Tuesday, November 25, 2014

እስክንደር ነጋ አሸባሪ ከተባለ ጆን ኬሪና አል ባራዴየም አሸባሪዎች ናቸው ማለት ነው!

 በግርማ ካሳ

በየትም የሰለጠነው አለም እንደሚደረገው፣ በአገርና በሕዝብ ላይ ችግር የሚፈጥር ወንጀለኛ መያዝና መቀጣት አለበት። ሕግ መከበር አለበት። ይሄ ብዙ አያከራክረንም። ነገር ግን «ሕግ፣ ሕግ» እየተባለ፣ ፍጹም ሕገ ወጥ የሆኑ ተግባራት፣ ሕግ አስከባሪ ነን በሚሉ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ገዢዎች እየተፈጸመ መሆኑን ነዉ አጥበቀን የምንቃወመዉና የምናወግዘው። የምንታገለውም። ሕግ ሁላችንንም በእኩልነት የሚዳኝ መሆኑ ቀርቶ፣ ጥቂቶች እንደፈለጉ የሚገለባብጡት፣ የመጨቆኛ መሳሪያ በትር መሆኑ ነዉ እያሳሰብን ያለው።

በአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት በተደረገ ስብሰባ ላይ «እንችላለን! በሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች እንደሚቻል አይተናል። ኢትዮጵያ ከእነሱ ቢያንስ ቢያንስ አታንስም። ታሪክ እንስራ!» ሲል እስክንደር ነጋ ተናግሮ ነበር። በተለያዩ ድህረ ገጾች ላይ ይሄንን አቋሙን ሳይፈራ በግልጽ አስፍሯል። እንግዲህ በግብጽ የታየውን እንቅስቃሴ መደገፉ ነው ሽብርትኛ አስብሎ ወደ ወህኒ ያስወሰደው።
«እስክንደር፣ በግብጽ የተከሰተዉ በኢትዮጵያ እንዲከሰት መፈለጉና በዚያ ዙሪያ መንቀሳቀሱ በምን መስፈርትና ሚዛን ነዉ ሽብርተኘንት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ? » በሚለው ላይ አንስተን ትንሽ እንበል።

በግብጽ የነበረው እንቅስቃሴ ፍጹም ሰላማዊ የነበረ እንቅስቃሴ ነዉ። ከዚህ እንቅስቃሴ መሪዎች መካከል የነበሩ አንዱ ዶክተር ሞሃመድ አል ባራዴ ይባላሉ። በተባበሩት መንግስታት የአለም አቀፍ ኑክሊያር ኤጀንሲ ሰብሳቢ ሆነው ለበርካታ አመት ያገለገሉ የተከበሩ ሰው ናቸው። እንደ ሳዳም ሁሴን የመሳሰሉ ሽብርተኛ መንግስታት ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች በማከማቸት ለአለም ስጋት እንዳይፈጥሩ የታገሉ፣ የሰላም ሰዉ ናቸው። እኝህ ሰውና የሚመሩት ድርጅታቸው እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ2005 የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ሆነዋል። ታዲያ ሰላማዊ በሆነ መልኩ፣ አምባገነኑ የሙባረክ መንግስት ለሕዝብ ፍቃድ ተጠያቂ እንዲሆን፣ የስርዓት ለዉጥ እንዲመጣ፣ መታገላቸው እኝህ የሰላም የኖቤል ተሸላሚን ሽብርተኛ ያደርጋቸዋልን ?

በአዲስ አበባ ጆን ኬሪ፣ ሃርድ ቶክ ቢቢሲ ባዘጋጀው ዝግጅት ላይ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተማሪዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሰጥተው ነበር። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ቴዎድሮስ አዳኖም በዚያ ነበሩ። ጆን ኬሪ ንግግራቸውን ሲጀመሩ የተናገሩትን ማንሳት እፈልጋለሁ። በግብጽ ስለነበረው ፣ ሕወሃት/ኢሕአዴግ ሽብርተኘንት ብሎ ስለሚጠራዉ፣ እንቅስቃሴ ሲናገሩ የሚከተለዉን ነበር ያሉት፡

«…the greatest concern has to be the lack of the fulfillment by governments in many countries, of the aspirations of people. Particularly the creation of jobs, and tሀ educational opportunities that are needed, for this modern world….In Egypt, that was not a revolution that was moved by Islamism, or any ideology ….It was young people.. ..it was you ..people who came to the square , and twitted each other , texted each other , e-mail each other and brought people»


ጆን ኬሪ፣ ሕወሃት/ኢሕአዴግን እንደ ሽብርተኝነት የሚቆጥረዉን በግብጽ የታየውን ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንደ ትልቅ ምሳሌ አጉልተው፣ እስክንደር ነጋና ሌሎች ከተናገሩት አባባሎች ጋር የሚስማማ ንግግር ሲናገሩ፣ የሕወሃት/ኢሕአዴጉ ዶር ቴዎዶርስ ቁጭ ብለው ያዳምጡ ነበር። ታዲያ ጆን ኬሪ፣ የግብጽን እንቅስቃሴ በመደገፋቸው፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ከግብጽ ወጣቶች እንዲማሩ በማባረታታቸው ሽብርተኛ ሆኑን ? ሌላ ሌላም ምሳሌዎች ማቅረብ ይቻላል።

እስክንደር ነጋ ቦምብ አላፈነዳም። ቤቱ ተበርብሮ አንድም ጥፋተኝነቱን የሚገልጽ መረጃ አልተገኘም። ወንጀሉ እንደ ጆን ኬሪ፣ ሞሃመድ አልባራዴ የግብጽ ሕዝባዊ እንቅስቃሴን መደገፉ ፣ በሕዝብ ጉልበት ኃይል መተማመኑ ነዉ። ወንጀሉ አገሩን መዉደዱ ነዉ።

ገዢዎች፣ ልቦና ካላቸው፣ እንደ እንስሳ ሳይሆን እንደ ሰው ማሰብ ከቻሉ፣ በአቸኳይ እስክንደር ነጋና ቆጥረናቸው የማንጨርሳቸውን የሕሊና እስረኞች እንዲፈቱና ለሕዝብ ጥያቄ ርሳቸዉን እንዲያስገዙ እመክራለሁ።

No comments:

Post a Comment