በቅዱስ ዮሃንስ
ኢትዮጵያ ሀገራችን ረጅም የህላዌ ዘመንና የመንግሥትነት ታሪክ ካላቸው ጥቂት አገሮች አንዷ በመሆን ትታወቃለች፡፡ በሌላ ወገን መንግሥታት ወይንም ገዢዎች በህዝብ ላይ አሠቃቂ የጭቆናና የአፈና ሥርዓት በመዘርጋት ሕዝቡ ሁለንተናዊ ክብሩን ተገፎ የሚኖርባት አገር በመሆንም ትታወቃለች፡፡ ጭቆናውን እጅግ የከፋ የሚያደርገው ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ የነፃነቱ፣ የሀገሩ እና የመብቱ ባለቤት ለመሆን ካደረገው ረጅምና እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ከእለት ወደ እለት እየከፋ በሚሄድ የጭቆና ሥርዓት ውስጥ እየማቀቀ መገኘቱ ነው፡፡ በተለይም በአለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን የነፃነትና የእኩልነት ጉዳይ የሁሉም ሰብአዊ መብቶች፣ ልማት ሁሉን አቀፍ እሴቶች ማዕከላዊ አጀንዳ በሆኑበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ግን አሁን በአለም ላይ ከሚገኙ ለሰብአዊ ክብር፣ ለሀገር ሉዓላዊነትና እድገት ቁብ ከማይሰጡ ጥቂት አምባገነን መንግሥታት በአንደኛው በህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሓት)መዳፍ ውስጥ ትገኛለች፡፡
የአለፉት 23 አመታት መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በአንድ በኩል በደርግ አምባገነናዊ መንግሥት ከደረሰበት ሠፊ አፈና እፎይ ለማለት ከፍተኛ ጉጉት ያደረበት፣ በሌላ ወገን ደግሞ የህወሓት ወያኔ የማያባራ የማማለያ ፕሮፓጋንዳ እውነት ይሆናል ብሎ በመገመት የነፃነት ንጋት በኢትዮጵያ ምድር ላይ ሲበራ ለማየትና የአለፉትን ክፉ ዓመታት ለመርሳት በዝግጅት ላይ ነበር፡፡ ይሁን እንጅ የሆነው ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ ያለፉት ክፉ የጭቆና ዓመታት በሌላ የከፋ ጭቆናና ክፉ ዓመታት ተተኩ፡፡ ዘመነ ወያኔ ከታሪካዊ ክፋት ሁሉ የከፋ የክፉ-ክፉ ዘመን ነው። የነጻነት ብርሀን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የደበዘዘበት ዘመን ነው። የአገሪቱ ሉዓላዊነት ከመቼውም በበለጠ አደጋ ላይ የወደቀበት ዘመን ነው። ሕዝባችን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የድኅነት አርንቋ ውስጥ የተዘፈቀበት፣ ከሥቃዩ ማምለጫ ጠፍቶት የሚዋዥቅበት፣ አበሳውን ያየበት፣ ተስፋ የቆረጠበት ዘመን ነው። ሕዝባችን በደዌ የተመረዘበት፣ ሕይወት የረከሰበት ዘመን ነው። ዘመኑ፣ ዘመነ አበሳ ነው። የወያኔ ዘመን “ዘመነ ጨለማ” ነው። ይኸንን ሃቅ ሆዱ ልቦናውን ያልደፈነበት፣ ጥቅም የህሊና ዓይኑን ያላሳወረበት ኢትዮጵያዊ ሁሉ በግልጽ እያየ በቁጭት ቆሽቱ ይደብናል። ግን ከዚህ ሁሉ በደል ጋር ተስማምቶ እንዴት መኖር ይቻላል? ወይንስ ስለ እውነት በደል ይለመዳልን?
ፋሽስቱ ወያኔ አዲስ አባባን ከተቆጣጠራት ጊዜ ጀምሮ ድኅነት ድባቡን በአገሪቱ ዘርግቶባታል። ሕዝባችን ከምን ጊዜውም የበለጠ ተርቧል፣ ተጠማቷል፣ ታረዟል፣ ደኽይቷል! እርስብርስ አናቁረውት አነካክሰውታል፣ አበጣብጠውታል። ሰላሙን ነስተውታል። ሕዝባችንን ከፋፍለውት እያፋጁት ነው። የአምልኮ ቦታዎች ሳይቀሩ፣ በዘረኞች የወያኔ ካድሬዎች ቁጥጥር ሥር ውለዋል። አገራችን ላይ የፋሽስቱ ወያኔ ዘረኞች ነገሡ። ከሀዲዎች ፈነጩባት። ብሔራዊ ውርደትን አከናነቧት። ወያኔዎች የአገራችንን ለም የእርሻ መሬቶች ሸንሽነው፣ ባለርስቶቹን ከቄያቸው መንግለው ለባዕድ ቱጃሮች ቸብችበዋል። ሕዝቡን በወረዳና በቀበሌ ከፋፍለው ከመቆጣጠር አልፈው፣ በጎጥ ታች ድረስ ወርደው አንድ ለአምስት የሚባል የመቆጣጠሪያ ሕዋስ ፈጥረዋል። በዚህ ክትትል መሠረት፣ ማንም ዜጋ፣ ለምሳሌ ገብሬ፣ ከተወሰነለት ሁኔታ የማፈንገጥ ምልክት ካሳየ፣ ለዘር ብድር ከባንክ አያገኝም፣ ማዳበሪያ በብድር አይሸጥለትም፣ ከውጭ በልመና የመጣውን የዕርዳታ እህል እንኳን አያገኝም። እናት ኢትዮጵያ ለጠላቶቿ ተመቻችታ፣ ደረቷን ለሞት እንደትገልጥ ተገዳለች! ምነው ታዲያ ይኸ ሁሉ ግፍ ሲፈጸምበት ጀግናውና ቆራጡ ሕዝባችን ግፍን ለመከላከል ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲህ ወኔ ራቀው?
እብሪተኞቹ ወያኔዎች፣ የአገራችንን ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ ዘርፈው ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ እንዲሁ የሕዝባችንን ሕልውና ተቆጣጥረውታል። ኑሮውን፣ ውሎውን አዳሩን ሙሉ በሙሉ አንቀው ይዘውታል። ድምጽ እንዳያሰማ ጎሮሮውን አንቀውታል። እንዳይሰማ ጆሮውን ድፍነውበታል። በአገር ቤት፣ ነጻ ሬዲዮ የለም ቢባል ይሻላል! ነጻ ቴሌቪዢንማ ከቶ ማን አስቦት! ነጻ ጋዜጣን ድራሹን አጥፍተውታል! የተመጣጠን ዕውነተኛ መረጃ ከውጭ ለሕዝባችን እንዳይደርሰው ብዙ ሚሊዮን ዶላሮችን እያፈሰሰ ተግቶ የሚሰራው ፋሽስቱ ወያኔ፣ ኢሳት ቴሌቪዥንን፣ ሳተላየት እንዴት ማፈን እንደሚቻል የአፋኝ ቴክኖሎጂ መለማመጃ አድርጎታል። ዛሬ ሕዝባችን መጮህ ቀርቶ ከውጭ የምንጮለትን እንኳን እንዳይሰማ ምንም ዓይነት መረጃ እንዳይደርሰው ቀፍድደው ይዘውታል። እንዳይዘዋውር፣ እግሮችን ጠፍረው አስረውታል። በአገሩ እንደድሮው ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ አርሶ አምርቶ፣ ነግዶ አትርፎ እንዳይበላ ከልክለውታል። ግን ግን ከዚህ ሁሉ በደል ጋር ተስማምቶ እንዴትስ ይኖራ?
ፋሽስቱ ወያኔ በአሁኑ ጊዜ የአገሪቱን ሃብት ለአገዛዙ ታማኝ ለሆኑና ከአንድ ጎሳና ከተለጣፊ ድርጅቶች በተሰባሰቡ ግለሰቦች ቁጥጥር ሥር እንዲሆን አድርጓል። በአገዛዙ የተዛባ የኢኮኖሚ ፓሊሲ ግድፈትና የአቅርቦትና ስርጭት ችግር በንግዱ ሕብረተሰብ እንደተፈጠረ ተደርጎ የንግድ ህብረተሰብ አባላትን በማዋከብ ምክንያት ፈጥሮ በማሰርና ንብረታቸዉንም በመዝረፍ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸዉ ሥር እያደረጉ ይገኛሉ። በወያኔ የወንጀል ምርመራ፣ የወህኒና የእሥር ቤቶች አስተዳደር እና የፓሊስ፣ የፌደራልና የደህንነት ባልደረባ የሆኑ የአገዛዙ ገራፊዎች በግፍ ባሰሩዋቸዉ ወገኖቻቸዉ ላይ የሚፈጽሙባቸዉ ሰቆቃን በተመለከተ በየጊዜው የሚወጡትን አለማቀፍ ሪፖርቶች ያነበበ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ህዝባችን በወያኔ አገዛዝ አንድም ቀን መቆየት እንደሌለበት አመላካች ነዉ። ዛሬ በኢትዮጵያ ዉስጥ የእስረኛዉ ብዛት ደርግ ከፍተኛ ግፍ ሲፈጽምበት ከነበረበት ከ1969 እስከ 1970 ከቆየዉ ዋናዉ የቀይ ሽብር ዘመን ጋር ሲነጻጸር በትንሹ ከ50 እጥፍ በላይ አድጓል። ይህን የወያኔ አገዛዝ የግፍ መጠን ህዝባችን ሊሸከም የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን በግልጽ የሚያሳይ ነዉ።
በርግጥ በህዝባችን ትክሻ ላይ ተጭኖ ያለዉን የወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ለመንቀል በምኞት ሳይሆን በትግል መሆን እንዳለበት በመረዳት፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ለትግል የተንቀሳቀሱ የፓለቲካ ድርጅቶችን ጥሪ በመመለስ የትግሉ ተሳታፊ በመሆን ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሉአል፣ አሁንም እየከፈለ ይገኛል። በምርጫ 1997 የኢትዮጵያ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ለአስራ ዘጠኝ ዓመታት በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ስም በጉልበት የተጫነበትን የወያኔ አገዛዝ ለማስወገድ ተንቀሳቅሶ ለዘላቂ ሰላም፣ ለዲሞክራሲ፣ ለእድገትና ለእኩልነት ለቆሙ ዲሞክራሲያዊ የህዝብ ልጆች አመኔታዉን ሰጥቶ እንደነበር የአጭር ጊዜ ትዝታ ነዉ። የኢትዮጵያ ህዝብ በረጅም ዘመን ታሪኩ የፍርሃትን ሰንሰለት በጥሶ በመብቱ የቀለደ፣ በማንነቱ ያሾፉትንና በጭንቀቱ የተሳለቁትን በምርጫ ሳጥን ነበር የቀጣቸው። በመሳሪያ ሃይል በህዝብ ተከሻ ላይ መቆየት የወሰነዉ የፋሽስቱ ወያኔ አገዛዝ ግን የህዝብ ድምጽን በመቀማት የፓለቲካ መሪዎችን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን፣ የነፃዉ ጋዜጣ ባልደረባዎችን፣ በብዙ ሽህ የሚቆጠሩትን ገበሬዎች፣ ነጋዴዎች፣ ሠራተኞችን፣ አስተማሪዎች፣ ተማሪዎችን እንዲሁም የእድሜ ባለጸጋ የሆኑትን ሽማግሌ አረጋዊያንን በማሰር፤ ለድምጻቸዉ የጮሁትን የህዝብ ልጆች በዓደባባይ በግፍ በመግደል በድፍን ኢትዮጵያዊ ላይ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል።
በመጨረሻም የወያኔን ግፈኛ አገዛዝና በህዝቡ ላይ እያደረሰ ያለዉን መዘርዘር የዚህች መጣጥፌ አብይ ዓላማ አይደለም፤ ለምን ቢባል ለቀባሪዉ አረዱት እንዳይሆን ነው። መልዕክቴ ይህ ሁለ ግፍና መከራ በህዝባችን ላይ እየደረሰበትና የግፎ ጽዋ ሞልቶ መፍሰስ ከጀመረ ሰንበት ቢልም፣ ትግል ያለ ትብብር የትም ሊደርስ አይችልምና የተጀመረው ህዝባዊ እንቅስቃሴዉ ተጠናክሮ የፋሽስቱ ወያኔን አገዛዝ ከህዝብ ትከሻ ላይ ለማዉረድ የሚያስችል አቅም ላይ ይደርስ ዘንድ የሁላችንንም ተነሳሽነትና ምላሽ ስለሚጠይቅ ዝግጁ በመሆን አጋርነታችንን በቁርጠኝነት ማሳየት ይኖርብናል። ይህንን ማድረግ ስንችል ነው ሠርተን የምንኖርባት፣ ወልደን የምንስምባት፣ አንዱ በይ አንዱ ተመልካች ያልሆነባትን የጋራ ቤት የሆነችዉን ኢትዮጵያን መፍጠር የምንችለው። በዲሞክራሲ ያበበች፣ በኢኮኖሚ የበለጸገች፣ በዓለም የተከበረች የኢትዮጵያን ትንሳዔን እዉን ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንነሳ ወገናዊ ጥሪየን አቀርባለሁ።
ድል ለጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ!
No comments:
Post a Comment