Friday, July 4, 2014

ታጋይ ይሞታል እንጂ ትግል አይሞትም!!!


ጆሴፍ ስታሊን ስልጣኔን ይቀማኛል፣ ወንበር አሳጥቶ ያሳንሰኛል ብሎ ጥምድ አድርጎ የያዘዉን አስተዋዩን ምሁር ፣ማርክሳዊ አብዮተኛ ፣የንድፈ ሃሳብ ወጣኝ፣ የቀዩ ጦር መስራችና መሪ የነበረዉን ድንቁን ሌዮን ትሮትስኪይን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት እንደእብድ ተነሳስቶ እግር በእግር እየተከታተለ ከሞስኮ አንስቶ ካዛኪስታን ፣ቱርክ፣ፈረንሳይ ፣ኖርዌይ ኦስሎ ድረስ ሌት ከቀን አሳደደው ።በመጨረሻም የፖለቲካ ጥገኝነት ተሰጥቶት እሚኖርበት ሜክሲኮ ድረስ ገዳዮች አሰማርቶ ጥይት በማርከፍከፍ ቤቱን አስነዳድሎ ኢላማው ባይሰምርለት፣ የስፓኝ ተወላጅ በሆነ ቅጥረኛ በበረዶ መፈቅፈቂያ መሮ አናቱን አስጨቅጭቆ በማስገደል ለፍፃሜ አበቃው ።ቤተሰቦቹንም በተናጥል አድኖ ድራሻቸዉን አጠፋቸው ።

የወያኔ አገዛዝም በሳሉን የፖለቲካ ሰው ፣የነፃነት ታጋዩን ፣አስተዋዩንና ቆራጡን አንዳርጋቸው ፅጌን እንዲሁ ሃብቱን ጠርጎ ወርሶ፣ቤተሰቦቹን ሁሉ አስሮ በዘግናኝ ሁኔታ አሰቃይቶ፣የሰማንያ ዓመት አዛዉንት አባቱን በስተርጅና በማረፊያ በመጦሪያ ጊዜያቸው አዋክቦ አስሮ አንገላቶ ፣በኢሰብአዊ መንገድ ወንድሙን አስሮ አሰቃይቶ አካሉንም አጉድሎ ወህኒ የዘላለም ቤቱ እንዲሆን ፈረደበት ። አንዳርጋቸዉን ወህኒ ለሁለት አመታት አግቶ፣መግቢያና መዉጫ አሳጥቶ ከሀገር አባሮ፣ ኤርትራ በረሃዎች ድረስ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች አስታጥቆ ልኮ ነፍሱን ሲጥ ለማድረግ ያቀደው እቅድ ባይሳካለት ፣ አድብቶና አስልቶ የመን ላይ ትራንዚት ሲያደርግ አሳፍኖ ወደ አዲስ አበባ ወስዶታል ።

አዎ አንዳርጋቸው በወያኔ ፍትህ አልባ ፍርድቤት ፍርደገምድል ችሎት በሌለበት ሞት የተፈረደበት ሰው ነው ። አንዳርጋቸዉ ጭራቆቹ እጅ ገብቶ የሚጠብቀዉን ግርፊያ፣ስቃይ ለመገመት ነቢይ መሆን አያሻም ።ወያኔ ያልተረዳው ነገር ቢኖር፣ይህ ትግሉን እንደሰደድ እሳት ዳር እስከዳር ያቀጣጥለዋል እንጂ አያበርደዉም።ያፋፍመዋል እንጂ አያከስመዉም።


አንዳርጋቸው ምንም ለሞት የሚያበቃ በማስረጃ የተረጋገጠ ወንጀል አልሰራም።ተዋደን ተፋቅረን የምንኖርባትን ፣እኩልነታችን የሚረጋገጥባትን፣ፍትህ የሚነግስባትን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ነው ራዕይ ሰንቆ እድሜ ልኩን ሲለፋ የኖረው ። ወያኔ ዘላለም ስልጣን ላይ ለመዘፍዘፍ ሲል ያፍናል ። ያስራል።ይገርፋል።ይገድላል ።ህዝብን ማንገላታት ፣ማሰቃየት ፣ማደህየትና መፍጀት ለማንም ለምንም አይበጅም ።

መንግስት ጊዜያዊ እንጂ የዘላለም ርስት የለዉም ።ይዋል ይደር እንጂ መዉደቁ አይቀርም ።ዜጎችን መግደል ዘላለም ስልጣን ላይ ለመቆየት ዋስትና አይሆንም ።የሰፊዉን ምስኪን ህዝብ ትግል ከቶም ሊያኮላሽም አይችልም። በፍፁም !ታጋይ ይሞታል እንጂ ትግል አይሞትም። አንድ ታጋይ በሞተ ቁጥር ሚሊዮን ታጋዮች ይወለዳሉ ።ግን እስከመቼ ድረስ ነው ገዳዮቻችን የሚገዙን? ሁሉንም ከርመን እናየዋለን።ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ቀሪው ትዝብት ነው ።

No comments:

Post a Comment