ሁኔ አቢሲኒያ
የኢሳቱ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና እንግዳ ሆነው ቀርበው የነበሩት አንጋፎቹ ፖለቲከኞች አቶ ቻላቸው አባይ እና አቶ ጎሹ ገብሩ በወልቃይት ጠገዴ ህዝብና እየተፈፀሙበት ስላሉት ኢሠብዐዊ ድርጊቶች ዙሪያ ሠፊ ውይይት አካሂደው ነበር ውይይቱ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ስለአካባቢው ፖለቲካ ከፍተኛ መረጃ የሚሠጥ ከመሆኑም በላይ አሳዛኝ የሆኑ እውነታዎች የተነሡበት ነበር፡፡
የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር በትግርኛ አጠራሩ ህወሀት ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ግፎችን በወልቃይት ህዝብ ላይ እንደፈፀመ ያስረዱት ተወያዮቹ በ1984 በአካባቢው ይኖር የነበረው ቁጥሩ ከ83,000 በላይ እንደነበር ገልፀው በአሁኑ ወቅት ይህ አሐዝ ወደ 48,000 እንደወረደ ለማወቅ ተችሏል 35,000 ያህል የወልቃይት ጠገዴ ፀለምትን ህዝብ ምን ዋጠው መቼም ሁሉም ሠው በእርጅና እና በበሽታ ሞቷል አይባልም ቢሞትስ አካባቢው ላይ ሟች ብቻ ነው እንዴ ያለው ተወላጅ አይኖርም የወልቃይት ማህፀኖች ልጅ አያፈሩም?
ህወሀት ገና ጫካ በነበረበት ሠዓት ከድርጅቱ አመራሮች አንዱ የሆነው ስብሐት ነጋ መኮንን ባዘዘው ወይም በትግል ስሙ ዮሴፍ ባዘዘው የተባለን አባቱ የወልቃይት እናቱ የትግራይ ሰው ከሆኑ ቤተሰብ ውስጥ የተገኘን ታጋይ የወልቃይት ህዝብን ከትግራይ ጋር የመገንጠል ፍላጎት እንዲያጣራ እና ጥናት እንዲሠራ በሚል ወደወልቃይት ይላካል ሪፖርቱ ግን ለእነ ስብሐት ነጋ እና ጓደኞቹ አስደንጋጭ ነበር አንድም የወልቃይት ህዝብ ከትግራይ ህዝብ ጋር አብሮ በመሆን ከኢትዮጵያ መገንጠል እንደማይፈልግ በማሳወቁ የህወሀት አመራሮች ጥርስ ውስጥ እንደገባ አቶ ቻላቸው እና አቶ ጎሹ ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ቂም በቀል ውስጥ የገባው ህወሀት አቶ ልጅዓለም የተባሉ የ80 ዓመት አዛውንትን ጨምሮ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎችን መግደል፣ማሠር እና ማሳደድ ጀመረ፡፡ የወልቃይት ህዝብ ከሞት ለማምለጥ በርካታ ጥረትን ቢያደርግም ተሳክቶለት ከሞት የተረፈው ግን እጅግ ጥቂቱ ነው፡፡
የወልቃይት ህዝብ በብዛት ይኖርባቸው ከነበረባቸው አካባቢዎች አንዷ ሁመራ ነች በሠላሙ ጊዜ የወልቃይት ህዝብ ለእርሻ ምቹ የሆነውን የሁመራን መሬት አርሶ ይኖር እንደነበር የገለፁት ፖለቲከኞቹ በወቅቱ ከሁመራ ህዝብ ከ80 በላይ የወልቃይት ተወላጅ እንደነበር በአሁኑ ወቅት በአስደንጋጭ ሁኔታ በሁመራ የሚኖር የወልቃይት ህዝብ 11 ቤተሠብ ብቻ ነው፡፡ ይህንን የወልቃይት ህዝብ ችግር ኢህአዴግ ሐገሪቱን ከተቆጣጠረበት 1983 ዓ.ም ጀምሮ ለመንግስት በየጊዜው ሪፖርት ቢያደርጉም የመንግስት ባለስልጣናት ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው የወልቃይት ህዝብ እንደጨፈጨፉ እና እንዳሳደዱ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከመንግስት በላስልጣናት መካከል ህወሀት ከመከፋፈሉ በፊት የመከላከያ ሚኒስቴር የነበረው አቶ ስዬ አብርሐ፣ ዶ/ር አረጋዊ በርሔ የህዝቡ ጉዳይ በድምፀ ውሳኔ እንደሚፈታ ይናገሩ እንደነበር ገልፀው አቶ ገብሩ አስራት ግን እጅግ አስነዋሪ የሆነ ስድብ የወልቃይትን ህዝብ ሲሳደቡ እንደነበር አውስተዋል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በርካታ ስድተኛ የወልቃይት ተወላጅ ወደአለበት ኮሎምቦስ አሜሪካ መጥተው የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ቴዎድሮስ አድሐኖም ከ2000 በላይ የወልቃይት ተወላጆችን አነጋግራለው ብለው አስበው የነበሩ ቢሆንም የስብሠባ አደራሹ ውስጥ የተገኘው የወልቃይት ተወላጅ ቁጥር 13 ብቻ ነበር፡፡ በሌላ በኩል በ2007 እ.ኤ.አ በሟቹ ጠ/ሚኒስቴር ትዕዛዝ በኮሎምቦስ የወልቃይት ተወላጆችን ለመደለል ኮሎሞቦስ የተገኙት የወልቃይት ዞን አስተዳዳደሪ የነበሩት አቶ ፈረደ የሺወንድም ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባ ገልፀው ወደሀገራቸው ለሚመለሱ ወልቃይቶች የእርሻ መሬት እና ትራክተር እንደሚያመቻቹ የገለፁ ቢሆንም በወልቃይቶች ወያኔ ድሮውንም አጭበርባሪ ስለሆነ ማመን የለብንም በማለታቸው ጥቂቶችን ብቻ አሳምነው ሄደዋል እርሳቸውን ተከትለው ወደሑመራ የተጓዙት ዲያስፖራዎች በትግራይ ክልል አመራሮች ከፍተኛ ጫና ደርሶባቸው ዳግም ስደተኛ ሆነዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት አብዛኛው የወልቃይት መሬት ወደትግራይ ቢጠቃለልም እና ስልጣን ላይ ያሉት በርካቶቹ የትግራይ ተወላጆች ቢሆኑም ከአዜብ መስፍን በስተቀር የወልቃይት ህዝብን ከድቶ ባለስልጣን የሆነ እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የወልቃይት ህዝብ ጎንደሬ፣ አማራ እና ኢትዮጵያዊ እንጂ ትግሬ አለመሆኑን ገልፀው በአሁኑ ሠዓት በመሬቱ ዙሪያ ህዝበ ውሳኔ ይካሄድ ቢባል እንኳን በስፍራው የሰፈሩት አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች በመሆናቸው ምንም ፋይዳ የለውም ካሉ በኋላ የወልቃይን ህዝብ ችግር ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ መፍታት ያለበት ጉዳይ ነው ኢትዮጵያ በቅርቡ ነጻ ትወጣለች የወልቃይት ህዝብ ጉዳይ ካልተፈታ ግን ነፃ በምትወጣው ኢትዮጵያ ውስጥ አንድም የወልቃይት ተወላጅ ማግኘት ከባድ ይሆናል
#ሁኔአቢሲኒያ
No comments:
Post a Comment