ከ9ኙ ፓርዎች ትብብር የተሰጠ መግለጫ
ባለፈው ሣምንት በተፈጸመብን ሴራ ያለመንበርከካችንን ከቀረበው ደብዳቤ የተረዱ የሚመስሉት እኚሁ ባለሥልጣን በቀጣዩ ቀን(12/03/07 ዓ.ም) የባለፈውን የአደባባይ ስብሰባ እንዲያስተባብር ኃላፊነት በሰጠነው ሰማያዊ ፓርቲ ላይ ‹‹ማስጠንቀቂያ›› በሚል ለተጨማሪ ማስፈራሪያ ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ይህ ዛሬ በወህኒ የሚገኙ በሽብርተኝነትና ህገመንግሥት በመጣስ በሚል የታሰሩ የፓርቲ አመራሮችና አባላት፣የኃይማኖት መሪዎች፣ጋዜጠኞች ፣ብሎጌሮች፣ከገዢው ፓርቲ የተለየ አመለካከት ያላቸውን ዜጎች በመፈረጅ ለማሰር፣ ማሰቃት… የተከደበትን ስልት፣ዛሬም በእኛም ሆነ ሌሎች ላይ እየተሞከረ ያለውን የማስፈራራትና የማሸማቀቅ ሙከራ ከሚያስተውሰን በቀር በህጋዊና ሠላማዊ ትግላችን የሚፈለገውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ስለተዘጋጀን የሚፈራ አልተገኘም፣ ከቁብ አልቆጠርነውም፡፡
በዚያው ዕለት(12/03/07 ዓ.ም) በአካል ተገኝተን አንቀበልም የተባልነውን ደብዳቤ በመንግሥታዊው የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በፈጣን መልዕክት አገልግሎት/ኢ.ኤም.ኤስ/ በቁጥር eg156846735et ብንልክም የቱም የመስተዳድሩ አካል ደብዳቤውን ለመቀበል ፈቃደኛ ያለመሆኑ በ16/03/07 ከፖስታ አገልግሎቱ ተገልጾልናል፡፡ ይህ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 12 የተቀመጠውን ‹‹የመንግስት አሠራር ተጠያቂነት›› የጨፈለቀ ድርጊት በተገለጸልን ተመሳሳይ ጊዜ ደብዳቤውን የጻፈው የመላው ኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/መኢዴፓ/ ሊቀመንበርና የትብብሩ ፋይናንስ ኃላፊ (ደብዳቤውን ሲያቀርቡ አንቀበልም የተባሉት) አቶ ኑሪ ሙዴሲር ‹‹ በመኪና ተገጭተው መደባደብ በሚችሉ ጀግና›› እና ግብረ-አበሮቻቸው ተደብድበው በአካላቸው ሦስት ቦታዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ይህ ትናንት በአቡበከር ላይ የተሞከረውን ተመሳሳይ የፈጠራ ውንጀላና ክስ የሚያስታውሰን ሲሆን ክሱ የማያዋጣ መሆኑ ሲታወቅ ‹‹ ተገጭቶ የሚደበድብ›› ወሮበላ ወደማሰማራት መሸጋገሩን ያረጋግጣል፡፡ እነዚህ ድርጊቶች በገዢው ፓርቲ/መንግስት የሚፈጸሙ ከተለመዱ የፈጠራ ውንጀላ፣እሥራት፣ድብደባ … የፍርኃቱ እርከን ወደከፋ ደረጃ መሸጋገሩን ከማረጋገጣቸው በተጨማሪ ቀጣይ ትግላችን የሚጠይቀውን ከፍተኛ መስዋዕትነት ያመለክታሉ እንጂ የህዝቡን የለውጥ ፍላጎትና ለዚያ የሚደረገውን ትግል አፍነው አያቆሙም ፣ለውጡን አያስቀሩትም፡፡ ትብብሩን ከትግሉ እንዲያፈገፍግ አያደርጉም፡፡
በመሆኑም ዛሬም የዕውቅና ጥያቄኣችንን በመስተዳድሩ የፋክስ አድራሻዎች ደግመን አድርሰናቸዋል፡፡
እኛ የጋራ ትግላችንን ‹‹ ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› ብለን ስንጀምር ‹‹ነጻነት በሌለበት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አይኖርም›› በሚል እምነት በመሆኑ ጥያቄው የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና የሠላማዊ ሥልጣን ሽግግር ነው፡፡ከሌሎች የተቃውሞ ጎራ ፓርቲዎች ጋር ከምርጫ በፊት ‹‹ስለ ፖለቲካ ምህዳሩ›› እና ብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ እንነጋገር ስንል ህዝቡ የአገሩና የሥልጣን ባለቤት ይሁን፣በውስጡ ከያዘው መልዕክት አንዱ ስለ ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ አሳታፊ፣ ተኣማኒ ምርጫ እንነጋገር የሚል ነው፡፡ ከምርጫ አንጻር እነዚህ ጥያቄዎች በዋነኛነት፡- ፍትሃዊ የሚዲያ አጠቃቀምን፣የፖለቲካ ፓርቲዎችን ነጻ እንቅስቃሴና የፓርቲዎችን እኩልነት፣ የምርጫ ሂደቱን አሳታፊነትና የምርጫ ቦርድን ገለልተኝነትና ግልጽነት፣ የመራጩን ህዝብ በህገ መንግስታዊ መብቱ ተጠቅሞ በነጻነትና በባለቤትነት (ሳይፈራና ሳይሸማቀቅ) በንቃት የመሳተፍ፣የሲቪክና ዲሞክራቲክ ድርጅቶችና ማኅበራት ነጻ ተሳትፎ መረጋገጥ… እነዚህን መብቶች ለመቀማት የተዘጋጁ ህገመንግሥቱን የሚቃረኑ አፋኝ ህጎች መሻር/መታረምና በነዚህ ህጎች የታሰሩ ዜጎች ተፈተው በሙያቸውና አደረጃጀታቸው ሠላማዊ ትግሉን እንዲቀላቀሉ ማለታችን ነው፡፡
ጥያቄዎቻችን ግልጽ፣ ትግላችንም ህጋዊና ሠላማዊ በሆነበት ከላይ የተገለጹት ድርጊቶች የሚያሳዩት በገዢው ፓርቲ/መንግሥት የተመረጠው ኢህገመንግሥታዊና ኢዲሞክራሲያዊ የአፈና አካሄድ መሆኑንና የመንግሥት አስፈጻሚ ተቋማት በገዢው ፓርቲ ሙሉ ቁጥጥር ሥር ወድቀው ለተቋቋሙበት ዓላማ ለስፈጸሚያ በህግ የተሰጣቸውን መብት እንኳ ሊጠቀሙ የማይችሉ መሆኑን፣ ይህም ያነሳናቸው ጥያቄዎችን ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በመሆኑም በእኛ በኩል ‹‹ ነጻነታችን በእጃችን›› በመሆኑ በኢህገመንግሥታዊና ኢዲሞክራሲያዊ እርምጃዎች ወደኋላ ሳናፈገፍግ፣ እያንዳንዳችን በተናጠል የተደረጀንበትን፣ በጋራ የተባበርንበትንና የቆምንለትን ዓላማ በአፈና ላለመጣል ለአገራችንንና ህዝቧ የምንቆጥበው የለንምና በሰላማዊ ትግሉ እስከ ህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ዕቅዳችንን በህጋዊ መንገድ ለማስቀጠል ያለንን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት ዛሬም ደግመን እያረጋገጥን ፡-
1ኛ/ ገዢው ፓርቲ/መንግሥት የሚከተለውን አምባገነናዊ አካሄድ እያወገዝን፣ ከነዚህ ድርጊቶች እንዲገታና ህገመንግስቱን አክብሮ የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ ላቀረብነው ህጋዊ የዕውቅና ጥያቄ በአስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ፤
2ኛ/ ጥያቄዎቻችን የአገርና የህዝብ ጉዳይ ፣የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በመሆኑ ቀዳሚ ባለቤቶቹ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ የምትገኙ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ለቀጣዩ ሠላማዊ ትግል የምናቀርበውን ጥሪ በንቃት እንድትከታተሉና ከጎናችን እንድትቆሙ፤
3ኛ/በትብብሩ ያልታቀፋችሁ፣ በተለይም በሂደቱ ከጅምሩ እስከ መጨረሻው ተሳትፋችሁ የስምምነቱን ሰነድ ያልፈረማችሁ፣ ዲሞክራቲክ የፖለቲካ ኃይሎች ከትብብሩና ከተያያዝነው ትግል በአስቸኳይ እንድትቀላቀሉ፤
4ኛ/ ለሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብት መከበርና ለዘላቂ ሠላም የቆማችሁ የዓለም አቀፉና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላትና መንግስታት በገዢው ፓርቲ/መንግሥት ላይ አዎንታዊ ጫና እንድታሳድሩ፤ጥሪያችንን በድጋሚ እናቀርባለን፡፡
ያለመስዋዕትነት ድል የለም//
ሕዳር 17 ቀን 2007 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፡፡
No comments:
Post a Comment