Thursday, July 31, 2014

የወያኔ የጥፋት ሴራ በወጣቱ!


በቅዱስ ዮሃንስ

ከኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዘው በወጣትነት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ሃይል ነው። ይህ የህብረተሰብ ክፍል ማንኛውንም ዓይነት እውቀት ለመቅሰም የሚያስችል ቀልጣፋና ብሩህ አእምሮ፣ ለምርታማነት ተግባር ሊውል የሚያስችል ጉልበትና በቀላሉ የማይዝል አካላዊ ጥንካሬ ያለው እንደሆነ ይታመናል። በዚያው ልክ በአግባቡ ካልተያዘ ከወጣትነቱ ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ጋር ተዳምሮ ለተለያዩ አደጋዎች በቀላሉ ሊጋለጥ ይችላል። የወጣቱ ዝንባሌ የብዙ ጉዳዮች ድምር ውጤት ነው። ብዙ ጊዜ በወጣትነት እድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ዜጎች መካከል በጣት የሚቆጠሩት ጥፋት በሚፈፅሙበት ወቅት ወጣቱን እንዳለ የማውገዝ፤ የማንቋሸሽና የማማረር አዝማሚያ ጎልቶ ይንፀባረቃል፡፡ የዘቀጠ፣ ደካማ፣ የሀገር ፍቅር የሌለው፣ አደገኛ ቦዘኔ፣ በንቀት የተወጠረ ወዘተ ትውልድ በማለት የወጣቱን ባሕሪይ መጥፎ ምስል የሚሰጡ ግለሰቦች ጥቂት አይደሉም፡፡

ኢትዮጵያን በቀኝ ግዛት የያዘው ፋሽስቱ ወያኔም እነዚህ ተቀፅላ ስሞች በመጠቀም የአገራችንን ወጣት አቅሙንና እውቀቱን በመጠቀም ተፈጥሮዊ ዝንባሌውንና አገራዊ ራዕዩን እንዳያሳካ እያሸማቀቀ ከየትኛውም ጊዜ በላይ መሰናክል እንደሆነበት የአደባባይ ሃቅ ነው፡፡ ወጣቱን ረግጦና ከፋፍሎ ለመግዛት የተለያዩ ስልቶችን የሚጠቀመው የጉጅሌው ወያኔ የወጣቱን ሃይል በአገራዊ አጀንዳዎች ላይ ገለልተኛ ለማድረግና አካዳሚያዊ እውቀቱንም ጭምር የላሸቀ በማድረግ የፈረንጅ ባህል ተከታይ እና በተለያዩ ሱሶች በቀላሉ ተጠቂና ተጋላጭ በማድረግ ራዕይ የሌለው ወጣት ለመፍጠር ፖሊሲ በአገር ደረጃ ቀርፆ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ይሄ አይነቱ ሰይጣናዊ ድርጊት ደግሞ ትውልድን ከመግደል ጀምሮ በአገራዊ ጉዳይ ላይ የነቃ ተሳትፎ የሚያደርግ ወጣት እንዳይፈጠር በማድረግ የአገዛዙን ዕድሜ ለማርዘም የተሸረበ እኩይ ሴራ እንደሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠንቅቆ ያውቀዋል ብየ አምናለሁ። የጉጅሌው ወያኔ አገዛዝ ለወጣቱ ጥራቱን የጠበቀ የትምህርት ፖሊሲ ሳይቀርፁለት፣ ጤንነቱን የጠበቀና ዘላቂ ህልውናውን የሚጠቅም የሥራ ዕድል ሳይፈጥሩለት፣ የዴሞክራሲና የልማት አጀንዳዎችን ሳይዘረለጉ እንዲሁ እንደዋዛ ትላንት ወጣት የነበረው ክፍል ዛሬ በከንቱ ጎልማሳ እየሆነ ዘመን ዘመንን እየተካው መኖር የተለመደ ሆኗል። በዚህ በ21 ኛው ክፍለ ዘመን በአለም ውስጥ ካሉት አገራት እንደ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ሁሉንም አይነት ዕድል የተነፈጋቸው፤ ለመከራና ለስቃይ ብቻ የተጋለጡ አሳዛኝ ፍጥረቶች የሉም ብል ፈፅሞ ማጋነን አይሆንም። እንደ ኢትዮጵያ ወጣት ጦርነት የሚለበልበው፣ ርሃብ የሚጨርሰው፣ እስርና ግርፋት የበዛበት፣ አገሩን ጥሎ መሰደድ ያንገሸገሸው፤ የመማርና ስራ የማግኘት፤ የዜግነት መብቱ የተገፈፈበት፣ ለጭቆና እና ለተለያዩ አደጋዎች የተጋለጠ በዓለም ላይ አለ ለማለት አያስደፍርም።


ፋሽስቱ ወያኔ ወጣቱ ተፈጥሮአዊ አቅሙንና ለጋ አእምሮውን ተጠቅሞ ክብሩንና ሰብዓዊ መብቱን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ እንዳይችል፤ በአገዛዙ ላይ ሀሳቡን በነጻነት እንዳይገልጽ፤ በአገዛዙ እየደረሰበት ላለው ግፍና መከራ ተቃውሞውን እንዳያሰማ ለትንታኔ በማይመች ህገ አራዊት በመቆላለፍ እና ቅርቃር ውስጥ በማስገባት ከፍተኛ አደጋ ጋርጦበት ይገኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሽብርተኝነት ሕግ ተብየውን ከብዙ በጥቂቱ መመልከት በቂ ነው፡፡ ይህ በወጣቱ ላይ እየተሰራበት ያለውን ደባ የስርአቱን መሰሪ የጥፋት መንገድ የሚያጋልጡና ለአገራቸው የተሻለ ህልም አለን የሚሉ ወጣቶችን ጠልፎ ለመጣል የተዘጋጀ መሆኑ ለማንም ኢትዮጵያዊ ግልጽ ነው። እዚህ ላይ ማስረጃ መጥቀስ ካስፈለገ በቅርቡ የተከሰቱትን የዞን 9 ወጣት ጦማያንን፤ ወጣት ጋዜጠኞችንና ፖለቲከኞችን ህገ ወጥ እስር መመልከት በቂ ነው። ለሚያልሟት ነፃ፤ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንዲሁም ለራሳቸውና ለወገኖቻቸው ሰብዓዊ መብት መከበር ዘብ ስለቆሙ በአሸባሪው የወያኔ አገዛዝ ተወንጅለው ለእስር ተዳርገዋል። በእስር ቤትም የከፋ ሰቆቃና ቶርቸር እየተፈፀመባቸው ይገኛል። ይህ በወጣት ጦማርያኑ፤ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ላይ የተቃጣው ድርጊት አገዛዙ በወጣቱ ላይ የከፈተው የጥፋት ዘመቻ ከመሆኑም በላይ ስርዓቱ የሚያራምደው የላሸቀ የፖለቲካ ድምር ውጤት መሆኑ ግልፅ ነው።

ፋሽስቱ ወያኔ ‹‹መብቴ ተነካ፣ ጥቅሜ ተጓደለ፣ ነጻነቴ ተገፈፈ›› የሚሉትን ወጣቶች ሳያዳምጡ በማሰር፤ በመግልና በማሰደድ እንዲሁ ከማንኛውም አገራዊ የውይይት አጀንዳ ውጭ አድርገው የረሱትን ወጣት፤ በአገር ላይ ውጥረትና ግጭት ሲያይል፤ የአገር አንድነት ሲናጋና አገዛዙ መውጫ መግቢያ ሲጠፋው ብቻ ‹‹አገር ተረካቢ ወጣቱ፣ የአገር ተስፋ ወጣቱ፣ የአገር መከታ ወዘተ›› እያሉ በመሸምገል የወጣቱን ቀልብ ለመሳብና ርካሽ የፖለቲካ ድጋፍ ለማጋበስ ሲውተረተሩ ተመልክተናል። ይህ የአገዛዙ ቁማር እዚህ ጋ በቃ ተብሎ ሊገታና ሊቆም ይገባል። እንደሚታወቀው የአገራችን ወጣት አብይ ፍላጎቶች ነፃ፤ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ ተፈጥራ ማየት፤ ሰብአዊ መብትን የሚያከብር  ስርዓት በመፍጠር የተረጋጋ ሰላም ማግኘት፣ ጤናው የተጠበቀ ዜጋ ተፈጥሮ ማየት፤ መማር እውቀቱን ማስፋትና ለአገሩ እድገት አስተዋፅኦ ማበርከት፤ በተመረቀበትና በአለው ሙያ ስራ ማግኘትና ወገኑን ማገልገል የመሳሰሉት ከብዙ ጥቂቶቹ መሆናቸው በተያዩ ጊዜያቶች የተጠኑ ጥናቶች ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ በዚህ በወያኔ ክፉ የአገዛዝ ዘመን የኢትዮጵያ ወጣቶች እንደ አለመታደል ሆኖ በሁሉም ሁኔታ ፈተና ውስጥ ወድቀዋል። ሞትን፣ ራሃብን፣ ስደትን፣ መሃይምነትን፣ ጭቆና፤ ጦርነትን፣ የመብት ረገጣን እየኖሩበት ስለሆነ ጉዳቱን በሚገባ ጠንቅቀው ያውቁታል። ከዚህ የጭቆና፤ የድህነትና የግፍ አገዛዝ ለመላቀቅ ደግሞ የሞት ሽረት ትግሉ የወደቀው በወጣቱ ጫንቃ ላይ መሆኑ ግልጽ ነው። በርግጥ በየትም አገር ቢሆን የወጣቱ የወደፊት እድል ያለው በራሱ በወጣቱ እጅ ውስጥ ነው። በመሆኑም ወጣቱ የተሻለ ህይወት እንዲኖረው ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለአገርና ለጠቅላላው ማህበረሰብ ፍላጎት መሳካት፤ ለነፃነት፤ ለፍትህና ለእኩልነት በሚደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ላይ በተናጠል እንዲሁም በተደራጀ አካሄድ አቅም በመፍጠር ምላሽ መስጠትና በትግሉ ላይ የራሱን ታሪካዊ አሻራ ማሳረፍ ያለበት ሰአት አሁን ነው፡፡ የአገሬ ወጣት ሆይ አሁንም ደግሜ ላሳስብህ የምፈልገው ነገር ቢኖር አቅምህንና ጉልበትህን ተጠቅመህ እንደ ፈጣን ባቡር በመገስገስ ላይ ያለውን የነፃነት ትግል መቀላቀል ያለብህ ከየትኛው ጊዜ በላይ አሁን መሆኑን ነው።  ላለፉት 23 አመታት ፋሽስቱ ወያኔ በአንተና በአገርህ ላይ እያደረሰ ያለውን መራራ ውርደት ተሸክሞ መቆየት ጥሩ የህይወት አማራጭ እንዳልሆነ መቼም ላንተ አልነግርህም። ስለዚህ ዛሬ ነገ፤ ጨርቄን ማቄን ሳትል በመነሳት በተባበረ ክንድህ ጠላትህ የሆነውን የወያኔ አገዛዝ ከኢትዮጵያ ምድረ አስወግድ!!!

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!



No comments:

Post a Comment