Thursday, October 9, 2014

ህወሓት፡- ተገንጣዩ ገዥ ‹‹ፓርቲ››

(#ነገረ #ህወሓት፡- ክፍል ሁለት)

ጌታቸው ሺፈራው
...
ደቡብ አሜሪካ፣ አፍሪካ፣ ኤሲያ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ታጣቂ ቡድኖች የተፈለፈሉባቸው አህጉራት ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ታጣቂ ቡድኖች ደግሞ አንድም ከጨቋኝ የአገራቸው መንግስት አሊያም ከቅኝ ገዥዎች ነጻ ለመውጣት የሚንቀሳቀሱ ነበሩ፡፡ በመሆኑም ከአላማቸውም ባሻገር ነጻ አውጭነታቸውን በስማቸውም ይገለጻሉ፡፡ ሆኖም አብዛኛዎቹ ‹‹ነጻነት፣ አርነት›› የሚል ስም ቢይዙም ነጻ የሚወጡት ከአውሮፓውያኑ ስለነበር ክፋት አልነበረውም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካ ውስጥ ገብተዋል የሚባሉ አገራት ይገኙ የነበሩ አገራት ፓርቲዎች ሳይቀር ይህን ተገንጣይ ስሞች ሳይሆን አገራዊ አንዳንዶቹ ደግሞ አህጉራዊ ስም ይዘው ነው የተዋጉት፡፡ የጥቂት ነጮች አገዛዝ ደቡብ አፍሪካዊያንን ነጭ፣ ህንዳዊ፣ ጥቁር ብሎ በተለያዩ ቡድኖች ከፋፍሎ በሚገዛበት የእነ ማንዴላ የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረንስ ነበር ነጻ አውጭው፡፡ ሆኖም በጥቁሮች አሊያም በተወሰኑ ጎሳዎች ስም ‹‹ነጻ አውጭ ነን!›› አላሉም፡፡ ከዚህ ይልቅ ከደቡብ አፍሪካም አልፈው አህጉራዊ ስም ነው ይዘው ነው የታገሉት፡፡

በተመሳሳይ በሞዛምቢክ፣ አንጎላ፣ ዚምባብዊ የነበሩ ታጣቂ ቡድኖችና ፓርቲዎች አገራዊ ከዚያም አልፎ አህጉራዊ ስሞችን ይዘው ነው የተነሱት፡፡ ነጻ አውጭዎች ቢሆኑም ከአገራቸው በላይ አፍሪካንም ነጻ ማውጣት መሆን አምነው ነው ወደ ትግሉ የገቡት፡፡ በሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ዩጋንዳ፣ ሱዳንና ኮንጎ የነበሩትና ያሉትም በተመሳሳይ አገራዊና አህጉራዊ የነጻ አውጭነት ሚናን የያዙ ስሞችን መጠሪያቸው አድርገዋል፡፡ ለአብነት ያህል በአሁኑ ወቅት ችግር የገጠመውና ቆይቶ ደቡብ ሱዳንን ነጻ አገር ያደረገው የእነ ሳልቫኪር ፓርቲ ‹‹የሱዳን ህዝቦች ነጻ አውጭ ንቅናቄ›› ነው የሚባለው፡፡ ራሱን በደቡብ ሱዳን እንኳ አልሰየመም፡፡ አሊያም ከዚህ ወርዶ ራሱን ደቡብ ሱዳን ውስጥ በሚገኙ ጎሳዎች ስም አልጠራም፡፡

በእርግጥ በአሁኑ ወቅትም ቢሆን ተገንጣይ ቡድኖች ከዓለም ከነ አካቴው አልጠፉም፡፡ በሲሪላንካ፣ ኔፓል፣ እንዶኔዢያ፣ ሶማሊያ፣ ኮንጎ፣ ሱዳንና የመሳሰሉት አገራት አሁንም ታጣቂና ተገንጣይ ቡድኖች ይገኛሉ፡፡ ቱርክና የመሳሰሉት አገራት ውስጥ ስለ ኩርድ ህዝብ የሚንቀሳቀሱ ቢኖሩም የኩርድ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲና የመሳሰሉት ከተገንጣይነት ስም (ነጻነት፣ ሀርነት) ግንባር ያለፉ ስም የያዙ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ጉዳዩ የተለየ ነው፡፡ ይህን የጀመረው ጀብሃ ነው፡፡ ከዛ እነ ህወሓት መጡ፡፡ በአሁኑ ወቅት ሻዕቢያ እንኳን ያን ገንጣይ ስሙን ቀይሯል፡፡ ሻዕቢያ (የኤርትራ ህዝቦች አርነት ግንባር ይባል ከነበረው ስሙ) እ.ኤ.አ በ1994 ኤርትራን ውስጥ ስልጣን ከያዘ ከአንድ አመት (አገር ከሆነችበት) በኋላ ስሙን ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትህ ብሎ ቀይሯል፡፡ አብሮ አደጉ ህወሓት ግን አሁንም ድረስ ገዥ ፓርቲ ሆኖ፣ ሌሎች ድርጅቶችን በበላይነት እየመራ፣ ከ90 በላይ የሆነውን የመከላከያና ሌሎች የአገሪቱን ስልጣን ቦታዎች ጨብጦ የተገንጣይ ስሙን እንዳነገበ ነው፡፡ ከእሱ ይልቅ ከእሱ ጋር ኢህአዴግን የመሰረቱት ‹‹ፓርቲዎች›› ከህወሓት አንጻር የተሻለ ስያሜ አላቸው ማለት ይቻላል፡፡

  ከህወሓት ስር ከትራንስፖርት ሚኒስትርነት፣ ፕሬዝዳንትነትና የመሳሰሉት ዝቅተኛ ስልጣኖች የተወሰነው ኦህዴድ የጎሳ ወኪልነቱ እንዳለ ሆነ ቢያንስ በስም ደረጃ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ድርጅት›› ነው፡፡ ብአዴንና ደኢህዴንም ልክ እንደ ህወሓት በጎሳ ስም መጠራታቸው ከዓለም ወቅታዊ ሁኔታም ሆነ ከኢትዮጵያ አንጻር የሚገባ ባይሆንም የገንጣይ ስምነትን አለመሸከማቸው በአንጻራዊነት(ቢያንስ በስም) ከህወሓት የተሻሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ምንም አይነት ወይንም ከዚህ ግባ የማይባል ስልጣን ያላቸው ‹‹አጋር›› የሚባሉት ‹‹ፓርቲዎች››ም ቢሆን በስም ደረጃ የተሻሉ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከህወሓት ውጭ ተገንጣይ ስማቸውን ያልጣሉት ኦነግ፣ ኦብነግ የመሰሉ ህወሓት/ኢህአዴግ ‹‹አሸባሪ›› የሚላቸው ቡድኖች ብቻ ናቸው፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ ለምሰሌ የመለስ ጓደኛ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ለንጮ ለታ የሚመሩት ቡድን ተገንጣይ ስማቸውን ያለፈበት መሆኑን አውቀው ለወቅቱ ይመጥናል ያሉትን ስም በመጠሪያነት መጠቀም ጀምረዋል፡፡

ህወሓት ግን ገዥ ሆኖም፣ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖችን ‹‹አሸባሪ›› ብሎ እየፈረጀም ቢሆን የተገንጣይ ስሙን መቀየር አልቻለም፡፡ በዓለም ገዥ ፓርቲ ሆኖ ነጻ አውጭ ስም ያነገቡት ፓርቲዎች በጣት የሚቆጠሩት ብቻ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል ቲሞር ውስጥ ለበርካታ ጊዜ ገዥ ፓርቲ የሆነው ‹‹የምስራቅ ቲሞር ነጻነት አብዮታዊ ግንባር፣ የኢልሳቫዶሩ ፋራቡንዶ ማርቲ ብሄራዊ የነጻነት ግንባር፣ የዶሚኒካ ነጻነት ፓርቲ ይገኙበታል፡፡ ሆኖም ስማቸውን ‹‹ነጻ›› አውጭ ብለው የሰየሙበት ምክንያት ከህወሓት ጋር ለየቅል ነው፡፡

የቲሞሩ ገዥ ፓርቲ መጀመሪያ እንደ ፓርቹጋል ካሉ ቅኝ ገዥዎች ጋር የተዋጋ ፓርቲ ነው፡፡ ይህ ፓርቲ በተለያዩ ጊዜያት በምርጫ ተሸንፎ ለተቃዋሚዎች ስልጣኑን በሰላማዊ መንገድ አስረክቧል፡፡ ለአብነት ያህል እ.አ.አ በ2007ና 2012 ስልጣኑን በሰላማዊ መንገድ አጥቷል፡፡ የኢልሳቫዶሩ ገዥ ፓርቲም ብቻውን ሳይሆን ከሌላኛው የአገሪቱ ፓርቲ ጋር ነው አብሮ እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህ ፓርቲ በአብዛኛው እያሸነፈ የሚገኘው ከ40ና ከ30 በታች ድምጽ ነው፡፡ የዶምኒካን ፓርቲ ‹‹ማዕከላዊነቱ››ና ሌሎች አንዳንድ ፖሊሲዎቹ ከኢህአዴግ ጋር የሚያመሳስሉት ቢሆኑም የጎሳ ነጻ አውጭ አይደለም፡፡ ኢልሳቫዶር 6 ሚሊዮን ያህል ህዝብ ይኖርባታል፡፡ ዶሚኒካ ሪፖብሊክ 9 ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርባት ትንሽ አገር ናት፡፡ ምስራቅ ቲሞር ደግሞ ከአብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ትልልቅ ከተሞች የሚያንስ አንድ ሚሊዮን ህዝብ መኖሪያ አገር ነች፡፡ በእነዚህ አገራት የሚኖሩ ገዥ ፓርቲዎች ከኢትዮጵያ አንጻር በጣም ጥቂት ህዝብ ነው የሚያስተዳድሩት፡፡

መንግስትን እመራለሁ የሚል ገዥ ፓርቲ የሚቀረጸው እንደ ህዝብ ብዛትና ሌሎች የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ይሆናልና ኢትዮጵያ በእነዚህ ትንንሽ አገራት ከሚገኙት ገዥ ፓርቲዎች የተሻለ ገዥ ፓርቲ ያስፈልጋት ነበር፡፡ በእነዚህ ሶስት አገራት የሚገኙ ገዥ ፓርቲዎች ራሳቸውን ነጻ ቢያደርጉም አገራዊ እንጅ ጎሳዊ ውክልናን ይዘው አልተነሱም፡፡ አልቀጠሉምም፡፡ የ90 ሚሊዮን ህዝብ ባለቤቷ ኢትዮጵያን ገዥ የሆነው ህወሓት ግን አሁንም የጎሳ/ብሄር ነጻ አውጭነት ስሙን መቀየር አልቻለም፡፡ በርካታ ጉዳዮችን ከተማረበት ሻዕቢያ እንኳ መማር አልቻለም፡፡ እንዲያውም ከሻዕቢያም በላይ ህወሓት ነው ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት እንደነበረች በተደጋጋሚ ይገልጽ የነበረው፡፡ የህወሓቱ መለስ ዜናዊ በዚህ ጉዳይ ከሁለት በላይ መጽሃፍቶችን መጻፋቸው ይታወቃል፡፡ ሆኖም ሻዕቢያ ‹‹የኤርትራ ነጻ አውጭ›› ስሙን ጥሎ አገራዊ ስም ሲይዝ የቀድሞ አቋሙን በመቀየር ድል ሲቀናው ‹‹ትግራይ ከኢትዮጵያ ጋር ከኤርትራ የተሻለ ታሪካዊ ትስስር አላት›› ብሎ ወደ ምኒሊክ ቤተመንግስት ያቀናው ህወሓት አሁንም ድረስ ነጻ አውጭነቱን እንደተሸከመ ነው፡፡ ይህ ነጻን ህዝብ ነጻ የማውጣት ተግባር አሁንም እወክለዋለሁ የሚሉትን ህዝብ መያዧና ከሌላው ጋር የረባ ግንኙነትና አንድነት እንዳይኖረው ማጎሪያ መሆኑን የብዙዎቹ እምነት ነው፡፡

ይህ የገዥ ተገንጣይነቱ ህወሓትን ለኢትዮጵያ የማይመጥን ብቻ ሳይሆን በዓለምም ለየት ያለ (የማይመጥን) የፖለቲካ ቡድን ያደርገዋል፡፡ ይህ የህወሓት የገዥ ተገንጣይነት ከኢትዮጵያ በባሰ ውድቀት ላይ ባሉ አገራት የማይታይ ዓለም የማትሸከመው የፖለቲካ ቁመና ነው፡፡ እየተበጣበጠች በምትገኘው ደቡብ ሱዳን አንድም በጎሳ መሰረት ነጻ አውጭ ሆኖ የተቀመጠ ፓርቲ የለም፡፡ የሱዳን ህዝቦች ነጻ አውጭ ንቅናቄ፣ የተባበሩት ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ የደቡብ ሱዳን ዴሞክራሲያዊ መድረክ፣ የደቡብ ሱዳን ሌብራል ፓርቲ፣…… የመሳሰሉት ስሞች ነው ያላቸው ናቸው፡፡ የእርስ በእርስ ጦርነት በሚንጣት ሱዳንም ቢሆን ፓርቲዎች አገራዊ ስም የያዙ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ሌብራል ዴሞክራሲ ፓርቲ፣ ብሄራዊ ኮንግረንስ፣ የሱዳዝ ባዝ ፓርቲ፣ ዴሞክራሲያዊ የአንድነት ፓርቲ….. የመሳሰሉትን የሚይዝ ነው፡፡ ታጣቂ ቡድኖችም እንኳ ይህን ከዓለም የጠፋ አስነዋሪ ስም አልያዙም፡፡ ሰላም አስከባሪ በሚጠብቃት ላይቤሪያ የአንድነት ፓርቲ፣ ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ጥምረት ለሰላምና ዴሞክራሲ…. የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

 ህወሓት ከተመሰረተ አራት አስርት አመታት እየሞላው ነው፡፡ የተዋጋውም የውጭ ወራሪን ሳይሆን የአገር ውስጥ ገዥዎችን ነው፡፡ ቅኝ ተገዝተዋል ያላቸው ኤርትራውያን ፓርቲ የሆነው ሻዕቢያ እንኳን ስሙን ሲቀይር ህወሓት ግን እስካሁን አልቀየረም፡፡ ማንም ነጭ የትግራይን ህዝብ አልገዛም፡፡ ህወሓት ከተማሪዎችም ሆነ ከቀዳማይ ወያኔ ወጥቻለሁ ሲል የትግራይን ህዝብ ነጻ የሚያወጣም ከኢትዮጵያ ገዥዎች ነው ብሎ የሚያስብ ሊኖር ይችላል፡፡ ሆኖም የንጉሱ ስርዓት ተንኮታኩቶ ደርግ ሲወድቅ ህወሓት የነጻ አውጭነት ስሙን አሁንም እንዳነገበ ቀጥሏል፡፡ ህወሓት ይህንን የገንጣይ ስም በስያሜነት ሲጠቀም ጥቁር አሜሪካውያን ስለ ነጻነታቸው የሚታገሉበት ወቅት ነበር፡፡ አሜሪካች አሁን ኦባማን ከአለም ትልቁ የስልጣን ማማ ላይ አስቀምጠዋል፡፡ በእርግጥ በዚህ ወቅት ነጭ አሜሪካውያን እንደሰው የማይቆጥሯቸው የነበሩት ጥቁር አሜሪካውያን ነጻ አውጭ ስምም ሆነ አላማ አልነበራቸውም፡፡ አሁንም ቢሆን አድሎና መገለል ሙሉ በሙሉ ከአሜሪካ ባይጠፋም ጥቁር አሜሪካውያን ግን ነጻ አውጭ አላስፈለጋቸውም፡፡ ምክንያቱም አገራዊ አላማ ይዞ እንደመታገል ያለ ሞራላዊ ጉዳይ ስለሌለ ነው፡፡

 ለአሜሪካውያን ጥቁሮች ነጸነት ሲታገሉ በሞቱበት ወቅት ስሙን ‹‹ህወሓት›› ብሎ የሰየመው በጥቁሮች ዘንድ ነጻ ተደርጋ የምትወሰደው የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ ግን እነ ኦባማ ስልጣን ላይ በወጡበት በአሁኑ ወቅትም በገንጣይ ስሙ ቀጥሏል፡፡ ህወሓት ራሱ ስልጣን በያዘበት ህዝብን ከማን ነው ነጻ የሚያወጣው? ከ99 በላይ የመከላከያ ሰራዊቱ አባል፣ የደህንነት መስሪያቤትና ሌሎቹም ተቋማት በእሱው ታጋዮች በተሞሉበት ህዝብን ከማን ነጻ ያወጣል? ኢትዮጵያ ማለት የአቶ መለስ ዜናዊ ታሪክና ዝና በእያንዳንዱ ተቋም አልፎ ቤት ለቤት እንዲዘመርባት የምትደርግ አገር ነች፡፡ ስፖርት፣ ጎዳና፣ ትምህርት ቤት፣ ……..ሁሉም በሟቹ የህወሓት አመራር ስም ተሰይመዋል፡፡ የህወሓት ባለስልጣናት፣ ካድሬዎች፣ ደህንነቶች፣ የመከላከያ አባላት በመላው የአገሪቱ ክፍል አዲስ ፊውዳል ሆነዋል፡፡ ታዲያ ማንን ከማን ነው ነጸ የሚያወጣው?

ህወሓት ገዥ ፓርቲ እንደመሆኑ በውጭ ጉዳይ፣ በመከላከያ፣ በደህንነቱ፣ በአጠቃላይ በአገሪቱ በሚገኙት ስልጣኖች የትግራይን ህዝብ ሳይሆን ኢትዮጵያውያንን እያገለገልኩ ነው እያለን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ብሎም መንግስትን በትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ስም መንግስት እየመራሁ ነው እያለን ነው፡፡ መሪው በሞቱ ወቅት ደግሞ መለስ ሶማሊም፣ አፋርም፣ አማራም፣ ወላይታም፣…….ብቻ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች አባል፣ ወኪልም ናቸው ብለውናል፡፡ ታዲያ ህወሓት ለምን እስካሁን አንድን ‹‹ብሄር›› ነጻ አውጭ ስም ተሸክሞ ቀጠለ? እስከመቼስ ይቀጥላል? እንቆቅልሽ ነው!

No comments:

Post a Comment