Wednesday, October 22, 2014

አሳዳጅነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገለጫ አይደለም


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊትና ታሪካዊት እንደ መሆኗ መጠን ለሀገራችን ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን ስታበረክት መኖሯ የታወቀ ነው፡፡ ለአብነት ያህል ብንመለከትም በኪነ ሕንፃ፣ በዘመን አቆጣጠር፣ ፊደልን ቀርጾ በመስጠት፣  በመቻቻል፣ በመከባበር፣ ትውልድን በማነፅ ያበረከተቻቸው አስተዋጽኦዎች በጥቂቱ የሚነሱ ምሳሌዎች ናቸው፡፡

በእነዚህ እና ሌሎች መልካም ሥራዎቿ ከኢትዮጵያ አልፋ ለዓለም ሀገራት ያበረከተችው አስተዋጽኦ እጅግ የሚያስደንቅና የሚያስመሰግን ነው፡፡ በዚህም ትውልድ ይኮራባታል፤ ሀገርም ይመካባታል፡፡

በጎቿ ከእቅፏ እንዳይወጡ ከማድረግ በተጨማሪ በብሔራዊና ማኅበረ ሰባዊ ጉዳዮች በትጋት የምትሠራው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ትውልዱ ተከባብሮና ተቻችሎ በፍቅር እንዲኖር ለማድረግ ብዙ አስተዋጽኦ አድርጋለች፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰው ልጆች በነፃ ፈቃዳቸው የመረጡትን እምነት የመከተል መብት ያላቸው መሆኑን ከአምላኳ በተማረችው መሠረት በተግባርም ትፈጽመዋለች፡፡

ለዚህ ሁነኛ መሣሪያዎቹም ብዙ ናቸው፡፡ ለአብነትም የነቢዩ መሀመድ ወገኖች የነበሩት ጥቂት ስደተኞች ነቢዩ ገና ኃይል ባላገኘበትና ጦር ባላሰባሰበበት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ጥገኝነትን የፈቀደች፣ ሌሎች ቤተ እምነቶች ሲመጡም ከእኔ ውጭ ሌላ አይኑር ያላለች ናት፡፡ ይህንንም ዓለም የሚመሠክረው የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን መቻቻል የተቀበለችው ከፈጣሪዋ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በክርስቶስ ደም ተመሥርታለችና ክርስቶስ የፈጸመውን ሁሉ ትፈጽማለች፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን ስታደርግ በጎቿን በማስተማርና በመጠበቅ ሲሆን በረቱን ለመስበር የሚሞክርን ቀሣጭ ተኩላ ግን ተው ከማለት ወደ ኋላ አትልም፡፡

ሌሎች ቤተ እምነቶችም ተከታዮቻቸውን ይጠብቃሉ፤ የሚነካባቸውንም አይወዱም፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ሌሎች እንዲኖሩ መብታቸውን ሳትነፍግ፣ ልጆቿ ወደ ተሳሳተ መንገድ እንዳይገቡና ሰማያዊ መንግሥትን እንዲወርሱ አበክራ ትሠራለች፡፡


ይህንን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውለታ የዘነጉት ወጭት ሰባሪዎችና በጎቿን መጠበቋ የሚከነክናቸው እና ያልተመቻቸው፣ በ "world council of churches" የምእመናን መሰራረቅ (sheep stealing) ስምምነት ለመፈረም ፈቃደኛ ያልሆኑት መናፍቃን ተኩላዎች ግን በተለያዩ ጊዜያት በዓለም መድረክ የቤተ ክርስቲያኒቱን ስም ጥላሸት ሲቀቡ ተስተውለዋል፡፡

ለዚህም በቅርቡ ወርልድ ወች ሊስት (World Watch List) የተባለ በዓለም ላሉ ክርስቲያኖች መብት እቆረቆራለሁ የሚል ምዕራባዊ የሚዲያ አካል በዓለም ክርስቲያኖችን ከሚያሳድዱ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን ከከፍተኛዎቹ አሳዳጅ ሀገራት ጎራ በመመደብ በ15ኛ ደረጃ ማውጣቱ እጅግ የሚያሳዝንና ቆም ብለን እንድናስብ የሚያደርገን ነው፡፡


እንደ ወርልድ ወች ሊስት ዘገባ ከሆነ ኢትዮጵያ ክርስቲያኖችን በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ ከሚያደርጉ ሀገሮች መካከል ሊታመን በማይችል ሁኔታ በ15ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ያደረጋት ሲሆን፤ ለዚህም ተጠያቂ ያደረገው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ነው፡፡


ኢትዮጵያ ክርስቲያኖችን በማሳደድ ደረጃ ከእነ ሊቢያ (17ኛ ደረጃ) እና ግብጽ (25ኛ ደረጃ) በላይ ዋና አሳዳጅ ተደርጋ ተቀምጣለች፡፡ ለምሳሌ በግብጽ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ እንኳ በአክራሪ ሙስሊሞች ብዙ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ተገድለዋል፤ ተሰድደዋል፤ አብያተ ክርስቲያናት ፈርሰዋል፤ ተቃጥለዋል፡፡


እነዚህ እጅግ ዘግናኝ የሆኑ ድርጊቶች የተፈጸሙባት ሀገር ግን በእነርሱ ፕሮፖጋንዳ አሳዳጅነቷ ከኢትዮጵያ በታች ናት፡፡ ይህ የሚያመለክተው ለወርልድ ወች ሊስት ክርስትና ማለት ኦርቶዶክስ ሳይሆን ፕሮቴስታንትና ተሐድሶ መሆናቸውን ነው፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ መናፍቃንና እነሱ የፈጠሯቸው ተሐድሶዎች በፈለጉት መጠን ኦርቶዶክሳውያኑን አመናምነው መስፋፋት ስላልቻሉ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ቤተ ዕምነት መሆኗን ዕውቅና ባለመስጠት ይህንን የሚድያ ሥነ ምግባርን ያልተላበሰ ተራ ወሬ  አውጥቷል፡፡

በኢትዮጵያ የሃይማኖት እኩልነት በሕገ መንግሥቱ ተረጋግጦ ሁሉም ሰው የመሰለውን እየተከተለ ባለበት ሰዓት፣ ሌሎች እምነቶችም በነጻነት እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ወቅት ይህንን ዜና ለዓለም ማሰማት ማለት እውነትን በዐደባባይ መካድ ከመሆኑ በተጨማሪ ከጀርባው ሌላ ተልእኮ ያለው መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ ወርልድ ወች ሊስት ይህንን ዘገባ ሲያወጣ ከጀርባው የራሱ የሆኑ ዓላማዎች አሉት፡፡

ከእነዚህም መካከል የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል ሀገሪቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟን ጥላሸት ለመቀባትና በዓለም ያላትን ክርስቲያናዊ ገጽታ  ለማደብዘዝ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውልዱ ባሕሉንና ትውፊቱን ጠብቆ እንዲጓዝ ከማድረግ አንጻር የምታደርገውን ታላቅ አገልግሎትና አስተዋጽኦ ለመግታት፣ ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉትን ብፁዓን አበውን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን፣ ምእመናንንና የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማሸማቀቅና አንገት ለማስደፋት የተደረገ ስልታዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡

እነዚህ አካላት ሌላው የሚቆጩበትና በኢትዮጵያ ለማጥፋት የሚፈልጉት እነሱ የሚደግፉትንና የሚያበረታቱትን ሕገ እግዚአብሔርን የጣሰ የግብረ ሰዶማዊነት ሥነ ምግባርን የምታወግዝበትን አቋም ነው፡፡


በመሆኑም የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች ብፁዓን አበው፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ይህ ዘገባ ለምን እንደ ወጣ፣ ከጀርባው ምን ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ቆም ብለው ሊያጤኑት ይገባል፡፡ እውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሌሎች እምነቶች እንዳይኖሩ ታሳድዳለችን?

የሃይማኖት መቻቻልን ተግባራዊ ያደረገች ሀገር ክርስቲያንን በማሳደድ በዐደባባይ ክርስቲያኖችን ከሚያርዱ አረማውያን ቀድማ የምትጠቀስ ሀገር ናትን? ለኢትዮጵያና ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚከፈለው ውለታስ ይህ ነውን? እውነት ይነገር ቢባል ልጆቿ እንደ በግ በዐደባባይ ታርደውባት እንኳ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው እያለች የምትጸልይ ቤተ ክርስቲያን ማን ናት?

ገዳማቷና አብያተ ክርስቲያናቷ የተቃጠሉባት ቤተ ክርስቲያን ማን ናት? የራሷን መብት እያጣች ያለችው ማን ናት? ሲረግሟት የምትመርቅ፣ ሲገፏት የምትከተል፣ እየጣሏት የምታነሣ፣ እየተበደለች የምትክስ የሰላም እመቤት ማን ናት?

ይህ የተሳሳተና ፍጹም ውሸት የሆነ ዘገባ መውጣቱ ለኢትዮጵያ በተለይም ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉንዳን ሳይገባ አመድ ነስንሱ የሚያስብል ነው፤ ምክንያቱም አመዱ ካልተነሰነሰ መንገድ ላይ ያለው ወደ ኋላ አይመለስምና፡፡

ዓለሙ የሳይንስ ውጤቶችንና ዕውቀቶችን ለልማትም ለጥፋትም ይጠቀምበታልና ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት እየቀሰጠ ያለው አጽራረ ቤተ ክርስቲያንም በጀት በመመደብ ተሐድሶ የሚል ቡድን አቋቁሞ የቤተ ክርስቲያንን በጎች እየነጠለ ለመስረቅ ያለውን ዓላማ፣ ስልትና አሠራር ለቤተ ክርስቲያን አባቶች ማኅበሩ እያቀረበ እርምጃ ያስወሰደበት ሁኔታ የሚዘነጋ አይደለም፡፡


በዚህ ላይም የወጡ የጽሑፍ፣ የድምፅና የምስል ሰነዶች በማኅበሩ ሱቅ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ይህንን መሰል ዘመቻ ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ ቤተ ክርስቲያንን (ምእመናንን) ለማጥፋት ሲያደርግ የነበረው ቀጣይ ሥራ ስለሆነ አዲስ አይደለም፡፡ በመሆኑም "በአፍ የመጣውን በአፍ፣ በመጻፍ የመጣውን በመጻፍ" እንዲሉ፣ ዝም ተብሎ የማይታይና የሚጠበቅ አይደለም፡፡

ይህ ዓለም አቀፋዊ ነኝ የሚለው አካል መግለጫ ዓላማ ያለውና በውጭ ብቻ ተወርቶ የሚቀር ሳይሆን፣ የተለያዩ ወኪሎችን በማሰማራትና የተለያዩ አካላትን በመጠቀም ዘገባው እንዲወጣ የተደረገበትን ዓላማ ለማሳካት ጥረት የሚያደርግ ነው፡፡

በመሆኑም ቤተ ክርስቲያንንና ሀገርን አፍራሽ የሆነውን አካሄድ መርምሮ በማወቅ ለማስተማርና ለመገሠጽ ሁሉም በየድርሻውና በየተዋረዱ ሁኔታውን ሊመረምርና ተባባሪ ካለመሆን ጀምሮ  ሓላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡

ይህ ሪፖርት በአንድም በሌላም መንገድ የሚያስገነዝበን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት የሚደረገው ዘመቻ ምን ያህል እየረቀቀ እንደሆነና እነዚህ አካላት ሀገሪቱንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የመናፍቃን መፈንጫ ለማድረግ ያላቸውን ረጅም ዓላማና ጠንካራ አቋም ነው፡፡

ይህ አላማቸው ደግሞ ሕያው የሆነው እግዚአብሔር፣ ቅዱሳኑና የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች እስካሉ ድረስ ይሳካላቸዋል የሚል እምነት የለንም፡፡ ነገር ግን እንቅሰቃሴያቸው እጅግ ስልታዊና የተቀነባበረ በመሆኑ አርቆ ማሰብን የሚጠይቅ ነው፡፡ በመሆኑም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የቤተ ክህነት ሓላፊዎች፣ እንዲሁም በየተዋረዱ ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ይህንን በውጭም ሆነ በቅርብ ሆኖ በውክልና ኦርቶዶክሳዊነትን ለማዳከም የሚደረግ እንቅስቃሴና የስም ማጥፋት ዘመቻ ሃይ ለማለት እግዚአብሔርን አጋዥ አድርጎ በትጋት መሥራት ግድ ይላቸዋል፡፡

እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ለምእመናኑ በማሳወቅ፣ የሚወጡት የስም ማጥፋት ዘመቻዎች መሠረተ ቢስ መሆናቸውን ለዓለም በማሳወቅና የቤተ ክርስቲያኒቱን መልካም ገጽታ በመገንባት ከመቼውም በተሻለ መልኩ መንቀሳቀስ ስለሚያስፈልግ መሬት ላይ ጠብ የሚል  ተጨባጭ ሥራ መሥራት ግድ ይላል፡፡

እነርሱ ቤተ ክርስቲያኒቱ በመናፍቃን እንድትዋጥ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ሥራዎችን ሌትና ቀን እየሠሩ ስለሆነ በቤተ ክርስቲያን አባቶች በኩል ዘመኑ የሚጠይቀው የኖላዊነት ተግባር ፋታ የማይሰጥ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡

ምእመናን የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሾች እንዳይሆኑ ሰይጣን የተቻለውን ሁሉ ሲያደርግ ቆይቷል፤ አሁንም እያደረገ ይገኛል፤ ወደ ፊትም ማድረጉን አያቆምም፡፡ በመሆኑም ይህ ዓለም አቀፍ ነኝ የሚለው ሚዲያ ዘገባ፣ በዕቅድና በሥልት የቀረበ፣ በመጨረሻ ላይ ሊያሳካ ከሚፈልገው ግብ አንጻር የተዘጋጀ ስለሆነ፤ ምእመናን የሰይጣንን ዓላማና ግብ እንደ ተለመደው በቅንዓትና በጸሎት በማሸነፍ፣ በሚወጡ አሉባልታዎች ሳይደናገጡና ሳይበገሩ የአሉባልታውን ግብና ዓላማ በመረዳት እንደ እስካሁኑ ሁሉ አበው በደማቸው ያቆይዋት ሃይማኖት በጽናትና በረድኤተ እግዚአብሔር ተጠብቃ ትውልዱን የዋጀች እንድትሆን መትጋትና የቤተ ክርስቲያንን ጠላቶች ሩቅና ጥልቅ የሆነ ተንኮልና ዘመቻም በአግባቡ መረዳት ይገባቸዋል፡፡

ዘመቻውና ፈተናው እንደ ዘመኑና ወቅታዊ ሁኔታዎች የረቀቀ እየሆነ ስለሚሔድ በፈተና ውስጥ አልፎ ሰማያዊ መንግሥትን መውረስ የክርስቲያን መገለጫ ነውና እንደተለመደው ሁሉ ምእመናን፣ የነገሮችን አመጣጥና አካሔድ መርምሮ በማወቅ፣ ምክረ አበውን በመስማትና የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ጠብቆ በመጓዝ ኦርቶዶክሳዊነታቸውን በተግባር ማሳየት ይኖርባቸዋል፡፡

ለዚህም በዘመኑ ያለውን ፈተና መርምሮና አገናዝቦ መሔድ ወሳኝነት ያለው ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚሆነው ከጸሎት ባሻገር ክርስትናን በአግባቡ ማወቅና መረዳት፣ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን፣ ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚጠቀሙባቸውን አካላት እና የሚሔዱባቸውን መንገዶች በማወቅ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በማስፋፋት ዘመኑን የዋጀች ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው፡፡

ሰንበት ትምህርት ቤቶች ቤተ ክርስቲያንን በመጠበቁ በኩል ድርሻ ያላቸው ስለሆነ፤ በቃለ እግዚአብሔር ላይ በተመሠረተ ትጋት ጠላት ዲያብሎስ የሚነዛውን ከንቱ ወሬና ዓላማ ራሱ እንዲገሠጽበትና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የማፍረስ ተልእኮው እንዳይሳካለት፣ ራሳቸውን በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር በማነፅ የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ አገልግሎት ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል፡፡


ወጣቱ ለመረጃ ቅርብ እንደ መሆኑ መጠን እንደነዚህ ዓይነት የተዛቡ አመለካከቶች በማንኛውም ደረጃ ሲከሰቱ መረጃውን ለአባቶች በማድረስ፣ በተቻለ መጠን በዕውቀትና በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር እውነታውን በማስረዳትና የመፍትሔው አካል በመሆን የበኩሉን መወጣት ይኖርበታል፡፡ ወጣቱም አባቶቹ ያስቀመጡለትን ሀገርና ሃይማኖት ተረክቦ ለቀጣዩ ትውልድ ሊያስተላልፍ የሚችለው፣ ሀገሩንና ሃይማኖቱን እስከ መገለጫቸው ጠብቆ ሲያቆይ ነው፡፡

በአጠቃላይም በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ቦታዎች ሀገረ እግዚአብሔር የተባለች ኢትዮጵያና ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን እንደ «አህዛብ» አሳዳጅ በመቁጠር ክርስቲያኖችን ታሳድዳለች በማለት የወጣው ዘገባ የራሱ የሆነ ዓላማና ግብ ያለው እንጂ ዕውነትነት የሌለው ነው፡፡

ለዚህ መርዛም እቅድ ተፈጻሚነትም በበጀት ካቋቋሟቸው ጀምሮ የተለያዩ አካላትን ለመጠቀም እየወጡ እየወረዱ እንዲሁም በእነሱ በኩል ካልተሳካላቸው ደግሞ ዱላ ለማቀበል ጥረት እያደረጉ ስለሆነ ማንኛውም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አማኝ ሃይማኖቱ ህልውናው እንደ መሆኑ መጠን  ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ ቀድሞ እየሔደ የሚያሰቀምጠውን የማሰናከያ ድንጋይና ደባ በማጋለጥና ርቃኑን በማስቀረት የጌታችን ቅዱስ ወንጌል እንዲሰበክ ለማድረግ «ማሳደድ የቤተ ክርስቲያኗ መገለጫ አለመሆኑን» ክርስቲያናዊ በሆነ ሥነ ምግባር ማስረዳት ይኖርበታል፡፡


ኦርቶዶክሳዊነትን ለማጥፋት ለተያዘው ጥልቅና ዓለም አቀፋዊ ረቂቅ ተልእኮም አንዱ ስልት እነርሱ በፈጠሯቸውና እንደ ልባቸው ያሻቸውን በሚናኙባቸው ዓለም አቀፍ ሚድያዎቻቸው እና ሊጠቀሙባቸው በሚችሉባቸው መንገዶች ሁሉ ሁኔታዎችን አሟጦ በመጠቀም ኦርቶዶክሳዊነትንና ኦርቶዶክሳውያኑን ማሸማቀቅና አንገት ማስደፋት መሆኑን ተጨባጭነት ያላቸውን አስረጂዎች እየጠቀሱ በማስረዳትና በማስገንዘብ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ልንተጋ ይገባል፡፡

                                 ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!

No comments:

Post a Comment