Monday, March 16, 2015

የነጻነት ትግሉን በየፈርጁ: ከዲሲ ግብረሃይል የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ የአንድነትና የዲሞክራሲ ሃይሎች በጠላት ጥቃት ደርሶባቸው ተጎድተው ተሸማቀው አንገታቸውን እንዲቀብሩ ሲገደዱ አድርባይ ሃይሎች በመድረኩ መቧረቃቸው የሚጠበቅ ነው፤ይህንን ጊዜያዊ ክስተት እንደ ዘላለማዊ ሃቅ የሚወስዱ ካሉ እጣ ክፍላቸው ተስፋ መቁረጥና ጨለምተኝነት ይሆናል። ከጨለማው ባሻገር የኮከቢቱን ብርሃን የሚያዩ ግን ለወያኔ ግፍ የማይበገሩ የሃቅን አሸናፊነት እና የኢትዮጵያን ትንሳኤ አይጠራጠሩም።

ሊነጋጋ ሲል ይጨልማል እንደሚባለው ዛሬ ወያኔ የተባለው መርገምት የጣር በትሩን በዘጠና ሚሊዮን ህዝብ ላይ እያሳረፈ ይገኛል፤ይህን የግፍ አገዛዝ ለመቋቋም ዜጋው ሁሉ እምቢኝ አልገዛም እያለ በሁሉም አቅጣጫ ሁሉንም የትግል አይነት ያልጀመረው ለመጀመር የጀመረው ለመቀጠል እየተሟሟቀ በሚገኝበት በአሁኑ ሰዓት ይህን ሃቅ እያዩ እንዳላዩ እየሰሙ እንዳልሰሙ የሚሆኑት ፍጥሮች ያለመንቃት መብታቸው የተጠበቀ ቢሆንም እኛ ግን ከተስፋው መቁረጥ አለም የሌለንበት ሁሉንም ጸረ ወያኔ ሃይላት የማበረታቻ ቃል ብቻ ሳይሆን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ለመለገስ በያለንበት ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን፤ዛሬ በሃገር ቤት ያሉ ተቃዋሚዎች፣ የመብት ጠያቂዎች፣ የድምጻችን ይሰማ ሚሊዮን ሙስሊሞች ሌሎችም ተጠቂ ዜጎች በሙሉ እያስገመገሙት ያለው ህዝባዊ እምቢተኝነት፤ በሌላው ፈርጅ ደግሞ ተምቹን የወያኔ ስርአት በብረት ለመፋለም ስልታቸው ያደረጉ የነጻነት ታጋዮች በሙሉ በየፈርጃቸው ይበርቱ እያልን እኛም በውጪው አለም በስደት ያለነው የዲሲ የጋራ ግብረ ሃይል አባሎች ከኢትዮጵያ ውጪ ብንሆንም ኢትዮጵያ ግን ከኛ ውጪ አይደለችምና የበለጠ ለመትጋት ያለንን አቋም በኢትዮጵያ ስም ነው የምናረጋግጠው።

እኛ በተለያዩ የትግል ስልት በሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ስር ያለንና እንዲሁም በአገር ወዳድነት ስም በግልም የምንቀሳቀስ ከሌሎች የመብትና የፍትሕ ተቋሞች ጋር በጋራ እየሰራን ያለን ስንሆን በመጨረሻው ሰዓት ባለው ግፈኛ የወያኔ ስርዓት ላይ ትግሉን በማጧጧፍ ለእምቢተኝነቱ ትግል የአቅማችንን ሁሉ እያደረግን እንዳለን ስንገልጽ አበክረን የምንለው ነገር አለ፤ ለጋራ ሃገራችን ኢትዮጵያ፣ ለሁላችን ጠላት ከሆነው የወያኔ ስርዓት ለመገላገል ዋናው አብነቱ የታጋዮች ህብረት ነውና በማንኛውም አይነት የጸረ ወያኔው የትግል አምባ የተሰለፉት ሁሉ በየፈርጃቸው እንዲተባበሩ እና በጋራ እንዲሰሩ ስንል በትሕትና እንጠይቃለን።


ይህ በሆነበት በትንንሽ ነገሮችና በትግል አካሄዶች የሃሳብ ልዩነት ቢኖርንም ልዩነቱን በውይይት እየፈታን በዋናው ጠላት ላይ እያበርን ትግላችንን እስከድል ደጃፍ እንቀጥል እንላለን፤ ነገር ግን ይሄንን እየተቀጣጠለ የሚገኘውን የህዝብ ትግል በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በማንኛውም መልኩ ለመጉዳት ወይም ለመከፋፈል የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንዲያቆሙ እየጠየቅን ነገር ግን በአፍራሽ ድርጊታቸው የሚቀጥሉበት ከሆነ በዝምታ እንደማንመለከታቸው እንገልጻለን።

ኢትዮጵያ በአንድነት እና በነጻነት ለዘላለም በክብር ትኖራለች!!!

No comments:

Post a Comment