ኢሳት ዜና :-የህዝቦችን ደህንነት ከመንግስታት ጥቃት ለመከላከል የተቋቋመው ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል የተባለው ተቋም ለእንግሊዝ መንግስት የገቢዎቸና ጉምሩክ መስሪያ ቤት በጻፈው ደብዳቤ “ጋማ ኢንተርናሽናል የተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ በአለም ላይ የሰብአዊ መብቶችን በመጣስ ለሚታወቁ አገሮች ኮምፒይተሮችን፣ የሞባይልና የስካይፕ የስልክ ግንኙነቶችን እንዲሁም የኢሜል ልውውጦችን በርቀት ሆኖ ለመከታተል የሚያስችለውን ፊን ፊሸር ወይም ፊን ስፓይ በሚል ስም የሚጠራውን የመሰለያ መሳሪያ ከአውሮፓ ህብረት ውጭ ላሉ አገሮች በመሸጥ ዜጎች እንዲሰለሉና ደህንነታቸው አደጋ ላይ እንዲወድቅ በማድረጉ ምርመራ እንዲጀመር” ሲል ጠይቋል።
የግንቦት7 ከፍተኛ አመራር በሆኑት በ ዶ/ር ታደሰ ብሩ የግል ኮምፒዩተር ላይ የመሰለያ ቫይረሱ መገኘቱን በቶሮንቶ ዩኒቨርስቲ የሙንክ ስኩል ግሎባል አፌርስ የምርምር ተቋም የሆነው ሲትዝን ላብ ማረጋገጡን ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል በደብዳቤው ገልጿል።
የመሰለያ መሳሪያው የሰብአዊ መብቶችን በሚጥሱ 36 አገራት ላይ መሸጡን የገለጸው ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል፣ በተለይም በቬትናም፣ ማሌዚያና ኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን ለመሰለያነት እየዋለ ነው ብሎአል።
በኢትዮጵያ የግንቦት7 ከፍተኛ አመራር የሆኑት ዶ/ር ታደሰ ብሩ ኮምፒተራቸው ሲሰለል መቆየቱን የገለጸው ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል፣ በአንድ የብሃሬን የሰብአዊ መብት ተማጓች ኮምፒዩተር ላይም ተመሳሳይ የስለላ ሶፍት ዌር መገኘቱን ገልጿል።
ዶ/ር ታደሰ ብሩ ለፕራይቪሴ ኢንተርናሽናል ጠበቃ የምስክርነት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተናግረዋል። ፕራይቪሲ ኢንተርናሽናል የስለላ ቫይረሱን የሸጠውን ጋማ ኢንተርናሽናልን የተባለውን ድርጅት ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ማቀዱን ዶ/ር ታደሰ ገልጸዋል፡