Friday, April 25, 2014

የአብዮቱ የልደት ቀን

በፋሲል የኔያለም

ክፍል አንድ

በማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ውስጥ መተንበይ ከባድ ፈተና ነው፣ ቢሆንም ምሁራን መረጃዎችን አሰባስበው ከመተንበይ ወደ ሁዋላ አይሉም። ቶማስ ፍሬድማን ከ100 ዓመታት በሁዋላ በዓለማችን ስለሚፈጠረው የፖለቲካ ሁኔታ መጽሃፍ አሳትሟል። ሳሙኤል ሃንቲንግተንም ስለመጪው ጊዜ ግጭቶች ያሳተመው Clash of Civilizations በአንድ ወቅት ሰፊ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። የአሜሪካ መንግስት የ25 ዓመታት ትንበያ በየጊዜው ያወጣል። አንዳንዱ ትንበያ ይሳካል ሌላው ደግሞ ተኖ ይቀራል። የሶቭየትን መፈራረስ የተነበዩ ብዙ ምሁራን ነበሩ ፣ የአሜሪካን መፈራረስም የተነበዩ ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም። በሶቭየት ላይ "ያሟረቱ ሲሳካላቸው"፣ በአሜሪካ ላይ "ያሟረቱት ግን ሳይሳካለቸው ቀረ"። በቻይናም ላይ ብዙ ትንቢቶችን እያነበብን ነው። አንድሪው ፍራንክ ReOrient በሚለው መጽሃፉ ቻይና የነገዋ ልዕለ ሃያል ናት ይለናል፣ ፍሬድማን ደግሞ የለም የቻይ እድሜ የጤዛ ያክል ነው፣ ከጥቂት አመታት በሁዋላ ትበታተናለች ይለናል። በአጭሩ ትንበያ ማካሄድ ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ሲቀል ለማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ግን እጅግ ከባድ ነው።

አንድ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ "በኢትዮጵያ ውስጥ አብዮት ይከሰታል አይከሰትም" ብሎ ለመተንበይ ከመሞከሩ በፊት የሚመጣውን አደጋ ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለበት። ትንቢቱ ሳይሳካ ከቀረ "ስነልቦናን" የሚጎዳ ትችት ሊያስተናግድ ይችላል። ይህን መቋቋም እንደሚችል ካመነ ነጻነቱን እንዳወጀ ይቁጥረው። አንዳንዱ ትንቢት ጻሃፊ ትችትን በመሸሽ ትንቢቱ የሚፈጸምበትን ጊዜ ወይም የጊዜ ገደብ ለመጥቀስ አይፈልግም፤ "እንዲህ ይሆናል" ብሎ ይናገራል እንጅ " በዚህ ጊዜ እንዲህ ይሆናል" ብሎ ለመናገር አይደፍርም። ይሄ ደግሞ ትንቢት አይባልም። "በኢትዮጵያ ውስጥ አብዮት ይነሳል" ብሎ በደፈናው መተንበይና "በ2010 ዓም በኢትዮጵያ ውስጥ አብዮት ይነሳል" ብሎ መተንበይ ሰፊ የሆነ ልዩነት አላቸው። አንድ ጊዜ አንዲት ተማሪ ዴንማርክን ካርታ ላይ እንድታመለክት ተጠየቀች፣ ተነሳችና መላውን አውሮፓ አመለከተች። ተማሪዎችም ሳቁ። ተማሪዋ አውሮፓን መጠቆሟ ትክክል ቢሆንም፣ ከአውሮፓ ውስጥ ዴንማርክን ነጥላ ባለማሳየቷ ግን ተሳሳተች። የጊዜ ገደብ ያልተቀመጠለት ትንበያም ዴንማርክን ጠቁም ሲባል አውሮፓን እንደመጠቆም ይቆጠራል ። በጽሁፌ ማጠቃለያ ላይ የለውጡን ( አብዮቱን) ጊዜ በድፍረት አስቀምጣለሁ። (ካልተሳካልኝ ትችቱን ለማስተናገድ ዝግጁ ነኝ፣ ድንገት ከተሳካለኝ ግን አደራ ኮከባችንን ቁጠርልን እያላችሁ እንዳታስቸግሩኝ)


የአብዮት ትርጉም አሻሚ ነው። አብዮት ደም አፋሳሽ ወይም ሰላማዊ ሊሆን ይችላል፤ በመፈንቅለ መንግስት በአንድ ቀን፣ ወይም እንደ ፈረንሳይ አብዮት ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ በሂደት ሊከናወን ይችላል። አብዮትን አብዮት ከሚያሰኙት መስፈርቶች አንዱ፣ ምናልባትም ዋናው፣ ከምርጫ ውጭ የስርአት ለውጥ እንዲመጣ ማድረጉ ነው። በዚህም የተነሳ ምርጫ አልባ የስርአት ለውጥንና አብዮትን አንድ አይነት ትርጉም እሰጣቸዋለሁ።

የአብዮት መነሻ ምልክቶች
አብዮት ከመጀመሩ በፊት አንዳንድ ምልክቶች ይታያሉ። ዋና ዋናዎቹን ቀጥሎ እናያለን።

1 የአብዮት ወሬ መኖር

አንድ አብዮት ከመነሳቱ በፊት ስለአብዮት ወሬ መወራት ይጀምራል። ትንሹም ትልቁም ስለስርዓት ለውጥ አስፈላጊነት ይነጋገራል። የመገናኝ ብዙሃን ስለለውጥ ይዘግባሉ፣ ደፈር ያሉት ደግሞ ከዚህም ከዚያም ትንኮሳ ያካሂዳሉ። ስርአቱ እንዲቆይ የሚመኙ እንኳ ከጭንቀትም በመነሳት ወይም ለውጡን ለማሰናክል በማለም ስለ አብዮት ጉዳቶች ያወራሉ። መንግስትም ለውጡን ለማስቀረት የተለያዩ እርምጃዎችን ይወስዳል። የአንድ አገር አየር በለውጥ ወሬ መሞላት ከጀመረ፣ ለውጥ አይቀሬ ነው።

በኢትዮጵያ የ66 ቱ አብዮት ከመጀመሩ በፊት የአብዮት ወሬዎች ለ10 አመታት ያክል ተናፍሰዋል። ትንንሽ የሚመስሉ ትንኮሳዎች ተካሂደዋል። ስርአቱን የሚደግፉ ሃይሎች ለውጡን ለማስቀረት አንዳንድ እርምጃዎችን ወስደዋል። ሳይሳካ ቀረ። ታላላቆቹ የፈርንሳይና የሩሲያ አብዮቶች ከመከሰታቸው በፊትም እንዲሁ የተለያዩ ወሬዎችና ትንኮሳዎች ይካሄዱ ነበር። የኩባ አብዮት ከመነሳቱ በፊት እነ ፊደል ካስትሮ የአብዮት ወሬዎችን ከማስወራት ባለፈ የጦር ሰፈር እስከመውረር የደረሰ ትንኮሳዎችን ያደርጉ ነበር። በዛሬዋ ኢትዮጵያም በአራቱም ማእዘናት የአብዮት ወሬ እየተናፈሰ ነው። ወሬው የአረቡን የጸደይ አብዮት አስታኮ በስሱ ቢጀመርም፣ ከጊዜ ወደጊዜ ጉልበት እያገኘ በመሄድ ላይ ነው። አቶ መለስ የዚህን አደገኛ ወሬ ስርጭት በአባይ ግድብ ለማስቆም ቢሞክሩም አልቻሉም ። አቶ መለስ በህይወት እያሉ በ2ኛ ማርሽ "በክሩዝ ኮንትሮል" ሲጓዝ የነበረው ወሬ፣ እርሳቸው ከሞቱ በሁዋላ በ3ኛ ማርሽ እየተጓዘ ነው። ሰሞኑን ኢቲቪ ያስተላለፈው የቀለም አብዮት ፊልም የወሬውን ፍጥነት ለመግታት ታስቦ የተሰራ እንደነበር አይካድም።

አብዮት ከመፈንዳቱ በፊት ትናንሽ የሚመስሉ ትንኮሳዎች በየቦታው ይፈጠራሉ። ሰማያዊ እና አንድነት ፓርቲዎች በሚጠሩዋቸው ሰልፎች ላይ የሚወጣው ህዝብ ቁጥር እየጨመረ ነው፣ መንግስትን የሚተነኩሱ ንግግሮችና መፈክሮችም እየተሰሙ ነው፤ የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ በአስገራሚ ሁኔታ ቀጥሎአል ። በአፋር እና በደቡብ ክልሎች መጠነኛ ተቃውሞዎች ይታያሉ። በአማራና በትግራይ ክልሎችም ከቤት ፈረሳ ጋር ተያይዞ ህዝብና ፖሊስ በተደጋጋሚ ይጋጫሉ።ህዝቡ ባገኘው መድረክ ሁሉ መንግስትን በድፍረት እየተቸ ነው። በድፍረት ኢሳት ላይ መናገር ጀምሯል፣ ወጣቱ በፌስቡክ ጉልበት ያላቸውን ጽሁፎች ይጽፋል።

የለውጥ ንፋስ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ እየነፈሰ ነው። ንፋሱ ወደ አውሎ ንፋስ ደረጃ ሲያድግ ያን ጊዜ አብዮቱ እውን ይሆናል። መቼ?

ይቀጥላል

No comments:

Post a Comment