ከዋልን ካደርን ገና ብዙ ጉድ እንሰማለን። የኢትዮጵያን ታሪክ ማጠልሸት ሰሞኑን እንደ ወረርሽኝ ሆኗል። የኢትጵያን ታሪክ የደብተራ ተረት ነው ብሎ ማጣጣል፣ ደብተራን ከአማራ ጋር ብቻ ማያያዝ ያለማወቅ በሽታ ካልሆነ ምን ይባላል? አለማወቅን ማወቅ ጤና፣ አለማወቅን አለማወቅ ደግሞ በሽታ ነው።
ደብተራ ያየውን የሰማውን በከተበ ለምን ይንቋሸሻል? የደብተራ ጥፋቱ አስቀድሞ መሰለጠኑ ነው፤ ፊደል የስልጣኔ በር ነው፤ ደብተራ ደግሞ ፊደል የቆጠረ የመጀመሪያ ሰው ነው፤ የኢትዮጵያ ደብተሮች በጊዜያቸው ከነበሩት ሰዎች አስቀድመው የሰለጠኑ ናቸው፤ ስልጣኔውን ያገኙትም በፊደል በኩል ነው። አስቀድመው በመሰልጠናቸውም፣ ለሁላችንም የሚሆን ነገር ጽፈው አለፉ። ባይሰለጥኑ ኖሮ ታሪክን ለመጪው ትውልድ ስለማስተላለፍ አይጨነቁም ነበር። ከደብተራ ውጭ ታሪክን ለመጪው ትውልድ ጽፎ ስለማስቀረት ያሰበ ማን ነው? ተራው ገበሬ ዝናብ መጣ ሄደ፣ ተራው ነጋዴ አሞሌ ተወደደ ረከሰ፣ ተራው ወታደር ድንበር ሰፋ ጠበበ፣ ንጉስ ግብር ጨመረ ቀነሰ ከማለት ውጭ ታሪክ ጽፎ ስለማስተላለፍ ተጨንቆ ያውቃል? ስለጥበብ ስለውበት ተጨንቆ የጻፈውም ደብተራው ነው።
ደብተራ ባየው በሰማው፣ የጆግራፊ እውቀቱ፣ የእግሩ ጥንካሬ፣ የቀለም አቀባበሉና እድሜው በፈቀደለት መጠን ጻፈ። ሲጽፍ ይጨምራል፣ ይቀንሳል። የጨመረውን የቀነሰውን ማስተካከል ከደብተራ የተሻለ እውቀት ያገኘው የሁዋለኛው ትውልድ ሃላፊነት ነው። ታዲያ እንዲህ ሲባል ደብተራን በማድነቅ እንጅ በማንቋሸሽ አይጀመርም። ኒውተን ጋሊሊዮን አንቋሾ ጥናት አልጀመረም፣ አንስታይን ኒውተንን አንቋሾ አልተነሳም። የኛ ዘመንኛ ጻፊዎች ደግሞ የሁዋላውን አንቋሾ መጀመር እውቀት ይመስላቸዋል። ጽሁፋቸውም በውሃ ላይ እንደበቀለ ተክል የሚሆነው ለዚህ ነው፣ ስር አልባ ነው፤ እፍ ቢሉት እንደ ላባ በኖ ይጠፋል።
አሁን ደብተራ ባይጽፍ ኖሮ ታሪካችን የሰሃራ በታች ካሉት አገራት ይለይ ነበር?። ከሰራሃ በታች ካሉ አገራት በራሱ ቋንቋ ታሪኩን ጽፎ ያስቀረ ከእኛዋ ኢትዮጵያ ውጭ ሌላ አለ? አብዛኛው የጥቁሩ የአፍሪካ ታሪክ የተጻፈው በቅኝ ግዛት ጊዜ አይደለምን? ፈረንጆቹ ለእነሱ በሚጥማቸው መንገድ አይደለም የከተቡት? ምንጫቸውስ ምንድነው? ህንጻዎች እና ቁሳቁሶች አይደሉም? ታዲያ ደብተራ ታሪክ ጽፎ ባስቀረ፣ ድንጋይና ቁሳቁስ ከመፈለግ ባዳነ ለምን ይሰደብ?
ደብተራ ታሪክ የሚጽፈውስ በእኛ አገር ብቻ ነው? የአውሮፓ የጥንት ታሪክ በማን ተጻፈና ነው? የአውሮፓ የታሪክ ወመዘክር ካቶሊክ ቤ/ክ አይደለችም? ስኮላስቲስዝም የሚባለው ታላላቅ ምሁራን የወጡበት የትምህርት ስርዓት የሚመራው በደብተሮች አልነበረምን? የአውሮፓን ታሪክ ከደብተራ ታሪክ መነጠል ይቻላል? የፈረንጅን ደብተራ አቆለጳጵሰን የሃበሻን ደብተራ የምናዋርድበት ምክንያቱ ምን ይሆን? አውሮፓ ውስጥ በኢራስመስ ስም ስኮላርሽፕ የምትመጣው ኢራስመስ ማን ሆነና ነው? የፈረንጅ ደብተራ አይደለም?
ከአገራችን ደብተራ ብንማር ኖሮ ዛሬ እንደ አውሮፓውያን 6 ቢሊዮን ኪሜትር የሚጓዝ መንኮራኩር እናመጥቅ ነበር። ኮፐርኪነከስና ጋሊሊዮ ማን ናቸው? ደብተሮች አይደሉም? የሰማይን ምስጢር ለማወቅ ሰማይ ሲያንጋጥጡ በመኖራቸው የኸው ለዛሬው አስደማሚ የህዋ ምርምር በር ከፈቱ። የእኛዎቹ ደብተሮች ስለአስትሮሎጂ ምርጥ የሆነ እውቀት ቢያከማቹም አጣጥለነው በዘመናዊ መንገድ ሳንማረው ቀረን፤ የማጣጣላችን ውጤትም ፈረንጅ ወደ ላይ ሲመጥቅ እኛ መሬት መሬት እያየን ተቀብረን ቀረን። ዛሬ በየጋዜጣው ጀርባ የምታነበው ሆሮስኮፕ፣ የእኛ ደብተሮች ከዘመናት በፊት ኮከብ ቆጠራ እያሉ ሲያሰሉት የነበረ ነው። ፈርንጅ የተለየ ስም ስለሰጠው እንጅ ስራውና ይዘቱ ያው ነው። ልጅ እያለሁ አንድ ደብተራ ስለ ኮከብ ቆጠራ እና ስለጨረቃ አወጣጥ ቀመር አስተምረውኝ ነበር፤ የደብተራ ትምህርት ዳቦ አያበላም ብየ ሳልገፋበት ቀረሁ። የአገራችን ደብተሮች እምቅ እውቀት ቢኖራቸውም እያጣጣልነው ሳንጠቀምበት ቀረን።
ደብተራ ማለት ፊደል የገደለ ከሆነ ታሪኩን ጽፎ ያስቀረ ስንት የእስላም ደብተራስ አለ? በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ወደ አማርኛ የተተረጎሙ የሃይማኖት መጽሃፍት በአረብ ደብተራ የተጻፉ ናቸው። ደብተራንስ ማነው አማራ ብቻ ያደረገው? የትግሬ ደብተራም ሞልቷል።
ለታሪካችን የምንሰጠው ዝቅተኛ ቦታ ገና ዋጋ ያስከፍለናል፤ ታሪክ አልባነት የሚፈጥረውን ስሜት ለማወቅ ወደ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ሂዱና እዩት። በ20ኛ ክፍለዘመን መግቢያ ፈረንሳይ ውስጥ እነ ሴዳር ሴንጎር ያቋቋሙት ኔግሪቲውድ የሚባል እንቅስቃሴ ነበር። ኔግሪቲውድ የተመሰረተው ፈረንሳይ ጥቁር አፍሪካውያንን ፓሪዛውያን አደርጋለሁ ብላ ወደ ፈረንሳይ ሰብስባ ካመጣቻቸው በሁዋላ ነው። ጥቁር አፍሪካዊያኑ ፈረንሳይ ከመጡ በሁዋላ ሲያዩት ባዶነት ተሰማቸው፣ የሚወራው ታሪክ ታሪካቸው አልመስል አላቸው፤ ታሪካቸውንና ባህላቸውን ፈልጎ ለማግኘት ተነሳሱ፤ ኔግሪቲውድን ፈጠሩ። ያን ጊዜ የነበሩ ጻሃፎች ሁኔታውን ታቡላ ራሳ (tabular rasa) ብለው ይገልጹት ነበር። በግርድፍ ትርጉሙ፣ ባዶ ሰሌዳ ማለት ነው፤ አዎ የመጡበትን ታሪክ አለማወቅ ጭንቅላትን ጥቁር ሰሌዳ ያደርጋል፤ ጭንቅላትህ ጥቁር ሰሌዳ ከሆነ ደግሞ ነጭ ጠመኔ ( ቾክ) እንደፈለገ ይጽፍብሃል። ያን ጊዜ የምታነበንበው ነጩ ቾክ የጻፈልህን ይሆናል። ራስን ለባርነት አሳልፎ መስጠት ይሉሃል ( ይሉሻል) ይህ ነው።
No comments:
Post a Comment