Saturday, April 12, 2014

ዲያስፖራዉ ለወገኖቹ የሚልከዉ ገንዘብ የኢትዮጵያ ቀዳሚ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ መሆኑ ታወቀ

ኢትዮጵያ በ2005 በጀት ዓመት ምረቶቿን ለዉጭ ገበያ ልካ ካገኘችዉ ገቢ ይበልጥ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለወገኖቻቸዉ ከሚልኩት ገንዘብ ያገኘችው ገቢ እንደሚበልጥ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የተገኘ የጹሑፍ መረጃ አመልክቷል። ይህ አክራሪ ወይን አገሩን የከዳ ዳያስፖራ እየተባለ በወያኔና በደጋፊዎቹ የሚጠላዉ ዳያስፖራ በብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዝብ ወደ አገሩ በመላክ የዳያስፖራዉ ችግር የወያኔ ዘረኝነት ነዉ እንጂ አገሩና ወገኑ አለመሆኑን በተግባር አሳይቷል ሲሉ አንድ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪ ተናግረዋል።

ከወያኔ ባለስልጣኖች የተገኘዉ መረጃ እንደሚያሳየው በ2005 በጀት ዓመት አገሪቱ ከኤክስፖርት 3.1 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ያገኘች ሲሆን ኢትዮጵያውያን ከውጭ ከሚልኩት ገንዘብ ደግሞ 3 ቢሊዮን 9 መቶ ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች። በ2004 በጀት ዓመትም ከሐዋላ እና ከኤክስፖርት ያገኘቸው ገቢ ተመሳሳይ ማለትም እያንዳንዳቸው 3.2 ቢሊየን ዶላር መሆኑን መረጃው ያሳያል።መረጃው የሐዋላ ገንዘብ በፍጥነት እያደገ ሲመጣ በአንጻሩ አገሪቱ እንደቡና ፣የቅባት እህሎችና ጥራጥሬና የመሣሠሉትን በመላክ የምታገኘው ዓመታዊ ገቢ እያሽቆለቆለ መምጣቱን ያሳያል።


የኤክስፖርት ዘርፍ ባለፉት ሶስት ዓመታት መንግስት ከያዘው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አንጻር አፈጻጸሙ ደካማ መሆኑን መረጃው የሚጠቁም ሲሆን ከገቢ ንግድ ጋር ያለው የንግድ ሚዛን ጉድለት እየሰፋ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑን ያመለክታል።በ2004 የገቢ ንግድ(ኢምፖርት) መጠን 11 ቢሊየን ዶላር ሲሆን በ2005 ዓ.ም ወደ 11. ቢሊዮን 500 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ብሎአል። የሸቀጦች የወጪ ንግድ ገቢ ከሸቀጦች የገቢ ንግድ ወጪ ጋር ሲነጻጸር በሚጠበቀው ደረጃ ዕድገት ባላማሳየቱ የንግድ ሚዛን ጉድለቱ በ2003 ዓ.ም ከነበረበት 5 ቢሊዮን 500 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በ2005 ዓ.ም ወደ 8. ቢሊየን 400 ሚሊዮን ዶላር እንዲሰፋ ማድረጉን መረጃው ጠቁሟል። ይህን የንግድ ሚዛን ጉድለት ለማጥበብ መፍትሔው ኤክስፖርትን ማሳደግ ነውም ብሏል።እጅግ የተለጠጠ ነው በሚል ትችት የሚቀርብበት የመንግስት የአምስት ዓመቱ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት ታሳቢ ከተደረገው ገንዘብ መካከል ብድርና እርዳታ አንዱ መሆኑ ይታወቃል። መረጃው እንደሚያሳየው ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ለጋሽ መንግስታት አገሪቱ ያገኘችው ዕርዳታ በ2005 ዓ.ም ማሽቆልቆል አሳይቷል።

No comments:

Post a Comment