Tuesday, January 13, 2015

ታሪካዊው የጣይቱ ሆቴል በእሳት መጋየት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀሰቀሰ


በቅዱስ ዮሃንስ 

ባሳልፍነው እሁድ ጥር 3-2007 ማለዳ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ዘመናዊ ሆቴል የሆነው ታሪካዊው ጣይቱ ሆቴል ሙሉ በሙሉ በእሳት የወደመ ሲሆን ድርጊቱ ሆን ተብሎ የታሪክ ጸር በሆነው የወያኔ አገዛዝ ሴራ የተፈጸመ ነው ሲሉ ኢትዮጵያውያን በአገዛዙ ላይ ቁጣቸውን እየገለፁ ይገኛሉ።  የእሳት አደጋ ብርጌድ መስሪያ ቤት በሆቴሉ አቅራቢያ ሆኖ ሳለ እሳቱ ከተነሳ በትንሹ ለአንድ ሰአት ተኩል ያህል አንድም የእሳት አደጋ መኪና አለመታዬቱና ብሆቴሉ አለመድረሱ በርካቶችን ከማስቆጣቱም ባሻገር በአገዛዙ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ሴራ ለመሆኑ እንደ አንድ አብይ ማስረጃ በስፋት እየተጠቀሰ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ታሪካዊውን የጣይቱ ሆቴል መውደም ተከትሎ  ቁጣቸውን በማህበራዊ ገፃቸው ላይ ያሰፈሩት አንድ ግለሰብ እንዳሉት በቅርቡ ለዘመናት በወመዘክር ይገኙ የነበሩ በተለያዩ የአለም ቋንቋዎች የተፃፉ የኢትዮዽያን ታሪክ የያዙ መዛግብትና ጽሁፎችን በወያኔ ትዕዛዝ ለስኳር መጠቅለያነት በሚል እንዲሸጡና የቀሩት እንዲቃጠል አደረጉ። ዛሬ ደግሞ በኢትዮዽያ ታሪክ የመጀመሪያዉ ሆቴል የሆነዉንና ታሪካዊ ቅርሳችንን የእቴጌ ጣይቱ ሆቴል በተቀነባበረ ሴራ እንዲቃጠል አደረጉ። እነዚህ የባንዳ ዉላጆች በተመሳሳይ የጥፋት ድርጊታቸው በልማት ተብየ ስም የአቡነ ዼጥሮስን ሀዉልት እንዲነሳ አድገዋል፤ ጥንታዊ ገዳማትና አድባራትን አፈራርሰዋል። የቅርስ ምዝገባ በሚል ሰበብ የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ንዋዬ ቅድሳትና ጽላትን ሳይቀር ለምዕራቡ አለም መቸብቸባቸዉ የአደባባይ ሚስጢር ከሆነ ሰነባብቷል በማለት ይህ የወያኔ ቅርስን የማውደም ሴራ የአገዛዙን ሞት ያፋጥናል ሲሉ ቁጭታቸውን አስፍረዋል።

ሌላኛው ኢትዮጵያዊ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ በማንነትህ፣ በታሪክህ፣ በቅርሥህ ላይ እያላገጡ ያሉት የባንዳ ልጆች እምቢተኝነትህ በዝምታህም፤ በጩኸትም ገብቷቸዋል፣ ከቁጥጥራቸው በላይ ሆኖባቸዋል። የሕዝብ ምሬት ሊገነፍል ጫፍ ላይ መድረሱ ታይቷቸዋል፣ ጨንቋቸዋል፣ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ተንቀጥቅጠዋል፣ ፈርተዋል፣ አሁን ላይ በደመነፍስ ነው እየገዙን ያሉት። ዛሬም እንደትናንቱ የአጥፍቶ አጥፊነት ባህሪያቸውን ነው እየደገሙት ያሉት። የጣይቱ ሆቴል መቃጠል የታሪካዊ ቅርስ ጥላቻቸው ጫፍ መድረስ መገለጫ ነው። አጥፊነታቸው ምን ደረጃ ድረስ እንደሆን ነው የሚያሳየው፣ የአውዳሚነት ባህሪያቸው ለታሪካችንና ለቅርሶቻችን ያላቸውን ጥላቻ ያሳያል። ዛሬ የታሪክ ቅርሥ የሆነው ጣይቱ ሆቴል ወደመ ነገሥ ባለተራው ማን ይሆን ? ሲሉ ቁጭታቸውን በጥያቄ ደምድመዋል።

የፋሽስቱ ወያኔን ከዚህ በላይ የምንታገስ ከሆነ ነገ ምንም ዓይነት የታሪክ አሻራ አናገኝም በማለት ቁጭታቸውን ያሰፈሩት ሌላኛው በድርጊቱ የተቆጬ ግለሰብ በበኩላቸው አምባገነኑ ወያኔ ታሪክን በጠራራ ፀሐይ ማቃጠሉን አሁንም ቀጥሎበታል። በዛሬው እለት በኢትዮጵያ የሆቴሎች ታሪክ የመጀመሪያውን የታሪክ ቤተ መዘክር የሆነውን የጣይቱ ሆቴልን እሳት ለኩሰው አጋይተውታል። እነዚህ የአገር ነቀርሳዎች እሳቱን ለኩሰው ሰዎች ገብተው እንዳያጠፉ ፖሊስ በቆመጥ እየጎመደ አባረረ፤ ዐይናችን እያየ ታሪካችን ሲቃጥል ተመለከትን። የእሳት አደጋ መከላከያ በሁለት መቶ ሜትር ርቀት ላይ እያለ በአራቱም አቅጣጫ እሳቱን ለማጥፋት አመቺ ቦታ ላይ ተቀምጦ ሆቴሉ ሙሉ በሙሉ እስኪወድም ድረስ የውሸት ቋት በሆነው ቴሌቪዢናቸው ገና እሳቱን አልተቆጣጠርነውም እያለ በህዝብ ሲሳለቅብ ተመለከትን። ያሳዝናል። በነገራችን ላይ ባለፈው ጊዜ ይህ ሆቴል በመልሶ ማልማት ስም እንዲፈርስ ወያኔ ወስኖ ነበር፤ ሕዝቡ ቁጣውን ሲያሰማ ግን ጊዜ ጠብቆ አቃጥለውታል ። ከዚህ በላይ ወያኔን መታገስ አገራችንና እና ታሪኳን ከፋሽስቶች ጋር አብሮ እንደማጥፋት ነው የማየው። ከዚህ በላይ የሃገራችንን ጥፋት ለማየት መፍቀድ ከባንዳነትም በላይ ባንዳነት ነው ሲሉ ግለሰቡ በጋራ የታሪክና የቅርስ ጸር የሆነውን የወያኔ አገዛዝ ለማስወገድ እንነሳ በማለት ወገናዊ ጥሪያቸውን በማቅረብ መልዕክታቸውን አስተላልፍዋል።

No comments:

Post a Comment