Monday, February 23, 2015

ከህወሃት ምርጫ የሚገኘው ትርፍ ውርደት ብቻ ነው

ህወሃት ኢሕአዴግ የተባለውን ጭንብል አጥልቆ አገሪቷን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር ካስገባ ግዜ ጀምሮ በኢትዮጵያዊያን ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች ፈርጀ ብዙ ናቸው። እነዚህ ፈርጀ ብዙ ወንጀሎች በልዩ ልዩ ተቋማት እና ግለሰቦች በማስረጃ ተደግፈው ተመዝግበው ተቀምጠዋል። ከሰሞኑ እንኳ በአውሮፓ ህብረት ውስጥ በተደረገው አንድ ጉባኤ ላይ ግራሃም ፔብል የተባሉ ታዋቂ ሰው ህወሃቶች የፈፀሟቸውን ወንጀሎች በማስረጃ አስደግፈው ከዘረዘሩ በኋላ ህወሃት “አሸባሪ መንግስት” ነው ብለዋል። ይሄ እውነት ነው። ኢትዮጵያ ከአምባገነን ገዥዎች ተላቃ የምታውቅ አገር አለመሆኗ የታወቀ ቢሆንም እንደ ህወሃት ያለ የህዝብ ጠላት መሆንን መርጦ የገዛ ህዝቡን የሚያሸብር መንግስት ነኝ የሚል አካል ግን አልታየም።

ህወሃት አሸባሪ ነው። ይሄ አሸባሪ ቡድን በሚያካሂደው ምርጫ ውስጥ የተሳተፈ ሁሉ እድል ፈንታው ውርደት፤ እስራት፤ ስደት እና ግዲያ መሆኑን እሰክ ዛሬ በተካሄዱት ምርጫዎች አይተናል። ህወሃት ኢሕአዴግ የተባለውን ጭንብል አጥልቆ በምርጫ ሰበብ የብዙ ንፁህን ዜጎችን ደም አፍስሷል። በምርጫ ሰበብ ያፈረሰው ቤት፤ የበተነው ቤተሰብ ብዙ ነው። አገራችን በፖለቲካ እስረኞች ብዛት አቻ ያልተገኘላት ሁናለች። በስደተኛ ብዛትም የመሪነቱን ደረጃ ይዛለች። ይህን ሁሉ ግፍ ያዩ የውጭ ታዛቢዎች ኢትዮጵያን ከውዳቂ አገራት መካከል መድበዋታል።

ህወሃቶች በታሪክ አጋጣሚ ከተቆናጠጡበት ወንበር ከሚወርዱ ሞታቸውን እንደሚመርጡ ደጋግመው በአደባባይ ተናግረዋል። ለዚህም እነርሱ ምክንያት የሚሉት ይህን ወንበር ያገኘነው በደማችን ነው። በደም ያገኘነውንም ወንበር እንዲሁ የምናስረክብ አይደለንም ይላሉ። ወንበሩን አንለቅም ብለው ቢያቆሙ መልካም ነበር፤ ወንበሩን የምንለቅ ከሆነ አገሪቷን እንበትናታለን የሚለውን ነውር ሃሰብ ማቀንቀናቸው ደግሞ ህወሃቶቹ አንዳች ዓይነት የአዕምሮ ቀውስ ውስጥ መግባታቸውን ያመለክታል። የእነዚህን ቡድኖች ነውረኛነት በ1997 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ ደህና አድርገን ታዝበናል። በሌብነት እና በሌላ ነውር ምክንያት ከድርጅቱ የተባረሩት ሳይቀሩ ተሰባስበው ህወሃትን ለማዳን የሚል የጥፋት ዘመቻ በአገሪቷ ላይ መክፈታቸው የሚረሳ አይደለም። ህወሃት ወንበሩን የሚለቅ ከሆነ ተመልሰን ወደ ጫካ እንገባለን ማለታቸው የአደባባይ ሚስጢር መሆኑም የሚረሳ አይደለም።

እስከ አሁን በተደረገው ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ ያተረፈው ነገር ቢኖር ውርደት እንጂ ክብር አይደለም። ህወሃቶች ምርጫ እያሉ ህዝቡን እያዋረዱ፤ የአገሪቷንም ሃብት እየበዘበዙ፤ እነርሱ ከህግ በላይ ሌላው ከእነርሱ ጫማ ስር ሁኖ የሚኖርበትን ሥርዓት እየሰሩ ኑረዋል። ይህ እነርሱ ለእነርሱ የሠሩት ሥርዓት እንዲሁ እንዲለወጥ ይፈልጋሉ ብሎ ከማሰብ የምናተርፈው ነገር ቢኖር ውርደት ብቻ ነው። ህወሃቶች የተፈጠሩበትም ምክንያት አገሪቷንና ህዝቧን ለማዋረድ ነው ለማለት የሚያስችሉን ከበቂ በላይ ምክንያቶች አሉ።

ህወሃቶች እንደ ጤነኛ ሰው ለማሰብ የሚያስችላቸው ስብዕና የሌላቸው መሆኑ ይታወቃል። እኛ ከስልጣን የምንወርድ ከሆነ አገሪቷን እንበትናታለን በሚል ቅዥት ውስጥ የመገኘታቸው ምስጢርም የስብዕናቸውን የዝቅጠት ደረጃ የሚያመላክት ነው።በሰላማዊ መንገድ ተወዳድረው እና ተመርጠው ስልጣን ለመያዝ በጎ ራዕይ ያላቸውን ሁሉ በጠላትነት ፈርጀው እና የአሸባሪነት ካባ ደርበውላቸው በጎ ራዕያቸውን እያመከኑ እንደሆነ እያየን ነው። አሁን በአንድነት እና በመኢህአድ ላይ የተወሰደው እርምጃ የዜጎችን በጎ ራዕይ የማምከን ተግባር መገለጫ ሁኖ ሊጠቀስ ይችላል። ህወሃቶች ራዕይ አልባ ናቸው።ለኢትዮጵያ በጎ ራዕይ ቢኖራቸው ኑሮ “እኛ ከሌለን አገሪቷን እንበትናታለን” አይሉም ነበር። ራዕይ ያለው ከእኔ የተሻለ ካለ ይሥራ ይላል እንጂ እኔ ካልሆንኩ ሞቼ እገኛለሁ አይልም። ህወሃቶች ቅዥታቸውን ራዕይ ብለው ይጠራሉ። በቅዥት ዓለም ውስጥም እንደሚኖሩ የሚነገራቸው ከተገኘም ዘራፍ ብለው አሸባሪ ይላሉ እንጂ ለማድመጥ ችሎታ እና ትዕግስት የላቸውም።



እንግዲህ ህወሃቶች ኢሕአዴግ የተባለውን የምናምንቴዎችን ስብሰብ ጭንብል አጥልቀው በሚያካሂዱት ምርጫ ላይ የተሳተፈ ሁሉ ያተረፈው ውርደት መሆኑን እናውቃለን። ይሄን ውርደት መምረጥ ትክክለኛ ምርጫ ሊሆን አይችልም። ህወሃት የያዘው ስልጣን የነብር ጭራ ሁኖበታል። የነብሩን ጭራ ከለቅኩ ደግሞ እጠፋለሁ የሚል ፍርሃት ውስጥ ወድቋል። ከዚህ ውድቀት ለመነሳት የሚያስችል እውቀትና ቅንነት ስለሌለው ጥላው እያስበረገገው መኖር ግድ ሁኖበታል። ይሄ በርጋጋ ቡድን በኢትዮጵያዊያን ላይ የፈፀመው ወንጀል በሰላማዊ መንገድ በሚደረግ ምርጫ ስልጣኑን እንዲለቅ ያደርገዋል የሚል እምነት የለንም። ይሄ ቡድን ካፈጣጠሩ ጀምሮ ቂመኛና ምህረትን የማያውቅ በመሆኑ ሌሎችንም የሚያየው ራሱን በሚያየው ዓይኑ ነው። ይሄ ቡድን ከራሱ ክበብ ወጥቶ በተለየ እና በተሻለ ሁኔታ ለማሰብ ቅንነት ስለሌለው ሁሉም ሰው እርሱ ራሱን ይመስለዋል። ይሄ ቡድን በዚህ መንፈስ ሁኖ በሚያካሂደው ምርጫ ውስጥ መሳተፍ ትክክለኛ አካሄድ ስለማይሆን ምርጫውን ህወሃትን ከመሠረቱ ለመቀየር መጠቀም ተገቢ አካሄድ ይሆናል። ምርጫው ህወሃትን ከሥሩ የማይቀይረው ከሆነ ይህ ዘረኛና ዘራፊ ቡድን ለሌሎች ማሳየት የሚፈልገውን ህጋዊ ሽፋን በማግኘት በጥፋት ጎዳናው እንዲቆይ ያደርገዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ !

ህወሃቶች አገሪቷን ከተቆጣጠሩ ዘመን ጀምሮ ከተደረጉት ምርጫዎች ያተርፍከው ውርደት ነው። ህወሃቶች ምርጫ እያካሄዱ ልጆችህን ይቀጠቅጣሉ፤ ይገድላሉ። ምርጫ ብለው ሲያበቁ አልመረጥከኝም ብለው መሬትህን ይነጥቃሉ፤ ከአቅምህ በላይ ግብር ይጥሉብሃል። ናና ምረጥ ብለው ሲያበቁ አልመረጥከኝም ብለው ከሥራህ ያባርሩሃል፤ ቤተሰቦችህንም ይበትናሉ። ህወሃቶች ምርጫ በሚሉት ቧልት የደረሰብህ ውርደት ብዙ ነው። እንግዲህ በህወሃቶች ምርጫ የምትሳተፍ ከሆነ እስከ ዛሬ ሲፈፀም የቆየውን ውርደት ለመጨረሻ ግዜ በቃ ልትለው ቆርጠህ ተነሳ። ህወሃቶች የኢትዮጵያ ጠላት መሆንን የመረጡ ቡድኖች ናቸው። የራስህን ጠላት በራስህ ላይ መርጠህ እንዳትሾም ለራስህ ተጠንቀቅ።

እኛ አርበኞች-ግንቦት ሰባት የአንድነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ህወሃት በሰለጠነ መንገድ በሚደረግ የፖለቲካ ውድድር ውስጥ ገብቶ ለመፎካከር ችሎታ እንደሌለው አይተናል። ችሎታ ብቻ ሳይሆን ቅንነትም የሌለው ክፉ ቡድን መሆኑንም እናውቃለን። ህወሃት የጨበጥኩትን ስልጣን የምለቀው “በሬሳየ ላይ ነው” ያለው ሃሳብ የያዝነውን የትግል መንገድ እንድንመርጥ አድርጎናል። ህወሃትም ”ሞት ወይም ስልጣን ላይ መቆየት” የሚል የማይናወፅ እምነቱ እንዲሁ በዋዛ እንደማይቀየር አበክሮ ነግሮናል። እነዚህ ቡድኖች በጎ የሆነ አገራዊ ራዕይ ኑሯቸው እና የዜጎችን ብሄራዊ ስሜት አጠናክረው አገሪቷን በአንድነት ለመምራት በጎ ምኞት ቢኖራቸው ኑሮ በስልጣን ላይ ለመቆየት ቢሟገቱ ግድ ባላላን ነበር። እነርሱ ግን አገር እያፈረሱ፤ በየእለቱ የንፁህ ዜጋ ደም እያፈሰሱ፤ ወጣቱን ለስደት እየዳረጉ፤ ገበሬውን መሬት አልባ አድርገው የአረብና የህንድ ባሪያ እያደረጉት፤ ቀና ብሎ ያያቸውን ሁሉ አሸባሪ እያሉ ለእስር እየዳረጉ፤ ብዙ ዜጎችን አገር አልባ አድርገው እያየን ዝም ለማለት ሰው መሆናችን አይፈቅድልንም። በሚገባቸው ቋንቋ ልናናግራቸው ተዘጋጅተናል። ብዙ ወጣቶች ከመላው የአገሪቷ ክፍሎች ህወሃቶች የገነቡትን የዘረኝነት አጥር እያፈረሱ ወደ ትግሉ እየተቀላቀሉ ነው። በእኛ ዘንድ ማንነታችን ኢትዮጵያዊነት እንጂ ሌላ መሰፍረት አይደለም። ኢትዮጵያዊነት በቀይ ቀለም በልባችን ውስጥ የተቀረፀ የምንሰዋለት ማህተማችን ሁኗል።

በህወሃት ዘመን ስሟ የጎደፈው ኢትዮጵያችንን ስሟን በደማቅ ብዕር ልንፅፍ ተነስተናል። ኢትዮጵያን ወደ ቀደመው ክብሯ ልንመልሳት አያቶቻችን በተመላለሱበት ተራራ ላይ ተሰማርተናል። ኢትዮጵያችን እንደ ነብር የተዋበ ዥንጉርጉርነቷን እንደያዘች የታፈረች አገር ሁና ስሟ እንዲነሳ ለማድረግ የሚያስችለንን የትግል ስልት መርጠናል። ወጣቶቿ የማይሰደዱባት፤ዜጎቿ በልተው የሚያድሩባት፤ ምሁራኖቿ እውቀታቸውን ያለ ገደብ የሚያፈሱባት፤ ነጋዴዎች ያለ ፍርሃት ነግደው የሚያተርፉባት፤ አዛውንቶች የሚጦሩባት፤ ህፃናት በደስታ የሚቧርቁባት፤ ገበሬው መሬት አልባ የማይሆንባት፤ ጋዜጠኛው ከሂሊናው ተስማምቶ ለሙያው ብቻ ታማኝ ሁኖ የሚኖርባት፤ ኪነ-ጥበብ የአደርባዮች መናኽሪያ ከመሆን ወጥታ አደርባዮችን ለመገሰፅ የምትችለበት፤ ዜጎቿ ያለ ፍርሃት የሚኖሩባት፤ ፍፁም ሠላም የሰፈነባት፤ በአጠቃላይ እግዚአብሄር አገሩ ኢትዮጵያ ነች ተብላ የምትታወቅ አገር ለመፈጠር ቆርጠን ተነስተናል። በዚህ መሠረትነት የጀመርነው ትግል ዕለት ዕለት እያማረበት፤ እየተጠናከረ እና እየጎለበተ እየሄደ ነው። ካሁን በኋላ ህወሃትን ከስልጣን ለማስወገድ ግዜውን የምንመርጠው እኛ እንጂ ማንም አይሆንም። ግዜው በደረሰ ግዜ አገራችንን እና ዜጎቿን ያዋረዱ በሙሉ ወየውላቸው። ከእኩይ አስተሳሰባቸው አንመለስም ያሉ በሙሉ የመጥፊያ ጉድጓዳቸውን እየማሱ እንደሆነ ስንነግራቸው ከክፉ አስተሳሰባቸው ለመመለስ አሁንም ቢሆን እንዳልዘገየ ልናስታውሳቸው እንወዳለን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!

No comments:

Post a Comment