በአርኣያ ጌታቸው
ኢሳት እንደ በርካታ የኢትዮጵያ ተቋሞች በበርካታ ችግሮችና ጉድለቶች ያሉበት መሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ አፍጥጦ እየወጣ ነው፡፡ የገንዘብ፣ የፕሮግራም ጥራት፣ የግልጽነት፣ የገለልተኝነት፣ …. በጣም በርካታ ችግሮች ይጠቀሳሉ በአብዛኛዎቹም እስማማለሁ፤ ይሄን እራሳቸው ኢሳቶችም የሚክዱት አይመስለኝም፡፡ ልዩነቱ ግን “እና ምን ይሁን?” የሚለው ላይ ነው? ኢሳት ችግሮች ስላሉበት ይጥፋ፤ ይዘጋ?
ምን ያህሎቻችንስ ለዚህ ሚዲያ ከመመስረት አንስቶ አሁን እስካለበት ሲደርስ ምን አስተዋጽኦ አድርገን ነው ለድክመቱ ብቻ እንደደመራ እንጨት ዙሪያውን ከበን ወደ ምስራቅ፤ ወደ ምዕራብ ሊወደቀ ነው እያልን የምንጠቋቆመው፡፡ አዎ ምንአልባት በዚህ ማህበራዊ ገጽ ዙሪያ የምንገናኝ ጥቂቶች ከኢሳት የተሻለ መረጃ እናገኝ ይሆናል፤ ከዚህም ሶሻል ሚዲያም ተጠቃሚዎች አብዛኛዎቹ በተለይ ፖለቲካ ነክ ሀሳቦችን የሚጦምሩ ከሀገር ውጭ የሚገኙ /ዲያስፖራ/ ናቸው ፡፡ የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን የእድሜ ፤ የአቅም እና የእውቀት ገደብ ሳያንበረክከው የሚከታተለው ሚዲያ ከነችግሩ ኢሳትን ነው፡፡ ኢሳትም ብቸኛ አማራጭ እየሆነ ያለውም ለዚህ ነው፡፡
የኢሳት መዳከምም ሆነ ውድቀት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ትልቅ አደጋ ይዞ ይመጣል፤ ፖለቲካውን አንድ እርምጃ ሳይሆን ሁለትና ሶስት እርምጃ ወደ ኋላ ይጎትተዋል ባይ ነኘ፤ ምንም አማራጭ ሚዲያ በሌለበት ብቸኛ የሆነውን ኢሳት ቆመን ውድቀቱን እና እድገቱን ከምንተነትን አቅም ያለው በገንዘቡ፤ እውቀት ያለው በእውቀቱ በመተባበር መለያችን ወደመሆን የተቃረበው የመክሸፍ እጣ ፈንታ በኢሳትም ላይ እንዳይደርስበት ሁላችንም ተረባርበን ኢሳትን ወደ ተሻለ ሚዲያ ልናሸጋግረው ይገባል፡፡
በተመሳሳይ የኢሳት ባልደረቦች እና ማናጅመንቶች የሚሰነዘርባቸውን ትችት እና ግሳጼ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ከማለፍ ነገሮችን በጥሞና በመመልከት እና ተገቢውን መልስ በመስጠት እና ማስተካካያዎችን በማድረግ ለኢሳት እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ቢያደርጉ መልካም ይሆናል፡፡
ኢሳት ‘አይነኬ’ ነው ማለት አይደለም በሚሰራቸው ስህተቶች ይወቀሳል፤ ይተቻል፤ ይከሰሳልም፡፡ የሁሉም መነሻ ሀሳብ ግን ለተቋሙ እድገት ከማሰብ እና ከመጨነቅ የመነጨ መሆን ይገባዋል፡፡ በሌላ ጎኑ እነዚህን ትችቶች ተቀብሎ ማስተናገድ እና መልስ መስጠት የማይችል ማናጅመት ከሆነ፤ በአንድ እጅ እንደ ማጨብጨብ ይሆናል፡፡ በዚህም መሰረት ኢሳትን ወደላይ በደንብ ከፍ ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን ይወጣ፡፡
ኢሳት የኢትዮጵያ ህዝብ አይን እና ጆሮ ነው!
No comments:
Post a Comment