Thursday, January 8, 2015
መታረም የሚገባዉ ማነዉ? (ርዕዮት አለሙ ከቃሊቲ እስር ቤት)
በግል የህትመት ዉጤቶች አማካኝነት በሀገሬ ዉስጥ የምመለከታቸዉን ችግሮች ለህዝብ ማቅረብና እንደዜጋም መፍትሔ ይሆናሉ ብዬ የማስባቸዉን ሀሳቦች መጠቆም ከጀመርኩ አምስት አመታት አለፉ፡፡ የመጀመሪያ ፅሑፌን ያዘጋጀሁት " "ስህተቶችን" ለማረም የተፈፀሙ ስህተቶችና የስህተት ማረሚያ እርምጃዎች" በሚል ርዕስ እንደነበረ አስታዉሳለሁ፡፡ በዚህም ፅሑፍ የፕሬስ፣የፖለቲካፓርቲዎች ምዝገባና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የተመለከቱ አዋጆች የወጡበት ምክንያትና እንደሀገር የሚያሳድሩትን ተፅእኖ ለመዳሰስ ብሎም ኢህአዴግ ከስህተቶቹ እንዲታረም ለመምከር ሞክሬያለሁ፡፡
የኢህአዴግ ሰዎች በአንድ የገዢዉ ፓርቲ ልሳን በሆነ ድረገፅ አማካኝነት የማስጠንቀቂያ ይዘት ያለዉ ምላሽ መስጠት የጀመሩት ከላይ ከጠቀስኩት የመጀመሪያ ፅሁፌ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም በአዲስፕሬስ ጋዜጣ ላይ በአዘጋጅነት ተቀጥሬ መስራት ስጀምር ግን ሁኔታዉ እየባሰ መጣ፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም አዳማ ላይ ከተለያዩ ሚዲያዎች ለተዉጣጣን ጋዜጠኞች የሰጠዉን ስልጠና ከተካፈልኩ በኋል ከስልጠናዉ ጋር በተያያዘ ለህትመት ያበቃሁት ፅሁፍ ኢህአዴጎችን በእጅጉ አስቆጣቸዉ፡፡ በመሆኑም ወደቢሮአችን ተደዉሎ ከኢህአዴግ ፅህፈት ቤት የተደወለ መሆኑ ከተገለፀ በኋላ ለጽሑፌ ምላሽ የላኩ በመሆኑ በፍጥነነት እንድናወጣዉ ቀጭን ትዕዛዝ ተሰጠን፡፡ ምላሻቸዉን ለማዉጣት የእነሱ መደወልም ሆነ ትዕዛዝ አስፈላጊ አልነበረም፡፡ የዝግጅት ክፍላችን አንድ ጽሑፍ የቀረበበት አካል ምላሹን በዚያዉ በተፃፈበት የህትመት ዉጤት ላይ ማስነበብ እንደሚችል በህግ የተደነገገ መሆኑን ከማወቁም በላይ የትኛዉንም አይነት ሀሳብ ለማስተናገድ ክፍት ነበርና ምላሻቸዉን በጋዜጣችን ላይ ታተመ፡፡ በዚህ ብቻ ግን አልተገቱም፤ በወቅቱ የገዢዉ ፓርቲን ሀሳብ በማቀንቀን ይታወቁ የነበሩት እንደ ዳጉ ኢትዮጵያና ሰነድ ያሉ ጋዜጦች ሀሳቦቼን በሃሳብ መምታት ባለመቻላቸዉ ይሁን ባለመፈለጋቸዉ ተራ ዘለፋዎችን ያወርዱብኝ ጀመር፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የገዢዉ ፓርቲ ደህንነቶች ስልክ በመደወል፣ በዝግጅት ክፍላችን አድራሻ በስሜ ደብዳቤ በመላክና በአካልም በማግኘት ጭምር መንግስትን የሚተቹ ፅሑፎችን እንዳልፅፍ ሊያስፈራሩኝ ሞከሩ፡፡ "ማስፈራራት የሚቻለዉ የሚፈራ ሲኖር ነዉ" እንዲሉ ሙከራቸዉ ዋጋ አልነበረዉም፡፡ ምክንያቱም የመጀመሪያ ፅሑፌን ለህትመት ከማብቃቴ በፊት ልከፍለዉ ስለምችለዉ መስዋዕትነት በሚገባ አስቤበታለሁ፡፡ የሀገሬን ጉዳይ በንቃት የምከታተል ዜጋ እንደመሆኔም ከገዢዉ ፓርቲ የተለየ ሀሳብ ያቀነቀኑ ሰዎች የደረሰባቸዉን በሚገባ አዉቃለሁ፡፡ በመሆኑም ከሁለት መጥፎ ምርጫዎች አንዱን ማለትም እነሱ የደረሰባቸዉን ግፍ እንዳይደርስብኝ የሀገሬን ጉዳይ በተመለከተ ፍዝ ተመልካች መሆንን ወይም በሙያዬ የምችለዉን አስተዋፅኦ አበርክቼ የሚመጣዉን መቀበል መምረጥ ነበረብኝ፡፡ ሁለተኛዉን የተሻለ መጥፎ ምርጫ ከመረጥኩ የሰነበትኩ በመሆኑም እየበረከቱ የመጡትን ማስፈራሪያዎች ከቁብ ሳልቆጥር የጋዜጠኝነት ስራዬን መቀጠል ቻልኩ፡፡ በዚሁ መሰረት ስራ ለመያዝ፣ የደረጃ እድገት ለማግኘትም ሆነ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ ከደህንነት ስጋት የፀዳ ኑሮ ለመኖር የኢህአዴግ አባል ካልሆነም ደጋፊ መሆን ከጊዜ ጊዜ ግድ እየሆነ መምጣቱን የሚያሳዩ፣ ገዢዉ ፓርቲ እንዳጎናፀፈን የሚገልፅልን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በተጨባጭ አለመኖሩን የሚሞግቱ፣ የኢህአዴግን እንደሀገር የማሰብ ችሎታ ወይም ፍቃደኝነት አናሳ መሆን የሚተቹና ሌሎችም መንግስት ቀናነት ቢኖረዉ ኖሮ ሊታረምበት የሚያስችሉትን በርካታ ፅሑፎች አቀረብኩ፡፡ አንድ ቀን ጧት ግን አምባገነኑ መንግስታችን ከጀመርኩት ጉዞ ገታኝ፡፡ ሰኔ10/2003 በወቅቱ እሰራባት በነበረችዉ ተወዳጇ ፍትህ ጋዜጣ ላይ የቀድሞዉን ጠቅላይ ሚኒስትር በተመለከተ ፅሑፍ ለህዝብ ማቅረቤን ተከትሎ ሰኔ14/2003 ዓ.ም ለእስር ተዳረግሁ፡፡
ማዕከላዊና ቃሊቲ ምንና ምን ናቸዉ?
ዉድ አንባብያን፤ ፊዘኛዉ መንግስታችን በሽብርተኝነት እንደሚጠረጥረኝ ገልፆ በእጆቼ ካቴና በማጥለቅ በቁጥጥር ስር አዋለኝ ካዋለኝ ከዚያ ቀን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለቁጥር የሚያታክቱ የመብት ጥሰቶችን እየፈፀመብኝ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህል እጅግ በጣም ጥቂቶቹን እነሆ!
ከህጎች ሁሉ የበላይ ህግ ነዉ የሚባልለት ህገመንግስት በጥበቃ ስር ያሉ ሰዎች በጠበቆቻቸዉ የመጎብኘት መብት እንዳላቸዉ ቢገልፅም እኔና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ግን ይሄ መብታችን በማዕከላዊ አለቆች ተጥሷል፡፡ ጠበቃዬን ለማግኘት የተፈቀደልኝ ምርመራዉ ከተጠናቀቀና ቃል ከሰጠሁ በኋላ ወደቃሊቲ ለመዉረድ የአስርቀናት ዕድሜ ያህል ሲቀረኝ ነበር፡፡ በቤተሰብና በጓደኞቼ ለመጎብኘት የተፈቀደልኝም ሁለት ወር ከ3 ሳምንታት ክልከላ በኋላ ነበር፡፡ ከጠበቃዬ ጋር እንዳልገናኝ ተደርጎ የሚካሄደዉ ምርመራ የፃፍኳቸዉን ፅሑፎች ለምን እንደፃፍኩ፣ ከበስተኋላዬ ሆኖ የሚገፋኝ አካል ስለመኖር አለመኖሩና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ላይ ያተኮረ ቢሆንም አልፎ አልፎ ደግሞ መልኩን ይቀይራል፡፡ አንዳንድ ቀን መርማሪዎቹ በማስተምርበት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በተካሄዱ ስብሰባዎች ላይ ያቀረብኳቸዉን ሀሳቦች እያነሱ ከመንግስት የደህንነት ሀይሎች የሚያመልጥ ምንም ነገር እንደሌለ በመግለፅ ቢጤ ያሰሙኝ እንደነበር ሳልጠቅስ ማለፍ አልፈልግም፡፡፡ እንዲህ አይነቱ ንግግራቸዉ አሰልቺዉን ምርመራ ዘና እልበት ዘንድ የሚረዳኝ የእፎይታ ጊዜ ሰጥቶኛል፡፡ በአደባባይ ስብሰባዎች ላይ የተናገርኩትንና ደህንነት ሊሰልለዉ የማያስፈልገዉን ግልፅ ነገር እንደ ትልቅ የደህንነቶች የስራ ዉጤት ተደርጎ ሲገለፅ ከመስማት በላይ ምን የሚያዝናና ነገር ይገኛል? የት/ቤት ርዕሰ መምህራኖች በሙሉ የኢህአዴግ አባል እንዲሆኑ የተደረገበት ምክንያት መንግስት እንደሚለዉ የትምህርት ፖሊሲዉን ለማስፈፀም ሳይሆን የመምህራንንና የተማሪዎችን የፖለቲካ አቋም ለማወቅና ይህንኑ ሪፖርት ለማድረግ መሆኑን የማይረዳ መምህር ይኖራል? ይህንን ለማድረግ ፍቃደኛ ያልሆኑ ርዕሰ መምህራኖች ሰበብ እየተፈለገላቸዉ ከቦታቸዉ እንዲነሱ ሲደረግስ ስንታዘብ አልኖርንም? "ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል" አለ ያገሬ ሰዉ! ሆዴ ባዶ እንዳይቀር ሁሉን መተንፈሴን ትቼ የጀመርኩትን የማዕከላዊ ምርመራ ጉዳይ ልቀጥል፡፡
የምርመራዉ ይዘት ከጥቂት ሳምንታት በኋላ መልኩን እየቀየረ መጣ፡፡ በሪፖርተርነት እሰራበት የነበረዉ የኢትዮጵያ ሪቪዉ ድረገፅ አዘጋጅ ኤልያስ ክፍሌ የሽብር ተልዕኮ እንደሰጠኝ በሀሰት እንድናገርና ተከሳሽነቴ ቀርቶ ምስክር ሆኜ እንድፈታ ለማድረግ የተለያዩ ጫናዎቸው ይደርሱብኝ ጀመር፡፡ ለአምስት ደቂቃ ያህል ጧትና ማታ ወደመፀዳጃ ቤት ለመሄድ ከሚከፍቱልኝ በስተቀር ለአስራሶስት ቀናት ያህል ብቻዬን አንድ መጥፎ ሽታ ያለዉ ክፍል ዉስጥ ተዘግቶብኝ ከረምኩ፡፡ በዚህ ወቅት ጉዳዬን የያዘዉ ዐቃቤህግ ማዕከላዊ በመምጣት እያስጠራኝ ሀሳቤን የማልለዉጥ ከሆነ እድሜ ልክ ወይም ሞት እንደሚያስፈርድብኝ ይዝትብኝ ነበር፡፡ ሀሰን ሽፋ በበኩሉ በሀሳባቸዉ የማልስማማ ከሆነ የያዘኝን የወጣት ጀብደኝነት ማስተንፈስ ለነሱ ከባድ ስራ አለመሆኑን ነግሮኛል፡፡ በኔ በኩል ደግሞ ከተጠረጠርኩበት ወንጀል ንፁህ መሆኔ እንጂ ኤልያስ ላይ በሀሰት መመስከሬ ሊያስፈታኝ እንደማይገባ ስለማምን ይህንኑ በተደጋጋሚ አስታዉቄ ተከሳሽ መሆንን መረጥኩ፡፡ ኢህአዴግ እስካለ ድረስ የተሻለዉን መጥፎ እየመረጡ መኖር ዕጣፋንታችን ከሆነ ቆየ አይደል?
ማዕከላዊ እያለሁ ከተፈፀሙብኝ የመብት ረገጣዎች ዉስጥ አንዱ የሆነዉ በአንድ ፖሊስ የተሰጠኝ ጥፊና ከግድግዳ ጋር ማጋጨት በተለይ ወንድ የፖለቲካ እስረኞች ከሚፈፀምባቸዉ ለዘላቂ የአካል ጉዳት የሚዳርግ ከባድ ድብደባ አንፃር ሳስተያየዉ የማዕከላዊ መርማሪዎች እንደሚሉት "ቁንጥጫ" ተብሎ ከመግለፅ የሚያልፍ ባለመሆኑ ብዙ ልልበት አልፈልግም፡፡ በወቅቱ የነበርነዉ ሴት እስረኞች ላይ ያን ያህል የከፋ አካላዊ ድብደባ አልተፈፀመም ማለት ግን የማዕከላዊ መርማሪዎች ለሴቶች ይሳሳሉ ማለት አይደለም፡፡ ለማሳያነት እስካሁን ድረስ ማዕከላዊ በተፈፀመባት ከባድ ድብደባ የተነሳ በህመም የምትሰቃየዋን የፖለቲካ እስረኛ እማዋይሽ አለሙን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አይ ማዕከላዊ! ማዕከላዊ ዘና ብለዉ የሚራመዱ ኩሩ የኢትዮጵያ ልጆች በገቡ ሳምንት በማይሞላ ጊዜ ዉስጥ በቃሬዛና በሰዎች ድጋፍ በሸክም ሲያሳልፉና የድረሱልኝ ዋይታ ሲያቀርቡ የሰማሁበት አሰቃቂ ቦታ ነዉ፡፡ ምስላቸዉ ከአይኔ ላይ፣ ጩኸታቸዉ ከጆሮዬ ተጣብቆ የሚኖረዉ እነዚህ ወገኖቼን እያሰብኩ መናደድ መቆጨት የዕለት ተዕለት የኑሮዬ አካል ሆኗል፡፡
የማዕከላዊዉን የመብት ረገጣ እዚህጋ ገታ ላድርገዉና በተለይ የፖለቲካ እስረኞችን ሰብአዊ መብት ከመጨፍለቅ አንፃር አምሳያዉ ወደ ሆነዉ የቃሊቲ እስር ቤት ልለፍ፡፡ ጳጉሜ3/2003 ዓ.ም ቃሊቲ እንደገባሁ በኋላ ላይ የጥበቃ ክፍል ሀላፊ እንደሆነች በተገነዘብኩት ሀላፊ አማካኝነት ጋዜጠኝነቴ ከታሰርኩ በኋላ የቀረ በመሆኑ ግቢዉ ዉስጥ በሚኖረኝ ቆይታ አርፌ መቀመጥ እንደሚኖርብኝ ተነገረኝ፡፡ አልጋ እስከሚለቀቅ ተብሎም እኔና በአንድ መዝገብ የተከሰስነዉ ወ/ሮ ሂሩት ክፍሌ ምንም እንኳን ሁለታችንም የሳይነስ በሽታ ያለብን ቢሆንም ሽንት ቤት አጠገብ መሬት ላይ ፍራሽ አንጥፈን እንድንተኛ ተደረገ፡፡ ዉድ አንባቢያን ስለቃሊቲ ስታስቡ ወደ አዕምሮአችሁ የሚመጡት ያማሩ ግንብ ቤቶችና የተዋቡ አልጋዎች ከሆኑ ኢቲቪ እንደሸወዳችሁ ልነግራችሁ እወዳለሁ፡፡ የፓስተር ዳንኤል ገ/ስላሴ ፕሪዝን ፌሎሽፕ የተባለ ድርጅት እንዳሰራቸዉ የሚናገሩት እነዚህ ያማሩ ግንብ ቤቶች ሁለት ክፍሎችና መፀዳጃ ቤት ብቻ ያሏቸዉ ሲሆኑ የተቀሩት በሴቶች ዞን ዉስጥ ያሉ ክፍሎች ከሁለት ያረጁ ግንብ ቤቶች በስተቀር በቆርቆሮ የተሰሩና እስረኞች በተጨናነቀ ሁኔታ የሚኖሩባቸዉ ናቸዉ፡፡ የቃሊቲ ምቾት አልባነት የሚሰማዉ አካልን ብቻ አይደለም፡፡ ቃሊቲ ከአካል በከፋ ሁኔታ ለነፍስና ለመንፈስ ይጎረብጣል፡፡ እንዴት ቢሉ እንዲህ እልዎታለሁ፡፡ የቃሊቲ የሴቶች ዞን ቤተመፃሕፍት ከጥቂት ወራት ጀምሮ በመፅሐፍቱ አይነትም ሆነ ቁጥር መሻሻልን ቢያሳይም እኔ ቃሊቲ ከገባሁ ጀምሮ እስከቅርብ ጊዜያት ድረስ ግን ከመኖር በማይቆጠር ደረጃ የሚገኝ ነበር፡፡ ይህንን ክፍተት ቤተሰብና ጓደኞቼ በሚያስገቡልኝ መፀሐፍት ለመሙላት ባስብም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሚመጡልኝ መፅሐፍት የቃሊቲን ሳንሱር እንደወደቁ ተገልፆ እኔጋ ሳይደርሱ ይመለሳሉ፡፡ ከነዚህ መፅሐፍት ዉስጥ አዲስአበባ ዩኒቨርስቲ የሚሳትማቸዉ የታሪክ መፅሐፍት ሳይቀር ይገኙበታል፡፡ ቃሊቲ ለመንፈስም አይመችም ያልኳችሁ በዚህ ብቻ አይደለም፡፡ በራሴ ወጪ ኢንድራ ጋኒዲ ናሽናል ኦፕን ዩኒቨርስቲ በርቀት ፖለቲካል ሳይንስ ለማጥናት ከብዙ ዉጣዉረድ በኋላ ተፈቅዶልኝ የተበዘገብኩ ቢሆንም የመማሪያ ሞጁሎቹን ለማስገባት ግን የቃሊቲ አለቆች ፍቃደኛ አልነበሩም፡፡ ከብዙ ደጅጥናት በኋላ ሞጁሎቹ ሲገቡ ደግሞ በትምህርቱ ዙሪያ ላነባቸዉ የሚገቡኝ አጋዥ መፅሐፍት ስለፖለቲካ የሚያወሩ በመሆናቸዉ በፍጹም ሊገቡ እንደማይችሉ የመፅሐፍት ገምጋሚዎቹ አረዱኝ፡፡ ይባስ ብሎ በዚያን ወቅት ከሌላዉ ጊዜ በተለየ ሁኔታ ምንም አይነት መፅሐፍት እንዳይገቡልኝ በመደረጉ ለጠቅላላ ዕዉቀት ያህል ሞጁሎቹን ማንበቤን ብቀጥልም ትምህርቱ ግን በዚህና በሌሎች ምክንያት ለማቋረጥ ተገደድኩ፡፡
በቃሊቲ የኔ ብቻ ሳይሆን ከእኔ ጋር የተቀራረቡ ወይም ደግሞ ሰላምታ ያቀረቡልኝ ሰዎች ሳይቀር መብታቸዉ ተጥሷል፡፡ ከሁለት አመታት በላይ የሚሆነዉን ጊዜ በርካታ እስረኞች በነበሩበት ክፍል ያሳለፍኩ ቢሆንም እኔን እንደሌላዉ እስረኛ ለመቅረብ የሞከሩ በሙሉ ስሜትን የሚጎዳ ወከባ፣ዘለፋና ለየት ያሉ ፍተሻዎችን አስተናግደዋል፡፡
በህክምና ጉዳይ የነበሩብኝን ችግሮች በተመለከተ ቤተሰቦቼ ደጋግመዉ የገለፁት መሠረታዊ ችግር በመሆኑ በዚህ ፅሑፍ ነካ አድርጌዉ ብቻ አልፋለሁ፡፡ ጡቴ ዉስጥ በበቀለዉ እጢ ምክንያት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህክምና ክትትል በማደርግበት ወቅት በቀጠሮዬ ቀን ወደ ሆስፒታሉ ከምወሰድባቸዉ ይልቅ የማልወሰድባቸዉ ጊዜያት ይበዙ ነበር፡፡ የግራ ጡቴ ቀዶጥገና ከተደረገለት በኋላ በወቅቱ ክትትል ታደርግልኝ የነበረችዉ ዶክተር በሶስተኛ ቀን የቁስሉ ፕላስትር መቀየር እንዳለበትና በሳምንቱ ደግሞ ክሩ መዉጣት እንዳለበት ገለፀችልኝ፡፡ አብረዉኝ የሚሄዱት አጃቢ ፖሊሶች ከዶክተሬም ጋር ስነጋገር እዛዉ ነዉና የሚቆሙት እንዲህ አይነቱን ነገር ለማድረግ የሚችል ጤናጣቢያ ማረሚያቤቱ እንዳለዉ ተናገሩ፡፡ እኔም ቀጠሮ ቢሰጠኝ እንኳ በዚህ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ወደሆስፒታሉ ተመልሼ መሄድ አዳጋች መሆኑን ስለማዉቅ የተባሉት ነገሮች ቃሊቲ መፈፀማቸዉን አልጠላሁትም፡፡ በመሆኑም ለህክምና ክትትል የሶስት ወራት ቀጠሮ ተሰጠኝ፡፡ ክሩ መዉጣት ባለበት ቀን ስለጉዳዩ ለጥበቃ ክፍሉ አስታወቅኩ፡፡ እነሱም አሁን ደቡብ ሱዳን ከሚገኝዉ ጦር ጋር አብራ ከተጓዘች አንዲት የህወሐት ታጋይ የነበረች ነርስ ጋር አገናኙኝ፡፡ እሷም እዛዉ ጨርሼ መምጣት እንደነበረብኝና እዚህ ክሩን ማዉጣት እንደማይችሉ ነገረችኝ፡፡ የምታሳየኝ ጥላቻ በሷ እጅ የህክምና አገልግሎት ከማግኘት ቢቀር የሚሻል መሆኑን የሚጠቁም በመሆኑ ብዙም ልከራከራት አልፈለኩም፡፡ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉ ሌሎች ሀላፊዎች ወደጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንዲወስዱኝ ብጠይቅም "ቀጠሮ የለሽም" በሚል ሰበብ ሳይወስዱብኝ ቀሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት የቀኝ ጡቴም ተመሳሳይ እጢ ያለበት በመሆኑ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ወደ ምኒሊክ ሆስፒታል ቀዶጥገና አደርግ ዘንድ የላከኝ ቢሆንም (ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በእድሳት ላይ በመሆኑ)እጅግ የከፋ ህመም ካልታመምኩ በቀር ቃሊቲ ሆኜ ቀዶጥገና ማድረጉን አልፈለኩም፡፡ በመሆኑም አልፎ አልፎ የሚሰማኝን ህመም በህመም ማስታገሻ መድሀኒቶች በማቃለል የቃሊቲን አስቀያሚ ቀኖች በመግፋት ላይ እገኛለሁ፡፡
ሌላዉ የቃሊቲ ቆይታዬን በተመለከተ ልጠቅሰዉ የምፈልገዉ ጉዳይ ከመንግስት አካላትና ከተለጣፊዎቻቸዉ ጋር ካለፍላጎቴ እንድንገናኝ እየተደረገ የሚፈፀምብኝ የሰብአዊ መብት ረገጣ ነዉ፡፡ ለምሳሌ ያህልአንዱን ብቻ ልጥቀስ፡፡ አምና መጋቢት ወር ዉስጥ አምባሳደር ጥሩነህ ዜናን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መምጣታቸዉን የገለፁ ሌሎች አስር ሰዎች ከአመት በፊት ወደገባሁበትና ከሌሎች ከአራት ሰዎች ጋር ብቻ ወደምኖርበት ክፍል መጡ፡፡ እኔም ኮሚሽኑ በተለይም ደግሞ አምባሳደሩ የሰብአዊ መብት አከባበርን አስመልክቶ የሚሰጧቸዉ ከእዉነት የራቁ መግለጫዎች የሚያሳዝኑኝ በመሆኑ ለመነጋገር ፍቃደኛ አለመሆኔን በማስታወቅ ከክፍሉ ወጥቼ በሩ ላይ ቆምኩ፡፡ ከሰዎች አንዱ የምኖርበትን ክፍልና አልጋዎቻችንን ፎቶ ሲያነሳ ተመለከትኩ፡፡ ገረመኝ፤ መሬት አንጥፌ ስተኛ፣በተደራራቢ አልጋ የላኛዉ ክፍል ላይ ከጡት ህመም ጋር እየታገልኩ ስተኛና በተፋፈገ ክፍል ዉስጥ ስኖር ለምን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ፎቶ አላነሳም? ማረሚያ ቤቱ በጥሩ ሁኔታ እስረኞቹን የያዘ መሆኑን ማሳያ ለማድረግ እንደተፈለገ ገመትኩ፡፡ እዉነታዉ ግን ይቺ ያለሁባት በቆርቆሮ የተሰራች ክፍልና ጠባቧ ግቢ አምና መስከረም ላይ በጠያቂዎች የመጎብኘት መብቴ መጣሱን ተከትሎ በጥድፊያ የተዘጋጀች ማግለያ ቦታ መሆኗ ነዉ፡፡ ክፍሉን ብቻ ፎቶ አንስተዉ መሄዳቸዉ ያላረካቸዉ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሰዎች በማግስቱ አራት ሆነዉ መጡ፡፡ ሁለቱ ወደግቢዉ ዉስጥ ሲገቡ ሌሎቹ ሁለቱ ደግሞ በሩጋ ቆሙ፡፡ ግቢዉ ዉስጥ ከገቡት አንዱ ትላንት ለምን ላናግራቸዉ እንዳልፈለኩ ጠይቆኝ በድጋሚ ከነሱ ጋር መነጋገር ያልፈለኩበትን ምክንያት እያስረዳኋቸዉ እያለ የግቢዉ በር ክፍት ስለነበር ግቢዉ በርጋ ከቆሙት አንዱ ፎቶ ሊያነሳኝ ሲሞክር ለመመልከት ቻልኩ፡፡ ምስሌን አንስቶ ቢሆንና ስለኔ አንዳች አይነት ዉሽት ሲናገሩ ብሰማ ጉዳዩን በዝምታ እነደማላልፈዉ ነገርኩትና ወደቤት ዉስጥ ገብቼ በሩን ዘጋሁት፡፡ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ከክፍሉ ወጥቼ ኢህአዴግ ማሰሩ ሳይበቃዉ ሰብአዊ መብትን ለማስከበር እንዳቋቋማቸዉ በሚናገረዉ ተለጣፊ ድርጅቶቹ ሳይቀር ሰብአዊ መብቴን ለምን እንደሚጥስ ከሀላፊዎቹ አንዷን በማስጠራት ጥያቄ አቀረብኩላት እሷም ሰዎቹ ካሜራ መያዛቸዉን እንደማታዉቅ ነገረችኝ፡፡ በ2005ዓ.ም ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የህዝብ ግኑኝነት ክፍል እኔን ለማናገር እንደመጣ የገለፀልኝ ሰዉ ኮቱ ዉስጥ ደብቆ በያዘዉ ሪከርደር ድምፄን ለመቅረፅ ሲሞክር ደርሼበት ይህንን ማድረግ የሚችለዉ የግል ፕሬስም ተገኝቶ ንግግራችንን የሚቀርፅ ከሆነ ብቻ መሆኑን ነግሬዉ ነበር፡፡ ይሄንን ያልኩበት ምክንያት የግል ፕሬሱ ባልተገኘበት ለመንግስት ሚዲያዎች ብቻ አስተያየታቸዉን የሰጡ ግለሰቦች ሀሳባቸዉ ተቆርጦና ተቀጥሎ ለማለት ያልፈለጉት ይዘት ይዞ እንደሚቀርብ አዉቅ ስለነበር ነዉ፡፡ የተናገርኩትን ሙሉዉን ነገር ቀርፀዉ ሊያወጡልኝ የሚችሉ አካላት በሌሉበት ለሰዉዬዉ አስተያየቴን መስጠት ያለፈለኩትም ይኸዉ እንዳይደርስብኝ በመስጋት ነበር፡፡ አስገራሚዉ ነገር ይቺ የኮሚሽኑ ሰዎች ካሜራ መያዛቸዉን እንደማይታወቅ የገለፀችልኝ ሀላፊ ያኔም የሰዉየዉን የድምፅ ሪከርደር መያዝ በተመለከተ ላቀረብኩላት ጥያቄ የሰጠችኝ ተመሳሳይ መልስ ነበር፡፡
የቃሊቲ ጉድ ማብቂያ ስለሌለዉ አንድ የመጨረሻ ጉዳይ ላንሳና የፅሁፌ መነሻ ወደሆነዉ የአመክሮ ጉዳይ አልፋለሁ፡፡ ዉድ አንባቢያን በሀገሪቱ ዉስጥ ያሉ የትኞቹንም እስረኞች አያያዝ የተመለከቱ ህጎችን፣ አዋጆችን፣ ደንቦችንም ሆኑ መመሪያዎችን በጣሰ ሁኔታ ከወላጆቼ በቀር ጠበቃን ጨምሮ በሌላ በማንም ሰዉ የመጎብኘት መብቴን ከተነጠቅኩ አመት ከኣራት ወራት አልፎኛል፡፡ አዛዉንት እናትና አባቴም ከእርጅና፣ ህመምና ድካም ጋር እየታገሉ የቃሊቲን ፈታኝ መንገድ መዉጣትና መዉረዳቸዉን ቀጥለዋል፡፡
ነገረ አመክሮ
ያለፈዉ አመት ነሐሴ ስምንት ቀን ከሰአት በኋላ ወደ ጠበቃ ክፍል ሃላፊዋ ቢሮ በአንዲት ፖሊስ ተጠርቼ ተወሰድኩ፡፡ እዚያም ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች ዋናዉ መስሪያ ቤት የይቅርታና የአመክሮ ጉዳይ ክፍል እንደመጣና ኮማንደር አስቻላዉ እንደሚባል ከነገረኝ ሰዉ ጋር ተገናኘሁ፡፡ ኮማንደሩ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ያቀረበልኝ የመጀመሪያዉ ጥቃቄ "ይቅርታ ለምን አልጠየቅሽም? ይቅርታ በመጠየቅ ላይ ያለሽ ሀሳብስ አልተቀየረም ወይ?" የሚል ነበር፡፡ ይቅርታ ያልጠየኩት ስላላጠፋሁና የተፀፀትኩበት ጉዳይ ስለሌለ በመሆኑና አሁንም ምንም የተቀየረ አቋም እንደሌለኝ አስረዳሁተ፡፡ "ይሄ የፍርድቤት ጉዳይ ነዉ፡፡ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ እስካለሽ ድረስ ወደዚያ መመለስ አይኖርብንም" አለኝ፡፡ እኔም አምባገነኑ የኢህአዴግ መንግስት እንዳሻዉ የሚያሽከረክረዉ ፍርድቤት በንፁሃን ላይ የጥፋተኝነት ዉሳኔና ፍርድ ማስተላለፉን አሜን ብዬ ይቅርታ የምጠይቅበት ምንም አይነት ምክንያት እንደሌለ ገለፅኩለት፡፡ ጥቂት ደቂቃዎች ያህል ስለጤንነቴና በጊቢዉ ዉስጥ ስለሚያጋጥሙኝ ችግሮች በተመለከተ ጥያዎችን ስያቀርብልኝ ቆየና ወደ መጣበት ሌላዉ ዋና ጉዳይ ተመለሰ፡፡
"ቅድም ይቅርታ የማልጠይቀዉ ስላልተፀፀትኩ ነዉ ብለሻል፡፡ አመክሮ እኮ የሚሰጠዉ ለተፀፀተ ሰዉ ነዉና እንዴት ልታደርጊ ነዉ?" በማለት ስለ በአመክሮ የመፈታት አካሄድ አንዳንድ የሚኒስተሮች ምክር ቤት ደንቦችን ጭምር በመጥቀስ ሊያብራራልኝ ሞከረ፡፡ "ታዲያ እንዲህ ከሆነ በይቅርታና በአመክሮ መሀል ምንም አይነት መሰረታዊ ልዩነት የለም ማለት ነዋ?" ለሚለዉ ጥያቄ ቀጥታ መልስ ሊሰጠኝ አልፈለገም ይልቁኑ ሁሉም ታራሚ 2/3ኛዉን የእስር ቅጣቱን ለመፈፀም ሁለት ወራት ገደማ ሲቀሩት እንደታረመና እንደተፀፀተ የሚገልፅ ፎርም መሙላት ስለሚኖርበት እኔም ለመፈታት ከፈለኩ ይህንኑ ማድረግ እንደሚጠበቅብኝ አስረግጦ ነገረኝ፡፡ የፃፍኩት የማምንበትንና መቼም ልቆምለት የምችለዉ እዉነት መሆኑን፣ በዚህ የተነሳ አሸባሪ መባሌ ደግሞ የበለጠ ኢህአዴግን እንድታገለዉ የሚየደርገኝ እንጂ የሚያፀፅተኝ ባለመሆኑ እንዲህ አይነቱን ከማንነቴ ጋር የሚቃረን ፎርም እንደማልሞላ አስረግጬ ነገርኩት፡፡ ኮማንደሩም ላልታረመና ለልተፀፀተ ሰዉ አመክሮ መስጠት ለእነሱም እንደሚከብዳቸዉ ከገለጸልኝ በኋላ "እኛ ፎርሙን ብንሞላልሽስ?" የሚል አስገራሚ ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡ እኔ "ታርሜያለሁ" እንዳልኩ ተደርጎ ምንም አይነት ነገር ቢደረግ ሀሰት መሆኑን ከማጋለጥ ወደኋላ እንደማልል አስታወቅኩት፡፡ በዚህ አይነት ተመሳሳይ ሀሳቦች ላይ እየተሸከረከርን ጥቂት ጊዜ ከፈጀን በኋላ እንዳሰብበት አሳስቦኝ ተለያየን፡፡
ይህ ከሆነ ሀሁለት ወራት በኋላ የመፈቻዬ ቀን የነበረዉ ጥቅምት 14/2007 ማለፊን ተከትሎ "የአመክሮ ፎርሙን ለምን አትሞይም?" የሚል ጥያቄ ከተለያዩ ሀላፊዎች ይቀርብልኝ ጀመረ፡፡ ከህዳር አጋማሽ ጀምሮ ደግሞ ጥያቄዉ እየጨመረ መጣ፡፡ በተለይ በመጨረሻዎቹ የህዳር ወር ቀናት በአንዱ አራት ሆነዉ ክፍሌ ድረስ በመምጣት አነጋገሩኝ፡፡ ለኮማንደሩ የሰጠሁትን ምላሽ ሰጠኋቸዉ፡፡ የሃለፊዎቹ ሁኔታ ከሁለት አመት በፊት የሆነዉን አስታወሰኝ፡፡ ያኔም የይቅርታ ፎርም ለመሙላት ፍቃደኛ ሳልሆን በመቅረቴ እንዳሁኑ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ፎርሙን እሞላ ዘንድ ይጠይቁኝ ነበር፡፡ በእንቢታዬ ስፀና ግን የተለያዩና አብዛኛዎቹም እስከዛሬ የዘለቁ የመብት ጥሰቶችን ይፈፅመብኝ ጀመር፡፡ ያሁኑስ እምቢታዬ ምን ያስከትል ይሆን? አላዉቅም፡፡ አንድ ነገር ግን አዉቃለሁ፡፡ መታረምና መፀፀት ያለብን ኢህአዴግ በሀገር ላይ የሚያደርሰዉን ጥፋት በመቃወማችን ምክንያት የታሰርን እኛ ሳንሆን አምባገነኑ መንግስት መሆኑን!
ዉድ አንባቢያን በመጨረሻ ሰብአዊ መብቶች የተከበሩባት ኢትዮጰያን ለማየት እንዲያበቃን እየተመኘሁ፣ ለተግባራዊነቱም የምችለዉን ሁሉ እንደማደርግና እንደምከፍል ቃል እየገባሁ እሰናበታችኋለሁ፡፡ "ምን ልታደርጊ ትችያለሽ?" የምትሉኝ ካላችሁ መልሴ የሚሆነዉ ማን እንደተናገረዉ ባላስታዉስም "የፍቅር አብዮት" የተሰኘ መጸሀፍ ሳነብ ያገኘሁት አንድ አባባል ነዉ ፡፡
" ሁሉን ማድረግ አልችልም ሁሉን ማድረግ አለመቻሌ ግን የምችለዉን ከማድረግ ወደ ኋላ አያስቀረኝም"
ርዕዮት አለሙ
ከቃሊቲ እስር ቤት
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment