ታሪኩ አባዳማ
ከ1990ዎቹ የቀዝቃዛ ጦርነት ፍፃሜ ወዲህ የአምባገነኖች ባህሪ እንኳ ተለውጦ እንደ አዲሱ ዘመን ሁሉ እነሱም ስልጣን ላይ የተቀመጡት በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ያውም በህዝብ ፈቃድ መሆኑን ለማሳየት ተግተው እየሰሩ ነው። በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ይታይ እንደነበረው አይነት ሁሉን ነገር በይፋ ጨፈላልቆ በማን አለብኝነት በብቸኛ ፓርቲ ስልጣን ላይ መቀመጥ የሌጅትመሲ ጥያቄ ከማስነሳቱም በላይ አስተማማኝ እንዳልሆነ ጠንቅቀው ተገንዝበዋል። በመሆኑም ጨካኝ አምባገነኖች ሳይቀሩ ምርጫ ሲጠሩ ፣ መድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርዓት መፈጠሩንም ሲሰብኩ ማየት እና መስማት እየተለመደ ነው። ለምርጫው ሂደት ፣ ለውድድሩ ድራማ ብሎም ለማይቀረው የመጨረሻ ውጤት አዋጅ የተቀነባበረ አሰራር ቀይሰዋል።
የምዕራቡ እና ምስራቁ ዓለም ፍጥጫ በረድ ብሎ የፖለቲካው አየር የሚነፍስበት አቀጣጫ ሲቀየር ከወጀቡ ጋር ተቀላቅሎ ከማዝገም ሌላ አማራጭ አልተገኘም። ስለሆነም ከዲሞክራሲያዊ ባህሪያት አንዱ የሆነውን ምርጫ የተቀበሉ ስልጡኖች መሆናቸውን ለለጋሽ የምዕራቡ ዓለም ለማሳየት ደፋ ቀና ብለዋል። ህዝባቸው እንደሚወዳቸው ፣ እንደሚመካባቸው እንደሚመርጣቸውም ደጋግመው ያስተጋባሉ።
አሸነፍን ያሉቱ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ ወንበር በተቆጣጠሩበት ፓርላማ ባንድ ጀምበር ህግ አርቅቀው ያውጃሉ ፣ ህጉን ራሳቸው ይፈፅሙታል ወይንም ይጥሱታል… ተሸነፉ የተባሉት ፀባይ አሳምረው ፣ አንገት ደፍተው ካልተቀመጡ ህገ ረቂቅ ይፃፍባቸዋል… አሸባሪ ተብለው ወህኒ ይጋዛሉ… ስለዚህ አምባገነኖች ምርጫ ለመጥራት አይፈሩም ፣ አያፍሩም… እንደሚያሸንፉም አይጠራጠሩም። ምክንያቱም ድል የሚታወጀው በብቸኛው መገናኛ በራሳቸው ራዲዮና ቲቪ ነውና!!
የኢንዶኔዢያው ሱሀርቶ ፣ የዛምቢያው ካውንዳ ፣ የኬንያው ሞይ ዓለም አቀፍ ፖለቲካው ባሳደረው ግፊት ምርጫ ጠርተው ተሸንፈው ስልጣናቸውን ለተመረጡ ዜጎች አስረክበዋል ፤ የግብፁ ሙባረክ እና የቡርኪና ፋሶው ካምፓዎሬ ምርጫ መጥራት ማለት ማሸነፍ ሆኖ ስላገኙት ያለገደብ ስልጣን ላይ ለመቀመጥ የሚያስችል ህግ ከልሶ ለማርቀቅ ሲሰናዱ ህዝብ በቃ ብሎ በቁጣ አስወግዷቸዋል ፣ የዙምባቤው ሙጋቤ የዩጋንዳው ሙሰቬኒ እና ሩዋንዳው ካጋሜ ዛሬም ምርጫ እየጠሩ ተፎካካሪያቸውን በብረት እያደቀቁ በስልጣን ላይ ናቸው – ምርጫ ሳይተጓጎል በየዓምስት አመቱ ሲጠሩ ውነትም ዲሞክረሲ የሰፈነ ይመስላል።የአይቮሪኮስቱ ሎሬት ባግቦ እና የኛዎቹ ወያኔዎች ምርጫ መጥራት ባይታክቱም ተወዳዳሪን በምርጫ ሳጥን ብቻ ሳይሆን በሬሳ ሳጥን መሸኘት ላይ የተካኑ ሆነው ተገኝተዋል።
እነኝህ ሁሉ የድህረ ቀዝቃዛ ጦርነት ዘመን ወጀብ የሚቀዝፉበትን አቅጣጫ እንዲሞርዱ ካስገደዳቸው መካከል ናቸው። ሁሉም በገዛ ህዝባቸው ላይ ሰቆቃ የፈፀሙ ፤ የዘረጉት መንግስታዊ መዋቅር በዘር እና አድልዎ ላይ የተገነባ ፤ ሙስና እስከ አንገታቸው የዋጣቸው ፣ ስልጣንን አላንዳች ተጠያቂነት በመዳፋቸው ጨምድደው ለመዝለቅ ቅንጣት የማያመነቱ ገዢዎች መሆናቸውን ህዝባቸው ፣ አለምም ይመሰክራል።
ኢንዶኔዢያ ከ200 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት ፣ ከ250 በላይ ቋንቋዎች የሚነገርባት እና ከ300 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባት አገር ናት። ሱሀርቶ ወደ ስልጣን የመጣው በወታደራዊ ሀይል ሲሆን ለ31 ዓመታት ሰልጣን ላይ ቆይቷል – አገዛዙ በየ አምስቱ ዓመት ምርጫ የሚጠራ ሲሆን ሱሀርቶ ለሰባተኛ ጊዜ ለመመረጥ እየተሰናዳ ባለበት ሁኔታ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማግስት በግንቦት 1998 በህዝባዊ እምቢተኝነት ከስልጣን ተወግዷል። የሱሀርቶ አገዛዝ ቃላት ሊገልፁት በማይቻል መጠን የነቀዘ ፣ አፈና አና ግድያ የተንሰራፋበት ሲሆን ከምዕራቡ ጋር በነበረው ቁርኝት በተገኘ ብድር የተገነቡ ፎቆች እና መንገዶች ምክንያት አገሪቱ በርሱ አገዛዝ ዘመን አድጋ ነበር የሚሉ አሉ። የመሬት ልማት በፖለቲካ ጥፋት!!
ሁዋላ ላይ ይፋ እንደ ሆነው የሱዋርቶ አገዛዝ ብልሹነት ተጋልጦ ስልጣኑን እንዲለቅ ሲገደድ በመጨረሻው ሰዓት “I am sorry for my mistakes” ሲል ተመፃድቋል። ስህተቱ በቢሊየን የሚቆጠር ሀብት ለራሱ እና ለቤተሰቦቹ ማግበስበሱ ፣ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ተቃዋሚ ዜጎች ለሞት እና ስደት መዳረጉ ፣ እጅግ አድርጎ በሙስና የነቀዘ አስተዳደር መሆኑ ነበር።
ዛምቢያ ከቅኝ አገዛዝ እንድትላቀቅ መሪ ሚና የተጫወቱት ካውንዳ ለስልጣናቸው እጅግ አድርገው የሚሳሱ እሳቸው ከሌሉ አገሪቱ ያበቃላት የሚል ዝንባሌ ነበራቸው። የፖለቲካው አየር ሲለወጥ እና ተቀዋሚ ድርጅቶች የለውጥ ጥያቄያቸውን አንግበው ሲነሱ ምርጫ ለመጥራት ተገደዋል። እሳቸው ምርጫ ውድድር ውስጥ ሲገቡ ለነፃነት ያበቃሁት ‘ህዝብ ካለኔ ማንን ሊመርጥ ይችላል?’ የሚል እምነት አድሮባቸው ቆይቷል። ውነትም ሀያ በመቶ ድምፅ ማግኘታቸው ሲታይ አሁንም የሚወዳቸው አለ ያሰኛል። ይሔ ሀያ በመቶ ድምፅ ግን ዘር ግንድ ቆጥሮ የለገሳቸው የራሳቸው ብሔረሰብ ህዝብ ብቻ ነበር። የምርጫው ውጤት በዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ምስክርነት ይፋ ሲሆን እና መሸነፋቸውን ሲገነዘቡ ጓዛቸውን ጠቅልለው ከቤተመንግስት ለመውጣት አላንገራገሩም። ከነጭ ቅኝ ግዛት ነፃ ያወጡት ህዝብ ድምፁን ሲነፍጋቸው ህዝቡ ውለታ ቢስ መሆኑን በምሬት ሳይጠቁሙ ግን አላለፉም። በኔ የደረሰ እንዳይደርስባችሁ ፣ ህዝብን አምናችሁ ምርጫ የሚባል ጣጣ ውስጥ አትግቡ ብለው ቀሪ አምባገነን የአፍሪካ መሪዎችን ምክር ከመለገስም አልቦዘኑም። ጉዳዩ ምርጫ ከሆነ ሌላ መላ ፈልጉለት የሚል መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል።
እነሆ ምርጫዎች እየተካሄዱ ነው። በዩጋንዳ ፣ በኬንያ ፣ በደቡብ ሱዳን ፣ በሩዋንዳ፣ በኢትዮጵያ … ምርጫ ይጠራል… ደም ይፈሳል… አምባገነኖቹ ተቃዋሚ ነው ብለው በጠላትነት የፈረጁትን እጃቸው ላይ ባገኙት በማናቸውም የማጥቂያ ዘዴ ተጠቅመው ያምቃሉ። እናም ስልጣን ላይ ይቆያሉ… በምርጫ!!
ዘመኑ የዲሞክረሲ ነዋ! ዲሞክረሲ ደግሞ ‘ሂደት’ ነው ይላሉ። ዛሬ ተዘርቶ ነገ አይበቅልም ይሉናል። ሀያሶስት ዓመትም መብቀል አይችልም… ሀምሌ ላይ ዘርቶ ታህሳስ ላይ እንደሚታጨድ ሰብል ጊዜ ይወስዳል ይሉናል…እንደ ማሳው እንደ አፈሩ ነው። ዲሞክረሲ ጎምርቶ የሚታጨደው በስንት ዘመን እንደሆነ ግን የሚነግረን የዲሞክረሲ አዝመራ ጠቢብ ሊጠሩልን አልቻሉም… ብቻ ሂደት ነው… ምርጫ ደግሞ በያምስት ዓመቱ ይጠራል… ማን ይፈራል?
በዘረኝነት ቀንበር ጠምደው የከፋፈሉትን ህዝብ በማይጎመራው የዲሞክረሲ ማሳ ላይ እየነዱት ነው። ቀንበሩን ተሸክመው ከሚወላከፉት ዜጎች መካከል የምናውቃቸው የሚያውቁን ብዙ ናቸው።
ከአስር ዓመት በፊት በ1997 ወያኔ ምርጫ ውድድር ይደረግ ብሎ የፖለቲካ ምህዳሩን በመጠኑ ሰፋ ሲያደርግ ፉክክሩን ባሸናፊነት እንደሚወጣ አልተጠራጠረም ነበር። ወያኔ በወቅቱ በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ መለስ ዜናዊ እንዳረጋገጠው ‘… ሳናጭበረብር ግልፅ በሆነ ምርጫ የምናሸንፍ መሆኑን ይህ ሰልፍ ያራጋግጣል’ ብሎ እንደነበር ያስታውሷል። ባለ ‘ራዕዩ መሪ’ ህዝቡንም ልቡንም ማንበብ አልቻለም። ውድድሩ ተጠናቆ ወያኔ መሸነፉ ሲረጋገጥ ታንክ እና መትረየስ ይዞ መጣ – አዲስ አበባን የጦር ቀጠና አደረጋት። የፈሰሰው ደም ፣ የጎደለው አካል እና የፈረሰው ቤት ጩኸቱ ዛሬ ድረስ ያስተጋባል።
ታዛቢ አይፈሩም ምክንያቱም ማን እንደሚታዘባቸው አስቀድመው የሚወስኑትም እነሱ ናቸው። ከወያኔ የዘርኝነት ቀንበር ነፃ የሆነው ብዙሀኑ ህዝብ ግን ሳይመርጡት በነፃ ይታዘባል ፤ ሸፍጡንም ፣ ኮረጆ ግልበጣውንም ፣ ዱላውንም ፣ ጥይቱንም ፣ ወህኒውንም አይቶ ቀምሶ በዝምታ ይመሰክራል። ማን ተወዳድሮ ማን እንዳሸነፈ ያውቃል ፣ ድምፁን ሲሰርቁበት ግን ሌቦችን ለመታደግ አቅም የለውምና በዝምታ ታዝቦ ፣ አድፍጦ ሌላ ቀን ይጠብቃል።
አምባገነን ገዢዎች በስልጣን መቆየት የሚችሉበትን ሰበብ እያሰላሰልኩ ሳለሁ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ሔሮዶቱስ በማስታወሻው ያሰፈረው ገጠመኝ ትዝ አለኝ።
ጉዳዩ እንዲህ ነበር። ፐርቲንደር የተባለው ንጉስ ኮሪንዝ በተሰኘች ምድር በለጋ ዕድሜው ወደ ዙፋን ይወጣል። ታዲያ ሰልጣኑን ጠብቆ ለማቆየት የሚችልበትን ልምድ ለመቅሰም እንዲረዳው መልዕክተኛውን በስልጣን ለረዢም ዘመናት የቆየ ዝራቡለስ ወደ ተባለ የሚልተስ አምባገነን ገዢ ዘንድ ይልከዋል።
አንጋፋው አምባገነን ዝራቡለስ መልዕክተኛውን በጠዋት ተቀብሎ የመጣበትን ጉዳይ ካጣራ በሁዋላ ፈረሱን አስጭኖ ወደ በቆሎ እርሻ ይዞት ይሄዳል። እዚያም ከማሳው መካከል እየተንጎራደደ ለመልዕክተኛው የሆነ ያልሆነውን እያወራ በያዘው ገጀራ ከሌሎቹ ተክሎች ቀድመው ረዘም ረዘም ያሉትን አንገት እየቀላ ይጥላል። ረዣዢም በቆሎ ካናቱ እየተጎመደ ሲወድቅ ማየቱ ግራ የገባው መልዕክተኛ ወደ መጣበት ተመልሶ የሆነውን ለወጣቱ ንጉስ ፐርቲንደር በዝርዝር ይነግረዋል። ወጣቱ ንጉስ የተላለፈለት መልዕክት ምን እንደሆነ ለመረዳት ጊዜ አልፈጀበትም – ስልጣንህን ለማቆየት ከፈለክ ከሌሎች ሁሉ ቀድመው የነቁ ረዘም ያሉትን እየመረጥክ ሳይቀድሙህ በመቀንደብ ማስወገድ ነው። ይኸው ነው መልዕክቱ –
ጥንትም ዛሬም ረዣዢም ተቀናቃኞችን ሳይቀድሙህ ቅደማቸው… ‘ለምሳ ሲያስቡን ለቁርስ አደረግናቸው…’ የመንግስቱ ፖሊሲ እንደነበር ሁሉ የመለስ ዜናዊ ‘ጃኬታቸውን አስወልቀን አባረርናቸው…’ የተግባር መመሪያ ነበር – ወያኔ ዛሬ የሚጠቀመው በዚሁ ነው። በተቀዋሚ ሰፈር ረዘም ብሎ የወጣውን እሸት አናቱን ቀንጥሰው ለመጣል ቆርጠው ሲሰሩ ቆይተዋል። ትናንት በቅንጅት ፣ በነ ፕሮፌሰር አስራት እንዲሁም ዛሬ – በአንድነት እና በመኢአድ ላይ የተፈፀመው ይኸው ነው። በወያኔ ዘመን ድንክዬ በቆሎዎች ሲሻቸው መኖር ይፈቀድላቸዋል – የአምባገነኖች ዲሞክረሲ በነሱ አንገት ላይ አይመትርም።
ዋ ለረዣዢም በቆሎዎች!!
No comments:
Post a Comment