Monday, April 28, 2014

የጋዜጠኞቹና የአክቲቪስቶቹ እስር አሳሳቢ ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋመ) የተሰጠ መግለጫ
------------------------------------------------------------------------
የጋዜጠኞቹና የአክቲቪስቶቹ እስር አሳሳቢ ነው፡፡
------------------------------------------------------------------------
ትላንት ሚያዝያ 17 2006 አመሻሽ ላይ ዞን 9 በተሰኘ ድረ ገጽ (ብሎግ) ላይ በሳል ፖለቲካዊና ማህበራዊ ትችቶችን በማቅረብ ከሚታወቁት ፀኀፍት መሀከል 6ቱ ማለትም ማህሌት ፋንታሁን፣ በፍቃዱ ሀይሉ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ ዘላለም ክብረት፣ አጥናፍ ብርሀን፣ አቤል ዋበላ እንዲሁም ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ፣ ጋዜጠኛ አስማመው ኃ/ጊዎርጊስ እና ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል፡፡

ግለሰቦቹ በተለያየ ቦታ በየስራ ገበታቸው ላይ እያሉ ሁሉም በተመሳሳይ ሰዓት በፀጥታ ሀይሎች ተይዘው በማዕከላዊ ምርመራ ማዕከል ታስረው የሚገኙ ሲሆን፤ የተለያዩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት እስሩ በደንብ የታሰበበት ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ ታሳሪዎቹ ታሰሩ ከተባለበት ሰዓትና ደቂቃ ጀምሮ የሚገኙበትን አጠቃላይ ሁኔታ ለማጣራት አየሰራ ሲሆን ፤ እስካሁን በሰበሰበው መረጃ መሰረት ልጆቹን ለእስር የሚያበቃ ምን አይነት ማስረጃ እንደተገኘባቸው ለማወቅ አልቻለም፡፡

ሆኖም ግን ለእስር ከመዳረጋቸው በፊት ከመንግስት ሲርስባቸው በነበረው ህገወጥ ድርጊቶች ምክንያት ለረጅም ጊዜ ስራቸዉን ካቋረጡ በኋላ በቅርቡ ወደ ስራ መመለሳቸዉን ይፋ አድርገው እንደ ነበር ከድረ-ገጻቸው ላይ ለመረዳት ችለናል፡፡ ይህ ጉዳይ እስሩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎብናል፡፡


ስለሆነም የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ መንግስት ታሳሪዎቹን ለማሰር ያበቃው ተጨባጭ ማስረጃ ካለ ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ፤ ያ ካልሆነ ግን እስረኞቹን በአስቸኳይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቅ እናሳስባለን፡፡

የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

No comments:

Post a Comment