Wednesday, October 8, 2014

መንግስት ብዙሃን መገናኛዎችን ለማጥፋት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እናወግዛለን! የፕሬስ እና ሀሳብን የመግለፅ ነፃነት እንደረጋገጥም እንታገላለን!



የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ(ኢጋመ) 
-------------------------------------
መንግስት ብዙሃን መገናኛዎችን ለማጥፋት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እናወግዛለን! የፕሬስ እና ሀሳብን የመግለፅ ነፃነት እንደረጋገጥም እንታገላለን! 
-------------------------------------
ከኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ(ኢጋመ) የተሰጠ መግለጫ
-------------------------------------
ብዙሃን መገናኛዎች ለሀገራችን ሁለንታናዊ እድገት፣ ለዴሞክራሲ ግንባታና ለዜጎች መብትና ጥቅም መከበር ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳላቸው አያከራክርም፡፡ ሚዲያዎች የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ ለማዋጣት እንዲችሉ የፕሬስ ነፃነት መከበር መሰረታዊ ቢሆንም የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ እውነታ በተቀቃራኒ አጥፊ እርምጃዎቸን እየወሰደ መሆኑ ማህበራችንን አሳስቦታል፡፡
የሚዲያ ተቋም ባለቤትነትም ሆነ በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ መሰማራት “ወንጀል” እስኪመስል ድረስ መንግስት ተቋማቱን ከስራ ውጪ በማድረግ፣ ጋዜጠኞችን ማሰርና ማሰደድን ስራዬ ብሎ መያዙ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት ፀሐይ እያዘቀዘቀች መሆኑን አመላካች ነው፡፡

1. ማህበራችንም የዚህ የመንግስት የተሳሳተ ዕይታ ሰለባ ሆኗል፤ አስፈላጊውን ህጋዊ ቅድመ ሁኔታ አሟልቶ ያቀረበው የዕውቅና ጥያቄ ያለህግ አግባብ እስከ አሁን ድረስ ተባይነት ሳያገኝ ቆይቷል፡፡ ይባስ ተብሎም በመንግስት አካላት ማህበራችን ላይ “ለአፍራሽ አላማ የተቋቋመ” የሚል የፍረጃ ታፔላ በመለጠፍ በቴሌቪዥን ማስታወቂያ ስም እስከማስጠፋትም የዘለቀ እርምጃ ተወስዷል፡፡
2. በቅርቡ በአምስት መፅሔቶችና በአንድ ጋዜጣ አሳታሚዎች ላይ መንግስት ክስ ከፍቶ በትላንትናው ዕለትም መስከረመ 27 2007ዓ.ም ከተከሰሱት 6 የሚዲያ ተቋማት መሀከል የሶስቱ (የፋክት፣ የአዲስ ጉዳይና የሎሚ መጽሔት) ስራ አስኪያጆች ላይ በሌሉበት የእስር ቅጣት ተላልፎባቸዋል፡፡
3. በመንግስት የሰላ ሒስ በማቅረብ የሚታወቁ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን የሚያትሙ ማተሚያ ቤቶች ከመንግስት በሚደርስባቸው ማስፈራሪያና ጫና ምክኒያት እነዚህን የፕሬስ ውጤቶች አናትምም በማለታቸው በርካቶቸቹ ከህትመት ውጪ ሆነዋል፡፡ መታተም ካቆመች 6 ሳምንታትን ያስቆጠረችው የኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና የማህበራችን የጠቅላላ ጉባኤ አመራር የሆነው ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ በትላንትናው ዕለት ማዕከላዊ ተጠርቶ ክስ እንደቀረበበት ከተነገረውና ቃሉን ከሰጠ በኋላ በ 5000.00 ብር ዋስ ተለቋል፡፡
4. በ5 መፅሔቶችና በአንድ ጋዜጣ አሳታሚዎች ላይ መንግስት የከፈተውን ክስ ተከትሎ ከ25 በላይ የሆኑ ጋዜጠኞች ለደህንነታቸው በመስጋት ከሀገራቸው ሊሰደዱ ችለዋል፡፡


የሰሞኑ ክስና ጫና ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ሃሳባቸውን በብዙሃን መገናኛዎች በይፋ የፃፉ ጋዜጠኞችን እስከ 18 አመት በዘለቀ እስር እንዲቀጡ እስከማድረግ መድረሱ የጋዜጠኞቹ የስደት ምክንያት መሆኑን እንገነዘባለን፤ ሆኖም ማህበራችን ስደት የዚህ መፍትሄ ይሆናል ብሎ አያምንም፤ ይልቁኑም መንግስት ይህን ኢህገመንግስታዊ የሆነ የጥፋት እርምጃ እንዲያቆም ከባለድርሻ አከላላት ጋር የተቀናጀ ትግል ማድረግ ትክክለኛው መፍትሄ እንደሆነ ያምናል፡፡ በቅርቡ የተከሰተው ጋዜጠኞች ስደት የማህበራችንን አመራሮችም ጭምር ያካተተ መሆኑ ታቅደው የነበሩ ስራዎች በጊዜአቸው እንዳይሰሩ እንቅፋት ሆኖብን ቆይቷል፡፡ ማህበራችን በተከታታይ ከውስጥና ከውጪ ያጋጠሙትን ችግሮች ለመፍታት አስፈላጊውን ዝግጅትና ጥናት በማጠናቀቁ በያዝነው አመት የተጠናከረ እንቅስቃሴ ለማድረግ አቅዷል፡፡

ማህበራችን መንግስት ብዙሃን መገናኛዎችን ለማጥፋት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በዝምታ አይመለከተውም፤ የፕሬስና ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት በሀገራችን በምልዐት እንዲተገበር በውጤቱም የጋዜጠኞች መብትና ደህንነት እንዲከበር ከአባላቱ፣ ከደጋፊዎቹና ከሌሌች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አዋጭ ስልቶችን በመቀየስ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ቁርጠኝነቱን ይገልፃል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊደረግ የታሰበውን የተቃውሞ ትዕይንት ዝርዘር ሁኔታ፣ ቀኑንና ቦታውን ጨምሮ በቅርቡ ይፋ እንደምናደርግ እየገለፅን የፕሬስና ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ዕውን እንዲሆን መሻቱ ያላቸው አካላት ሁሉ የሚቀርብላቸውን ጥሪ ተቀብለው አጋርነታቸውን እንዲያሳዩን ከወዲሁ እንጠይቃለን፡፡

የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ(ኢጋመ)
መስከረም 28 2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

No comments:

Post a Comment