Tuesday, March 4, 2014

አድዋ…. አድዋ…. አድዋ…. የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም

በቅዱስ ዬሃንስ

የካቲት ወር የአፍሪካውያን ወር ይባላል፡፡ ይህን ወር የአፍሪካውያን ወር ያሰኘው ብቸኛ ምክንያት የዓድዋ ድል ነው፡፡ ነጮች አፍሪካውያንን በግፍ በሚረግጡበት፣ በባርነት በሚገዙበት፣ ያሻቸውን ያለከልካይ በሚፈፅሙበት በዚያን ወቅት " እምቢኝ! ሀገሬን በቅኝ አላስገዛም " ብሎ በጀግንነት የተነሳ፣ ተነስቶም የቅኝ ገዢዎችን በትር በሀይል መስበር የተቻለበት ወር ይህ የካቲት ወር ነው፡፡  

የአውሮፓ ሀገራት አፍሪካን በተቀራመቱበት ዘመን ኢጣሊያም ኢትዮጲያን በቅኝ ግዛቷ ለማድረግ መንገድ የሚከፍትላትን የውጫሌ ውል ከአፄ ምኒልክ ጋር ውጫሌ ከተማ ላይ በተወካይዋ አንቶሌኒ መሰረት ተዋዋለች፡፡ ከተደረገው ውል አንቀፅ 17 ግን የአማርኛ እና የኢጣልያንኛ ትርጓሜው የተለያየ ነው፡፡ በአማርኛ የተፃፈው ‹‹ ግርማዊ የኢትዮጲያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮፓ መንግስታ ጋር ግንኙነት ለማድረግ ወይም ለመነጋገር ሲፈልጉ በግርማዊ የኢጣሊያ ንጉሥ አማካይነት ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡›› የሚል ሲሆን የኢጣሊያንኛው ትርጉም ግን እንዲህ የሚል ነበር….‹‹ ግርማዊ የኢትዮጲያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮፓ መንግስታት ጋር ግንኙነት ለማድረግ ወይም ለመነጋር ሲፈልጉ በግርማዊ የኢጣሊያ ንጉሥ አማካይነት ያደርጋሉ፡፡›› የዚህ ፍቺው ኢትዮጲያ በኢጣሊያ ሞግዚት አስተዳደር ስር መሆኗን የሚገልፅ ነው፡፡ ይህንንም የኢጣሊያ መንግስት ለአውሮፓ መንግስታት በደብዳቤ አሳውቋል፡፡  
ይህም በታወቀ ግዜ አንቀፅ 17 ይቅር በሚል አፄ ምኒልክ ከባለሟሎቻቸው ጋር ወሰኑ በዚህም ሌላ ውል ተፈረመ፡፡ ኮንት አንቶሌኒ ‹ይቅር› የሚለውን ቃል የተረዳው እንዳለ ይቀመጥ አይለወጥ በሚል ነበርና አለመሆኑን ሲረዳ ምኒልክ እልፍኝ ገብቶ ደነፋ፡፡ የኢጣሊያ መንግስት ይህን እንደውርደት ይቆጥራል፡፡ ክብሩን ለማስጠበቅ ጦርነት ያደርጋል፡፡ ክብሩን በጉልበት ያስጠብቃል ብሎ ፎከረ፡፡  

እቴጌ ጣይቱ እንዲህ አሉት… ‹‹የዛሬ ሳምንት አድርገው፡፡ እኔ ሴት ነኝ፡፡ ጦርነት አልወድም፤ ነገር ግን ሀገሬን እንደዚህ ያለ ክብር የሚነካ ዘለፋ ከምትሸከም ጦርነትን እመርጣለሁ፡፡ ሂድ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ! እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር አስጥቶ ደሙን ለሀገሩ ፍቅር አፍስሶ ለአፈሩ ክብር ለብሶ እሱ ወድቆ ሀገሩን የማያቆም እዚህ ያለ እንዳይመስልህ! ሂድ! የኢትዮጲያን ሰው ባታውቀው ነው፡፡ ለሀገሩ መሞት ማለት ለሀበሻ ጌጡ ነው፡፡ ሂድ ባሻህ ግዜ ተመለስ ተሰናድተን እንጠብቅሃለን፡፡ ያንተን ወንድነትና የጣይቱን ሴትነትም ያን ግዜ እናየዋለን ሂድ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ፡፡››


በዚህም የኢትዮጲያና የኢጣሊያ ወዳጅነት ጥያቄው፡ የጦርነቱ አይቀሬነትም ተረጋገጠ።  

የኢጣሊያ መንግስት በተወካዩ አማካይነት ኢትዮጲያ ላይ ጦርነት ሲያውጁ አፄ ምኒልክ የኢጣሊያ በጦር መሳሪያም ሆነ በስልጣኔ ከፍ ማለቱ ሳያሸብራቸው ‹‹ቴዎድሮስ በመቅደላ ዮሐንስ በመተማ የሞቱላትን ሀገር እኔም ደሜን አፍስሼ ነፃነቷን አስጠብቃለሁ፡፡ እሞትላታለሁ›› ብለው አዋጅ አወጁ…

‹‹….የሀገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም፤ አንተም አላስቀየምኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ዕርዳኝ፤ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ ለሚስትህ ለሃይማኖትህ ስትል በሐዘን ዕርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፤ አልተውህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም..ዘመቻዬ በጥቅምት ነው እና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ፡፡››  
         
አዋጁን ተከትሎ ህዝብ ከዳር አስከ ዳር ተመመ፡፡ እቴጌይቱ እንዳሉት ደረቱን ለጥይት እግሩን ለጠጠር ሰጥቶ ሀገሩን ከጠላት ሊታደግ የኢትዮጲያ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ነቅሎ ተነሳ፡፡

የሩቁንም ሀገር የጎጃሙንም፣ የደንቢያውንም፣ የቋራውንም፣ የበጌምድሩንም ከጨጨሆ በላይ ያለውን አገር ሁሉ አሸንጌ ድረስ ክተት ብለው አዘዙ፡፡ የሰሜንና የወልቃይት ጠገዴንም ሰው መቀሌ ድረስ ክተት ብለው አዘዙ፡፡ ከዚህ በኋላ ራስ መኮንን የሐረርጌን ጦር ይዘው በመስከረም እኩሌታ አዲስ አበባ ገቡ፡፡ ከጊቤ በታች ያለው አገር ጦር የወለጋው ሹም ፊታውራሪ ተክሌ ጦራቸውን ይዘው ገቡ፡፡ አፄ ምኒልክ አዋጃቸውን በመስከረም ወር ካስነገሩ በኋላ ለአገር ጥበቃ አጎታቸውን ራስ ዳርጌ ሣህለ ሥላሴን ሾመው እርሳቸው በጥቅምት 2 ቀን 1888 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ተነስተው በጊዳ በኩል አድርገው ጥቅምት 18 ቀን ወረይሉ ከተማ ገቡ፡፡  
ከዚያም ራስ ሚካኤልን፣ ራስ ወሌን፣ ራስ መኮንንን፣ ራስ መንገሻ አቲከምን፣ ራስ አሉላን፣ ዋግሹም ጓንጉልን፣ ደጃች ወልዴን፣ ፊታውራሪ ገበየሁን፣ ፊታውራሪ ተክሌን፣ ሊቀ መኳስ አድነውን፣ ቀኛዝማች ታፈሰን ‹‹ቀድማችሁ ወደ አላጌ ዝመቱ የሚቀላችሁ ከሆነ ወጉት፡፡ የሚከብዳችሁ ከሆነ ላኩብኝ ›› ብለው አስቀድመው መላካቸውን ይነገራል፡፡

ምን አልባትም ይህ አዋጅ ታውጆ የኢትዮጲያ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ተሞ አድዋ ላይ ጣሊያንን ድባቅ ባይመታ ኖሮ የኛ ዕጣ እንደሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት በባርነት ቀንበር ወድቀን በኛ ማምነት ላይ የኢጣሊያ ማንነት ተለጥፎብን እንቀር ነበር፡፡ ለዛም አይደል ‹‹ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ፡ ግብሩ እንቁላል ነበር ይሄን ግዜ ሐበሻ›› የተባለው፡፡  

የአድዋ ጦርነት የተጀመረው የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም ከማለዳው 11 ሰዓት ከ 32 ደቂቃ ላይ ነበር፡፡ የጄኔራል አልቤርቶኔ ክፍለ ጦር በፊታውራሪ ገበየሁ፣ በዋግሹም ጓንጉል፣ በራስ ሚካኤል እና በራስ መንገሻ ጦር ላይ በሰነዘረው ጥቃት ተከፈተ፡፡ የንጉሰ ነገስቱ ሠራዊት የመሐል ጦር አዛዥ ፊታውራሪ ገበየሁ በዚህ ከጣሊያኖች ጋር በተደረገው ጦርነት የተመሰከረለት ጀግና ነበር፡፡ ጎራዴውን መዞ በዋናው የትግል አውድማ ላይ ተወርውሮ ገባ፡፡ በዚህም ጊዜ በጠመንጃ ጥይት ተመትቶ ህይወቱ አለፈ፡፡

በገበየሁ መሞት ተሸብሮ የነበረው የኢትዮጵያ ወታደር ወድያው መልሶ ተረጋጋ፡፡ በታላቅ ቆራጥነት አልቤርቶኔን እንደገና ገጠመው፡፡ በ4 ሰዓት አከባቢ ላይ አልቤርቶኔ ከመኮንኖቹ አብዛኞቹን አጥቷል፡፡ በጦርነቱ እንደተሸነፈ ግልፅ ነበር፡፡ የኢጣሊያ ወታደሮች በድንጋጤ ተውጠው ፈረጠጡ፡፡ ከፊሉ ተማረከ፡ የቀረውም ወደ ሌሎቹ ክፍላተ ጦር በመሸሽ ራሱን አተረፈ፡፡ በዚህ ጊዜ ያልተነካው ክፍል የሚይዘውን አጥቶ ይተራመስ ገባ፡፡ በዚህ ሰዓት ቀጥታ በአጼ ምኒሊክ የሚታዘዘው ጦር ከውጊያው ገባ፡፡ በጦርነቱ ወቅት አጼ ምንሊክ በትክክል ወዴት እንደሚገኙ ጣልያኖች አያውቁም ነበር፡፡ ሁልጊዜ ሳይለዩት አብረውት ከሚገኙት ሁለት ሊቀመኳሶች አንዱ በአለባበሱ ንጉሱን መስሎ በስፍራው ይገኛል፡፡ ከሊቀመኳስ ተግባሮች ውስጥ አንዱ የጠላትን ትኩረት ወደ እሱ በመሳብ ንጉሰ ነገስቱን መጠበቅ ነው፡፡ በጦርነቱ ስፍራ አጼምኒሊክ እንደ አንድ ተራ ወታደር ለብሶ በጦርነቱ መሃከል ተገኝቶ ያዋጋም ይዋጋም ነበር፡፡

ቀኑን ሙሉ ውጊያ ሆኖ ከምሽቱ ዐስራ ሁለት ሰዓት ላይ ድሉ የኢትዮጲያ መሆኑ ታወቀ፡፡  
   
በአድዋው ጦርነት እቴጌ ጣይቱ ብጡል የኢትዮጵያን ጦር በሞራል በማነቃቃትና በማበረታት እንዲሁም ሠራዊቱን እግር በእግር እየተከተሉ በፉከራ ያበረታቱ ነበር፡፡ እቴጌ ጣይቱ ጥቁር ጥላ አስይዘው ዓይነ ርግባቸውን ገልጠው በእግር እየተራመዱ በንጉሠ ነገሥቱ ልጅ ወ/ሮ ዘውዲቱና በደንገጡሮቻቸው ታጅበው ከወታደሩ ጎን ተሰልፈው ነበር፡፡ የኋላው ወታደር ሲያመነታ ‹ በርታ ምን ሆነሃል ድሉ የእኛ ነውና በለው › ብለው ይናገራሉ፡፡ ወንድ ሴት ሲያበረታው መሸሽ አይሆንለትምና ሁሉም በወኔና በጀግንነት ወደፊት ገፋ፡፡ እቴጌይቱም በዚህ ቀን የሴትነት ባሕሪያቸውን ትተው እንደ ወንድ ወታደሮቻቸውን በቀኝና በግራ አሰልፈው ወደ ጦርነቱ ገቡ፡፡ መድፈኞቻቸውንም በቀኛቸው በኩል ጠምደው እየተኮሱ በመካከል የሚዋጋውን የጠላት ጦር ይቆሉት ጀመር፡፡  
በየካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም መላው የኢትዮጲያ ህዝብ በአፄ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ አጋፋሪነት በባዶ እግሩ አድዋ ዘምቶ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀውን የኢጣሊያ ጦር ድል አደረገ፡፡ይህም ኢትዮጲያን አንድ የማድረጉን ዘመቻ ቋጨው፡፡ ወደ ማዕከላዊ መንግስት ለመጠቃለል እምቢተኛ የነበሩት ገዥች ለሀገራቸው ክብር ከሚቃወሟቸው አፄ ምኒልክ ጎን ተሰልፈው ጠላትን ድባቅ መቱት፡፡ ይህም ያ ትውልድ በተሻለ መልኩ በጎሳና በሃይማኖት ሳይለያይ ስለ ሀገር ፍቅር ስለ ክብርና ስለ ነፃነት ስለ መብት ያወቀና የተረዳ መሆኑን አስረግጦ ያስረዳናል፡፡  

ዛሬስ?

አፍሪካዉያን በቅኝ ገዥዎች ሥር በነበሩት ጊዜ ነፃነትን አሻግረዉ እያዩ ነበር፡፡  ኢትዮጵያ ከቅኝ ግዛት ተፅዕኖ ነፃ ሃገር በመሆን ህዝቦቿ የነፃነትን አየር እንዳሻቸው የሚምጉ የአፍሪካ ብሎም የአለም ተምሳሌት ነበረች፡፡  አሁን ግን በወያኔ መራሹ ፀረ ኢትዮጵያ ቡድን ነፃነትን ተነፍጋ ነፃነት አይታ የማታዉቅ ይመስል ነፃነትን አማትራ እያየች የምትገኝ ምስኪን አገር ሁና ትታያለች፡፡ ህዝባችን አገር በቀል በሁኑ አሳማ መሪዎች ሥር ወድቀዉ ተነግሮ ለማያልቅ መከራ ተዳርገዋል፡፡ እነዚህን ሃገር በቀል ፋሽስቶች በአድዋ የታየውን የአንድነትና የድል አድራጊነት መንፈስ ተላብሰን ድባቅ በመምታት ህዝባችን ዳግም ታሪክ ፅፎ በመጭው ትውልድ የሚወደስበትን አሻራ ጥሎ እንደሚያልፍ ጥርጥር የለውም፡ የክተቱ ነጋሪትም የሚጐሰምበት ጊዜ ሩቅ አደለም።  


ልዩነቶቻችሁን ሁሉ ወደጎን ገፍታችሁ... ስለሰውነት ክብር፣ ስለሀገር ነፃነትና ሉዓላዊነት፥ ሕይወታችሁን አሳልፋችሁ የሰጣችሁ አባቶቻችንና እናቶቻችን፥ ክብር ለናንተ ይሁን!!!

2 comments: