የ1966ቱ እና የ77ቱ ዓይነት የረሃብ እልቂት ከመድረሱ በፊት ለወገኖቻችን እንድረስላቸው!
ከፍል- ፪
በዲ/ን ኒቆዲሞስ
በአገራችን በኢትዮጵያ የተከሰተውን የረሃብ አደጋ አስመልክቶ ከሰሞኑን በመጀመሪያ ክፍል ያስነበብበኳችሁን ጽሑፍ ባወጣሁ ማግሥት አንዲት በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነች ወዳጄ የRFI ድረ-ገጽ ‹‹Sever Drought Threatens Millions of Ethiopia›› በሚል ርዕስ በአገራችን ስለተከሰተው ረሃብ የሚያትት ጽሑፍ በሾሻል ሚዲያ ላከችልኝ፡፡ ይህ የrfi ድረ ገጽ ያስነበበው ጽሑፍ እንደሚያትተው የኤሊኒኖ ክስተት በምሥራቅ አፍሪካና በኤዥያ በሚገኙ አገራት ባስከተለው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት አገራችን በድርቁ በከፍተኛ ኹኔታ ተጠቂ መሆኗን ዘግቦአል፡፡
ይህ ዘገባም አገራችን ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ1984-85 በርካታዎች ከቀዬአቸው በተፈናቀሉበትና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ካለቁበት የረሃብ ክስተት ጀምሮ አገሪቱ በምግብ እህል ራስን የመቻል ጥያቄ ውስጥ የወደቀች አገር መሆኗን በመግለጽ፤ የዘንድሮ በዝናም እጥረት ምክንያት የተከሰተው የድርቅም ከምሥራቅ አፋር ክልል እስከ ደቡብ ሶማሊያ ያለውን ሰፊ ቦታ እንደሚሸፍንና ረሃቡ በእነዚህ ቦታዎች ላይም ከፍተኛ የሆነ ማኅበራዊና ሰብአዊ ቀውስ እያደረሰ እንዳለ ይገልጻል፡፡
ይኸው rfi.fr ድረ ገጽ የተባበሩት መንግሥታት ባስነበበው ጽሑፉ ከጥቂት ወራት በፊት ያወጣውን ፬.፭ ሚሊዮን ተረጂዎች ቁጥር በአሁን ሰዓት ድርቁ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክልሎች በመስፋፋቱ የተነሣ ወደ ፰ ሚሊዮን እንዳሻቀበና ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል ጠቁሟል፡፡
ይህን በአገራችን የተከሰተውን የረሃብ አደጋ በተመለከተ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች ባደረጓቸው ሰፊ ምርምሮችና ጥናቶች የሚታወቁት የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ክርስቶፈር ክላፕሃም ለRFI በሰጡት ጠቅለል ያለ አስተያየት፡- ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ላለፉት ዐሥር ዓመታት ድርቅን ይህን ተከትሎም ሊከሰት የሚችለውን ረሃብን ለመከላከልና ዜጎቼ በምግብ እህል ራሳቸውን የሚችሉበትን የተሳካ ውጤታማ የሆነ ሥራን ሠርቼያለሁ በሚልበት በዚህ ወቅት እንዲህ ዓይነቱ የረሃብ አደጋ መከሰቱ ነገሩን እንቆቅልሽ ያደርገዋል ሲሉ ነው፡፡ አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡
The Ethiopian government having established what is generally considered to be quite an efficient system for controlling the effects of drought and malnutrition is probably embarrassed and surprised that such a serious issue has risen, Christopher Clapham, a Professor specialized in the region at Cambridge University, told to rfi. አሳዛኙ እውነታ ደግሞ ይህ የረሃብ አደጋ በቀጣይ ዓመታትም ተባብሶ የሚቀጥል መሆኑን ነው ጥናቶች የሚጠቁሙት፡፡
ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የኢትዮጵያ መንግሥት 33 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ መድቦ ድርቁ የከፋ አደጋ ባደረሰባቸው የአገሪቱ ክልሎች አፋጣኝ የሆነ የምግብ እህል እርዳታ እያደረገ መሆኑን ቢናገርም የተባበሩት መንግሥታት ከሰሞኑን ባወጣው ዘገባ ግን ለረሃብ የተጋለጡ ወገኖቻችንን ቁጥር መሻቀቡንና እነዚህን ወገኖቻችንንም ለመታደግ ከ237 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ጠቅሶአል፡፡
መንግሥት ዘግይቶም ቢሆን በአገሪቱ የተከሰተውን ድርቅ አስመልክቶ ለጋሽ አገራትና ዓለም አቀፍ እርዳታ ድርጅቶች እጁን እንዲዘረጉለት የተማጸነ ቢሆንም ድርቁ በአገሪቱ የጋረጠውን የከፋ የረሃብ አደጋና እልቂት በተመለከተ ግን ሰፋ ያለና የተብራራ መረጃ በመስጠት በኩል ጉልህ ችግር እንዳለበት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ብዙኃን በሰፊው እየተናገሩና እየወቀሱ ነው፡፡
በአገራችን በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱትን የረሃብ አደጋዎች ከወዲሁ አስቀድሞ በመግለጽ፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ረገድና በረሃብ የሚያልቁ ወገኖቻችንን ለመታደግና አደጋውን ለመቀነስ መወሰድ ስላለበት አፋጣኝ ዕርምጃዎችን በተመለከተ ትልቅ ችግር እንዳለ ግልጽ ነው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ፈጣን ልማትና ዕድገት እያስመዘገብን ነው፣ ሚሊዬነር የሆኑ አርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን እያፈራን ነው፣ ረሃብ ካሁን ወዲያ ታሪክ ይሆናል እያለ ባለበት ወቅት እንዲህ ዓይነቱ አንገትን የሚያስደፋ የረሃብ አደጋ መከሰቱ ራሱን በደንብ መፈተሽ እንዳለበት ትልቅ መሳያ ይመስለኛል፡፡
ይኸው የረሃብ አደጋ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ብቻ ሣይሆን በከተሞችም እየተስፋፋ ያለ መሆኑን መስማት፣ ማወቅ ደግሞ እጅጉን የሚያሰቅቅ ነው፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት መቀመጫና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚገኙባትና የአፍሪካ ርእሰ መዲና በምትባለው በአዲስ አበባ ሣይቀር ባሉ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ሕፃናት በረሃብ የተነሣ በትምህርት ገበታቸው ላይ እያሉ ተዘልልፍለፈው እወደቁ መሆናቸውንና እንዲሁም በኑሮ ውድነት ምክንያት በርካታ ቤተሰቦች በፈረቃ ለመብላት መገደዳቸውን በአገሪቱ የሚገኙ እንደ ሪፖርተር ጋዜጣና ሸገር ራዲዮ በተለያዩ ጊዜያት ዘግበዋል፡፡
በተለይ በብዙዎች ዘንድ አፍቃሪ ኢሕአዴግ፣ እንደው ያሰበውንና የተመኘውን ያህል ሰሚ ጆሮ፣ አስተዋይ ልቦና አላገኘም እንጂ የመንግሥት መልካም መካሪና ዘካሪ እንደሆነ አብዝቶ የሚታማው የሪፖርተር ጋዜጣ ባለፈው እሑድ ዕትሙ ርዕሰ አንቀጹ ላይ፡- ‹‹በድርቅ ለተጎዱትም ሆነ ለከተማ ድኅነት ፈጣን ምላሽ ያስፈልጋል›› በማለት ያስነበበው፣ በአደጋ ማስጠንቀቂያ የታጀበው ርዕሰ አንቀጹ አገሪቱ ያለችበትን እውነታና የተጋረጠባትን የረሃብ አደጋ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡
ዘንድሮ በአገራችን የተከሰተውን ድርቅና ይህንም ተከትሎ በአገራችን የተከሰተውን የረሃብ አደጋ በተመለከተ መንግሥትም ሆነ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የመገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን ሰጥተው እየዘገቡት ነው ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡ ያው በታሪካችን እንደምናውቀው ሺዎች ከቀዬአቸው ካልተፈናቀሉና ካልሞቱ በስተቀር ‹‹ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም›› እንደሚባለው እየሆነ ያለ ነው የሚመስለው፡፡
ታሪካችን እንደሚነግረን በ፲፱፻፷ዎቹ በአገራችን ሰሜናዊ ክፍል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ከቀዬአቸው ሲፈናቀሉና ለአሰቃቂ ሞት ሲዳረጉ የዘውዱ መንግሥት በክብረ በዓልና በሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ነበር ተጠመዶ የነበረው፡፡ እናም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቹን ከቀዬአቸውና ላፈናቀለውና ለአሰቃቂ ሞት ለዳረጋቸው ለነበረው የረሃብ አደጋ ምላሽ የሰጠው ዘግይቶ ነበር፡፡
በወቅቱ ይህ የረሃብ እልቂት እንዴት ወደ አደባባይ ሊወጣ እንደቻለ በሰማኒያዎቹ በሰሜን አሜሪካ ይታተም በነበረው ‹‹ሰምና ወርቅ›› በተባለው ጥናታዊ መጽሔት ‹‹ድርቅና ጠኔ በኢትዮጵያ›› በሚል ጥናታዊ ጽሑፋቸው ውስጥ ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ እንዲህ ገልጸውት ነበር፡፡ በወቅቱ የረሃቡን መከሰት የሰሙት ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ፣ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፣ ዶ/ር አሉላና ለሌሎች የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ባልደረቦቻቸው በግላቸው ሴስና አውሮፕላን ተከራይተው ረሃቡ የከፋ አደጋ ወዳደረሰበት ወደ አገራችን ሰሜናዊ ክፍል መረጃ ለመሰብሰብ ተጓዙ፡፡
ከወሬ ባለፈ በዓይናቸው ያዩትና ምስክር የሆኑበት የረሃብ አደጋና የወገኖቻቸው አሰቃቂ የሆነ እልቂት እጅጉን ልባቸውን የነካቸው እነዚህ ምሁራን በድርቅ የተጋለጡትን የአገሪቱን ግዛቶች፣ በረሃቡ የተነሣ እጅጉን የተጎዱትን ወገኖቻቸውን በማነጋገር በምስልና በቪዲዮ ያሰባበሰቧቸውን መረጃዎች በፕ/ር መስፍን አማካኝነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ እንዲታይ ተደረገ፡፡
ይህን አሰቃቂ የሆነ የወገኖቻቸውን እልቂት፣ የሞት ጥላ ያንዣበባቸውን፣ ቆዳቸው ገርጥቶና አንጀታቸው ተጣብቆ፣ ከሰው መልክና ወዘና የወጡትን ወገኖቻቸውን፣ በእናቶቻቸው ደረት ላይ ተጣብቀው የሟች እናቶቻቸውን ጡት ሲመገምጉ የሚታዩ ሕፃናትን ምሰልና ቪዲዮ የተመለከቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ማኅበረሰብ ወገኖቻችን በረሃብ እያለቁ አንማርም፣ መንግሥት የረሃቡን እልቂት ለለጋሽ አገራትና ለዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ያጋልጥ በሚል ያስነሱት ዓመፅ ቀስ በቀስ ተባብሶ ለዘውዱ ሥርዓት መገርሰስ ምክንያት ሊሆን እንደበቃ እናውቃለን፡፡
ፕ/ሮ ጌታቸው ኃይሌ በዚሁ ጥናታዊ ጽሑፋቸው ላይ እንደሚያትቱት በወቅቱ ረሃቡ በአገሪቱ ላይ ያደረሰውን የከፋ እልቂት ያሰባበሱትን መረጃዎች ለኤምባሲዎችና ለውጭ አገራት በመስጠታቸው ረሃቡ ሊጋለጥ መቻሉንና ከዚሁ የ፷፮ቱ የከፋ የረሃብ እልቂት ጋራ በተያያዘ ስሙ በእጅጉ የሚነሳው ጆንታን ዲምቢልቢም ረሃቡ የከፋ አደጋ ባደረሰበት በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ተገኝቶ መረጃውን በዓለም ሁሉ እንዲናኝ ያደረገው ከነፕሮፌሰር ባገኘው መረጃ በመነሣት እንደሆነ ጠቅሰውታል፡፡
ፕ/ር ጌታቸው በዚሁ ጥናታዊ ጽሑፋቸው መደምደሚያ ላይም፡- ‹‹ኢትዮጵያ ትገብር ፋሲካ ታኅፂባ በደም ውሉዳ፣ ወንዞቿንም በከንቱ ወደ ግብጽ ምድር ሰዳ›› በማለት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ን በፋሲካ በዓል ሌሊት፣ ካህናቱና ሊቃውንቱ ‹‹ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ታኅፂባ በደም ክርስቶስ››፣ ‹‹ምድር በክርስቶስ ኢየሱስ ደም ታጥባና ነጽታ በሐሤትና በደስታ የፋሲካን በዓል ታድርግ!›› የሚለውን ማኅሌት ‹‹ኢትዮጵያ በአብራኳ ክፋይ በገዛ ልጆቿ ደም ተነክራና ታጥባ፣ ከፈጣሪ የተሰጣትንም የተፈጥሮ ጸጋ ወንዞቿን ሳትጠቀምባቸው እንዲሁ በከንቱ ወደ ምድር ግብጽ ሰዳ በዓለ ፋሲካዋን ታድርግ!›› በማለት አገሪቱ በረሃብ አለንጋ የምትገረፍ፣ ልጆቿ በረሃብ የሚያልቁባት፣ ትውልድ በእርስ በርስ ጦርነት የሚጫረስባት፣ የእልቂት ምድር፣ አኬል-ዳማ መሆኗን እንዲህ አመስጥረውታል፤ ገልጸውታል፡፡
የ፷፮ቱን ረሃብ ተከትሎ ከዐሥር ዓመት በኋላ በ፲፱፻፸፯ ዓ.ም. በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተከሰተው ድርቅ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን ሲያፈናቅልና ብዙዎችንም ለሞት ሲዳርግ የደርግ መንግሥት ግን የአብዮቱን ፲ኛ ዓመት ለማክበር ሽር ጉድ እያደረገ፣ ሰማይ ምድሩ ጠቦት ፌሸታ ላይ ነበር፡፡ በተመሳሳይም በዘመነ ኢሕአዴግም በዘንድሮው ዓመት ስለተከሰተው የረሃብ አደጋ ለሕዝቡም ሆነ ለለጋሽ አገራት በቂ የሆነ መረጃ በመስጠት አፋጣኝ የሆነ ዕርምጃ ተወስዷል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡
ለአብነትም መንግሥት በወርኻ ክረምቱ ማብቂያ ላይ ‹‹የዲያስፖራ ቀን›› ብሎ በሰየመው ሳምንት በሺዎች ሚቆጠሩ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሰብስቦ በግብዣ ሲያንበሸብሻቸውና የልማታችን ውጤት ነው በሚል ፌሽታና ፈንጠዝያ ሲያደርግ በአገሪቱ ስለተከሰተው ድርቅና ስለተጋረጠብን ክፉ የረሃብ አደጋ በቅጡ አለመናገሩንና በቂ የሆነ የተብራራ መረጃ አለመስጠቱን ነው ያስተዋልነው፡፡ ወይስ መንግሥት ሆይ የድርቁ፣ የረሃቡ አደጋ ዜና ለመሆን የሚበቃው ሺዎችን ከቀዬአቸው ሲያፈናቅልና ለአሰቃቂ ሞት ሲዳርጋቸው ብቻ ነው ማለት ነው እንዴ …!?
በሌላም በኩል ከጠቅላይ ሚ/ሩ እስከ ታች ባሉ የወረዳ ካድሬና ሹመኛ ድረስ እስኪሰለቸን በነጋ ጠባ የሚነገረን፣ የሚደሰኮረው አገሪቱ አስመዝግበዋለች ስለሚሉት ባለ ኹለት ዲጂት ዕድገትና ፈጣን ልማት ጉዳይ ነው፡፡ እንደ ዜጋ እንደ ኢትዮጵያዊ የአገራችን ፈጣን ዕድገትና ልማት ሁላችንንም ያስደስተናል፡፡ የሁላችንም ምኞት አገራችን በልጽጋና አድጋ፣ ሕዝባችንም ከስደትና ከጉስቁልና ወጥቶ ማየት ነው፡፡ ግና መንግሥት አገሪቱ አስመዝግበዋለች በማለት ከሚያስተጋባው ፈጣን የሆነ የልማትና የዕድገት ድምፅ ይልቅ የሚሊዮኖች ወጎኖቻችን የዋይታና የሰቆቃ፣ የእልቂትና የመከራ ድምፅ፣ እንባና ጩኸት በምድሪቱ ኹሉ ጎልቶና ደምቆ እያስተጋባ መሆኑን ልብ ሊለው ይገባል፡፡
ኢሕአዴግ ከአጋር ድርጅቶች ጋራ በመሆን ባለፈው ባደረገው ዓመታዊው ስብሰባውና ግምገማው የመልካም አስተዳደር እጦት ድርቅ መመታቱን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና ለሥርዓቱ የከፋ አደጋ መሆናቸውን መማመኑንና ይህ አደጋም በአፍጢሙ ሊደፋው ያለ መሆኑን የገለጸበት እውነታ፣ የሙሰኛ ባለሥልጣናቱ ማን አለብኝነትና አምባ ገነንነት፣ ግፍና ዓመፃ፣ የፍትሕ ረሃብና የመልካም አሥተዳደር መታጣቱ ከተጋረጠብን የረሃብ አደጋ ባልተናነሰ ሕዝባችንን ክፉኛ አስጎብጦትና እንደ መርግ ተጭኖት፣ ምድሪቱን በእንባ አጨቅይቶ፣ የዋይታና የሰቆቃ ምድር እያደረጋት ነውና መንግሥት ቆም ብሎ አብዝቶ ሊያስብ፣ ሊጨነቅ ይገባዋል፡፡ አለዚያ አደጋው እጅጉን ሊከፋ እንደሚችል አያጠያይቅም!!
ይቀጥላል፡፡
ሰላም!
No comments:
Post a Comment