Friday, October 2, 2015

የትጥቅ ትግልና ግራ የሚያጋባ አስተያየት



 በፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ

በኢትዮጵያ ትከሻ ላይ የተቆለፈውን ቀምበር ለማላቀቅ ቍልፉ የትጥቅ ትግል መሆኑ በተነሣ ቍጥር ከአንዳንድ ሰዎች የሚሰጠው አስተያየት ግራ የሚያገባ ነው። ገዢዎቹና ደጋፊዎቻቸው ቢቃወሙ ይገባኛል። የሚሰጡት አስተያየት ግን ሕፃንን ሳይቀር የሚያሥቅ ነው።ጦርነት በቃንይላሉ።አትንኩንማለታቸውን የማናውቅ ይመስላቸዋል። ጦርነት ካላስፈለገ፥ ለምን ከንጉሣዊው አስተዳደር ጋር ተዋጉ? ለምን ከደርግ ጋር ተዋጉ? ጨቋኝ ገዢ የት አገር ነው በሌላ መንገድ ሥልጣን ለሕዝብ ሲለቅ የታየው? የምሥራቁ ዓለም ጨቋኞች የወደቁት በሕዝብ ዐመፅ ነው ማለት፥ የምዕራቡን ዓለም ከባድ እጅ ሚና መርሳት ይሆናል።

የኛዎቹ ጦርነት ከመረራቸው፥ ሕዝብን ወደጦርነት የሚመራ በደል አይሥሩበት። ምን ጊዜም ቢሆን የትጥቅ ትግል የመጨረሻው አማራጭ ነው። የትጥቅ ትግል የሚያደርሰው ጉዳት በአንዱ ወገን ላይ ብቻ አይደለም። መሣሪያ የሚያነሣ መሣሪያ ማንሣት የሚያመጣበትን ጉዳት ሳያውቅ አይነሣም። ሰው ሆኖ እንደከብት መገዛት ያልቻለ ሰው በቃኝ ሲል፥ ክብሩን በመጠበቁ ከተቀመጡበት ተነሥቶነወርየሚባል እንጂ፥ በባርነት ጥላ ሥር ተቀምጦ የሚተች አይደለም።ጦርነት መርሮናልየሚለውን ምክር መገዛት ለመረረው አይመክሩም።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ግራ አጋቢ አስተያየትጦርነትስ አስፈላጊ ነው፥ ግን . . .” የሚለው ነው። ይህ አስተያየት በቅን አሳብ፥ የተሰጠ ሊሆን ይችላል። ግን አዛኝ መስሎ፥ ቀምበረኛውን ለመደገፍ የተሰጠ አስተያየት አለመሆኑ በምን ይታወቃል? እውነተኛ አሳቢና ሠጊ ሰው አስተያየቱን የሚሰጠው ሲጠየቅ፥ ካልተጠየቀም በግሉ ትጥቅ ያነሡትን ፈልጎ በጨዋ ደምብ መንገር ነው። ሳይጠየቁ ተነሥቶ በይፋ ምክር መስጠት ግን ሰሚው ሕዝብ ትግሉን እንዳይደግፍ መገፋፋት ነው። የትጥቅ ትግል ከታመነበት እንዲፋፋም የማይፈለግበት ምክንያት ምንድን ነው?

ትጥቅ ትግል የራስን ሕይወት ለወገን ነፃነት መሠዋት ማድረግ ነው። ሌላ ዓለማ የሌለው ሰው መሣሪያ ሲያነሣ፥ እንዴት ይኸንን የሚሰነዘርበትንና የሚሰነዘርለትን ምክር ሳያስብበት ራሱን ለመሥዋዕትነት ያቀርባል? የሚካኼደው የትጥቅ ትግል የሚያዋጣ የመሰለው እርዳታውን ያቅርብ፤ የማያዋጣ የመሰለው ለምንድን ነው የሚቃወመው? ተቃውሞው ማንን ለመጥቀም ነው? ለታጋዮቹ አስቦ ከሆነ፥ ከባለቤት ያወቀ ቡዳ ነው።የኔን ያህል የማሰብ ችሎታ የላችሁምማለት ነው። እንዴት ነው ለታጋዮቹ ያልተገለጠ ሥጋት ለምክር ሰጪዎቹ የተገለጠው?

አንዳንዱ ደግሞ፥ይኸው እንታገላለን ሲሉ ዓመታት አሳለፉ፥ ግን አንዳች ውጤት አላሳዩምይላል፤ ውጤት እንዲያሳዩ የቀጠራቸውና ካልሆነላቸው የሚያሰናብታቸው ሹም ይመስል። አርፎ መቀመጥ ስንት ውጤት አሳየ? ሌሎችን ሙከራዎችምአንዳች ውጤት አላሳዩምብለን እንንቀፋቸዋ!ውይስ ውጤት አሳይተዋል?


በመካሄድ ላይ ያለው የትጥቅ ትግል ኢትዮጵያን የሚጎዳ ነውከተባለ፥ እርግጥ ሊታሰብበት ይገባል። ግን አሳሳቢው ምክንያት ሊቀበሉት በሚገባ መልኩ አልተሰጠንም። ይህ ትግል የሚያመጣው ጉዳት ከተሸከምነው ቀምበር ይበልጥ ሊከብድ እንደሚችል አሳዩን።

የወያኔ ቀምበር መሰበር አለበት የምንል ሁሉ በመሰለንና በተቻለን መንገድ እንታገል። ካልተቻለን፥ ካልመሰለን፥ አርፈን እንቀመጥ፤ ታጋዮችን አለማደናቀፍ፥ እንደ ትግል እንዲቈጠርልን።

No comments:

Post a Comment