ድግሶችን፣ ወታደራዊ ሰልፎችንና ሀውልቶችን ማብዛት የአባገነኖች ሁሉ የጋራ ባህርይ ነው። ዘረኛውና ፋሽስቱ የህወሓት አገዛዝም በሕዝብ እየተጠላ፣ እያረጀና እየወላለቀ በሄደ መጠን በየተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ደግሶ መብላት፤ ወታደራዊ ሰልፍና የመሣሪያ ጋጋታ ማሳየት እና በየመንደሩ ሀውልት መመረቅ ሙያው አድርጎት ቆይቷል።
የህወሓት ድግሶችና ፌሽታዎች የአገራችን ሀብት ከማሟጠጣቸውም በላይ የመንግሥት ሠራተኞችን፣ የአርሶ አደሮችንና የአነስተኛ ነጋዴዎችን ኪስ እያራቆቱ ናቸው። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች በእስር ቤቶች እየማቀቁ በሚገኙበት ሁኔታ፤ በመቶ ሺዎች የሚገመቱ የአማራ አርሶአደሮች ተፈናቅለው እያለ፤ በጋምቤላና በኦጋዴን ወገኖቻችን ላይ ዘግናኝ የጅምላ ጭፍጨፋዎች እየተደረጉ፤ በአፋር፣ በሲዳማ፣ በቦረና፣ በወልቃይት እና በመላው ኢትዮጵያ ግጭቶች በበዙበት፤ ሕዝብ እያለቀሰ ባለበት በአሁኑ ሰዓት “የብሔር፣ ብሔረሰቦች መብት ተከበረ” እያሉ እነዚህኑ በደል እየደረሰባቸው ያሉ ዜጎችን ማስጨፈር እና ለእነዚህ ጭፈራዎች በርካታ ሚሊዮኖች ብር ማውጣት በእጅጉ ያስቆጫል። እነዚህ ጭፈራዎች ለህወሓት ሰዎች የገቢ ምንጮች መሆናቸው ጥርጥር የለውም፤ ለድሀው ኢትዮጵያዊ ግን መራቆቻዎች ናቸው። ከዚህም አልፎ በዘረኝነት እየተበደለ ያለ ሕዝብ ስለእኩልነት ዝፈን ማለት ክብረ ነክ ተግባር ነው። ዘንድሮ በአሶሳ የተደረገው አገር አቀፍ ድግስ ካለቀ ጥቂት ወራት በኋላ አገራችን በሌላ ዙር የህወሓቶች ድግስ ተወጥራለች።
ሰሞኑን በባህር ዳር በተደረገው የጦር ሠራዊት ሰልፍ እና ሰልፉን ተከትሎ በነበረው የድግሶች ግርግር ከሁሉም በላይ የተሰደበውና የተዋረደው የሠራዊቱ አባል ነው። አዛዦቹ መቶ በመቶ የህወሓት አባላት የሆኑበትን ሠራዊት “የኢትዮጵያ መከላከያ” ተብሎ መጠራቱ ራሱ የሚያሳፍረው ኢትዮጵያዊ ወኔ በልባቸው ውስጥ እየተንቀለቀለና እልህ እየተናነቃቸው ያሉ የሠራዊቱን አባላት ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንዴት የኢትዮጵያ ጠላቶች በሆኑ የህወሓት ካድሬዎች ይመራል? እንዴት የአስር አለቃ እንኳን ሊሆን የማይገባው የህወሓት ካድሬ “ጄኔራል” ተብሎ ኢትዮጵያዊያን ወታደሮችን እንደ ሎሌው ያዛል? እንዴት አንድ የህወሓት ሎሌ ሹመት ተሰጥቶት እየፏለለ በልምድ፣ በትምህርትና በእውቀት የሚበልጠውን ኢትዮጵያዊ ተንቆ ይዋረዳል? ይህ ቁጭትና እልህ ሠራዊቱ የዘረኛውን ህወሓት ሰልፍ አድማቂ መሆኑ የሚያከትምበት ጊዜ ይበልጥ እንዲናፍቅ የሚደረገው ነው። አልያማ ሰልፍ ያሳመረ ሠራዊት ሁሉ አሸናፊ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። በሰልፍ ብዛትና በመሣሪያ ትዕይንት ማሸነፍ ቢቻል ኖሮ የትም አገር አምባገነኖች ባልወደቁም፤ ህወሓት ራሱን ስልጣን ላይ ባልወጣም ነበር።
የህወሓት ምሥረታ 40ኛ ዓመት ድግስም ሌላው የታሪክና የሀብት ውድመት የሚያስከትል ክስተት ነው። የካቲት 11 ቀን 1967፣ ጥቂት ኢትዮጵያዊያን እናታቸውን ኢትዮጵያን ለመግደል ያሴሩበት እና ልጆች በእናታቸው ላይ ቢላዋ የሳሉበት ዕለት በመሆኑ በሀዘንና በሱባኤ እንጂ በድግስና በጭፈራ የሚታሰብ ዕለት አይደለም። ሲነሳ ምንም ይሁን ምን ዛሬ በደረስንበት ሁኔታ ሲገመገም፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ ውስጥ ህወሓትን የመሰለ መሠሪና አድርባይ ድርጅት ገጥሟት አያውቅም። እነሆ ዘንድሮም ይኸው አድርባይ ድርጅት የመሪዎቹን የሀብትና ዝና ረሀብ ለማስታገስ ሲል ያልነበረ ታሪክ እየፈጠረ በድግስ ስም ከድሀው ገንዘብ እየሰበሰበ
ለሀብታም የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ያሸጋግራል። የድግሶቹ ሁሉ አዘጋጆች፣ እቃ አቅራቢዎችና ተጠቃሚዎች ራሳቸው የህወሓት መሪዎችና አሽቃባጮቻቸው ሲሆኑ ከፋዩ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። በህወሓት ድግስ የሚባክነው የሕዝብ ሀብት ስንት ሆስፒታል ይገነባ እንደነበር ስናስብ እና ይህ ሀብት በተገቢው ቦታ ውሎ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ስም ብቻ የያዙ ዩንቨርስቲዎቻችንን ትምህርት መቅሰሚያ ማድረግ እንችል እንደነበር ስናሰላ ሀዘናችን ጥልቅ ነው። ህወሓት ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፍ ዕዳ እየቆለለ ዳንኪራ ሲረግጥና ሲያስረግጥ ማየትና መስማት ህሊና ሊሸከመው ከሚችል በላይ ነው።
አርበኞች ግንቦት 7፡ የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በህወሓት ወታደራዊ ሰልፍ እና የመሣሪያዎች ትዕይንት የሚረበሽ ድርጅት አይደለም። ይልቁንም በሰልፉ ጨኸት የታፈነው የኢትዮጵያዊ ወታደር ጩኸት ይሰማዋል። ኢትዮጵያዊ ወታደር በአዛዦቹ ላይ ጥርሱን ነክሶ፣ ቂም አርግዞ ሰልፋቸውን እንደሚሰለፍ አርበኞች ግንቦት 7 ያውቃል። አርበኞች ግንቦት 7፣ የሠራዊቱ አባላት ውስጥ ውስጡን እየተሰቃዩ የታዘዙትን መፈፀማቸው መብቃት አለበት ይላል፤ ወይ ተቀላቀሉን፣ አሊያም እውስጡ ሆናችሁ ሥርዓቱን የማዳከም ሥራዎችን ሥሩ። በእናንተ ውርደት የዘራፊዎች፣ ሙሰኖች፣ ጎጠኞችና ዘረኞች ደረት አብጦ መታየት የለበትም።
አርበኞች ግንቦት 7፣ የዘንድሮው የህወሓት 40ኛ ዓመት በዓል የጨረሻው በዓል እንዲሆን፤ ከርሞም ተመሳሳይ አዋራጅ በዓል እንዳናከብር፤ ሠራዊቱ በዘራፊዎች ታዞ የሚሰለፍበት ውርደት እንዲያበቃ ተባብረን ህወሓትን እንቅበር ይላል።
No comments:
Post a Comment