ከወገኖቻችን ጐን በመቆም ብሄራዊ ክብራችንን እናስመልሳለን
ሰሞኑን የሳውዲ አረቢያ መንግሥት በኢትዮጵያዊያን ላይ እየፈፀመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመቃወም ሰማያዊ ፓርቲ ታላቅ የተቃውሞ ጥሪ አስተላልፏል፡፡
በመሆኑም በዜጎቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን ኢሰብዓዊ ድርጊት ለማስቆምና የዜጐችን ህይወት ለመታደግ እንዲሁም ዜጐቻችን በአፋጣኝ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ መንግሥት እንዲያመቻች እና በተጨማሪም በዜጐቻችን ላይ ለደረሰው የአካል መጉደል፣ እንግልት፣ ድብደባ፣ አስገድዶ መድፈርና የህይወት መጥፋት ኃላፊነቱን የሚወስዱ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ፤ ለተጐዱ ወገኖቻችንና ቤተሰቦቻቸውም አስፈላጊው ካሳ እንዲደረግላቸው ፓርቲያችን አበክሮ እያሳሰበ፤ የብሄራዊ ክብርና የወገኖች ስቃይ የሚያሳስባቸው አካላት በሙሉ በዚህ ታላቅ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
የተቃውሞ እንቅስቃሴ አፈፃፀም፡-
1. በዜጐቻችን ላይ የአካል መጉደል፣ እንግልት፣ ድብደባ፣ አስገድዶ መድፈርና የህይወት መጥፋት ያደረሰው የሳውዲ አረቢያ መንግሥት ኢምባሲ በሚገኝበት ቦታ አርብ ከረፋዱ 5፡30 ሰዓት ጀምሮ የሚደረግ የተቃውሞ ሰልፍ፣
2. ከአርብ ጠዋት ጀምሮ እስከ እሁድ ማታ ድረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሀዘን ልብስ (ጥቁር ልብስ) በመልበስ በግፍ ለሞቱና ለተንገላቱ ወገኖቻችን ሀዘናችንን መግለፅ፣
3. የእምነት ተቋማት አርብ በመስጊድ በጁምአ ሥነ ሥርዓት ላይ እና ቅዳሜና እሁድ በአብያተ ክርስቲያናት የፀሎት ሥነ ሥርዓቶች ላይ ወገኖቻችንን በፀሎት እንዲታሰቡ፣
4. ቅዳሜ በሚደረገው የኢትዮጵያና የናይጄሪያ የእግር ኳስ ጨዋታ ላይ ተጫዋቾቻችን ጥቁር ሪቫን በክንዶቻቸው ላይ አጥልቀው እንዲጫወቱ፣ እንዲሁም መላው ደጋፊ ጥቁር ጨርቆችን በመያዝ ወይም ልብስ በመልበስ ሀዘኑንና ቁጭቱን እንዲገልፅ፣
በፓርቲው የተወሰነ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ሲቪክ ተቋማት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ዓለም አቅፍ ማኅበረሰቡ በአጠቃላይ መላው ኢትዮጵያዊና የኢትዮጵያ ወዳጆች በጠራነው የተቃውሞ ሰልፍና እንቅስቃሴዎች ላይ በመገኘት ከግፉአን ወገኖቻችን ጐን መቆሙን እንዲያረጋግጥ በአፅንኦት እንጠይቃለን፡፡
የወገኖቻችን ሰቆቃ እስኪያበቃ በፅናት እንታገላለን!!!
No comments:
Post a Comment