Sunday, February 15, 2015

የወቅቱ ሰራዊት ‹‹ክብረ በዓል›› ይገባዋልን?

ጌታቸው ሺፈራው

እየተከበረ በሚገኘው የ‹‹መከላከያ ሰራዊት ቀን›› በደርግ ወቅት የነበረው የአገራችን ሰራዊት አባላት እንደ ኢትዮጵያዊ ሳይሆን እንደ ውጭ ወራሪ ተቆጥሮ ሞቱና ቁስለቱ ላይ እየተፎከረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከአሁን ቀደም ዳር ድንበሯን ያስጠበቀ ይጠብቅ፣ ታሪክ የሰራ ሰራዊት እንዳልነበራት ተደርጎ የአሁኑ ሰራዊት ብቻ እየተወደሰ ነው፡፡ ሆኖም በደርግና በኢህአዴግ መካከል የነበረው ጦርነት የእርስ በእርስ ጦርነት እንጂ ሌላ አገራዊ አላማን ያነገበና ይህን ያህል የሚኮራበት ተጋድሎ አይደለም፡፡ በተቃራኒው እልቂቱ የሚያሳዝን ጠባሳው የታሪካችን አንድ አካል ነው፡፡ እስካሁን የመከላከያ ሰራዊት በዓልን ከሚያከብሩ አገራት መካከል የእርስ በእርስ ጦርነትን ተከትሎ የአንድ ፓርቲ ወይንም ሸማቂ ሰራዊቱ ድል በማድረጉ በዓልን የሚያከብር አገር የለም፡፡

ከኤርትራ ጋር በተደረገው ጦርነት ኢትዮጵያ ያጣችው የሰው ሀይል፣ ኢኮኖሚና የባህር በር ሲታይ እነ አሉላ አባነጋ በዶጋሊና በሌሎቹ የጦር ሜዳዎች ያስመዘገቡት ድል ጋር በአላማም ሆነ በድል በምንም መልኩ አንድ ሚዛን ላይ የሚቀመጥ አይደለም፡፡ የመከላከያ ሰራዊት በዓል በፓርቲ ፍላጎት የሚከበር ሆኖ እንጂ የአሁኑ የመከላከያ ሰራዊታችንም እራሱ አስመዘገብኩት ከሚለው በተሻለ ለዶጋሊ፣ አድዋና ማይጨው እውቅና ቢሰጥ የሚከፋው አይመስልም፡፡ የአሁኑ የመከላከያ ሰራዊት ራሱ ሊያዝን በሚችልበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ወታደራዊ ታሪክ ተረካቢ ሆኖ እንዳይታወስ ተደርጓል፡፡ ለዚህም ኢህአዴግ በአሁኑ ወቅት ይጠቅመኛል ያለውን መከላከያ ሰራዊት ብቻ በመዘከር ሰራዊቱን ይበልጥ ወደ ፖለቲካው ለመዘፈቅ የሚደረግ ጥረት ነው፡፡
ኢህአዴግ የመከላከያ በዓሉን አላማ ሲገልጽ «የመከላከያ ሰራዊቱ ከ1988 ዓ/ም በኋላ ለሰላምና ለአገራቸው ሉዓላዊነት ህይወታቸውን ያጡ የሰራዊቱ አባላት ለመዘከር፣ «የብሄር ብሄሮችን» ተዋጽኦ ያካተተና መብታቸውን የሚያስከብር ሰራዊት መመስረቱን አስመልክቶ፣ ሰራዊቱ በልማቱ መስክ እያበረከተው የሚገኘው አስተዋጽኦ፣ የህዝብ ሰራዊት መሆኑን ለማሳየት» በሚል ነው፡፡ እንደ ኢህአዴግ እነ አጼ ቴወድሮስ፣እነ አሉላ፣ እነ ጦና፣ እነ ገበየሁ፣ እነ ጎበና የመሩት ሰራዊት በህዝብ ለአንድ ቀን ለመዘከር የግድ ኢህአዴግ በከለለው የቋንቋ ድንበር ስርና ማዕቀፍ ውስጥ መገኘት ነበረባቸው፡፡

በሌላ በኩል አንድ ሰራዊት የልማት ሰራዊት መሆኑን የሚጠላ የለም፡፡ ሰራዊቱ አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችን መላመዱም ሆነ የውጊያ ብቃቱን ማጠናከሩ ለዘመናት በተደረገው ወታደራዊ ታሪክ ለሚኮራው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስደስት ነው፡፡ ሆኖም በመካኒካል ኢንጅነሪንግ የተመረቀ የዩኒቨርሲቱ ተማሪ በጥቃቅንና አነስተኛ እየተደራጀ፣ ድንጋይ እንዲያነጥፍ እየተገደደና ከዚህም አለፍ ሲል በስራ አጥነት ቤቱ ቁጭ ብሎ እየዋለ «ወቶ አደሩ» መኪና መጠጋገኑን ከሚገባው በላይ አግንኖ ማውራት ሌሎች ችግሮችን መቅረፍ ያልቻለው ኢህአዴግ በመከላከያው ስም እየነገደ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በወታደሩ ስም የቀረበው ስራ የሲቪሉ ውጤት ቢሆንም ኢህአዴግ አገሪቱን በወታደራዊነት ስር ለማስተዳደር በመፈለጉ ብቻ ለወታደሩ የይስሙላህ ክብር እየሰጠ ነው፡፡ በአገሪቱ ዘመናዊ የህክምና ተቋም በጤና ጥበቃ ሚኒስተር ስር መመስረት ሲገባው «የመጀመሪያው ዘመናዊ ሆስፒታል» ተብሎ በመከላከያ ስም መገንባቱን ሰምተናል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሲቪል ከሚባለው የጤና ጥበቃ ይልቅ ሰራዊቱ ታዕምር ሰራ ቢባል የኢህአዴግ በተለይም መከላከያውን በበላይነት የሚቆጣጠረው ህወሓት ውጤታማ ስራ እያከናወነ መሆኑን በማሳየት ቅቡልነትን ለማግኘት ታስቦ ነው፡፡ በተጨማሪም መብታቸውን ሊያስጠብቅ ከሚችለው ሲቪል ይልቅ ከላይ የመጣ ትዕዛዝን እንደ ወታደርነቱ ከማስፈጸም ወደኋላ የማይለው መከላከያ ሰራዊት ወደ ፖለቲካው በመዘፈቅ አገሪቱን ለመቆጣጠር ነው፡፡ ይህ ችግራችን እንዳለ ሆኖም ቢሆን የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት በራሱ የሙያ መስክ ከዚህ በላይ ጥረት የሚጠበቅበት ሰራዊት ነው፡፡ የአባል ፓርቲዎች ተዋጽኦ በቀዳሚነት የሚነሳ ሆኖ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ለመከላከያው ሁለት አይነት አመለካከት ይስተዋላል፡፡ አንደኛው ያልተማረ እንደሆነ የሚጠቅስ ነው፡፡


የአሁኑ መከላከያ ሰራዊት እንቅስቃሴዎች መካከል በመልካምነታቸው የሚጠቀሱ ቢኖሩም በታሪካዊ ተቀናቃኝነት የሚታወቀው የግብጽ የመከላከያ ሰራዊት ይቅርና የሱዳንንና የኬንያን ያህል ዘመናዊ የመከላከያ ሰራዊት የለንም፡፡ በጦርነት ውስጥ ያለችው ሱዳን እንዲሁም ጦርነት እምብዛም የማያሰጋት ኬንያ ከእኛ የተሻሉ ቴክኖሎጅዎችን መታጠቅና ማምረት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በተለይ ሱዳን ምናልባትም ለኢህአዴግ በምሳሌነት ወስዷቸው ሊሆን ከሚችሉት ግዙፍ የመከላከያ ሰራዊት ተቋማቷ አሁን የእኛው መከላከያ ሰራዊት የሚያመርታቸውን ጨምሮ ሌሎች ቁሳቁሶችን ማምረት ከጀመረች ቆይታለች፡፡ በሌላ በኩል ኢህአዴግ የራሱን ታሪክ ለማግነን ካለው አላማ አንጻር ለአሁኑ የመከላከያ ሰራዊት ስኬት መሰረት የሆኑት ታሪኮች ባለመነገራቸው በህዝቡ ዘንድ የተዛባ መረጃን እያስተላለፈ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት መኪናና የጦር መሳሪያን ጨምሮ ሌሎች ቁሳቁሶችን የሚገጣጠምበት የቢሾፍቱው የመከላከያ ተቋም የተመሰረተው በኃ/ስላሴ ዘመን ቢሆንም በኢህአዴግ ዘመን እንደተመሰረተ ተደርጎ እየተወራ ነው፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ በደርግ ዘመን ጀምሮ ጥይት ማምረትና ቀላል መሳሪያዎችን ሲገጣጥም እንደነበር የሚካድ አይደለም፡፡ ሆኖም ይህ ጅምር ታሪክ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ሰራው የሚባለውን እንዳያደበዝዝ በመሰረትነት አልተነሳም፡፡

የንጉሱ ስርዓት አሁን ቁሳቁሶች የሚገጣጠሙበትን ተቋም አቋቁሟል፡፡ ደርግ በአራቱም የአገሪቱ ክፍሎች ጦርነት በነበረበትና እንደ መንግስት ለተቋቋመ ብቻ ሳይሆን በተገንጣይነት ለተሰበሰቡ ጥቂት ግለሰቦች መሳሪያ በገፍ በእርዳታ በሚሰጥበት በዚያን ወቅት ጥይት ማምረትና መሳሪያ የመገጣጠም ሙከራ አድርጓል፡፡ በእርግጥ እነዚህ ስርዓቶች ከዚህም በላይ መስራት ነበረባቸው፡፡ ሆኖም 24 አመት ቢያንስ አንጻራዊ ሰላም ብቻ ሳይሆን ለዘመናዊ ቴክኖሎጅ ምክንያት መልካም እድልን ያገኘው ኢህአዴግ በሁለቱ መንግስታት በተጀመሩ ተቋማት መከላከያው አሁን እየሰራ ያለውን እንዲያከናውን ቢያደርግ ለሳምንትና ከዚያ በላይ በታምዕርነት መወራት አልነበረበትም፡፡ ከምንም በላይ ኢትዮጵያ የረዥም አመት ወታደራዊ ታሪክ ያላት አገር ነች፡፡

ከ160 አመት በፊት መድፍ የተሰራባት አገር በአሁኑ ወቅት የጦር መሳሪያ መገጣጠምም ይህን ያህል ግርምት የሚፈጥር አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ከ3 አመት በኋላ ነጻነቷን ያገኘችውን ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ባለፉት 50ና 60 አመታት ከተመሰረቱ አገራት ጋር መወዳደር አልነበረብንም፡፡ ተወዳድረን ስንገኝም ቢሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ እንደተሰራ አሊያም በኢህአዴግ ዘመን የተሞከረ በማስመሰል ጮቤ የሚያስረግጥ አይደለም፡፡ ይህም የመከላከያ ሰራዊቱ በዓል አላማ፣ በፖለቲካው መዘፈቅና ኢህአዴግ እየተጠቀመበት መሆኑ ከትችት አልፎ ማስተካከያ የሚያስፈልገው ሆኖ አዳዲስ መልካም ጅምሮቹ የሚበረታቱ እንጂ በታምዕርነት መቅርብ አልነበረባቸው፡፡ ሆኖም ኢህአዴግ ነውና አድርጎታል፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ እንጂ ኢትዮጵያ እንዳላት ወታደራዊና የመንግስት ታሪክ ይህ የመከላከያ ሰራዊት በዓል መከበር የነበረበት ከ100ና 200 አመትም ቢሆን ቀደም ብሎ ነው፡፡ እነዚህ መንግስታት የመከላከያ ሰራዊቱን ቀን ሳያከብሩ አልፈዋል፡፡ ለ23 አመታት ያህል አገሪቱን ያስተዳደረው ኢህአዴግም ይህን በዓል መጀመሩ አንድ ነገር ሆኖ እስካሁን መዘግየቱ ኢህአዴግንም ከተጠያቂነት እንዳያመልጥ ያደርገዋል፡፡

መከበር ካለበት ደግሞ የአሁኑ የአገራችን የመከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያ የረዥም አመት የመከላከያ ሰራዊት ታሪክ አንድ አካል መሆኑን በሚያሳይ መልኩ እንጂ የአገሪቱን የመከላከያ ሰራዊት ታሪክ በኢህአዴግ ዘመን የተጀመረ ማስመሰል አልነበረበትም፡፡ በዚህ ቁንጽል አላማ ከሚከበር እንደ ኃ/ስላሴና ደርግ እንዲሁም እስካሁን የነበረው ኢህአዴግ እንዳደረገው ሳይከበር ቢቀር የተሻለ ነበር፡፡ ቢያንስ ቀጣዩ ትውልድ የአገሪቱን ረዥም የመከላከያ ሰራዊት ታሪክ ባገናዘበ መልኩና አላማው ሳይዛባ ያከብረው ነበር፡፡ ኢህአዴግ በሰንደቅ አላማው ጉዳይ በህዝብ ዘንድ አለመግባባት እንዲፈጠር እንዳደረገው ሁሉ የህወሓትን ተጋድሎና በህወሓት የበላይት የተያዘው መከላከያ ሰራዊቱን የሚወድሰው የ‹‹መከላያ ሰራዊት ቀን›› በዓል አላማ ላይም ተመሳሳይ ችግር ፈጥሯል፡፡ በዚህም ኢህአዴግ ስልጣኑን በሚለቅበት ወቅት እንደ ሰንደቅ አላማው ሁሉ የአገራችን ልዓላዊነት ደጀን መሆን የሚገባው መከላከያ ሰራዊት ቀን ላይም አለመግባባት መፈጠሩ የማይቀር ነው፡፡

No comments:

Post a Comment