Tuesday, December 8, 2015

በገዛ አፈ-ሙዙ መቃብሩን የሚቆፍር የሽንፈትን ጽዋ ይጎነጫል!

ከሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ

ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ የአዲስ አበባ ከተማንና ዙሪያን ለማከለል ከወጣው የማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ፤ ገቢራዊነትና ሃሳቡን የተቃወሙ የኦሮሞ ተወላጆች እና የዕቅዱ ተቃዋሚዎች፣ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ፣ ኮሌጆች እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንዲሁም የየከተማዎቹ ነዋሪዎች ላይ የኃይል እርምጃ እየተወሰደ እንዳለ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡

ዜጎች እያሰሙት ያለውን ተቃውሞና የሃሳብ ልዩነት በኃይልና በጠብ-መንጃ ለመመለስ የተደረገውም አግባብነትና ኃላፊነት የጎደለው ጭፍን ተግባር እንደሆነ የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት በጽኑ ያምናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ መቶ-በመቶ ሁሉንም ተቋማትና መንግሥታዊ መዋቅሮች በጠቅላላ እንደልቡ የሚያዘውና ያሻውን የሚፈጽመው የኢህአዲግ መራሹ ኃይል፣ ልማትንና እድገትን በኃይልና በጉልበት እፈጽማለሁ እንዲሁም አስፈጽማለሁ ብሎ መነሳቱም መሠረታዊ የእብሪት ተግባር መሆኑም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አሳምሮ ያውቀዋል፡፡

በተለይም ደግሞ፣ ኢህአዲግ መራሹ መንግሥት በኢትዮጵያ ምድር ላይና በኢትዮጵያውያን ላይ የተከለው የጎሳ ፌዴራሊዝም ችግር ምን ያህል አስከፊ እንደሆነና ውጤቱም የዜጎችን ሞት፣ እስራት፣ ስደት፣ የንብረት ውድመትና የትምህርት መስተጓጎል ማስከተል እንደሆነ ታይቶበታል፡፡ በመሆኑም፣ የአዲስ አበባ ዙሪያ ነዋሪዎችም ሆኑ በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚፈልጉት ልማትም ሆነ እድገት በ“እኔ አውቅልሃለሁ” ባዩ የኢህአዲግ አንባገነናዊ ልማትና የጎሳ ፌዴራሊዝም ሳይሆን፣ በሕዝብ-ለሕዝብ-ከሕዝብ ፍላጎትና ስምምነት ላይ የተመሠረተን ልማትና እድገት ብቻ እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡

ከዚህ ዓላማና ግብ ውጪ የሚተገበር ማንኛውም የልማት ዕቅድና የከተማ ማካለልም ሁሉ የኢህአዲግ መራሹ መንግሥት አንባገነናዊ አስተዳደር ሁነኛ መገለጫ በመሆኑ አጥብቀን እንቃወመዋለን፡፡ በተከሰተው ብሔራዊ ቀውስና ችግር ዙሪያም በቀጥታ ለችግሩ ተጋላጭ ከሆኑት ዜጎች ጋር ሆነ ችግሩ በዋነኛነት ከሚያሳስባቸው የአዲስ አበባ ከተማና ዙሪያ ነዋሪዎች እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት ተማሪዎች ጋር ባስቸኳይ ውይይትና ንግግር እንዲደረግ እያሳሰብን፤ አንባገነኑ የኢህአዲግ መንግሥት እየተከተለው ያለውን የዜጎችን ጥያቄ በኃይልና በጉልበት ለማፈን ከሚያደርገው ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ድርጊቱ እንዲቆጠብ እንጠይቃለን፡፡

በተመሳሳይ መልኩም፣ በጎንደር ከተማ በሚገኘው ማረሚያ ቤት ላይ ተከስቶ የነበረውን የእሳት ቃጠሎን ተከትሎ ኢህአዲግ መራሹ መንግሥት የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ በማጥፋት፤ በሕግ ቁጥጥር ሥር የሚገኙትን ዜጎች ሕይወትና ደሕንነት ለመታደግ መሯሯጥ ሲገባው፣ ሕይወታቸውን ከቃጠሎው ለማዳንና ለሞከሩት ዜጎች የጥይት እሩምታ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ከዚህ መንግሥታዊ ተግባርና ቸልተኝነት ተነስተን እንደምንረዳው ከሆነ፣ አገዛዙ ለማንኛውም ዜጋና አገራዊ ጉዳይ የሚሰጠው ምላሽ ከጠብ-መንዣና ከጉልበት የማይዘል መሆኑን በግልጽ አስመስክሯል፡፡ ይህንንም መሰሉን ኢ-ሰብአዊና ኢ-መንግሥታዊ ተግባር የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት በቸልታ እንደማይመለከተው ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመግለጽ ይገደዳል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤትም መንግሥት የሚፈጽማቸውን ኃላፊነት የጎደላቸው ተገባራት እስኪያቆሙ ድረስ፣ አንባገነናዊው ሥርዓት የሚፈጸመው የሕገ-አራዊት ተግባራት እስካለቆሙ ድረስ፣ ሕጋዊና ሰላማዊ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡


ከዚህም በተጨማሪ፣ ኢህአዲግ መራሹ መንግሥት የአዲስ አበባ ዙሪያ ማስተር ፕላንን በኃይል ለመተግበር ሲባል ስለሞቱት፣ ስለታፈሱት፣ ስለተሰደዱትና ስለተሰወሩት ዜጎች ጉዳይ የሚያጣራና በጎንደርም ከተማ በሚገኘው ማረሚያ ቤት ስለተከሰተው የእሳት ቃጠሎና ከርሱም ጋር ተያይዞም ስለተፈፀመው የጅምላ-ፍጅት ጉዳይ የሚያጣሩ ገለልተኛ የሆኑ አጣሪና አካል ተቋቁመው ስለተፈጠረው ዘግናኝና ኢ-ሰብአዊ ተግባር መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትክክለኛውን መረጃ እንዲያገኝ እና ወንጀለኞችም ለፍረድ እንዲቀርቡ መደረግ አለበት፡፡

ይህ ሳይሆን ቀርቶ፣ ኢህአዲግ መራሹ መንግሥት በያዘው የእብሪት መንገድ የሚገፋ ከሆነ የገዛ መቃብሩን በገዛ አፈ-ሙዙ እየቆፈረ እንደሆነም እየገለጽን፤ አጥፍቶ-ጠፊው ኢህአዲግም ሆነ ኢህአዲግአውያን አጀንዳቸውን በኃይል እናስፈጽማለን ብለው የቁም ሕልም ሲያልሙ፣ በቁማቸውም እንደሚቀበሩ ሊያውቁት ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር !!!
ኀዳር 27 ቀን 2008 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment