Thursday, January 8, 2015

እኔም ህልም አለኝ ለኢትዮጵያ በ2015 እና ባሻገር!!!

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም 
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

“ልጆቻችሁ ወደፊት ምን ሊሆን እንደሚችል ይተነብያሉ…እናም ርዕይን  ይሰንቃሉ፣ የእናንተታላላቆች ደግሞ ህልምን ያልማሉ…”   

በመላው ዓለም ለምትገኙ ሁሉም አንባቢዎቼ እንኳን ለአውሮፓውያን አዲስ ዓመት በሰላምአደረሳችሁ!!!

በየዓመቱ ሁለት የአዲስ ዓመት በዓላትን አከብራለሁ፡፡ የመጀመሪያው እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 1 ቀን የሚውለውን የኢትዮጵያን አዲስ የዓመት በዓል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እ.ኤ.አ ጃኗሪ 1 ቀን የሚውለውን የፈረንጆችን አዲስ የዓመት በዓል ነው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ የሁለት አዲስ ዓመቶች በዓላማ ጽናት ላይ የተመሰረቱ ውሳኔዎችን ለመተግበር ቃልኪዳን እገባለሁ፡፡

“ለ2007 የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ውሳኔዎች” በሚል ርዕስ ባለፈው መስከረም ወር ባቀረብኩት ትችት በርካታ ድፍረትን የተላበሱ ውሳኔዎችን አስተላልፌ ነበር፡፡ ጥቂቶቹ ውሳኔዎች ለጥቂት ሰዎች በምንም መንገድ ሊተገበሩ የማይችሉ ተምኔታዊ መስለው ሊታይያቸው ይችል ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ወጣቶች ሀሳቦች ለማቀጣጠል ብዕሬን (የኮምፒውተር መክፈቻ ቁልፌን) በመጠቀም በጽናት በመቆም እየዳኸ የሚሄደውን አስመሳይነት እንዲዋጉ፣ ጎጂ እንደምታ ያለውን ተስፋቢስነት እና የህዝቡን የተስፋቢስነት ሽባነትን በመዋጋት እንዲያዳክሙ ኃይሉን እንዲያዳክሙ እና የሰብአዊ መብትን በአዲስ መልክ እና በአዲስ አስተሳሰብ በማስተማር እና በመስበክ የህብረተሰቡን የጥላቻ ፖለቲካ በማስወገድ በሀገሪቱ ላይ በፍቅር እና በመተሳሰብ ላይ የተመሰረተ የሰለጠነ የፖለቲካ አካሄድ ስሩን እንዲሰድ ለማስቻል መጣር አለብን የሚል የግል ዉሳኔየን አስተላልፌ ነበር ላዲሱ ዓመት፡፡

ሁሉም ወጣቶች በጠንካራ ተስፋ የተሞሉ ሀሳባውያን ለመሆናቸው ጥርጥር የለኝም፡፡ የአዲስ ዓመት ውሳኔዎች በተፈጥሯቸው ስሜታዊነት የተንጸባረቀባቸው፣ ሀሳባዊነት የሞላባቸው እና እንዲያውም በእውነታ ላይ ያተመሰረቱ እና ተግባራዊ ሊደረጉ የማይችሉ መሆን አለባቸው ብዬ አምናለሁ ፡፡

አንድ ሰው የሰብአዊ መብትን ለማስከበር ቃል ኪዳን ሲገባ እና በጽናት ለመተግበር ውሳኔ ሲያሳልፍ ምክንያታዊ የሆኑ ሀሳቦችን በማቅረብ ሊደገፍ ይገባል ምክንያቱም በአምባገነኖች እና በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች መካከል የሚደረገው ጠንካራ የሞት ሽረት ትግል በእራሱ በበጎ ነገር እና በጭራቃዊነት ዕኩይ ምግባራት መካከል የሚደረግ ትግል ነው፡፡ ሆኖም ግን መልካም ነገርም ሆነ ጭራቃዊነት ምግባሮች ዘላለማዊ አይደሉም፣ ሚጉኤል ሰርቫንተስ እንዲህ በማለት ጽፈው ነበር፣ “የጭራቃዊ ምግባር እድሜው በረዘመ ቁጥር መልካም ነገር እየቀረበ መምጣት አለበት”፡፡ በኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በላይ ጭራቃዊነት ድርጊት ተንሰራፍቶ ባለበት ሁኔታ እ.ኤ.አ በ2015 በጎ ነገር በየማዕዘኑ ማንዣበብ አለበት! ስለሆነም እ.ኤ.አ በ2015 እና በቀጣይ ዓመታት ግዙፍ እና እጅግ በጣም ግዙፍ የሆኑ በጽናት ላይ የተሞሉ ውሳኔዎች በስራ ላይ መዋል አለባቸው፡፡ በኢትዮጵያ አዲስ ዓመት በጽናት እንዲተገበሩ ከተያዙት ከእነዚህ ግዙፍ እና እጅግ በጣም ግዙፍ ከሆኑ ውሳኔዎቼ መካከል አንደኛው እንዲህ የሚል ነበር፣ “ስለኢትዮጵያ ህልም የእራሴን ርዕይ ሳይሆን አመለካከቴን ዘርዝሬ ማቅረብ እና ሌሎች ደግሞ በተመሳሳይ መልኩ የእራሳቸውን እንዲያቀርቡ ማድረግ አለብኝ ፡፡“ ሆኖም ግን በመጀመሪያ ደረጃ ህልሞች ምንድን ናቸው? ማለም ማለት ምን ማለት ነው? በህልም እና በሌሊት ቅዥቶች መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

ህልሞች ለህልም አላሚው ብቻ የተተው ልዩ የሆኑ ነገሮች ናቸው፡፡ ህልም አላሚው/አላሚዋ የእራሱን/ሷን ህልም በማለም ለእዚያ ህልም የእየራሳቸውን ትርጉም ይሰጡ እና ወደ ተግባር ይለውጡታል፡፡ ህልሞች ለግለሰቦች ብቻ አይደለም ጠቃሚነታቸው ሆኖም ግን ለህዝቦችም ጭምር ነው፡፡ ህልሞች የግለሰቡን/ቧን የማድረግ ዝንባሌ በእጅጉ ይገፋፉታል፡፡ የአፕል ኩባንያ ባለቤት ስቴቭ ጆብስ “ኮምፒውተርን በእያንዳንዱ ሰው እጅ ማስገባት“ የሚል ህልም ነበራቸው፡፡ በዚህም መሰረት በዓለም ታላቅ  ተፈላጊነት ያላቸው የኤሌክትሮኒክስ መሳሪዎችን  መፍጠር ችለዋል።  ጆብስ እንዲህ በማለት ተናግረው ነበር፣ “በመቃብር ቦታ ላይ ታላቁ ሀብታም መባል ለእኔ ትርጉም አይሰጠኝም…ዛሬ ጥሩ የሆነ አስደናቂ ነገርን ሰርተናል በማለት ወደ አልጋዬ ስሄድ ያ ለእኔ ልዩ የሆነ ትርጉምን ይሰጠኛል፡፡“

ህልሞች ለሀገሮች እና ለህዝቦች በጣም ጠቃሚ ነገሮች ናቸው፡፡ የአሜሪካ ህገመንግስት አርቃቂዎች ህልም ለማለም እራሳቸውን ከማዘጋጀታቸው በፊት ሊተገበር ቀርቶ ሊታሰብ የማይችልን ህልም አልመው ነበር፡፡ ህዝብ እራሱን በእራሱ በመረጠው መንገድ ማስተዳደር የሚችልበትን “እንከን የለሽ ስርዓት መገንባትን፣ ፍትህን እና ነጻነትን ለእነርሱ እና ለቀጣዩ ትውልድ ያረጋገጠ ማህበረሰብን አልመው እውን አድርገዋል፡፡”


እንደ እድል ሆኖ በአፍሪካውያን/ት ላይ ያሏቸው ህልሞች ግን አፍሪካውያንን/ትን በግዳጅ በመርከብ በመጫን ወደ አሜሪካ እንዲጓዙ እየተደረገ በባርነት የሌሊት ቅዠት አዘቅት ውስጥ እንዲገቡ ተደረገ፡፡ የእነዚያ ባሮች ዝርያ የሆኑት በስም ማርቲን ሉተርኪንግ የተባሉት ጥቁር አሜሪካዊ ከሁለት ምዕተ ዓመታት በኋላ የአሜሪካንን ህልሞች ለመካፈል እንዲችሉ ጥያቄ አቀረቡ፣ እናም በመጀመሪያ ለሬፐብሊኩ የቃል ኪዳን ክፍያውን ወዲያውኑ በመክፈል “ሁሉም ሰው፣ አዎ ጥቁር ሰው እንዲሁም ነጭ ሰው የማይሸረሸሩ የህይወት፣ የነጻነት እና ደስታን የማግኘት መብቶችን ተጎናጽፈዋል“ በማለት ትግላቸውን ቀጠሉ፡፡

ሲግመንድ ፍሬውድ እንዲህ የሚል ምልከታ አድርገዋል፣ “ህልሞች ወዳልነቁት አዕምሮዎች የሚሄዱበት አውራ መንገድ“ በመሆን ከነቃው አዕምሮ በታች በሆኑ ያልሰለጠኑ ሃሳቦቻችን እና ስሜቶቻችን ላይ ለመድረስ ያስችሉናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ህልሞች የምኞት ማሳኪያዎች በመሆን ያልነቁ እና በጥልቅ ተቀብረው ለሚገኙት አስተሳሰቦች መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችሉ ሂደቶች እንደሆኑ እምነት አድርገዋል፡፡ የእኛ የሌሊት ቅዠቶች በእኛ ሀሳቦች ላይ በጥልቅ የተቀበሩ እና ከሌሊት ጨለማ በፈቃደኝነት እራሳቸውን ነጻ ያደረጉ እንደሆኑ እምነት አለኝ፡፡

ህልሞች የተደበቁ ሚስጥሮችን ግልጽ ለማድረግ እና ቀጣዩ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ከዓምላካዊ ኃይል ጋር የምንገናኝባቸው መንገዶች ናቸው፡፡ በብሉይ ኪዳን አምላክ ህልሞችን እና ርዕዮችን (የሚጓዙ ህልሞች) የእርሱ ትዕዛዝ ታዋቂ መሆኑን ለማሳየት ይጠቀምባቸው ነበር፡፡ አምላክ ለጠቢቡ ሰለሞን እንዲህ የሚል ህልም ገልጾለት ነበር፣ “ለአንተ ምን ልሰጥህ እንደምትፈልግ ጠይቅ“ ሲለው ሰለሞን ደግሞ እንዲህ አለ፣ “ጥበብ ህዝብህን ለማስተዳደር ችሎታው እንዲኖረኝ እና በመጥፎ እና በበጎ ነገሮች መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት እንድችል አስተዋይ ልብ ስጠኝ ብሎ መረጠ፡፡“ እግዚአብሄር አምላክ እንዲህ በማለት ደንግጓል፣ “…ወንዶች እና ሴቶች ልጆቻችሁ እምነት ይኑራቸው፣ ወጣቶች ርዕይ ይኖራቸዋል፣ አዋቂዎች ደግሞ ህልምን ያልማሉ፡፡“

የመጀመሪያ የአሜሪካ ትውልድ ያላቸው ዜጎች (አሜሪካን እንዲያንስ) በሌሊት ጨለማዎች በማይታይ መልኩ በበጎ እና በመጥፎ ህልሞች (የሌሊት ቅዠቶች) ሲጎበኙ እንደሚያድሩ እምነት አላቸው፡፡ መጥፎ የሆኑ የሌሊት ቅዠቶችን ለማስወገድ እና በጎ ህልሞችን ብቻ ለማየት የሚያስችሉ በእጅ የተሰሩ ክር መሳይ ቋጠሮ ነገር ያላቸው በሀብል ተሰክተው  የተደረደሩ ሀብሎችን ከመኝታቸው እራስጌ የማስቀመጥ የተለመደ ባህል አላቸው፡፡ የቅዠት መከላከያ ሀብሎቹ በበጎ እና በመጥፎ ነገር መካከል ያለውን ድርጊት ይወክላሉ፡፡ በጎ ነገሮችን ባለምን ጊዜ ከእንቅልፋችን ስንነቃ በቀን ብርሀን መልካም የሆኑ ነገሮችን እናከናውናለን፡፡ ሆኖም ግን የመጥፎ ነገሮችን መንገድ የምንከተል ከሆነ የሌሊት ቅዠቶች ይኖሩናል እናም እራሳችንን በጨለማው ጎን በኩል እናገኛለን፡፡ በጎ ህልሞች ከተፈጥሮ እና ከትልቅ ሀሳብ ጋር ጥሩ መስተጋብር አላቸው፡፡

ህልሞች የሚያልሙ ህልም አላሚዎች አሉ፡፡ ማህተመ ጋንዲ ህልም አላሚ ነበሩ፡፡ ህልሞቻችንን በአግባቡ እንድንይዝ አስተምረውናል፣ “ሁልጊዜ በህልሞቻችሁ ላይ እምነት ይኑራችሁ ምክንያቱም እምነት የሌላችሁ ከሆነ ተስፋ የላችሁም“ በማለት ጋንዲ አስተምረዋል፡፡ ጋንዲ ለህልም አላሚዎች የሚያቀርቧቸው ምክሮች ተስፋ እንዲያርጉ እና ያለሟቸውንም ህልሞች ጽናትን በተላበሰ እና ቆራጥነትን ባካተተ መልኩ ህያው እንዲሆኑ እና እንዲተገብሯቸው ማድረግ እንዲችሉ እምነትን ማሳደር ነው፡፡ ለህልም አላሚዎች እንዲህ የሚል ምክርን ለግሰዋል፣ “በመጀመሪያ ይተውሀል፣ ከዚያም ይስቁብሀል፣ በመቀጠልም ይወጉሀል፣ በመጨረሻም አሸናፊ ትሆናለህ፡፡“

ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ (ማሉክ) የጋንዲን አስተምህሮቶች በመከተል አሸናፊ ሆነዋል፡፡ የዶ/ር ማርቲን ሉተር ህልም “በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጥቁር ዝርያ ያላቸውን ባሮች ከኢፍትሀዊነት የእሳት ነበልባል ውስጥ በማውጣት እረዥሙን የምርኮኝነት ወጥመድ በመበጣጠስ ፍትህ እና ደስታ የሰፈነበት ስርዓትን መመስረት ነበር፡፡” እንዲህ በማለት አልመዋል፣ “አንድ ቀን አሜሪካ ትነሳለች፣ ‘እነዚህ እውነታዎች በእራሳቸው ገላጭ ናቸው፣ ሁሉም ሰዎች እኩል ሆነው ተፈጥረዋል‘“ የሚል መርህ አስተምረዋል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ሁሉም ወንዶች እና ሴቶች እኩል ሆነው ተፈጥረዋል የሚል እምነትን አራምደዋል፡፡

ማሉክ እና ማልኮም ኤክስ “ስለአሜሪካ ህልም” መሰረታዊ የሆነ ልዩነት ነበራቸው፡፡ ማልኮም እንዲህ ብለው ነበር፣ “በአሜሪካ ለሚኖሩ የአፍሪካ ዝርያ ላላቸው 20 ሚሊዮን ጥቁር ባሮች የአሜሪክ ህልም ሳይሆን የአሜሪካ ቅዠት ነው ያለው፡፡ ስለኢፍትሀዊነት ረዥም ታሪክ፣ ክብርን ስለማጣት፣ ስለአድልኦአዊነት እና በአፍሪካ አሜሪካውያን/ት ላይ ይጫን ስለነበረው ልዩነት ሁኔታ“ የመብት ጥያቄዎችን በማንሳት በጽናት ይታገሉ ነበር፡፡

ማሉክ ዋጋቢስ የሆነውን ኃይልን በመጠቀም ሳይሆን ፍቅርን በመሳሪያነት በመያዝ የአሜሪካንን ህልሞ ማሳካት ይቻላል በማለት ያስተምሩ ነበር፡፡ ሰላማዊ በሆኑ የእንቢተኝነት ተቃዉሞዎች አማካይነት ከጨቋኞች ጋር በሰላማዊ መንገድ እና ማህበራዊ ኢፍትሀዊነትን አሳማኝ በሆነ መንገዶች በመዋጋት የመንግስት ታዛዥ አለመሆንን በማረጋገጥ መብትን ማስከበር ይቻላል የሚል እምነትን ያራምዱ ነበር፡፡ ማልኮልም በማንኛውም አስፈላጊ ሆነው በተገኙ ነገሮች ሁሉ የአሜሪካንን ቅዠቶች ለማስወገድ ይፈልጉ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ መካ ሄዱ እናም እዚያ በመገኘት ዋናው ነገር የቆዳ ቀለም አይደለም፣ ይልቁንም ትልቁ ነገር የልብ ቀለም ጉዳይ ነው በማለት አስተምረው ነብር፡፡ የፍቅር ቀለም ሁልጊዜ በጥላቻ ቀለም ላይ ያንጸባርቃል፡፡

እንደዚሁም ደግሞ ኔልሰን ማንዴላ የጋንዲን እና የማሉክን ፈለግ በመከተል አሸናፊ ሆነዋል፡፡ ማዲባ ለ27 ዓመታት ያህል በአፓርታይድ የማጎሪያ እስር ቤት የማቀቁ ሲሆን ለዘረኛው የአፓርታይድ ስርዓት አላጎነበሱም፣ አልተንበረከኩም፣ ፍርሀት አላሳዩም፣ እናም ስለነጻዋ ደቡብ አፍሪካ ማለማቸውን ለአፍታ ያህል እንኳ አላቋረጡም፡፡ ማዲባ በፕሬዚዳንትነት የመክፈቻ ስነስርዓት በዓላቸው ላይ የሚከተለውን ንግግር አሰምተው ነብር፣ “በፍጹም በፍጹም እንደገና በፍጹም ይህች የተዋበች ምድር አንዱ በሌላው የሚጨቆንባት ልትሆን አትችልም፡፡“ የፕሬዚዳንት ዲ. ሩዝቬልት ባለቤት የነበሩት ወ/ሮ ኤሊኖር ሩዝቬልት ታላቅ ህልም የነበራቸው ሴት ነበሩ፡፡ ምንም ምን ይሁኑ ሁሉም የሰው ልጆች በህግ ሊጠበቁ የሚገባቸው መብቶች አሏቸው ብለው ነበር፡፡ ወይዘሮዋ ስለሰው ልጆች እኩልነት፣ ክብር እና መብት ለሁሉም ህዝቦች እና ሀገሮች አንድ ዓይነት የሆነ የስኬት መለኪያ ያዘጋጀው እ.ኤ.አ በ1948 የጸደቀው የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ (ዓሰመድ) እውን እንዲሆን ህልም ነበራቸው፡፡ ወ/ሮ ሩዝቬልት የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶችን ድንጋጌ ያረቀቀውን ኮሚቴ በሊቀመንበርነት መርተዋል፡፡ ወ/ሮ ሩዝቬልልት በዘመናዊው የሰብአዊ መብቶች ንቅናቄ ትግል ውስጥ እናት እና ያልተዘመረላቸው ጀግኒት ሴት ነበሩ፡፡ እስቲ ለአፍታ ያህል እናስተውል! ያለወ/ሮ ኤሊኖር ሩዝቬልት ጥረት ዓሰመድ የሚባል ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ድንጋጌ አይኖርም ነበር፣ እናም ያለ ዓሰመድ እውን መሆን በርካታ የሆኑት ተከታታይነት ያላቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች እና ከሰብአዊ መብት ጋር በተያየዘ መልኩ ቁጥጥር የሚያደርጉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ቡድኖች ህጎች ሁሉ እውን የመሆናቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ነበር፡፡

የጥቂት ሰዎች ህልሞች ለበርካታዎቹ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ለሌሎች ህዝቦች ደግሞ ቅዠቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለመናገር የሚያዳግት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ አይሁዶች እና ሌሎች ህዝቦች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው የዓርያን ዝርያ ያላቸው ምርጥ ህዝቦች የዓለም ህዝብ ጌታ ናቸው እና ዓለምን መግዛት አለባቸው የሚለው የሂትለር ህልም ግን ህልም ሳይሆን ንጹህ የሌሊት ቅዠት ነው፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የተጠርጣሪ ተቃዋሚዎች ግድያ፣ ሌሎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህዝቦች ያለፍላጎታቸው በግዳጅ ወደ ሰራተኛ ካምፖች መጋዝ እና ሌሎችን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን በግዳጅ የህብረት እርሻ እንዲያቋቁሙ እና እንዲያርሱ በማድረግ ሶቪዬት ህብረትን ኃያል ለማድረግ አልሞ ተነስቶ የነበረው የስታሊን ህልም በእርግጠኝነት ህልም ሳይሆን ተራ ቅዠት ነበር፡፡

አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ ለዘላለሙ በጎሳ እና በዘር እንድትከፋፈል፣ የኃይማኖት ልዩነትን በማራገብ አንድ ሀገራዊ ግንዛቤ እንዳይኖር በማድረግ እና የኃይማኖት ጥላቻን በመቀፍቀፍ እንዲሁም ህዝቦችን በክልል ወይም ደግሞ ባንቱስታንስ እየተባለ የሚጠራውን የአፓርታይድን የዘረኝነት የጥቂት ነጮች የበላይ አገዛዝ ዘረኛ ፖሊሲ የሚያራምድ ስርዓት ጥቂት ለወጥ በማድረግ የኢትዮጵያን ህዝብ በዘር ከፋፍሎ ለዘላለሙ ለመግዛት የሚያስችል በነባራዊው ዓለም እውን ሊሆን የማይችል ህልም ሳይሆን ከእንቅልፋ ሲባንን  የሚታየውን ባዶ የሌሊት ቅዠትን አልሞ ነበር፡፡ በቅዠት የተሞላው ዘረኛ አምባገነን የአናሳ ቡድን መሪ ይህችን ዕጣ ፈንታዋ ለመልካም ነገር ያላደላትን የጀግኖች ሀገር ቢያንስ ለ50 ዓመታት እንደ ብረት ቀጥቅጦ እንደ ሰም አቅልጦ ለመግዛት እና የእርሱ ፓርቲ የሆነው እና እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት)  እያለ የሚጠራው ዘረኛ ከፋፋይ የሸፍጥ ፓርቲ ቢያንስ ለቀጣይ 100 ዓመታትን እንዲገዛ በድቅድቅ ጨለማ የሚከሰተውን እና ለሰዎች የሚታየውን ህልም ሳይሆን ቅዠቱን አሳውቆ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ በይፋ እና በሚስጥር በ10 ሺህ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን በየማጎሪያ እስር ቤቶች በማሰር እና ኢትዮጵያ ከዓለም እጅግ በጣም አስከፊ የሆነ የፕሬስ ነጻነት ድፍጠጣ ያለባት ሀገር እንድትሆን በማድረግ የመለስ ቅዠት በመጠኑም ቢሆን ተሳክቷል፡፡ የመለስ እና የፓርቲው ህልሞች ለኢትዮጵያውያን/ት ከሰውነት የወረደ እና እጅግ የተወሳሰቡ የኢትዮጵያ እና የህዝቦቿ አንድነት ጸር የሆኑ ቅዠቶች መሆናቸው በተግባር ተረጋግጠዋል፡፡ ይህም ማለት በመንግስት ላይ መንግስትን በመፍጠር የተካነው የመለስ የማፊያ ቡድን በእውናዊ ህይወት ላይ በአሁኑ ዘመን ሊተገበር ቀርቶ ሊታሰብ የማይገባውን የዝንጀሮ/የይስሙላ ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም፣ እንደ ነቀርሳ ገዝግዞ የሚጥል ተቋማዊ የሙስና ቢሮክራሲን በመፍጠር እና የጭቆና እና የወሮበላ ዘራፊነት ስርዓትን በማጠናከር፣ ስምየለሽ፣ ምግባረቢስ፣ ጨካኝ እና ህሊናየለሽ የሆኑ ስልጣን እንደ ምግብ የራባቸው ዘራፊዎችን በማምረት የመለስ እና የፓርቲው የቀን ቅዠት ተሳክቶለታል፡፡

ህልሞች ለታላላቅ የፖለቲካ ሁኔቶች ብቻ የተተው አይደሉም፡፡ ይልቁንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህዝቦች በየዕለቱ ሊያገኗቸው ስለሚገቡ ጥቅሞቻቸው ያልማሉ፡፡ ጥቂቶቹ ስለእድል ዕጣ ፈንታ ያልማሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ ስለታዋቂነት ያልማሉ፡፡ ሆኖም ግን ጥቂቶች ገንዘብን ስለማሳደድ የሚያልሙ ብቻ አይደሉም፣ ሆኖም ግን ሌላ ጥልቅ እና ግዙፍ የሆነ ምኞት አላቸው፡፡ በጥያቄ ላይ ናቸው፡፡

ህልም አላሚዎች የሚመረጡ አይደሉም፣ በእራሳቸው የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ተራ የሚባሉ ሰዎች ታላቅ ህልም አላሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ ውብሸት ታዬ፣ አንዷለም አራጌ እና ሌሎች እንደ እነርሱ ያሉ በርካታ ተራ ኢትዮጵያውያን/ት ህልምን የሚያልሙ ዜጎች ናቸው፡፡ እስክንድር በኢትዮጵያ ነጻነት የማይቀር መሆኑን ህልም አልሟል፡፡ እንዲህ በማለት በይፋ ተናግሯል፣ “ነጻነት ለየትኛውም ዘር አድሎአዊ መሆን የለበትም፡፡ ነጻነት እምነት ወይም ኃይማኖት የለውም፡፡ ነጻነት ለየትኛውም ጎሳ አይወግንም፡፡ ነጻነት በሀብታም እና በደኃ ሀገሮች መካከል ልዩነት መፍጠር የለበትም፡፡ በሚያስደምም ሁኔታ ነጻነት ኢትዮጵያን ማጥለቅለቁ የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡“

ርዕዮት ለህልሞቿ ተግባራዊነት በድፍረት እና በጽናት በመቆም መስዋዕትነትን ለመክፈል በመዘጋጀት እንዲህ ትላለች፣ “ነጻነት እና ዴሞክራሲን ለመጠየቅ በሰላማዊ መንገድ በአደባባይ በወጡ ንጹሀን ዜጎች ላይ ጥይት በመተኮስ መግደል፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን እና ነጻ ጋዜጠኞችን ማሰር… የመናገር እና የመጻፍ መብትን፣ በነጻ የመደራጀት እና ሀሳብን የመግለጽ መብትን መከልከል፣ በሙስና መዘፈቅ እና በአንድ አናሳ የጎሳ አባላት የበላይነት መገዛት የመንግስታችን መጥፎ እና እኩይ ምግባራት ናቸው፡፡ በጽናት ለቆምኩለት ዓላማ በድፍረት በመናገሬ እና ዘገባ በማቅረቤ ዋጋ ሊያስከፍለኝ እንደሚችል ጠንቅቄ አውቃለሁ፣ ሆኖም ግን ያንን ዋጋ በጸጋ ለመቀበል ዝግጁ መሆኔን አሳውቂያለሁ፡፡“ ርዕዮት ህልሞቿን ለማሳካት የ14 ዓመታት የሸፍጥ እስራት ዋጋን በመቀበል ላይ ትገኛለች፡፡

ባለብሩህ አዕምሮ ባለቤቱ እና ፈጣኑ የህግ ባለሙያ እና የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር የሆነው አንዷለም አራጌ በጭቆና ላይ የጋራ የሆነ ትግል በማካሄድ የጋራ የሆነ ድልን መቀዳጀት ይቻላል በማለት የማይናወጥ የትግል መንፈሱን በማደስ በመታገል ላይ ይገኛል፡፡  ለመጭው ትውልድ የነጻነት ቅርስን አውርሰን ማለፍ አለብን የሚል ህልምን አልሟል፡፡ እንዲህ የሚል ጠቅለል ያለ ህልሙንም ይፋ አድርጓል፣ “በዚህ ዓለም ላይ ሰው ተወልዶ እስከሚሞት ድረስ የነጻነትን ያህል ዋጋ ያለው ነገር እንደሌለ በጽናት አምናለሁ…የኢትዮጵያ ህዝብ በዋናነት የነጻነታቸው ባለቤት ሊሆኑ ያልቻሉበት ምክንያት የኢትዮጵያ ህዝቦች የእራሳቸው ችግር ነው…እኛ ኢትዮጵያውያን/ት በፖለቲካ፣ በኃይማኖት፣ በእድሜ ወይም በኢኮኖሚያዊ መደብ ሳንከፋፈል  ለነጻነታችን ስንል በውል በተጠና ዕቅድ እና በተጠናከር የትግል መንፈስ በመታገዝ ለነጻነታችን በጋራ መታገል አለብን፡፡ እኛ የነጻነታችን ባለቤት ያለመሆናችን ሚስጥር እኛ በተናጠል ወይም ደግሞ በጋራ የምናደርገው ትግል በቀዳሚነት በሀገር አቀፍ ደረጃ የህዝቡን ደህንነት ለማስከበር እና የመጭውን ትውልድ የሀገር ተረካቢነት ሚና በሚያስጠበቅ መልኩ የተቃኘ ያለመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ ለእያንዳንዳችን ምንም ዓይነት የመቆርቆር ስሜት የለም እንደዚሁም ሁሉ እያንዳንዳችን ለሁላችን የምናደርገው ክብካቤ እና ያገባኛል የሚል የተቆርቋሪነት ስሜት የለም፡፡“

በጽናት የተሞላው የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባል የሆነው በቀለ ገርባ ምንም ዓይነት የመጀመሪያ ደረጃ ዜጋ፣ የሁለተኛ ደረጃ ዜጋ…የሌሉባት እና ሁሉም ህዝቦች በመፈቃቀር እና በመከባበር የሚኖሩባት ሀገር መኖርን አልሟል፡፡ ህወሀት እየተባለ በሚጠራው ዘረኛ ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠሩትን 4 ዓይነት የዜግነት መደብ ቅዠቶችን በመጻረር እንዲህ የሚል ዓላማውን አራምዷል፣ “የመጀመሪያው የዜግነት መደብ መሬትን በበላይነት ተቆጣጥረው እንደ ጉልት ድንች የሚቸበችቡ እና የሚዘርፉ፣ ሁለተኛው የዜግነት መደብ ይህንን ከህግ አግባብ ውጭ የሚሰጠውን መሬት የሚቀበሉ፣ ሶስተኛው የዜግነት መደብ ደግሞ እንደዚህ ያሉት ህገ ወጥ የግብይይት ድርጊቶችን በታዛቢነት የመመልከት ሚና ያላቸውን የሚያካትት ሲሆን የመጨረሻው እና አራተኛው የዜግነት መደብ ደግሞ መሬቶቻቸው ከህግ አግባብ ውጭ በኃይል ተነጥቀው የሚወሰዱባቻው ፍትህ ያጡ ዜጎች ናቸው፡፡“

ለእምነቶች እና ለኃይማኖቶች ነጻነት መከበር በጽናት የሚሟገተው አቡባከር አህመድ የህግ የበላይነት እንዲከበር እና ማንም ይሁን ማን በስልጣን ላይ ያለ ግለሰብ ወይም ቡድን የሀገሪቱን ህግ የማክበር ኃላፊነት እና ግዴታ አለበት የሚል ህልም አለው፡፡ አቡባከር ለሀሳቡ ማጠናከሪያ ጭብጥ ሊሰጡ በሚችሉ ነገሮች ላይ ትኩረት በማድረግ እንዲህ ይላል፣ “እኛ ማንንም አመራር አልተቃወምንም፣ እኛ ያቀረብነው ጥያቄ ህገ መንግስቱ ይከበር የሚል ነው፣ እኛ እያልን ያለነው ህገ መንግስቱን ማክበር አለባቸው የሚሉት አካላት እራሳቸው ህገ መንግስቱን በይስሙላ አፋዊ ንግግር ሳይሆን በተጨባጭ ማክበር አለባቸው፡፡“

ህልሞች በጽናት እና በመንፈሰ ጠንካራነት ወደታለመላቸው ተግባር ተመንዝረው እውን እስካልሆኑ ድረስ በተጨባጭ ሊታይ የሚችል ፋይዳ ላቸውም፡፡ ህልሞች ወደ ተግባር እንዲሸጋገሩ ከተፈለገ አንድ ሰው በህልሞቹ ላይ ፍጹም የሆነ እምነት ሊኖረው ይገባል፣ በህልሞቹ ላይ ፍቅር ሊኖረው የግድ ነው፣ እናም ህልሞቹን ወደ ተግባር ለማሸጋገር ዝርዝር የሆኑ የድርጊት መርሀ ግብሮች ሊኖሩት እና እነዚያንም ዝርዝር ተግባራት በመፈጸሙ ረገድ እራሱን ባተሌ ማድረግ ወይም ደግሞ በከፍተኝ ደረጃ በስራው መጠመድ ይኖርበታል፡፡ አንድ ሰው የሰነቀውን ህልም ወደ ተግባር ማሸጋገር ካልቻለ በጨለምተኝነት እና በተስፋቢስነት ባህር ውስጥ እንደመስጠም ይቆጠራል፡፡

እኔ በኢትዮጵያ ላይ ያሉኝ ህልሞች፣

እኔ እራሴን ህልም አላሚ አድርጌ እቆጥራለሁ፡፡ ሆኖም ግን እንደ ማሉክ፣ ማንዴላ፣ እስክንድር እና ሌሎች አይደለም፡፡ የእኔ ህልም አላሚነት እንደ አንድ ተራ የአካዳሚክ እና የህግ ባለሙያ ድንገተኛ ህልም አላሚነት ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 በኢትዮጵያ የተካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ተከስቶ በነበረው ውዝግብ መለስ ዜናዊ የጦር አዛዥነቱን እና የደህንነት ኃይሉን በእራሱ ቁጥጥር ስር አድርጎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ያልታጠቁ ንጹሀን ዜጎች እንዲገደሉ እና በርካታዎቹ ቁስለኛ እንዲሆኑ እንዲሁም ብዙዎቹ በጅምላ ወደ እስር ቤት እስከተጋዙበት ጊዜ ድረስ የአሜሪካ ህልም ያውም የካሊፎርኒያ አንድ ህልም ብቻ ነበረኝ፡፡ ሆኖም ግን የአሜሪካ ህልሜ ቁሳዊ ፍጎቴን እንድታሟላልኝ ብቻ አልነበረም፣ ሆኖም ግን የሁሉንም የአሜሪካ ህዝቦች ፍላጎት እና ደህንነት የሚያሟሉትን እና ማሉክ በጽናት የታገሉለት እና ህይወታቸውን አሳልፈው ስለሰጡበት የተቀደሰ ዓላማ አጠቃላይ ህልም እንጅ፡፡ ለእኔ የአሜሪካ ህልም በቦታ እና በጊዜ የተወሰነ ነው ቶማስ ዎልፍ እንዲህ ሲሉ እንደገለጹት፣ “…ለእያንዳንዱ ወንድ እና ሴት ከትውልዱ እና ከትውልዷ ውጭ አንጸባራቂ እና ወርቃማ የሆነ እድል ቢኖረውም ወይም ቢኖራትም…በህይወት የመኖር፣ የመስራት፣ እራሱን/ሷን የመሆን እና ማንኛውንም ሰው የመሆን መብት እና ርዕይውን/ርዕይዋን መተግበር አድል ማግኘት ነው፡፡“

የመለስ ዜናዊ የ2005 ሰይጣናዊ የእልቂት ቅዠት ኢትዮጵያን በጽናት እንድደግፍ እና ለኢትዮጵያ ህልም እንዲኖረኝ አደረገኝ፡፡ ይኸ ህልም ከቅዠት እልቂቶች፣ በሰው ልጆች ላይ ከተፈጸመ ለመናገር የሚዘገንን ወንጀል እና ከኃያሉ አምላክ ፈቃድ የተወለደ ህልም ነው፡፡ ይህ ህልም በሰው ልጆች ሰብአዊ መብቶች ላይ ወንጀልን የፈጸሙ ወንጀለኞችን፣ ህዝቡን ባሰቃዩ እና የወገኖቻችንን መሬት በተቀራመቱ እና በዘረፉ ግፈኞች ዙሪያ በማተኮር እነዚህን ወንጀለኞች ለህግ በማቅረብ ላይ መሰረት ያደረገ ህልም ነው፡፡ አረመኔነትን፣ ጨካኝነትን እና በሰው ልጆች ላይ የተፈጸመን እልቂት በመቃወም የመጣ የሞራል ግዴታ ነው፡፡ ባለፉት በርካታ ዓመታት የተወለደው ህልም ስለሀገር አንድነት፣ ስለህግ እና የሞራል ጥያቄ እንዲሁም ስለተጠያቂነት፣ ስለሰለጠነ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ነበር፡፡ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ከታጎሩበት እስር ቤት እንዲወጡ ነበር የተያዘው ህልም፡፡ እንደዚሁም ሀሳብን በነጻ ስለመግለጽ እና ስለነጻው ፕሬስ እንዲሁም ነጻ የሆነ የህግ ስርዓት እና መልካም አስተዳደር እንዲኖር ነበር የነበረው ህልም…
እ.ኤ.አ በ2012 “ሰላም በኢትዮጵያ ህልም” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት ላይ የእውነተኛ ህልም አላሚነትን ለመግለጽ የሚያስችል የሙያ ብቃት እንዳለኝ ግልጽ አድርጌ ነበር፡፡ በዚያ ትችቴ ላይ ትክክለኛ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ህልም አላሚ ተብሎ ሊወሰድ እንደሚገባ የክርክር ጭብጤን አቅርቤ ነበር፣ ምክንያቱም ያ ሰው የፖለቲካ ዓላማ የለውም/የላትምና፡፡ የሰብአዊ መብት ፖለቲካ ሌላ ሳይሆን ስለ ሰው ልጆች ክብር እና መብት ጠበቃ ጉዳይ እንጅ ስለፖለቲካ ፍልስፍና ጉዳይ አይደለም፣ ስለፖለተካ ፓርቲ ወገንተኝነት ወይም ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲ ጽ/ቤት በማቋቋም የፓርቲን ዓላማ የማራመድ ጉዳይም አይደለም፡፡ በጽናት የሚታገል የሰብአዊ መብት ተሟጋች ግለሰብ በወደፊት የተሻለ የህዝቦች ህይወት መኖር በተስፋ እና በህልሞች የተሞላ ሰው እንጅ የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ ወይም ደግሞ ደረጃውን፣ የስራ ኃላፊነቱን፣ እንዲሁም ክብሩን ከፍ ለማድረግ የሚቋምጥ ሰው አይደለም፡፡

እንደ ህልም አላሚ ኢትዮጵያን ለበርካታ ዓመታት ከበዋት በነበሩ የሌሊት ቅዠቶች ላይ በተከታታይ ሁኔታ እጨነቃለሁ፡፡ እኔ ስለኢትዮጵያ ሰላም ያለኝ የመጨረሻው ህልሜ በኢትዮጵያ በቅርቡ ባለው ታሪክ እና ፖለቲካ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስልጣን ሽግግር  የሌሊት ቅዠት ሆኗል፣ በመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኝ የውድድር መስክ ሆኗል፡፡ ከንጉሳዊ የፈላጭ ቆራጭነት ስርዓት ወደ ወታደራዊ አምባገነንነት ስርዓት የተደረገው ሽግግር ግዙፍ የሆነ ጥፋት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በሶሻሊዝም ስም በፖለቲካው ዳፋ እና የረሀብ ሰለባ በመሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህዝቦች ለእልቂት ተዳርገዋል፡፡ ከወታደራዊ የሶሻሊዝም ወደ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በተደረገው ሽግግር በዘመናዊት የአፍሪካ ታሪክ ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ ኢትዮጵያን አቻ ወደማይገኝለት የፖሊስ መንግስትነት ቀይሯታል፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 ብልጭ ብሎ ታይቶ የነበረው የዴሞክራሲ ጭላንጭል ከመቅጽበት በብርሀን ፍጥነት እልም ድርግም ብሏል፡፡ በዚህ ዓይነት የታሪክ የሌሊት ቅዠት ውስጥ ብንሆንም ኢትዮጵያ በእራሷ ሰላሟ የተረጋገጠ ሀገር እንደምትሆን እስከ አሁንም ድረስ ህልም አለኝ፡፡

እ.ኤ.አ ጃኗሪ 2010 “ኢትዮጵያ፡ የወደፊቱ ትውልድ የወደፊት ሀገር ክፍል 1 እና 2” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችቴ በቅርብ ጥቂት አስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአቅም ማጣት ውጤት እና አሁን በህይወት በሌለው በመለስ ዜናዊ እና እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ እያለ በሚጠራው የእርሱ የዘረኛ የሸፍጥ የፖለቲካ ቡድን ስበስብ አማካይነት አራት የምጻት ቅዠት ፈረሶች  እንደሚመጡ ርዕይ ታይቶኝ እንደነበር መገለጼ የሚታወስ ነው፡፡ እንደዚሁም በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በኢትዮጵያ በአካባቢያዊ ውድመት ቅዠት ውስጥ እየተጨነቅሁ ነው ያለሁት፡፡ በገደብ የለሹ የህዝብ ብዛት፣ በደን ጭፍጨፋ እና ውድመት፣ በመኖሪያ አካባቢዎች ጥፋት እና ውድመት፣ በአፈር መሸርሸር እና የለምነት መሟጠጥ፣ በንጹህ የመጠጥ ውኃ እጥረት እና መበከል፣ እንዲሁም አካባቢዎች ከመጠን በላይ በእንስሶች በመጋጥ፣ የበረሀነት እየተስፋፋ መምጣት እና በመሳሰሉት ምንም ዓይነት ስህተት በሌለው መልኩ ስለወደፊቱ የሚሰጡትን የማስጠንቀቂያ ምልክቶች እያየሁ ስወዲፊቱ የሚመጣ ውድመት በጣም እጨነቃለሁ፡፡

እንደ ዩናይትድ ስቴትስ የህዝብ ቆጠራ ቢሮ ዘገባ ከሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ከ35 ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በሶስት እጅ እጥፍ በማደግ ወደ 278 ሚሊዮን በመድረስ ከዓለም በህዝብ ብዛታቸው እጅግ ፈጣን ከሆኑት አስር ሀገሮች መካከል አንዷ እንደምትሆን በማያሻማ መልኩ ትንበያ ሰጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እድገት ለበርካታ አስርት ዓመታት ያለምንም ማቋረጥ ተከታታይነት ባለው መልኩ ወደ ላይ በማሻቀብ ላይ ይገኛል፡፡ እ.ኤ፣አ በ1967 የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር 23.5 ሚሊዮን ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1990 ይህ አሀዝ ወደ 51 ሚሊዮን ከፍ አለ፡፡ እ.ኤ.አ በ2003 68 ሚሊዮን ደረሰ፡፡ እ.ኤ.አ በ2008 ያ የህዝብ ብዛት ቁጥር ወደ 80 ሚሊዮን ከፍ በማለት ተመነደገ፡፡ እ.ኤ.አ  በ2014 የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት 98 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፡፡ እ.ኤ.አ ከ1995 ጀምሮ የኢትዮጵያ ዓመታዊ አማካይ የህዝብ እድገት መጣኔ 3 ከመቶ በላይ በመሆን እድገቱን ቀጥሏል፡፡ እ.ኤ.አ በ2050 የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት አሁን ካለበት በሁለት እጅ እጥፍ እንደሚጨምር የተተነበዬ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ወሳኝ፣ በውል በተጠና ሁለገብ ዕቅድ እና ፖሊሲ መሰረት መጠነ ሰፊ የሆነ ፈጣን የሆነ የፖሊሲ እርምጃ እስካልተወሰደ ድረስ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንዴት ልትቀጥል እና ልትኖር ትችላለች? በኢትዮጵያ ከሶስት አስርት ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይከሰታል ተብሎ የሚፈራው የአካባቢ እና የህዝብ ውድመት የሌሊት ቅዠትን ብቻ የሚሰጠኝ ሳይሆን በጠራራ ፀሐይ ፍንትው ባለው የቀን ብርሀን ወደ ገሀነም የሚጨምር አስፈሪ ክስተት ሆኖብኛል፡፡ ከዚህ በታች በቀረቡት በሁሉም የሌሊት ቅዠቶች በቅዠት በመጨነቅ ላይ እገኛለሁ፡ 1ኛ) እራሱን እንደ ደቡብ አፍሪካ የጥቂት ነጮች የዘረኝነት የበላይ አገዛዝ አስመስሎ ሳይሆን በእርግጠኝነት ሆኖ በማተራመስ ላይ ያለው የዘረኛ ቡድን የአፈና አገዛዝ ስርዓት ወደ ግብዓተ መሬቱ የሚገባው መች ነው? 2ኛ) ገጣሚ ቲ.ኤስ ኤሊዮት በግጥሞቻቸው የመካከለኛው ክፍል እንዲህ በማለት በገጠሟቸው መልኩ ባለው ሁኔታ ይጠናቀቅ ይሆን? ደናቁርት በሆኑ በማያውቁ ሰዎች፣

ሀሳብ በሌላቸው በባዶ ምንደኞች፣
የቅዠት ልብ እንጅ በራዕይየለሾች፣
በአምባገነኖች ኃይል ዓለም ትገዛለች፣
መሻሻልም ሳይሆን በዚያው ታከትማለች፣
ለውጥን ሳታመጣ በዚያው ትቀራለች፣
ዓለም የምታልፈው በጩኸት አይደለም፣
በነጎድጓድ ክስተት በኃይልም አይደለም፣
ወይም በመረገም በጥንቆላ አይደለም፣
በሌላም በሌላም በምንም አይደለም፡፡
ሆኖም ግን በጩኸት ጊዜን በወሰደ፣
ባጨር ጊዜ ሳይሆን በቋፍ በወረደ፣
ባምባገነን ስሜት ቅጥፈት በለመደ፣
በጎ ነገር ሳይሆን ክፋት በወደደ፣
ለሰው ክብር ሳይሰጥ ህዝብን ባዋረደ፡፡
በጊዜ ርዝመት ነው ዓለም የሚጠፋው፣
በእኩይ ምግባሮች ፍጹም በገለማው፣
በህዝቦች ዝምታ እንዳላዩ አይተው፣
እንዳልሰሙ ሰምተው ለመናገር ፈርተው፣
በፍርኃት እርደው በይሉንታ ታንቀው፣
ምን አገባኝ ብለው በሰላም ተኝተው፣
ሀገር በምጥ ሆና ሀሴትን አግኝተው፣
አፎች ዝም ሲሉ ነው ዓለም የሚጠፋው፣
ብዕር ሲነጥፍ ነው ዓለም የሚያከትመው፡፡

3ኛ) እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ የሚጠራው ከፋፋይ እና ባዶ የዘረኛ አናሳ ቡድን ስርዓት ማክተሚያው መቼ ሊሆን ይችላል?

እንደዚሁም ሁሉ ለአፍሪካ በጣም የተጋነኑ ህልሞች አሉኝ፡፡ እ.ኤ.አ ኤፕሪል 2014 “አፍሪካ ተስፋ ሊኖራት ይችላልን?” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት የመንግስታት የተቆለሉ ስህተቶች ሰብአዊ መብቶችን በማክበር እንደሚተኩ እና የአፍሪካ መንግስታት ህዝባቸውን የሚፈሩበት እንዲሁም ህዝቡ መንግስታትን የሚፈራበት ባህል ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እስከ ዘላለሙ የሚወገዱበት ጊዜ እንደሚመጣ ታላቅ ርዕይ እንዳለኝ ገልጫለሁ፡፡ እንደዚህ እና እንደዚህ ያሉ የተጋነኑ ህልሞች ናቸው እንግዲህ የአንድ ተምኔታዊ አፍሪካዊ የኢትዮጵያ ባለርዕይ ህልሞች፡፡
ታላቁ ፈላስፋ ሶቅራጥስ እንዳስተማሩት አልማለሁ ምክንያቱም ከህልም ውጭ ህይወት ትርጉምየሌለው ተመርምሮ የማያውቅ ህይወት ነውና፡፡

ጆርጅ በርናርድ ሻው ህልም ማለም አስፈላጊነቱ ለምን እንደሆነ በግልጽ አስቀምጠውታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የአውሮፓ የአንደኛውን ዓለም ጦርነት ተከትሎ በአውሮፓ ልብ ሰባሪ በሆነ መልኩ ተከስቶ በነበረው ድህነት እና ስቃይ ሻው “ወደ ማቱ ሳላ ለመመለስ” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጨዋታ ላይ ሁሉንም ጥያቄዎች ለማጠናቀቅ እንዲህ የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡ “ነገሮችን ትመለከታለህ እናም ለምን? ትላለህ፡፡ ሆኖም ግን ከዚህ ቀደም በፍጹም ታልመው የማያውቁ ህልሞችን አልማለሁ፣ እናም ለምን አይሆንም አላለሁ?”

ለእኔ ህልም አላሚዎች በማንኛውም ህልም ውስጥ ከአማካይ በላይ ማሰብ የሚችሉ ናቸው፡፡ ኤንስተን እንደተመለከቱት “ሀሳባዊነት ከእውቀት በላይ ጠቀሜታ አለው፡፡“ ህልም አላሚዎች የሀሳብ የእውቀት ፋብሪካዎች ናቸው፡፡ ሊሆኑ ከማይችሉ ህልሞች ሊሆኑ የሚችሉ ህልሞችን ያልማሉ፡፡ አላሚዎች ኮረብታዎችን እና ተራሮችን ለመውጣት እና በከፍተኛ ተነሳሽነት እና በታላቅ ሞራል ሊወጡ የሚችሉ ስንት ኮረብታዎች እና ተራሮች እንደቀሩ አስቀድመው ይመለከታሉ፡፡ ኮረብታ በኮረብታ፣ ተራራ በተራራ፣ ደረጃ በደረጃ፣ ትንሽ በትንሽ፣ ድንጋይ በድንጋይ፣ ጡብ በጡብ፣ ቀን በቀን፣ ማይል በማይል እና በመሳሰሉት ኋይትኔይ ሀውስተን እንደ ዘመረው ሁሉ በተከታታይ በመስራት ረገድ ያለምንም ድካም እና መሰላቸት መቀጠል እንዳለበት ግንዛቤ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡
ባለፉት በርካታ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለቁጥር የሚያዳግቱ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችን፣ የባህል እና የኃይማኖት መሪዎችን፣ ንግግሮች አዳምጫለሁ፡፡ እውነት ለመናገር ቃላትን ሲናገሩ እሰማለሁ ሆኖም ግን ህልም ሲያልሙ ሰምቸ አላውቅም፡፡ በቃላታቸው ህልምን ሲያልሙ አይቼ አላውቅም፡፡ የምሰማው ግን ስለሀገራችን በጥላቻ የተሞሉ የብስጭት ቃላትን ነው፡፡ ሆኖም ግን ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዳደረጉት ፍቅርን የተላበሰ ወንድማዊ የሆነ ቆንጆ የሽግግር ሂደትን ሲያከናውኑ አይታዩም፡፡ አሁን በህይወት የሌለውን እና ሎሌዎቹ እንደሚሉት ሳይሆን ታላቅ ያልሆነውን ባለራዕይ መሪ ተብዬው የሚያደርጋቸውን ንግግሮች ብዙ ጊዜ ተከታትያለሁ፡፡ የእርሱ ራዕይ ምን እንደነበረ እና ምን መሆን እንዳለበት ገና ነቅሸ ማውጣት አለብኝ፡፡ የእርሱ ደቀመዝሙሮች የእርሱን ራዕይ ለመከተል አላይም እታችም በመርገጥ በመደነባበር ላይ ይገኛሉ፡፡ ምናልባትም ራዕይ እንደተመልካቹ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አደገኛ  ሁኔታ ባለበት እና ዉጥረት በበዛበት የጥላቻ ከባቢ አየር ውስጥ ስለራዕይ ማውራት ለማስተማር እና ስምምነትን ለማምጣት ሳይሆን የማደናገር እና የማውገርገር ዓላማን ለማራመድ ብቻ ነው፡፡ ለአንዳንዶቹ ተምኔታዊ እና የተሳሳቱ ሀሳቦች ህልሞች ናቸው፡፡ እንዲህ የሚለውን የቻይና ፕሬዚዳንት የነበሩትን የኤክስ አይ ጂንፒንግ ንግግር እከተላለሁ፣ “ብሄርን ለማደስ፣ የህዝቦችን የኑሮ ህይወት ለመለወጥ፣ ለብልጽግና፣ የተሻለ ማህበረሰብን ለመፍጠር እና የወታደራዊ አቅምን ለማጎልበት የተያዘ ህልም ነው፡፡“ የቻይና ወጣቶች ህልም እንዲያልሙ ያደፋፍራሉ፣ እንዲሁም ህልሞቻቸውን በጥንቃቄ ወደ ተግባር በማሸጋገር የሀገሪቱን እድገት ማፋጠን ያስፈልጋል በማለት አጽንኦ ሰጥተው ተናግረው ነበር፡፡

ኢትዮጵያውያን/ት የእራሳቸው የሆነ ህልም ለምን እንደማይኖራቸው ምንም ዓይነት ምክንያት የለም ወይም በየትኛውም የስራ መስክ ያሉ ኢትዮጵያውያን/ት ሁሉ እና በተለይም ደግሞ በአመራር ቦታ ላይ ያሉ ወይም ወደ ስልጣን ማማ ላይ ለመውጣት በሚፈልጉ ሰዎች እንደዚሁም ለመማር የታደሉት ስለኢትዮጵያ ያላቸውን የእራሳቸውን ህልም ማለም አይችሉም፡፡
ስለሆነም የእኔ እ.ኤ.አ የ2015 እና በቀጣዮቹ ዓመታት የሚኖሩኝ ህልሞች ምንድን ናቸው?እነሆ!

1ኛ) ኢትዮጵያ በሰላም እንድትኖር አልማለሁ፣
2ኛ) ኢትየጵያ እንደ ሀገር በታሪኳ ተከብራ ህዝቦቿ ከስቃይ እና ከመከራ ተላቅቀው የተባበረች እና የተከበረች ሆና ለማየት አልማለሁ፣
3ኛ) በኢትዮጵያ ወንድማዊ እና የእህትነት ፍቅር እንዲነግስ አልማለሁ፣
4ኛ) ኢትዮጵያውያን/ት በጎሳ ማንነታቸው ሳይሆን ሰው ሆነው በመፈጠራቸው ብቻ መተባበር እንዳለባቸው አልማለሁ፣
5ኛ) ሁሉም ኢትዮጵያውያን/ት ከጎሳ፣ ከኃይማኖት እና ከአካባቢያዊ መንደርተኝነት ውጭ በሆነ መልኩ “እኔ የወንድሜ እና የእህቴ ጠባቂ ነኝ የሚል እምነትን እንዲያሳድሩ” አልማለሁ፣
6ኛ) እውነታው ከውሸት አመድ እንዲወጣ እና ሁሉም ኢትዮጵያውያን/ት በእውነተኛ የእርቅ መንገድ ላይ እንዲጓዙ አልማለሁ፣
7ኛ) በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ የመንግስት ስህተቶች አንድ ቀን በሰብአዊ መብቶች ጥንካሬ እንዲጠፉ አልማለሁ፣
8ኛ) ኢትዮጵያውያን/ት ሀገርን ለመግንባት ከሚደረገው ልዩነት ይልቅ የጦርነትን እና የግጭትን እርባናየለሽነት እንዲሁም አብሮ የመስራትን እና የመተባበርን ጠቃሚነት ከግንዛቤ በማስገባት ተባብረው እና ተፈቃቅረው እንዲሰሩ አልማለሁ፣
9ኛ) ህገወጦች በህግ ስም የሚሰሩት ደባ ለአንደዴ አና ለመጨረሻ ጊዜ ከሀገሪቱ ጠፍቶ በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት ለዘላለም እንዲሰፍን አልማለሁ፣
10ኛ) ኢትዮጵያ ከአምባገነኖች እና ከጨቋኝ ገዥዎች እራሷን ነጻ አድርጋ ትክክለኛ የብዙሀን የፖለቲካ ፓርቲ አስተዳደርን በማስፈን ለሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ጠንካራ ተቋም ገንብታ በደስታ እና በሰላም እንድትኖር አልማለሁ፣
11ኛ) የኢትዮጵያ ምሁራን ወንዶች እና ሴቶች በቀሰሙት ምሁራዊ ኃይል እና ባካባቱት መልካም ተሞክሮ እየተመሩ የኢትዮጵያን ህዝብ እንዲያስተምሩ፣ እንዲሰብኩ እና ከህዝቡ ጋር እጅ እና ጓንት በመሆን ሀገራቸውን እንዲገነቡ አልማለሁ፣
12ኛ) የእኔ ትውልድ የሆኑት ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያዊያት ከተኙበት እንቅልፍ በመነሳት እና ከተወሸቁበት የፍርሀት ቆፈን ውስጥ ፈንቅለው በመውጣት የተስፋ ጨለምተኝነትን፣ በእራስ ያለመተማመንን እና እራስ ወዳድነትን በማስወገድ ለመጭው ትውልድ መልካም አሻራ ጥለው እንዲያለፉ አልማለሁ፣
13ኛ) በሁሉም ኢትዮጵያውያን/ት ዘንድ የሰለጠነ አስተሳሰብ እና በዜጎች መካከል መቻቻል የሰፈነበት ግንኙነት እንዲኖር አልማለሁ፣
14ኛ) ሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ አስረኞች እንዲፈቱ እና ከቤተሰቦቻቸው እና ከወገኖቻቸው ጋር እንዲገናኙ አልማለሁ፣
15ኛ) በኢትዮጵያ ያሉ በሰው ልጆች ላይ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ወንጀልን የፈጸሙ ሁሉም ወንጀለኞች ለህግ ቀርበው ለጥፋታቸው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ አልማለሁ፣
16ኛ) ይህ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ትውልድ የመጨረሻ የሆነ ሰላም፣ ነጻነት እና ዴሞክራሲ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲያስተላልፍ አልማለሁ፣
17ኛ) ኢትዮጵያውያን/ት ሁሉ በእራሳቸው እምነት እንዲያድርባቸው እና የፖለቲካ ደባን በመስራት እና ተንኮልን በመሸረብ በፖለቲካ በመከፋፈል ከእኩይ ድርጊቱ የፖለቲካ ትርፍን ለማትረፍ ከሚቅበዘበዙ ሰው መሳይ ሸንጎዎች ላይ አምላክ እምነቱን በመንፈግ  ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥንካሬውን እና ጽናቱን እንዲሰጥ እና እንዲያጎናጽፍ አልማለሁ፣
18ኛ) የኢትዮጵያ ወጣቶች ሙሉ ኃላፊነት በመውሰድ የሀገራቸውን ዕጣ ፈንታ የጥላቻ እና የዘረኝነት ፖለቲካን በማስወገድ ፊታቸውን በሞራል ኪሳራ ወደሚዳክሩት የድሁር አስተሳሰብ ባለቤቶች በማዞር ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ በውይይት፣ በስምምነት እና በመግባባት ላይ የተመሰረተ አዲስ የፖለቲካ ስርዓትን በመፍጠር የታሪክን ጎማ ወደፊት እንዲያሽከረክሩ አልማለሁ፣
19ኛ) ወጣቶች ከቀዳሚ ትውልዶች ጥበብን በመማር አሁን ለወጣቱ ለማስረክብ እያዘጋጁት ያለውን ዓላማ በማፋጠን ኢትዮጵያ ነገ ለወጣቱ ትውልድ መሆን እንድትችል አልማለሁ፣

ባለፈው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ውሳኔዎቼ ላይ የኢትዮጵያን ህልሞች እንደማዘጋጅ እና ሌሎችም የእራሳቸውን ህልሞች እንዲያዘጋጁ የእራሴን ኃላፊነት (ርዕይ ሳይሆን) እንደምወስድ ቃል ገብቸ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ጓዶቸ አላሚዎችን እንደገና ለህልሞቻቸው በጽናት እንዲቆሙ እንዲህ በሚሉት በላንግስተን ሁግስ የግጥም ስንኞች ጀባ እላቸዋለሁ፡

ህልሞችን በአስቸኳይ ካልተገበርናቸው፣
ክንፍ እንደሌለው ወፍ ህይወት አልባ ናቸው፡፡
ክንፈ ሰባራ ወፍ በአየር ላይ አይበርም፣
እባብ በባህር ላይ አይስለከለክም፣
ባቡር ባስፋልት ላይ አይምዘገዘግም፣
ህልሙን ያልፈታም ሰው ድል አይቀዳጅም፡፡
ህልም እና ተግባራት ህብረት ካልፈጠሩ፣
ህልም ተፈብሮኮ ከቀረ ተግባሩ፣
አራምባና ቆቦ ይሆናል ነገሩ፣
ሀቅን ተናገሩ አትበሉ እሽሩሩ!…

ወደተግባር ያልተሸጋገረ ህልም ምን ይሆናል? የሌሊት ቅዠት ሊሆን ይችላልን?

ህልሞች ሁልጊዜ እውነት ይሆናሉ፡፡ ጥቂት ህልሞች ደግሞ ወደ ሌሊት ቅዠትነት ይቀየራሉ፡፡ ወደተግባር ያልተሸጋገሩ ህልሞችን ውስጣዊ ባህሪ ለመገንዘብ በጣም ከባዶች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ገጣሚ ላንግስተን ሁጌ እንዲህ የሚሉ የግጥም ስንኞቹን ለመቋጠር የተገደዱት፡

ህልም ባይፈጸም ምንድን ይደረጋል?
ህልምነቱ ቀርቶ በቅዠት ይለካል?
ወይስ ይህን ትቶ እንደገና ማለም?
ስቃይን ለማብዛት ባሻንጉሊቱ ዓለም?
በጠራራ ፀሐይ እንደደረቀ ወይን፣
አንደበሰበሰው እንደ ጥቅል ጎመን፣
አምልጦ ሊሄድ ነው ሊሰወር ከወገን?
ወይ እንደ ጠነባ እንደገማ ስጋ፣
የከረፋ ሽታው በሩቅ የሚወጋ፣
ወይ ደግሞ እንደ ኬኩ በስኳር ያበደው፣
እንደ ጣፋጩ ጁይስ በደንብ የተሰራው
እንደ ከባድ ጭነት ሸክም እንደጎዳው፣
ዘንበል ለጠጥ ማለት አቅም እንዳነሰው
ወይስ እንደ ቦምቡ ድኝ እንደተሞላው፣
ባሩድን በሆዱ ጠቅጥቆ እንደያዘው
ለመፈንዳት ብሎ ሁኔታው ሲመቸው?
የእኔ በኢትዮጵያ ሊሆን የሚችለው ህልም ነው፣

ወደ ተግባር ሊሸጋገሩ የማይችሉ ህልሞችን ነው በማሳደድ ላይ ያለሁት?

በዚህ ትችት የመክፈቻ ዓረፍተ ነገሮች ላይ ለኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ያቀረብኳቸው ውሳኔዎች እጅግ በጣም ግዙፍ የሆኑ እና ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚያስቸግሩ ሊመስሉ ይችላሉ የሚል ማስታዋሻ ማቅረቤ ይታወሳል፡፡ ከዚህ አንጻር “ተግባራዊ ሊሆን የማይችለው የወሮበላ የማፊያ ቡድን አመራር የሆነው የላ ማንቻ ሰው” በሚል ርዕስ የቀረበውን የሰርቫንቴን ታላቅ የጽሁፍ ማጣቀሻ ዋቢ በማድረግ አቅርቢያለሁ፡፡ ያ የስነጽሁፍ ባህሪ ያለው ሀረግ አይመስልም፡፡ የላ ማንቻን ሰው የምወዳቸው ብሆንም ሊሆኑ በማይችሉ ህልሞች ውሰጥ ተቆልፎባቸው የሚገኙትን እና ሊተገበሩ በሚችሉት ህልሞች ላይ ጥያቄ አቀርባለሁ፡፡ በስነጽሁፉ ጥያቄው ላይ (በቀን ብርሀን ሚች ሌህ በጆይ ዳሪዮን የተጻፈው “የላ ማንቻ ሰው” በሚል የተደረሰው ሙዚቃ) ህልም አልማለሁ…

ሊሆን የማይችለው ህልም (ታላቁ ጥያቄ)፣ 

ተግባር የማያየው ባዶ ህልም ማለም፣
ከማይቻል ጠላት ከጀግና መጋጠም፣
የማይቻል ግዙፍ ሀዘንን መሸከም፣
አንድ ውጤት ነው ያለው ያው የተለመደው፣
ባዶ ሆኖ መቅረት አንዱንም ሳይሰራው፡፡
እናም ለመፈትለክ የትም ለመብረር፣
ከታዋቂዎቹ ከጀግኖች መንደር፣
እውነትን አቅጥኖ ስህተት ማወፈር፣
ሆኖ መች ያውቅና ባባቶች ሰፈር፡፡
የተሳሳተውን እውነት ለማድረግ፣
ግልጽን ሀሳብ  ይዞ አጋር መፈለግ፡፡
እጆች እስኪዝሉ ደጋግሞ መጋፈጥ፣
የማይያዘውን ኮከብ ለመጨበጥ፣
ይህ ነው ጥያቄዬ አሁን ይረጋገጥ፡፡
ኮከቡን  ለመያዝ ተስፋቢስ ብሆንም፣
ምን ያህልም ቢርቅ ከተጨባጩ ዓለም፣
መድረሴ ሀቅ ነው በውድም በግድም፡፡
ጥያቄ ሳይመጣ የሚያጠዛጥዝ፣
ፈቃደኛ ሆኖ ብዕርን መምዘዝ፣
ለሀቁ ለእውነቱ እራስን ማዘዝ፡፡
ከተጨባጩ ላይ ከሀቁ ለመድረስ፣
ገሀነም ገብቶም ቢሆን እውነታውን ማደስ፣
እናም ትክክል ነኝ እኔ አውቃለሁኝ፣
ለዚህ ጥያቄዬ ልቦና ሁነኝ፡፡
ጸጥታ እና ሰላም ሁለቱ መልዕክቶች፣
ዓለም ክፉ ሳትሆን በጎ ትሆናለች፡፡
አንድ ሰው ቢቃጠል ወድቆ እስከሚነሳ፣
መቼ ያጣው እና ከእጁ ላይ ጠባሳ፡፡
ስለዚህ መድፈር ነው ውጤት ለማምጣት፣
የማይደረስን ደርሶ ከልብ ለማዬት፡፡
እናም አይነኬን ኮከቡን አያለሁ፣
በእጀ ለመጨበጥ ሁልጊዜ አስባለሁ፣
እናም ልምዴ ሆኖ ሁልጊዜ አልማለሁ፣
የማይሆነውን ህልም ተከናውኖ አያለሁ፡፡
ህይወት ያለ ህልም ጣዕም ሊኖረው የማይችል እርባናቢስ ክስተት ነው፡፡

በዓለም ላይ ላላችሁ ሁሉም አንባቢዎቼ እንኳን ለ2015 አዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት በሰላም አደረሳችሁ፡፡ አዲሱ ዓመት የደስታ እና የብልጽግና እንዲሆንላችሁ በድጋሜ እመኛሁ!!!
በሀገር ቤት ያላችሁ ወገኖቼም እንኳን ለጌታችን ለመድሀኒታችን ለእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልበሰላም አደረሳችሁ!!!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
 ታህሳስ 29 ቀን 2007 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment