Monday, July 21, 2014

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የኢትዮጵያ የምንግዜም ጀግና!


በቅዱስ ዮሃንስ

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በበርካታ የታሪክ ምዕራፎች ብሄራዊ ውርደትን አስተናግደናል። አንደኛውና ሁላችንም የምናውቀው በጣልያን ወረራ ወቅት፤ በራሳችን ባንዳዎች የተፈጸመብን ውርደት ነው። ሁለተኛውን ውርደት የተከናነብነው በቀይ ሽብር ዘመን ወንድም ወንድሙን ገድሎ የፎከረበት ወቅት ሲሆን፤ ሶስተኛው ብሄራዊ ውርደት ደግሞ፤ አሁን አገራችንን በቀኝ ግዛት የያዘው የወያኔ አገዛዝ ያከናነበን የቅሌት ቡሉኮ ነው። የዛሬ ጽሁፍ መነሻዬ ስለያንዳንዱ ዘመን ብሄራዊ ውርደት ለመተንተን አይደለም። ይልቁንም በእንደዚህ አይነት የውርደት ዘመን አንገታቸውን ቀና አድርገው፤ ለህዝባቸው ነፃነነት፤ ፍትህና ዲሞክራሲን ሊያጎናጽፉ፤ በወያኔ የአገዛዝ ዘመን ጨርቅ ተብሎ ክብር የተነፈገውን፤ ቀደምት አባቶቻችን ነፍሳቸውን ሳይሰስቱ የገበሩለትን ክቡር ሰንደቅ አላማችንን ከፍ አድርገው በድል ሊያውለበልቡ፤ ለህይወታቸው ሳይሰስቱ ኑሮዋችውን በዱር በገደል አድርገው ስለነበሩት የኢትዮጵያ የምንግዜም ጀግና ስለ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጥቂት ለማለት ፈልጌ እንጂ።

እኛ ኢትዮጵያውያን በተረትና በባህላዊ ወጎች በርካታ የተለያዩ ጀግኖች አሉ፡፡ አንዳንዶች በሚያጋጥማቸው አደጋ ወቅት በሚያሳዩት የሞራል ጥናካሬ  ይጀግናሉ፤ አንዳንዶች ደሞ ለክብራቸውና ለዓላማቸው በመቆማቸው ይጀግናሉ፡፡ እንዲሁም አንዳንዶች ጠላቶቻቸውን በፍልሚያው ሜዳ በመግደላቸው ድል በማሸነፋቸው ጀግና ይባላሉ፤ ለፍቅር የተሰዉ ጀግኖችም አሉ፤ ዘመናዊና ባህላዊ ጀግኖችም ይታያሉ፤ ያልታወቀላቸውም ጀግኖች አሉ፤ ደግሞም የድል አጥቢያ ጀግኖችም አሉ፡፡  በዚህም ሆነ  በዚያ ሁሉም የሚጋሩት አንድ ባህሪ አላቸው፡፡መስዋእትነት፤ ታማኝነት፤ ጥንካሬ፤ ቆራጥነት፤ እርግጠኛነት፤ ያለማወላወል እና ሌሎችም ሁኔታዎች፡፡

ከዚህ ሁሉ በተለየ አኳኋን ግን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሁሉንም ባህሪያት የተጎናጸፉ ዘመን የማይሽራቸው የኢትዮጵያ የምንግዜም ጀግና ናቸው። አዎ! አቶ  አንዳርጋቸው ለቆሙበት ትግል ቆራጥነትንና መስዋዕትነትን፤ ለአላማቸው ታማኝነትን፤ ለመንፈሳቸው ጥንካሬን፤ ለድሉ የእርግጠኝነትን ዝናርን የታጠቁ የህዝባችን የቁርጥ ቀን ልጅ ናቸው። አቶ አንዳርጋቸው ለነፃነት፡ ለፍትህና ለዲሞክራሲ የሚዋጉ ፋና ወጊ አርበኛ ናቸው፡፡ የህዝባችን ጭቆናና ድህነት ረፍትና እንቅልፍ የነሳቸው የነፃነት አርበኛ ናቸው፤ የወያኔ መሰረተ ቢስ መደለያና ማታለያም ሳይበግራቸው የወገናቸውን ፍቅር ያስቀደሙ አርቆ ተመልካች ባለራእይ ጀግና ማለት ክቡር አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ናቸው፡፡ ነገ የሚሆነውን ቀድመው ተመልክተው ሊመጣ ስላለው ክብር ክብራቸውን ሰውተዋል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ጀግና ናቸው፤ ሕዝባቸውን በወያኔ አገዛዝ እየደረሰበት ካለው መከራና ስቃይ ለማውጣት የራሳቸውን የተደላደለ ኑሮ የሰዎ፤ ወያኔዎቹ ፈርዖኖች የገነቡላቸውን የምቾት ዓለም ሳይቀር ለወገናቸው ፍቅር ሲል የናቁ ብልህ አርበኛ፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ማለት ሁሌም የወገናቸውን ጥቅም የሚያስቀድሙ፤ በእርሳቸው ሞት የሌሎችን ሕይወት የሚያደላድሉ፤ ወገኖቹ ነገ እንዲኖሩ ዛሬውን የሚሰው፤ ለሌላው ጥቅም ሲሉ የሚጎዱት ጉዳትንም እንደጥቅም የሚቆጥሩ፤ ስለከፈሉት መስዋዕትነት ፈጽሞ የማይጸጸቱ የነፃነት አርበኛ ናቸው፡፡


እርግጥ ነው እንደ ኢትዮጰያ ባለ የአምባ-ገነን ስርዓት በነገሰባት አገር ህይወቴ የሚሉትን ነገር በሙሉ በመዘንጋት ትግሉን ህይወታቸው ያደረጉ ጥቂት ሰዎችን ለማየት ታድለናል፡፡ ዕጣ-ፈንታቸው ሞት፤ እስራት ወይም መሰደድ እንደሆነ ቀድመው ተረድተው ዕጣው እስኪደርስባቸው ድረስ ያላቸውን ሁሉ ለሚወዷት አገራቸው ሰጥተዋል፤ እየሰጡም ነው፡፡ እንግዲህ ክቡር አቶ አንዳርጋቸውም ከነዚህ ጥቂቶች መካከል የሚመደቡ መሆኑን ስናገር በሙሉ ልቤ ነው፡፡ እርሳቸውንም ለማወደስ ስነሳ ፍርሃትን ሰብረው ከኋላ የሚከተሏቸውን የእርሳቸውን እልፍ አእላፍ ፍሬዎች መብዛት እያስተዋልኩ ነው፡፡ የወያኔ አገዛዝ ህዝቡን በጠመንጃ ኃይል አስገዝቼዋለሁ ብሎ ሲፎክርና ሲሸልል፤ ሕይወቴ እሳከለችና  መተንፈስ  እስከቻልኩ ድረስ ይህን የናንተን የጭቆና የግፍ አገዛዝ ተቀብዬ አልኖርም። ጭካኔያችሁን፤ አውሬነታችሁን፤ ግፋችሁንማ ጨርሶ ለመቀበል ቀርቶ ላስበውም አልሞክርምና እሱን መዋጋት ብቻ ነው ፍላጎቴ: በማለት የሞገቱና በጽናት የቆሙ አልበገርም ባይ የዕጣ ፈንታዬ ወሳኝ የመንፈሴ አዛዥ እኔ አንዳርጋቸው ጽጌ ነኝ፤ ያሉ የኢትዮጵያ ጀግና ናቸው::

አዎ! ዛሬ እኚህ የኢትዮጵያ ጀግና በየመን የጸጥታ ሃይሎች ተይዘው አለማቀፍ ህግን በተላልፈው አካሄድ ለጉጅሌው ወያኔ ተሰጥተው በጠላት እጅ ወድቀዋል። የፋሽስቱ ወያኔ በእስር ቤት በእኚሁ ጀግና የነፃነት አርበኛ ከፍተኛ ድብደባና እንግልትና እየፈጸመባቸው ይገኛሉ። ሕይወቴ እሳከለችና  መተንፈስ  እስከቻልኩ ድረስ የወያኔን የጭቆናና የግፍ አገዛዝ ህዝቤ ላይ ተጭኖ ማየት ፈፅሞ አልሻም እምቢኝ አሻፈረኝ በማለት የወያኔን አገዛዝ በሚገባው ቋንቋ ሁሉ ለማነጋገር ዝናራቸውን ታጥቀው ለኛ ለወገኖቹ ሲል እንደ ሻማ ቀልጠው የነፃነትን ብርሃን ሊፈነጥቁልን በረሃ የከተቱትን የነፃነት አርበኛችንን ለማስፈታት እኛ ኢትዮጵያውያንስ ምን አስተዋጽኦ እያደርግን እንገኛለን? በርግጥ ይኸው ዛሬ በእርሳቸው ጀግንነት የተማረኩና ከአላማቸው ጎን የተሰለፉ ጎበዞች በአርበኛቸው መታገት ሳት ለብሰውና ሳት ጎርሰው አለምን እያነቃነቁ እንደሆነ በአይናችን ለመመልከት ችለናል፡፡ ከዚህ በላይ ድልም ያለ አይመስለኝም፡፡ አዎ! የተጀመረውን የአጋርነት ንቅናቄ በእጥፍ በማሳደግ ተፅዕኖ በማሳረፍ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን መታደግ ያለብን አሁን ነው። የነፃነት አርበኛው አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በወያኔው የካንጋሮ ፍርድ ቤት የሞት ፍርድ የተፈረደባቸውና ወያኔዎች ለአገዛዛቸው ህልውና ሲሉ በጥብቅ የሚያፈላልጉት በመሆኑ፤ ነገር ግን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ለአገራቸውና ለወገናቸው ነፃነት፤ ለባንዲራቸው ክብር እየተዋደቁ ያሉ የነፃነት አርበኛችን መሆናቸውን በማስታወስ አለም አቀፍ መንግስታትና የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች የየራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ እኛ ኢትዮጵያኖች በሃይማኖት፣ በብሄርና በፖለቲካ አመለካከት ሳንለያይ በጋራ ልንረባረብ ይገባል።  በተለይ የእንግሊዝ ኤምባሲዎችን በያሉበት በተቃውሞ ማጨናነቅና እንቅልፍ መንሳት እንዲሁም አለም አቀፍ ጫና ማድረግ ያስፈልጋል። ግዜ ሳይረፍድ እኝህን የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ጀግና ለመታደግ በያለንበት በጋራ እንረባረብ ስል ወገናዊ ጥሪየን አቀርባለሁ!!! በመጨረሻም ወያኔዎቹ እንዲገነዘቡት የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር እውነተኛ የነፃነት አርበኛ ሊታሰር፤ ሊሞትና ሊሰዋ ይችላል። ነገር ግን ይህ የተጀመረውን የነፃነት ትግል ፈጽሞ ሊገታም ሆነ ሊያቆም ከቶ አይችልም። ኢትዮጵያ አንድ አንዳርጋቸውን ብቻ ሳይሆን ሚሊዮን አንዳርጋቸውን ፈጥራለችና በከንቱ አትድከሙ። ወደዳችሁም ጠላችሁም ድሉ የማታ ማታ የጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ይሆናል!



ኢትዮጵያ በልጆቿ መስዋትነት ለዘላለም ተከብራ ትኖራለች!!

ለገንቢ አስተያየትዎ፡ kiduszethiopia@gmail.com የኢሜል አድራሻየ ነው።

No comments:

Post a Comment