Friday, March 7, 2014

እኔ «ይህ ትውልድ» ነኝ

እውነት ነው... እኔ «ያ ትውልድ» አይደለሁም፤ ይህ ትውልድ እንጂ፡፡ እኔ ያ በሌኒንና ማርክስ አስተምሮ ልቡ የሸፈተው ለውጥ የጠማው ትውልድ አባል አይደለሁም፡፡ በሌሎች አገራት ይደረግ የነበረው የለውጥ እንቅስቃሴ ትኩረቴን አልሳበውም፡፡ «መሬት ላ'ራሹ!» ብየ የንጉስ ዘውድ አልነቀነኩም፤ «ፋኖ ተሰማራ ፋኖ ተሰማራ...እንደ ሆችምኒ እንደ ቼጉቬራ»ን አልዘመርኩም፡፡ «ትምህርት ለድሃው ልጅ!» ብዬ ወገንተኝነቴን በአደባባይ አልገለጽኩም፡፡

እኔ ፊውዳሊዝምንና ኢምፔራሊዝምን ለመዋጋት እጃቸውን ከጨበጡት አይደለሁም፡፡ የመሳፍንታዊ ካባን አሽቀንጥሮ ለመጣል ድንጋይ አልወረወርኩም፤ መፈንቅለ-መንግስት አላደረኩም፤ አልሞከርኩምም፡፡ አውሮፕላንም አልጠለፍኩም፡፡ በራሪ ወረቀቶችን በድብቅና በህቡ አላዘጋጀሁም፤ አልበተንኩም፤ በበተኑት ላይም «እርምጃ» አልወሰድኩም፡፡

እኔ ጎፈሬየን ነቅሼ ትዊስት አልደነስኩም፤ ማሪጌና ቡጊ ቡጊ አልተጫወትኩም፡፡ ቅኔ ሞልቶ ተርፎኝ በውስጠ-ወይራ አገላለፅ ገዝዎቼን አልሸነቆጥኩም፡፡ እንደነ አሳምነው ገብረወልድ በሙያዬ የህዝብ ልሳን መሆን አልደፈርኩም፡፡ እንደ በዓሉ ግርማ የተባ ብዕሬን በድፍረትና በትክክለኛው ሰዓት ከወረቀት ጋር አላገናኜሁም፤ ፍህራቴን ገና አልፈራሁትም፡፡ ምክንያቱም እኔ «ያ ትውልድ» አይደለሁም፡፡

እኔ ያን የተማሪ አብዮት አልቀለበስኩም፡፡ የህዝብ አጀንዳ በጠብመንጃ አልነጠኩም፤ በፖለቲካና በሌሎች ምክንያቶች ጎራ ለይቼ አልተታኮስኩም፤ ነፍጥ አንግቼ ጫካና በረሃ አልወጣሁም፤ ቀይ ሽብር...ነጭ ሽብር አላካሄድኩም፡፡ አድሃሪ፣ ወንበዴ፣ ገንጣይ፣ አስገንጣይ አልተባባልኩም፡፡ «አብዮት ልጆን ትበላለች» አላልኩም፤ ግዳይ ጣልኩ ብዬ ለሬሳ የጥይት ዋጋ አላስከፈልኩም፡፡ «ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም!»ን አልፈከርኩም፤ የ«ኢትዮጵያ ትቅደም ጠላ… ይውደም!» ፈፃሚም አስፈፃሚም አልነበርኩም፤ አይደለሁምም፡፡


እኔ ይህ ትውልድ ነኝ!

አዎ ይህ ትውልድ ነኝ... በልጅ ልቦናዬ የአገሬ አንገት ሲቆረጥ ያየሁኝ፤ የኢትዮጵያ በር (ወደብ) ሲዘጋ የታዘብኩኝ፡፡ እኔ የዚህ ትውልድ አባል ነኝ (አይደለሁም ብልስ ምን ትርጉም አለው):: ዘሬ ተቆጥሮ፣ ባህሌ ተለይቶ የተነገረኝ፤ አንድነቴ ሳይሆን ልዩነቴ የተወሳልኝ፤ ታውቃለህ ሳይሆን እናውቅልሃለን፣ አንተ ሳይሆን እናንተ የተባልኩኝና በቡድን የተዳኜሁ በጅምላ የተፈረጅኩ ይህ ትውልድ ነኝ፡፡ እኔ የመቶ ዓመት ታሪክ አለህ የተባልኩኝና «በባለ ራዕዩ መሪ» «የአክሱም ሃውልት ለወላይታው ምኑ ነው» ሲባል «አሜን» ያልኩኝ ነኝ፡፡

አዎ ይህ ትውልድ ነኝ... ሰንደቅ አላማህ ጨርቅ ነው ብባልም የብዙ ሰንደቆች የብዙ የህዝብ መዝሙሮች ባለቤት የሆንኩኝ፡፡ እኔ ስራ ባጣ አደገኛ ቦዘኔ፣ ብጽፍ አሸባሪ፣ ስለ ዴሞክራሲ ብሰብክ የኒዮሊብራል አቀንቃኝ፣ ታሪኬን ባወሳ የድሮ ስርዓት ናፋቂ፣ ሃይማኖቴን ብል አክራሪ፣ መብቴን ብጠይቅ ፀረ-ልማትና ፀረ-ሰላም፣ ስለ አገሬ ብወያይ የጥፋተኞች ተላላኪ፣ ብደራጅ ተበተን፣ ብበተን ተደራጅ የተባልኩኝ የዚህ ትውልድ አባል ነኝ፡፡

እኔ አገሬን ትቼ በመሰደድ ለውሃ ውስጥ አውሬ ራት፣ ለበረሃ ሲሳይ፣ ለሽፍታ መጫወቻ፣ ለጠላት መሳለቂያ፣ ለአረብ መመጻደቂያ፣ ለወገኔ ማፈሪያ... የሆንኩ ወይም እንድሆን የተገፋሁ «የአዲሲ… ኢትዮጵያ» ይህ ትውልድ ነኝ፡፡ እኔ በአገሬ እየኖርኩ ለአገሬ ባይተዋር ነኝ፤ ከአገሬ በበለጠ ስለ አሜሪካና አውሮፓ አውቃለሁ ወይም በዚህ ሁኔታ ተቃኝቻለሁ፣ ሙዚቃው፣ ስፖርቱ፣ አለባበሱ ሁሉም ከውጭ ብቀበላቸው «አለቆቼ» ደስ ይሰኙብኛል፡፡ የአሜሪካን ዴሞክራሲ ግን በአገሬ መተግበር ቀርቶ መመኜት በፀረ ምናምን ያስፈርጄኛል፤ በዜግነቴ ማግኜት ያለብኝን ነገሮች ብጠይቅ ኪራይ ሰብሳቢ ያስብለኛል፡፡ እናም እኔ ይህ ነኝ... ይህ ትውልድ!

እኔ የ«ያ ትውልድ» ድብት የተጫነኝ፤ የራሴን መንገድ እንዳልፈልግ በ«ቂመኛ» የፖለቲካ «አባቶቼ» መዳፍ የገባሁ የሽግግር ወቅት ትውልድ ነኝ፡፡ ይባስ ብሎ እድሜየን በአንድ የአገዛዝ ስርዓት ያለምንም አማራጭ ወይም የፖለቲካ ለውጥ የምገፋ፤ ከራሴ ራዕይና ከራሴ መንገድ ይልቅ በተቀደደልህ ቦይ ብቻ ፍሰስ የተባልኩ «ስልብ» መሳይ ወኔ ቢስ ነኝ፤ ወይም አድርገውኛል፡፡

እኔ የኑሮ ውድነት የእግር እሳት የሆነብኝ... የኔ ብቻ የሆነውን ጤፍ በሁለት ሺህ ብር የምሸምት፣ ጥሬ ስጋ ማየት እንጂ ለመግዛትና ለመመገብ አቅሜ ያልፈቀደልኝ፣ በአንድ ሺህ ብር ደመወዝ የአስር ሺህ ብር የኑሮ ተመን የወጣልኝ፣ ስለ ፈጠራና ስለ ግኝት ሳይሆን ስለ ቀን ዳቦዬ የማስብና የምለፋ ይህ ትውልድ ነኝ፡፡ የ«ኢኮኖሚ እድገቱን» በዜና እንጂ በአካል ያላገኜሁት፣ የከተማየ ጎዳናዎች በኔቢጤ ተሞልተው ዘወትር እንቅልፍ የሚነሳኝ፣ እራሴን ትቼ የጥቂት ባለ ሀብቶችና ፖለቲከኞች ንብረት የሆንኩ እስኪመስለኝ በነሱ ፍቃድ ብቻ ቀለቤ የሚሰፈርልኝ፣ መጠለያ ቤት ብርቅ የሆነብኝ... የዚህ ትውልድ አባል ነኝ፡፡

ሀገሬን በቴክኖሎጅ ከፍ ወዳለ ደረጃ አደርሳለሁ ብየ ዲግሪየን ጭኜ ከዩኒቨርሲቲ ስወጣ ዶሮ አርቢ ወይም ድንጋይ ጠራቢ የሆንኩ እኔኮ ነኝ... ይህ ትውልድ፡፡ ጥበቤን ነጥቀው ባዶ ፖለቲካ የሚሸጡልኝ «ደንበኞች» የበዙልኝ፣ በአጀንዳ ጋጋታ ትኩረቴን የተነጠኩኝ፣ የፈረንጅ ቲወሪ ቤተ-ሙከራ፣ ያረጀ ያፈጀ አስተሳሰብ ማራገፊያ ያደረጉኝ... እኔ ነኝ፡፡

የረጅም ጊዜ ክብሬን ያዋርዱብኝ፣ ቅርሴን ያረከሱብኝ፣ ያለፈ ማንነቴን ደምስሰው የራሳቸውን የጫኑብኝ እኔኮ... እኔ ነኝ፡፡ በአገሬ እየኖርኩኝ «ውጣ... ሂድ ወደ አገርህ ግባ» የተባልኩኝ የአገሬ ሁለተኛ ዜጋ እኔ ይህ ትውልድ ነኝ፡፡ እኔ ጀግናዎቼን ያጣጣሉብኝ፤ «ኩሊ ጀግኖች» የከበቡኝ፤ «ሙሰኞችን ያከበርኩኝ»፤ አስመሳዮችን የሾምኩኝ፤ ሳልመርጥ የመረጥኩኝ፤ ሳልደግፍ የደገፍኩኝ ወላዋይ መሳይ ነኝ፡፡ ይባስ ብሎ ዓለም ያወቀውን ፀሐይ የሞቀውን የጨፍጫፊውን ፋሽስት ግራዚያኒ ማስታወሻ ሐውልት መሰራት በተመለከተ ተቃውሞየን ማሰማት የተከለከልኩኝ በተቃራኒው አምባገነን መሪዎቼ በሚጠሩት ማነኛውም የ«ድጋፍ ሰልፍ» ቀድሜ የምሰለፍ «ልማት ወዳዱና ዴሞክራሲያዊው» ይህ ትውልድ ነኝ፡፡

በታሪኬና በማንነቴ ኮርቼ አገር ወዳድ ብሆን እንደ ጨፍላቂ የምቆጠር፤ የአገሬ ውርደትና መደፈር ቢያስቆጨኝና መቆርቆሬን ብገልፅ በፀረ-ኢንቨስትመንት የምፈረጅና አንድነት እንዳይኖረኝ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በጎጥ፣ በጎሳ፣ በታሪክና በመሳሰሉት እንደፈለጉ የሰነጣጠቁኝና በራሴ ጉዳይ የውጭ ተመልካች እንድሆን የተፈረደብኝ የዚህ ትውልድ አባል ነኝ፡፡ እኔ ከኢትዮጵያዊነት ስሜት ይልቅ የጎሳ ስሜትና መንፈስ ገንኖ ኢትዮጵያዊነት ቀስ በቀስ እንዲከስም በሚደረገው ጥረት «ኢንቨስት» እየተደረገብኝ ያለሁ ይህ ትውልድ ነኝ፡፡

ለስራ ፍለጋ በዕየለቱ ማስታወቂያ ቦርድ ፊት ለፊት የማፈጥ፣ በስራየ ዋስትና የሌለኝ የ«አባሎች» አጃቢ ነኝ፡፡ ቢፒር፣ ቢኤስሲ፣ ካይዘን፣ አንድ ለአምስት አደረጃጀት፣ ውጤት ተኮር ትግበራ፣ የልማት ሰራዊት ግንባታ ገለመሌ እየተባልኩ ወጥ ባልሆነ ሰሞንኛ የውጭ አሰራር ኩረጃ የምጣደፍ የዚህ ትውልድ አባል ነኝ፡፡ ምን ይሄ ብቻ... ውሃ ማቆርን፣ የጠብታ ውሃ «ቴክኖሎጅ» አጠቃቀምን፣ ጤፍ በመስመር መዝራትንና የመሳሰሉት የግብርና ምርት ማሳደጊያ «ምርጥ ተሞክሮዎችን» በተግባር ያዋልኩኝ «ምርጡ ኮራጅ» ወይም ኮራጆች ያሉኝ ይህ ትውልድ እኔኮ ነኝ፡፡

በገመድ አልባ ስልክ ወይም ሞባይል የተነጋገርኩ፤ በፌስቡክና ቲውተር ማህበራዊ ድህረ-ገጾች ፊደል የምከትብ፤ ሙዚቃን በዩቲዩብ የማዳምጥና የምጭን እኔ ይህ ትውልድ ነኝ፡፡ በሌላ በኩል ዛሬም ድረስ ኮምፒውተር ብርቅ የሆነብኝ፤ ከመቶ ዓመት በፊት ወደ አገሬ የገባን የባቡር ትራንስፖርት እንደ አዲስ ዛሬ ላይ የምናፍቅ፤ እኔኮ እኔ ነኝ፡፡

እኔ ሱሪየን ዝቅ አድርጌ የምታጠቅ፤ ቀሚስ ለምኔ ብየ ከወንድ አቻዎቼ እኩል ሱሪ ያጠለኩ፤ በዊግ ፀጉር የተሽሞነሞንኩ፤ ትንባሆ በአደባባይ የምምግ፤ በታይትና አጭር አለባበሴ «የምዘንጥ» የጨስኩ «አራዳ» ይህ ትውልድ ነኝ፡፡ በትምህርት ቤቴ የ«ከለር ዴይ፣ ከልቸር ዴይ፣ ክሬዚ ዴይ...»ን በማዘጋጀትና በመቀወጥ የምታወቅ፤ በማሪዮ ባላቶሊና በሊዊስ ናኒ የፀጉር «ስታይል» የተዋብኩኝ ምርጥ «የፋሽን» ተከታይ የዚህ ትውልድ አባል ነኝ፡፡

የእነ ጄዚ፣ ቢዮንሴ፣ ኤምነም፣ ማዶና፣ ሪሃና፣ ክሪስ ብራውን ወዘተ አለባበስ፣ አመጋገብ፣ አረማመድ፣ አነጋገር... የሚያስጨንቀኝ እኔ ይህ ትውልድ ነኝ፡፡ እኔ የሌዮኔል መሲ የቁመት ማጠር ያሳሰበኝ፤ የክርስቲያኖ ሮናልዶ የፍቅር ግንኙነት ያስፈነጠዘኝ፤ የአርሴናል ለረጅም ጊዜ ከዋንጫ መራቅ ያስተከዘኝ፤ ሁለቱ የጀርመን ክለቦች ለአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ መድረስ ያስደመመኝ ይህ ትውልድ ነኝ፡፡ ምን ይሄ ብቻ... የሴስክ ፋብሪጋስን የማሊያ ቁጥር በክንዴ የተነቀስኩ «ታማኝ» ደጋፊምኮ እኔ ነኝ፡፡

ሲኒማ ቤት ገብቼ የማያስቀው የሚያስቀኝ፣ የሚያስቀው የሚያስተክዘኝ፤ የሰዎች ህመም የማይሰማኝ፣ ሃዘናቸው የማያሳዝነኝ፣ ጉዳታቸው የማይታየኝ መበደል አዲስ ያልሆነብኝ ትከሻ ደንዳና እኔ ይህ ትውልድ ነኝ፡፡ እኔ ስሜን በትክክል ሳልጽፍ ለብሄራዊ ፈተና የምቀመጥና ዩኒቨርሲቲ የምበጥስ፣ የመመረቂያ ጥናቴን ገንዘብ ከፍየ የማሰራ «ሙድ የጫርኩ» ታታሪው «የውጤታማውና ትክክለኛው የትምህርት ፖሊሲ» ውጤት ነኝ፡፡

ሰርቼ በማገኘው ገቢ ቤት መስራት፣ ትዳርና ቤተሰብ መመስረት፣ ወላጆቼንና ወንድም እህቶቼን ማገዝ ተራራ እንደ መግፋት የከበደኝ እኔኮ የዚህ ትውልድ አባል ነኝ! ከደመወዜ ተርፎኝ የማነበው መጽሐፍ መግዛት የማልችል፣ መዝናናት የራቀኝ፣ አካባቢየንና አገሬን መጎብኘት ቅንጦት የሆነብኝ ተስፋ የራቀኝ ይህ ትውልድ ነኝ፡፡

እኔ ዘወትር ለታክሲ የምጋፋ፤ ለዳቦ ወረፋ የምሰለፍ፤ ለስንዴና ዘይት ቀበሌ የማጨናንቅ፣ አገልግሎት ለማግኜትና ጉዳይ ለማስፈጸም የባለስልጣናትን ደጅ የምጠና ይህ ትውልድ ነኝ፡፡ ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ የ«መንግስቴ የመተካካት» አሰራር ድራማ የሚያዝናናኝ የውጭ ተመልካች እኔ ነኝ፡፡ እኔኮ «አኬልዳማ»፣ «ጅሃዳዊ ሃረካት»፣ «አዲስ አበባን እንደ ባግዳድ» እና የመሳሰሉ «ምርጥ ፊልሞችን» በአገሬ ቲቪ የኮመኮምኩኝ «እድለኛ» ትውልድ ነኝ፡፡

እኔ ጋኖቼን አርክሼ ምንቼቶችን ጋን ያደረኩኝ፤ ግፈኞች የከበቡኝ፣ ሙሰኞች የጀገኑብኝ፣ አርዓያ የምለው ሰው የሌለኝ ይህ ትውልድ ነኝ፡፡ በውሸት የአገር ዳግም ውልደት ወይም «ህዳሴ» መፈክር ያደነቆሩኝ፤ በውሸት ዴሞክራሲ የሚነገድብኝ፣ በይስሙላህ ጥበብ የሸነገሉኝ፣ ጥራዝ ነጠቆች የሚሳለቁብኝ ይህ ትውልድ ነኝ፡፡

እኔ በድህነቴ ምክንያት በውሎ አበል ጥማት በየስብሰባው ጆሮ የሚያገማ ፕሮፖጋንዳ ስጋትና ስጠጣ የምውልና በጆሮ ጠቢዎችና ደህንነቶች ዘወትር «የምጠበቅ» ይህ ትውልድ ነኝ፡፡ በአጠቃላይ እኔ በሞራልም፣ በመንፈስም፣ በአካልም የቁልቁለት ጉዞ በማዝገም ላይ ያለሁ የዚህ ትውልድ አባል ነኝ፡፡
ግን... ግን... እኔ እነዚህን ሁሉ ነገሮች የማስተካከል ሃላፊነት ያለብኝ ይህ ትውልድ ነኝ! ተስፋዬም እጣ ፈንታዬም አገሬ ብቻ ስለሆነች በአገሬ ለውጥን አመጣለሁ፡፡ እንደ ትውልድ የሚታወስ ነገር አበረክታለሁ፡፡ ባለውለታዎቼንም ዳግም እዘክራለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment