Sunday, July 13, 2014

ኢህአዴግ በምርጫ ዋዜማ የጀመረው እስር በአምባገነንነት መስመሩ ለመቀጠል የቆረጠ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው!!!

ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) እና ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

ኢህአዴግ በምርጫ ዋዜማ የጀመረው እስር በአምባገነንነት መስመሩ ለመቀጠል የቆረጠ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው!!!
በፖለቲካ አመለካከታቸው እና እምነታቸው የታሰሩ ዜጎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ በድጋሚ እንጠይቃለን!!

ሕወሓት/ኢህአዴግ ለአለፉት 23 ዓመታት ወደር የሌለው የዴሞክራሲያዊ መብት ገፈፋና የሰብአዊ መብት ረገጣ በዜጎች ላይ ሲፈጽም መቆየቱና አሁንም በዚያው የአፈናና እስር መንገድ መቀጠሉን ዓለም የሚያውቀው እውነታ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለይም በሚቀጥለው ዓመት የሚካሔደውን ሀገራቀፍ ምርጫ ተከትሎና ሁለቱ ፓርቲዎች የጀመሩትን የውህድት ጉዞ ለማደናቀፍ ባለመ መልኩ የሰብአዊ መብት ረገጣና ድፍጠጣ እንዲሁም ማሰሩና ማዋከቡ በእጅጉ ተባብሶ ወደ መንግሥታዊ ሕገ ወጥነት ጥቃት ተቀይሯል፡፡ ዜጎች መንግሥት እንዳሰማራቸው በሚጠረጠሩ የደህንነት ኃይሎች ስርዓቱን በሃይል ለማስቀጠል በመቁረጥ ዜጎች ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በጅምላ መታሰራቸውን፣ መደብደባቸውንና በስውር እስር ቤቶች ተወርውረው ደብዛቸው እንዲጠፋ መደረጉ ቀጥሏል፡፡ እንደዚህ አይነቱ ሕገ ወጥነት ደግሞ ምርጫ ሲቃረብና የፖለቲካ ፓርቲዎች መሰባሰብ ብሎም መዋሃድ ሲገለፅ ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሆነ ከዚህ በፊት ከነበሩ ተሞክሮዎች ለመረዳት ይቻላል፡፡

ሕወሓት/ኢህአዴግ ለባለፉት 23 ዓመታት ሲያደርገው እንደነበረው ሁሉ ምርጫ ሲደርስ አባሎቻችንን ከመደብደብና ከማሳደድ በተጨማሪም በምርጫው ዋዜማ በተለመደውና አሰልቺ ፍረጃው ተደግፎ አመራሮቻችንን ማሰር ጀምሯል፡፡ እስሩም በፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ያነጣጠረ ሲሆን ሰሞኑን ብቻ አንድነት የስራ አስፈፃሚ አባልና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑትን አቶ ሀብታሙ አያሌውን፤ የምክር ቤት አባልና የድርጅት ጉዳይ ምክትል ሃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺን፤ የአረና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆነውን አቶ አብርሃ ደስታን እና የሰማያዊ ፓርቲ ም/ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ የሆነውን አቶ የሽዋስ አሰፋን አስሯል፡፡ በተጨማሪም ሰብዓዊ መብታቸውን በመግፈፍ ከ48 ሰዓት በላይ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡ በጠበቃም ሆነ በወዳጅ ዘመዶቻቸው አይጎበኙም፡፡ በአካላቸውም ሆነ በስነ ልቦናቸው የደረሰባቸውን ጉዳት ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ ስለዚህ ሁለቱ ፓርቲዎች እንደዚህ አይነቱን ሃላፊነት የማይሰማውና የጭካኔ ተግባር ማውገዝ ብቻ ሳይሆን እስከመጨረሻው ፍፁም ሠላማዊ በሆነ መንገድ አምርረን የምንታገለው መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡

የሰሞኑ እስር እንደተለመደው የተቀነባበረ የስርዓቱ ድራማ ከመሆኑም በተጨማሪ የ2007ን ሀገራቀፍ ምርጫ በተለመደው ማሸማቀቅና ማወናበድ ለመውሰድ የተጀመረ የመጀመሪያ ርምጃ ነው ብለንም እናምናለን፡፡ የተቀነባበረ ድራማም በሚቆጣጠራቸው ስማቸው የህዝብ ተግባራቸው ግን የኢህአዴግ የፓርቲ መገልገያ በሆኑ ሚዲያዎች ማቅረቡን እንደሚቀጥልም እናውቃለን፡፡ ይህ ሁሉ ግፍና ድራማ የሚከናወነው ከአፍ ባለፈ መተግበር ያልቻለውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማስመሰያነት ለመጠቀምና የቀጣዩን ዓመት ምርጫ በለመደው ሁኔታ ከቻለ አስሮና አደናግሮ ካልተቻለ ጉልበቱን ተጠቅሞ ለመጠቅለል ነው፡፡

አንድነትና መኢአድ አባላትንና አመራሮቻችንን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በማሰቃየትና በማሸማቀቅ፣ በመደብደብ የአካል ማጉደል ጉዳት በማድረስ የሚያደርገውን አስነዋሪ ተግባር እያወገዘን በግፍ የተታሰሩት አቶ ሀብታሙ አያሌው፤ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፤ አቶ አብርሃ ደስታ እና አቶ የሺዋስ አሰፋ እንዲሁም በስርዓቱ በፖለቲካ አመለካከታቸውና እምነታቸው ብቻ ለእስር የተዳረጉ ፖለቲከኞች፤ ጋዜጠኞችና ብሎገሮች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እናሳስባለን፡፡

በተጨማሪም በተቃውሞ ጎራ የተሰለፉ ፓርቲዎችም ይህን ህገ ወጥ እስር በማውገዝ እንዲሁም ኢ-ፍትሀዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚደረገውን ሩጫ በመቃወም እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንቆም እየጠየቅን ይህንን ህገ-ወጥነት በህዝባዊና ሠላማዊ ንቅናቄ፣ በነፃና ፍትሓዊ ምርጫ መለወጥ እንዲቻል በጋራ እንድንሰራ ሀገራዊና ወቅታዊ ጥሪ እናቀርባለባለን፡፡ የሲቪክ ተቀቋማት፤ ነፃው ሚዲያና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶችም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን መንግስታዊ ግፍና በደል በዓለማቀፍ ደረጃ በማጋለጥ ግዴታችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን፡፡ ገዢው ፓርቲ የሚከተለው የጉልበት ርምጃ ሀገሪቱን የሚያጠፋና ለትውልድ ጥላቻ የሚያወርስ በመሆኑ ከዚህ ድርጊቱ እንዲቆጠብ እንጠይቃለን፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም ስለሰብዓዊ መብት መከበርና ዴሞክራሲ መረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ትግል በመደገፍ የአምባገነኖችን ውድቀት እንዲያፋጥን ሀገር አቀፍ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

ድል ለሠፊው ህዝብ!!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) እና
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)
ሐምሌ 3 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment