Tuesday, April 22, 2014

በደል በቃ! ጭቆና በቃ! ብለህ ተነስ! አምጽ!!!

በቅዱስ ዮሃንስ

አመጽ የህዝብ መብት ነው። የተበደለና የተጨቆነ ህዝብ ማመፅ መብቱ ብቻ ሳይሆን ግዴታውም ጭምር  ነው። በአገራችን ኢትዮጵያ የየካቲት 66 ቱን አመፅ ብንመለከት መንስኤው ጭቆና ነበር። የቤኒዚል ዋጋ መጨመሩን የተቃወሙ ታክሲ ነጅዎችና በትምህርት ፖሊሲው ላይ ሊተገበር የታቀደውን ሴክቶሪያል ሪቪው የተቃወሙ አስተማሪዎችና ተማሪዎች ህዝባዊ እንቅስቃሴውን ለኩሰው እንዳቀጣጠሉትና ህዝባዊ አመፅ ወልዶና ተፋፍሞ የአፄውን አገዛዝ ወደ ከርሰ መቃብሩ እንደሸኘው ይታወሳል። ይህም ህዝባዊ አመጽ ከአንባገነንና ጨቋኝ ስርአት በላይ ሃይል እንዳለው ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።   

ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ አለማችንም በአዲስ አይነት ሕዝባዊ አመፅና የለውጥ ማዕበል እየተናጠች ትገኛለች፡፡ በ2002/3 ዓ.ም በቱኒዚያ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ አመፅ ፕሬዝዳንት ቤን አሊን ካሰናበተ በኋላ ወደ ግብፅ በማምራት ለ30 ዓመታት ተደላድለው ይመሩ የነበሩትን ሙባረክንም ከስልጣናቸው አሽቀንጥሯቸዋል፡፡ ቀጥሎም በየመን፣ በባህሬን፣ በሶሪያ፣ በአልጀሪያ፣ በሊቢያ፣ በኳታር፣ በዮርዳኖስ፣ በኩዌትና በሌሎችም አረብ አገራት ሕዝባዊ አመፅ መቀስቀሱ ይታወሳል፡፡ ከነዚህ ህዝባዊ አመጾች ጀርባ ደግሞ የመንግስታት ገደቡን ያለፈ በደል፤ ጭቆና፤ አምባገነንነት፤ ቅጥ ያጣ ዘረፋ እና ሙስና ይገኛል። በኢትዮጵያስ፤ በእውነት ግን ገደቡን ያለፈ በደል የለምን? ጭቆናስ? ኧረ ቅጥ ያጣ ዘረፋና ሙስናስ? ይህ ሁሉ እየሆነ ታዲያ ስለምን ህዝብ በቃ ብሎ መነሳትና ማመጽ ተሳነው? 

በአረብ ስፕሪጉ አብዮት በተለይም በቱኒዚያ፤ አልጀሪያና በሌሎቹም አገሮች እንደተመለከትነው ህዝቡ የኑሮ ውድነትንና ስራ አጥነትን በመቃወም ከአገዛዞቹ ፍቃድ ውጭ በተቀናጀ ሁኔታ ባካሄዱአችው የተቃውሞ አመፆች በርካቶች ቢሰውም እንቅስቃሴው ድልን ወልዶ አገዛዞቹን ቀብሮ ማለፉ አይዘነጋም። ድሉ የተገኘውም ህዝቡ አሻፈረኝ ብሎ ስለተነሳና ስለታገለ ብቻ ነው። አምባገነኑ የቱኒዚያ አገዛዝ፤ ፕሬዜዳንቱና መላ ቤተሰቦቹ እንደ ባንዳዎቹ የጉጅሌው ወያኔ ቁንጮዎችና ቱባ ካድሬዎች በሙስና የተጨማለቁ ሲሆን ተቃዋሚዎችን ቦዘኔዎች ሲሉ ቢከሱና በርካታ ንጹሃን ዜጎችን ቢገድሉም በህዝባዊ አመጽ ከመገርሰስ ግን ፈፅሞ ሊያመልጡ 
አልቻሉም፤ ላይመለስ አገዛዙ ተቀብሯልና። ቀደም ብሎ በሌሎች አገሮችም እንደታየው የኑሮ ውድነትን በመቃወም ህዝብ ሞት አይፈሬ ሆኖ በጀግንነት በመሰለፉና፤ በርካቶች ቢሰውም ትግሉ ግን ተፋፍሞ በመቀጠሉ አዎንታዊ ድልን አስመዝግቦ መጠናቀቁ ይታወቃል። ከዚህም የምንማረው አሁን በአገራችን በጉጅሌው ወያኔ የተዛባ ፖሊሲ ምክንያት የተንሰራፋውን የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነትን እንዲሁም ሙስና፤ የሰብአዊ መብት ረገጣ፤ ስልጣን የህዝብ እንዲሆን፤ ግለሰቦች በፖለቲካ አመለካከታቸው፤ በእምነታቸውና ሃሳባቸውን በነፃነት በመግለፃቸው የማይታሰሩባት ሃገር ለመፍጠር፤ ፍትህን ለማስፈን ጭቆናንና በደልን በዝምታ በመመልከት ሳይሆን መፍትሄው እምቢኝ አሻፈረኝ ብሎ በመነሳት የተቀናጀ ህዝባዊ አመጽ ማድረግና የችግሮቹን ሁሉ ምንጭ የሆነውን የጉጅሌ አገዛዝ መቅበር እንዳለብን ነው።   


በአገራችን በኢትዮጵያ በፋሽስቱ ወያኔ የተዛባ ፖሊስ ምክንያት የኑሮ ውድነቱ ጣራን በጥሶ ከመጠቀ ጊዜ አልፏል። የጉጅሌው ወያኔ  አገዛዙ የወለደውን የኑሮ ውድነት ለመሸፈንና ጭቁን ነጋዴዎችን ለቀውሱ መንስኤ አድርጎ ለማሳየት ተደጋጋሚ ዘመቻን ቢከፍትም ህዝብ የሚያውቀው ሃቅ ግን ለተከሰተው አገራዊ የኑሮ ውድነት ቀውስ ዋነኛ ተጠያቂው የህወሓት ቡድን መሆኑን ነው። ኢትዮጵያ በፋሽስቱ የወያኔ አገዛዝ በታሪኳ ገጥሟት በማያውቅ መልኩ በኢኮኖሚውም ሆነ በሌሎችም ዘርፍ ውድቀት ውስጥ ገብታለች። ለዚህ ውድቀትና ድቀት ብዙ ምክንያቶችን መጠቃቀስ ይቻላል መሰረታዊው ምክንያት ግን ጉጅሌው ወያኔና ወያኔ ብቻ ነው። ከቀን ወደ ቀን ወደ ከፋ ደረጃ እየተሸጋገረ የሚገኘው የኑሮ ውድነት ብዙ ሚሊዮን ዜጎች የእለት ጉርሳቸውን እንኳን ለመሸፈን አዳጋች  እንዲሆን አድርጎባቸዋል። የኑሮ ውድነቱ እንደ እግር እሳት ህዝቡን እየለበለበው ይገኛል። አሁንም በድጋሚ መሰመር ያለበት ጉዳይ ይህ በአገራችን የተንሰራፋው የኑሮ ውድነት ቀውስ የጉጅሌው ወያኔ የተሳሳተ ፖሊሲ ውጤት መሆኑ ነው። ይህንን ለመካድ በአጫፋሪ የፋሽስቱ ቡችሎች የሚደረግ መፍጨርጨር አገዛዙን የሚያዋርድ እንጂ ለችግሩ ሽፋን የሚሰጠው አይሆንም። ለኑሮ ውድነቱ ነጋዴዎችን ተጠያቂ ለማድረግ ብሎም በህዝብ ለማስጠላት በተለያዩ ጊዜያት የተከፈቱ ዘመቻዎች የአገዛዙን በቀውስ ውስጥ ሆኖ መንፈራገጥ ያሳያሉ። አምባገነኑ ደርግም በጊዜው በርበሬ ደበቁ የዋጋ ንረት አመጡ ብሎ ነጋዴዎችን ረሽኖ ነበር፤ ያገኘው ፋይዳ አልነበረም እንጂ። መሰረታዊው ጥያቄ ግን ህዝብ በአገራችን የተንሰራፋውን የኑሮ ውድነት ተሸክሞ ስለምን መገዛትን መረጠ የሚለው ነው? መቼስ ይሆን እንደ ጎረቤቶቹ ቱኒዝያ፤ አልጅርያ እንዲሁም ሌሎች አገራት ጀግና ህዝቦች፤ ህዝባችን ቆርጦ በመነሳትና በማመጽ ይህንን የወሮበላ አገዛዝ ወደ ከርሰ መቃብሩ የሚሸኘው? 

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከኑሮ ውድነቱ በተጨማሪ ስራ አጥነቱ በሰፊው ተንሰራፍቷል። ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንጅ እየቀነሰ አይደለም። በጉጅሌው ወያኔ አገዛዝ የስራ አጥነቱ የወለደው ነገር ቢኖር አገራችን በታሪኳ አይታው የማታውቀው ስደት ነው። ዜጎች ከፊት ለፊታቸው ሞት እንደሚጠብቃቸው እያወቁ ተጋፍጠው ለስደት የመነሳታቸው መንስኤ አገዛዙ ያስከተለው የስራ አጥነትና የኑሮ  ውድነት ነው። ስለዚህ ህዝብ ነጋ ጠባ የአገዛዙን የበደል ቀንበር እያፈራረቀ ከመሸከም፤ መከራውና ግፉ እጅግ በዝቷልና በቃ ብሎ በጋራ መነሳት አለበት። እንደ አረብ አገሮች አብዮትና፤ ዳግም እንደ የካቲት 66ቱ አብዮት ህዝብ በቃኝ አሻፈረኝ ብሎ ካልተነሳ፤ ካላመጸና የአረመኔው ወያኔን አገዛዝ የሚከፈለውን ሁሉ መስዋዕትነትን ከፍሎ ለመታገል ቆርጦ ካልተነሳ ጫንቃው እስኪሰበርና ከትቢያ እስኪደባለቅ ሸክሙና ግፉ ይጨምራል እንጂ አይቀንስም። ስለዚህ አመጽ ያስፈልጋል። ህዝብ ካላመፀና  የእንቢታን ጩኅት ካላሰማ ለሚደርስበት በደልና ጭቆና ሁሉ የሚያዝንለት ማንም አይኖርም። ከሌሎች አገሮች እንዳየነው ዋጋ ተወደደ፤ ስራ አጥነት በዛ የአገራችን መሬት ለባዕድ ተሸጠ ብለው የታገሉና ያመጹ ህዝቦች የፈለጉትን ለማግኘት ችለዋልና። በዝምታ  ሁሉንም ግፍ መቀበል ግን ትዕግስት ሳይሆን ባርነት ነው። ለሚደርስበት ኢ-ፍትሃዊ በደልና ጭቆና ተቃውሞውን የማያሰማ ህዝብ ቀንበሩን ወዶታል ተብሎ መታሰቡም አይቀሬ ነው። ስለሆነም ወገኔ ሆይ በደል በቃ! ጭቆና በቃ! ብለህ ተነስ! አምጽ!!! 

የኢትዮጵያ ህዝብ በነፍሰ በላው የህወሓት ቡድን የሚደርስበትን ጭቆና፤ በደልና ግፍ በዝምታ መቀበል ማቆም አለበት። ከአሁን ጀምሮ አመፅ/ አድማ በመምታት፤ ተቃውሞ ሰልፍ በማድረግና ሁሉንም የተቃውሞ እርምጃ በመውሰድ የኑሮ ውድነትን፤ ስራ አጥነትን ብሎም ጭቆናና በደልን መቃወም ያስፈልጋል። ራስን በጫትና በቀቢጸ ተስፋ አደንዝዞ አገሪቷ ለባዕድ ስትሸጥ በዝምታ መቀበልም ከፋሽስቶቹ ባንዳ አገር ሻጮች ጋር ከመተባበር በፍፁም ተለይቶ አይታይም፤ ከታሪክ ተጠያቂነትም አያድንም። ታሪካዊው የቋራ መሬት ለባዕድ ተሽጦ፤ የአገሪቷ ለም መሬት ከአርሶ አደሩ ተነጥቆ ለባዕድ ተሰጥቶ፤ የአገዛዙ ጭፍን ብዝበዛና ሙስና ተጧጡፎ፤ ብዙሃኑ ህዝባችን ለከፋ መከራና ስቃይ ተዳርጎ ባለበት ሁኔታ ዝምታን አቅፎ፤ ራስን ደፍቶና ተለጉሞ የመከራ ኑሮን መምረጡ ሽንፈት መሆኑን መገንዘብ ያሻል። ሽንፈት ደግሞ የአባትና እናቶቻችንን አኩሪ ታሪክ ሰራዥና ቀያሪ ነው። ስለዚህ ነው አምጽ የምልህ፡፡ ለምንስ ከእነሱ እንደ ችሮታ ስልጣኑ እስኪሰጥህ ትጠብቃለህ! አንተ በብቃትህ ውሰድ! በቃ ሐገርህን አስመልስ!!!    

በመጨረሻም አመጽ በርግጥ መስዋዕትነትን ይጠይቃል። ለዚህም ማሳያ በአገራችን ለየካቲት 66ቱም ሆነ ለደርግ መገርሰስ ብዙ ሺዎች ተሰውተዋል። ግን መስዋዕትነትን ከፍሎ ነፃነትን ከማምጣትና አገርን ከማዳን ሌላ የስርየት መንገድ የለም። ለዚህም ነው በተደጋጋሚ ለአምጽ ተነስ፤ እምቢተኝነት አስተጋባ የምልህ። ለዚህ ደግሞ ጭቁኑ ህዝብ ቢቻል በድርጅት በመታቀፍ ካልሆነ ደግሞ ከድርጅት ውጭ በመደራጀት የተቃውሞውን የአመጽ እንቅስቃሴ ተግባራዊ ለማድረግ መነሳት አለበት። ህዝቡ በማህበራቱ፤ በጎበዝ አለቃው፤ በቀበሌውና በአካባቢው በዘዴ ተሰባስቦ ዋጋ ይቀነስ፤ ስራ አጥነት ይወገድ፤ ሙስና ይብቃ፤ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ፤ የመሬታችን ባለቤት እንሁን፤ መሬታችን ለባዕድ አይሸጥ ብሎ መቃወም አለበት። ይህ ነው ህዝባዊ አመፅ። የኢትዮጵያ ህዝብ ፈሪ ነው፤ ዳተኛ ነው፤ እንቅልፋም ነው፤ ቀንበር አይከብደውም ብለው በንቀት የሚመለከቱትን የጉጅሌውን ቡችሎችም ሆነ ባዕዳንን ማሳፈር የምትችለው በቃ ብለህ በአመጽ ተነስተህ ሁሉንም ስታርበደብዳቸውና ግብአተ መሬታቸውን ስታፋጥን ብቻ ነው። በፋሽስቱ የጣልያን ወረራ ከሚሊዮን ያላነሰ ዜጋ ተሰውቶ አገርህን ነጻ አድርጓል። ደርግንም ሲታገል ከ 500 ሺህ በላይ ዜጋ አልቋል። ፋሽስቱ ወያኔን ሲታገሉም ብዙዎቹ የአገዛዙ ሰለባ ሆነዋል፤ ዛሬም እንደ ትላንቱ ብዙዎቹ መስዋዕትነትን ለመክፈል ቆርጠው ተነስተው አገዛዙን በሚገባው ቋንቋ ሁሉ እየተፋለሙ ይገኛሉ። ስለዚህ ወገን የጉጅሌው ወያኔ መጫዋቻ መሆንህ ያበቃ ዘንድ በቃ! እምቢኝ ብለህ አምፅ! በቃ አምጽ! እምቢ በል፡፡ ካልደፈረሰ አይጠራም ይሉ የለ አበው፡፡ ሐገርህ በግፈኛ ገዥዎችህ በኩል አንተን ባይተዋር ስታደርግህ ዝም ማለት ይብቃህ!!! 

No comments:

Post a Comment