Wednesday, November 20, 2013

ትግላችን መስጂዶቻችንን ለመንጠቅ ከሚሞክረው መንግስት የተሳሳተ ምልከታ ጋር ነው! ድምፃችን ይሰማ

ረቡእ ሕዳር 11/2006

መስጂዶች ለኢትዮጵያዊው ሙስሊም ልዩ የሚያደርጋቸው አያሌ ምክንያቶች አሉ፡፡ በዋነኝነት መስጂዶች የአምልኮ ስፍራ ከመሆናቸው በተጨማሪ ሌሎች አማራጮች በማይታሰብባት ሃገራችን የዳዕዋም ብቸኛ ማዕከላት ናቸው፡፡ ባሳለፍናቸው 20 እና 30 አመታት ‹‹አንፃራዊ የእምነት ነፃነት ነበር›› ተብሎ ቢነገርም ሙስሊሙ በነዚህ ግዜያት ከመስጂዶች ውጭ የገነባቸው ተቋማት የሉትም፡፡ ስለዚህም ነው ‹‹መስጂዶች የህዝበ ሙስሊሙ የአይን ብሌን ናቸው›› ቢባል ማጋነን የማይሆነው፡፡

በምናደርገው ሰላማዊ የመብት ትግል ደግሞ መስጂዶች የተቃውሞ ማዕከላት እና አለፍ ሲልም የእንቅስቃሴው መገለጫዎች ናቸው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ የመጅሊስን ህገ ወጥነት አውጆ እንቅስቃሴውን ሲጀምር በመጅሊስ የሚተገበረው መንግስታዊ ዘመቻ መስጂዶቻችንን እንዳይቆጣጠር ማድረግ ትልቁ ዓላማው ነበር፤ አወሊያን መጠበቅን ከአላማዎቹ አንዱ አድርጎ የተነሳ እንቅስቃሴ የሌሎቹን መስጂዶች ከህዝብ የመንጠቅ ዘመቻ ዝም ብሎ ያልፋል ተብሎ ሊጠበቅ አይችልምና!

በሃገራችን የሚገኙት አብዛኞቹ መስጂዶች ደሳሳ ቢሆኑም እድሜ ጠገብ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ በገጠር የሚገኙት ወለላቸው አፈር፣ ክዳናቸው ሳር ነው፡፡ በከተማዎች ያሉትም ቢሆን ከጥቂቶች በስተቀር ይዞታቸው የተጎሳቆለና እድሳት የናፈቃቸው ናቸው፡፡ የውጫዊ ይዘታቸውን ጎስቋላነት የሚያካከሱበት ግርማ ሞገሳቸው ግን በቀን አምስት ግዜ ለሰላት የሚያስጠልሉት ህዝበ ሙስሊም ነው፡፡

መስጂዶቻችን በእድሜ ጠገብ ቆይታቸው ሁሉንም አማኞች በእኩልነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ መንግስታት ሲቀያየሩ እና የተለያዩ አመለካከቶች ሲነሱና ሲወድቁ መስጂዶች አማኞችን በአንድነት አቅፈው ይዘው ለዛሬ አብቅተዋል፡፡ መላው ሙስሊምም ያለልዩነት ‹‹መስጂድ የኔ ቤት ነው›› ብሎ ያምናል፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ አሁን ላለበት ደረጃ የደረሰውም ቢሆን አልጋ በአልጋ በሆነ መንገድ አልፎ አይደለም፡፡ የመስጂዶች ይዞታ እና አስተዳደር ምቹ ባልሆነበት አጣብቂኝ ውስጥም እንኳን አሁን የምናየው የዲን ተቆርቋሪ ትውልድ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ትውልድ ነው መስጂድ የሁሉም ሙስሊም ቤት መሆኑን፣ ብሎም የመስጂድ ግርማ ሞገስ አማኞቹ መሆናቸውን በተግባር ሊያረጋግጥ የሚፈተንበት ወቅት ላይ የሚገኘው፡፡

አሁን በመተግበር ላይ ያለው መስጂዶችን ከባለቤታቸው የመንጠቅ ዘመቻ በሰከነ መንፈስ መታየት የሚገባው በመሆኑ ለረጅም ግዚያት የህዝበ ሙስሊሙ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከጉዳዩ አሳሳቢነት እና ከአተገባበሩ ውስብስብነት የተነሳም ቀጥተኛ መፍትሄ ማስቀመጥ ሲያዳግት በርካታ ባለድርሻ አካላት በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ምልከታ እንዲጠቁሙ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡


እስካሁን እውቅ የሃገራችን ዑለማዎች፣ ምሁራን፣ የመስጂድ ዒማሞች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት መስጂዶች ከህዝብ የሚነጠቁበትን ዋነኛ ምክንያት እና መፍትሄውን አስመልክተው ምልከታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሁሉም አካላት በጋራ የሚስማሙባቸው በርካታ ነጥቦች አሉ፡፡ ጥቂቶቹን ብንመለከት፡-

1/ አምልኮ የምንፈጽምባቸው መስጂዶቻችን በአሁኑ ወቅት በፖለቲካዊ እዝ ውስጥ በመውደቃቸው እውነታ ላይ ይስማማሉ፡፡ የዚህ ዋነኛ ተልዕኮ አማኞችን ከመስጂዶች በማራቅ በሂደት ከእምነታቸው ማራቅ መሆኑንም ጭምር ያምናሉ፡፡

2/ መስጂዶችን የመታደግ ትግላች ዋነኛ ትኩረት መንግስት መስጂዶችን ለመቆጣጠር የፈለገበትን ተልዕኮ ማምከንን ታሳቢ ያደረገ መሆን እንደሚገባው ያምናሉ፡፡

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የምናካሂደው ሰላማዊ ትግል ዋነኛ መነሻ ምን እንደሆነ ሁሉም ጥርት ባለ መልኩ ይረዳዋል፡፡ አላማችን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የህዝበ ሙስሊሙን ቁሳዊ ህይወት ከማስተዳደር በዘለለ መንፈሳዊ ህይወቱን በፖለቲካዊ ሰነድ ለመምራት በማሰብ የከፈተውን ግልፅ ፀረ እስልምና ዘመቻ ማምከን ነው፡፡ ይህ ዘመቻ ግዙፍ ከመሆኑ የተነሳ የማይነካው የህይወታችን ክፍል የለም፡፡ የመንግስት ባለስልጣናት መጅሊሳችንን በቀበሌ ሹመኞች ለማስተዳደር፣ ከቀበሌ በሚቀቡ ግለሰቦች እጅ ለመጣል፣ የአምልኮ ስርአታችንን በፖለቲከኞች ደንብ እና መልካም ፈቃድ ብቻ እንድናደርግ ለማስገደድ፣ ከዚህም አልፎ እንዴት ማሰብ እንዳለብን ሰነድ አርቅቀው እስከማስተግበር የደረሰ በቃላት የማይገለፅ አሳፋሪ ድፍረት ለመፈጸም እየሞከሩ ይገኛሉ፡፡

የምናደርገው ትግል ዋነኛ ድልም ይህንን አመለካከት መቅረፍ፣ አልያም መሰል ችግሮች የማይፈጠሩበት ሁኔታ እውን እንዲሆን ማድረግ ማስቻል ነው፡፡ መንግስት እየተመኘ ያለው ደግሞ በችግሮቹ መገለጫዎች ላይ አተኩረን የችግሩን ስር መሰረት ቸል እንድንል፣ በስተመጨረሻም ውጤት አልባ ፍፃሜ እንዲኖረን ነው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ ይህንን እውነታ ከተረዳ ውሎ ማደሩ በጀ እንጂ ያ ባይሆን በጠላት ወጥመድ ውስጥ የሚወድቅባቸውን በርካታ በአሜከላ የተሞሉ መንገዶች መሻገር ባልቻለ ነበር፡፡

መስጂዶችን በፖለቲካ እዝ ስር ለማስተዳደር የተከፈተው ዘመቻ አንገብጋቢ ከመሆኑም ጋር ከላይ እንዳየነው በችግሩ ዋነኛ ስር ላይ እንዳናተኩር የተሸረበ አደገኛ ተንኮል መሆኑን ልንረዳ ይገባናል፡፡ ይህን ተንኮል ዘመን ተሻጋሪ በሆነ ድል ልናልፍ የምንችልበት አማራጭ ስለሚያስፈልገን በአማራጮቹ ላይ መምከር ደግሞ በአላህ ፈቃድ የዚህ ሳምንት አብይ ትኩረታችን ይሆናል!

መስጂዶቻችን የህዝብ ደም ጠብታ ውጤቶች፣ የታሪካችን ውርሶች ናቸው!!!

ድምጻችን ይሰማ!

አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment