቲው አባላትና አመራሮች ተበታትነው ወደ ሳውዲ አረቢያ ኤምባሲ በመሄድ ላይ እያሉ ፖሊሰ ከፈተኛ መጎሳቆል ያደረሰባቸዉ ሲሆን በተለይ አንዲት ሴት ክፉኛ በመመታቷ ለህይወቷ እንዲያሰጋ ለማወቅ ችለኛል። አንድ አስተያየት ሰጪ አንደተናገሩት “በሰው አገር ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ለመቃወም ወጥተን ተመሳሳይ ስቃይ አስተናገድን” ብለዋል። የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆነው ወጣት ብርሀኑ ተክለያሬድ እስር ቤት ውስጥ ሆኖ በድብቅ በስልክ እንደተናገረው የድርጅቱን ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነትንና ምክትላቸው አቶ ስለሺ ፈይሳን ጨምሮ 15 አመራሮች ጃንሜዳ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ። ወጣት ጥላየ ታረቀኝ ታስሮና ድብደባ ተፈጽሞበት ከተለቀቁት መካከል አንዱ ሲሆን ፣ የወያኔን አገዛዝን ድርጊት ለመግለጽ እንደሚቸገር ገልጿል። ሰማያዊ ፓርቲ ከጥቃቱ በሁዋላ ባወጣው መግለጫ” የኢትዮጵያ መንግስት ከሳውዲ አረቢያ መንግስት ጎን በመቆም ዋና ተባባሪ መሆኑን በዛሬው እለት አስመስክሯል ብሎአል።

የግንቦት ሰባት ድምጽ ዘጋቢዎች ያናገሯቸዉ ብዙ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የወያኔ ፖሊሶች የራሳቸውን ዜጋ በመደብደብና በማሰቃየት ብሎም በማሰር በሳውዲ በሚገኙ ኢትዮጵያዊ ወገኖች ላይ የተፈጸመውን በደል ሀገር ውስጥ በሚገኙ ንጹሀን ወገኖቻቸው መድገማቸዉ እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነዉ ካሉ በኋላ በውሸት ዲሞክራሲ ስም የተደበቀው አምባገን አገዛዝ ህዝብን ለማሸማቀቅ የወሰደውን እርምጃ በመቋቋም አያት ቅድመ አያቶቻችን የሰጡንን አደራ በመቀበል ክብአችንንና ማንነታችንን በትግላችን እንደገና እናስከብራለን ብለዋል። የወያኔዉ ቃል አቀባይ ሽመልስ ከማል ለአልጀዚራ ቴሌቪዥን በሰጠዉ ቃለመጠይቅ ሰልፈኞቹ የተከለከሉት ባልተፈቀደ ሰልፍ ላይ በመገኘታቸውና ኢትዮጵያን ህዝብ በጸረ-አረብ ስሜት በማነሳሳታቸው ነው በማለት የተለመደዉን የቅጥፈት ንግግር ለአለም ህዝብ በማሰማት ለዜጎች ሳይሆን ለሳዑዲ ቱጃሮች ያለዉን ታማኝነትበግልጽ አሳይቷል።

No comments:

Post a Comment