Saturday, October 31, 2015

የአርበኞች ግንቦት 7 ስብስቦችን በመላ አገሪቱ እናደራጅ!


የኢትዮጵያ ወጣቶች የህወሓት አገዛዝ በአገራችን ላይ የሚያደርሰውን በደል የሚገልጹ እና ከዚህ በደል መገላገያ መንገድ የሚያመላክቱ ፓስተሮች በግድግዳዎችና ምሰሶች ላይ እየለጠፉ፤ በራሪ ወረቀቶችን እየበተኑ እና የግድግዳ ላይ ጽሁፎችን እየፃፉ ነው። ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ በተለያየ መጠን ቢሆንም በአገሪቱ አብዛኛዎቹ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ ይህ የቅስቀሳ ዘዴ ተግባራዊ ሆኗል። ይህ ተግባራዊ ሥራ የአርበኞች ግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ያሉ መሆኑ ተጨባጭ ማሳያ ሆኗል።

አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የሚገኙ ወጣቶች እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴ ያደንቃል፤ ተግባሮቻቸው ባነሰ ኪሳራ የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ በጠንካራ ሥነ ሥርዓት በተዋቀሩ የአርበኞች ግንቦት 7 ስብስቦች እንዲመሩ ያበረታታል። ከተግባራዊ ሥራዎች ጎን ለጎን የድርጅት አቅም ግንባታ መሠራት ያለበት አቢይ ጉዳይ መሆኑን አርበኞች ግንቦት 7 በአጽንዖት ያስገነዝባል። በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አባላትና ደጋፊዎችች ለድርጅትና ለአባላት ጥንካሬ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ አበክሮ ያሳስባል።

ነፃነት ናፋቂ ወጣቶች የሚያደርጉት የሕዝባዊ እምቢተኝነት መገለጫ ተግባራት ዓይነታቸው እየተቀያየረ እንዲቀጥል በእቅድ መመራትና በድርጅት መታገዝ አለባቸው። የመረጥነው ሁለገብ የትግል ስትራቴጂ እምንፈልገው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ላይ እንዲያደርሰን የኢትዮጵያ ሕዝብ በሁለቱም የትግል ስልቶች አኳያ መደራጀት ይኖርበታል።

በዚህም መሠረት ለሕዝባዊ አመጽ ጠንካራ የአርበኛ ሠራዊት ማደራጀት እንደሚያስፈልግ ሁሉ ለሕዝባዊ እምቢተኝነትም ጠንካራ ድርጅት በኢትዮጵያ ከተሞችና ገጠሮች፤ በሥራና በመኖሪያ አካባቢዎች ማደራጀት ይገባል። ስለሆነም በከፍተኛ ምስጢር የተደራጁ እና በከፍተኛ ብቃት የሚመሩ የአርበኛ ግንቦት 7 ክበባት በየቦታው፣ በብዛት እና በጥንቃቄ መደራጀት ይኖርባቸዋል። ድርጅት ድርጅት የሚሆነው ደግሞ በሥነ ሥርዓት ሲዋቀርና በብቃት ሲመራ ነው። ስለሆነም ነፃነት ናፋቂ የሆነ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በሥነ ሥርዓት በተዋቀሩ ትናንሽ ስብስቦች ራሱን እንዲያደራጅ፤ የፓለቲካ፣ የታሪክ እና የጠቅላላ እውቀት ግንዛቤውን ለማዳበር እንዲሁን መሠረታዊ የደህንነት ጥበቃ ክህሎቶችን እንዲያጎለብት ጥረት እንዲያደርግ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ መስጠት አስፈልጓል።


የተደራጀ ስብስብ ለሚንቀሳቀስበት አካባቢ ተስማሚ የሆኑ የቅስቀሳ ዘዴዎችን ለበላይ አመራር አሳውቆ ሲፈቀድ ተግባራዊ ማድረግ ይችላል። የተደራጀ ስብስብ ለአካባቢው ባህልና ስነልቦና ተስማሚ የሆነ መንገድ ተጠቅሞ የሕዝብን የልብ ትርታ ማዳመጥ፤ ለጥያቄዎቹም መፍትሄ መሻት ይችላል። የተደራጀ ስብስብ የጠላትን እንቅስቃሴ እየሰለለ መረጃ ለነፃነት ኃይሎች እንዲደርስ የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር ይችላል። የተደራጀ ስብስብ ሕዝብ በሥርዓቱ ላይ እንዲያምጽ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤ ሆኖም ግን አቅም ሳይጎለበትም አመጽ ተነስቶ በነፃነት ታጋዮች ላይ አላስፈላጊ መስዋዕትነት እንዳይከፈል ይከላከላል። ሁኔታዎች የተመቻቹ መሆናቸው የበላይ አመራር ሲያምንበት ደግሞ አመጽ በመቀስቀስ ትግሉ ግቡን ሳይመታ እንዳይበርድ ፀንቶ ይቆማል። የተደራጀ ስብስብ ከአርበኞች ግንቦት 7 የሚሰጠውን ድርጅታዊ መመሪያ ተከትሎ ተግባራቱን ይከውናል፤ “ተነስ!” ሲባል ለመነሳት ራሱን ዝግጁ ያደርጋል።

ስለሆነም በከፍተኛ ሥነሥርዓት የታነፁ፣ በብቃት የሚመሩ፣ ከአርበኞች ግንቦት 7 አመራር ጋር የጠበቀ ግኑኝነት ያላቸው በርካታ ስብስቦችን በመላ አገሪቱ ውስጥ እናደራጅ።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

No comments:

Post a Comment