Wednesday, October 29, 2014

የፋሽስቱ ወያኔ አገዛዝ በኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ያለው ጭቃኔ የተሞላበት የሰብአዊ መብት ጥሰት እጅግ ተባብሶ መቀጠሉን አምንስቲ ኢንተርናሽናል ገለፀ


የፋሽስቱ ወያኔ አገዛዝ በኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ላይ የእስራት፣ የስቃይ፣ የግድያ፤ የአስገድዶ መደፈር እና ሌሎችም ጭካኔ የተሞላባቸው ዘግናኝ የግፍ ተግባራትን እየፈጸመ ይገኛል ሲል ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምኒስቲ ኢንተርናሽናል ሰኞ ዕለት ባወጣው ሪፖርት ገለጿል። ድርጅቱ በፈረንጆች አቆጣጠር ከ 2011 እስካሁን ያለውን ሁኔታ አጥንቶ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ፣ ቁጥራቸው ከ 5 ሺ በላይ የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ኢትዮጵያውያን በእስር ላይ እንደሚገኙ በማመልከት በእስር ላይ የሚገኙት ሰዎች የግድያ፤ የከፋ ስቃይና ሰቆቃ እንዲሁም በሴት እህቶቻችን ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንደሚፈጸሙባቸው ተመልክቷል። 

«ምክንያቱም ኦሮሞ በመሆኔ» የሚል ርዕስ የተሰጠዉ የዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት አምኒስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ከ 200 በላይ ሰዎች ምስክርነትን በማየት ሰነዱ እንደተዘጋጀ የተመለከተ ሲሆን ፋሽስታዊው አገዛዝ ገበሬዎችን፤ አስተማሪዎችን፤ የጤና ባለሙያዎችን፤ የአገዛዙ ተቀጣሪዎች ሳይቀር በዘፈቀደ አስሮ የከፋ ስቃይ እየፈጸመባቸው እንደሚገኝ ጥናቱ አጋልጧል። መቀመጫውን በእንግሊዝ ያደረገው አምንስቲ ኢንተርናሽናል አብዛኛውን ለእስር ተዳርገው የከፋ ስቃይ እየተፈጸመባቸው የሚገኙት የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ኢትዮጵያውያን የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባርን ትደግፋላችሁ በሚል መሰረተ የለሽ ውንጀላ እንደሆነ ተመልክቷል። በግፍ ከታሰሩ ኦሮሞች ውስጥ ባሏ በኦነግ የተጠረጠረን ነፍሰ ጡር ሴት ያዋላደ ሃኪም፤ በማዳበሪያ አቅርቦትና ሽያጭ ቅሬታ ያሰሙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ገበሬዎች፤ ግበሬዎችን ለአመጽ አነሳስተሃል በሚል መሰረተ ቢስ ክስ የተከሰሰ የግብርና ባለሞያ እንደሚገኙበት ተገልጿል። 

በሪፖርቱ ላይ እንደተመለከተው የኦሮሞን ባህል ተግባራዊ የሚያደርጉ በ ብዙ 100 ዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በግፍ ለእስር መዳረጋቸው የተጠቆመ ሲሆን ሰዎቹ ይህን በማድረጋቸዉ አገዛዙን እንደሚፃረሩ ተደርጎ መወሰዱ እጅግ አሳዛኝና ህገወጥ ድርጊት መሆኑ ተመልክቷል። የአምንስቲ ኢንተርናሽናል አጥኚ ክሌር ቤስተን እንደገለጹት የፋሽስቱ ወያኔ አገዛዝ የኦሮሞ ተወላጅ ኢትዮጵያውያንን የሚያሰቃየዉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ደጋፊዎች ናቸዉ በሚል ጥርጣሬ መሆኑን በማመልከት ሰቆቃና ግፉ የሚፈፀምባቸዉ ሰዎች ደግሞ በሁሉም የሙያ መስክ የተሠማሩ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።


የአምንስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ተመራማሪ ክሌር ቤስተን አያይዘው እንደገለጹት የፋሽስቱ ወያኔ አገዛዝ በኦሮሞ ኢትዮጵያውያን ላይ እየፈጸማቸው የሚገኙትን እጅግ ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፍትሄ እንዲያገኙ በተደጋጋሚ ብናሳውቅም ፈጽሞ ፈቃደኛ ባለመሆኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ሁሉ በየዘርፉ በሰነድ በመያዝ ለአለማቀፍ መንግስታትና ማሕበረሰብ እናቀርባለን ሲሉ መናገራቸው ታውቋል። ኬንያ የሚገኙት የአምንስቲ ኢንተርናሽናል አጥኚ ክሌር ቤስተን አለማቀፉ ማህበረሰብ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንዲሁም የአፍሪቃዉ የሰብዓዊ ጉዳዮች ኮሚሽን በአስቸኳይ ነጻ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጣሪ ቡድን እንዲያሰማሩ ጠይቀዋል።

ይሁን እንጂ የተለያዩ የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ኢትዮጵያውያንና የፖለቲካ አራማጆች አገዛዙ ወደ እስር በማጋዝ ስቃይ እየተፈጸመባቸው የሚገኙት ኦሮሞዎች ቁጥር በአምንሲቲው ሪፖርት ከተጠቀሰው በእጅጉ እንደሚልቅ ምስክርነታቸውን እየሰጡ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል። ባለፉት 3 አመታት ከ 5 ሺ በላይ ኦሮሞች ለእስር ተዳርገው ስቃይ እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ ጥናቱ ይፋ ያድርግ እንጂ በተጠቀሱት ጥቂት አመት ውስጥ ብቻ የታሳሪዎች ቁጥር ከ 20 ሺ እንደሚልቅ እማኞች አመልክተዋል። በቅርቡ እንኳ ቁጥራቸው ከ 2000 በላይ የኦሮሞ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን አገዛዙ በአዲስ አበባ ዙሪያ ሊያደርግ ያቀደውን የመሬት ዘረፋ ጋር በተያያዘ ለእስር ተዳርገው ከፍተኛ ቶርቸር እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ እና ቁጥራቸው ከ 140 በላይ ኦሮሞዎች በአገዛዙ ቅጥረኛ አጋዚዎች በጥይት ተደብድበው መገደላቸው መዘገቡ አይዘነጋም። የፋሽስቱ ወያኔ በኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ላይ እያካሄደ ያለውን አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰትና አፈና ለማስቆም ህዝቡ በብሄር ሳይከፋፈል በጋራ መነሳት እንዳለበትም ተጠቋሟል።

No comments:

Post a Comment