Friday, May 8, 2015

ህወሃቶች እንደ ዘኬዎስ!!

ሰዉዬው በሕዝቡ በጣም የተጠላ ነው። የገዢው ቡድን አካል ነው። በሕዝቡ ላይ ብዙ ግፍ ይፈጽማል። ሰዎች የዚህን ሰው ሞት እንጂ መልካም ነገር አይመኙም። ሁልጊዜ እንደተረገመ ነው። ዘራፊ ነው። በሙስና የተጨማለቀ። ለሰው ፣ ለድሃው ርህራሄ የሌለው። የሌላዉን ደም እየጠጣ የከበረ። በጣም የተጠላ ሰው።

አንድ ቀን በሚያስደንቅ ሁኔታ ከዚህ ሰው የማይጠበቅ ነገር ተሰማ ። ከዚህ በፊት የበደላቸውን እንደሚክስ፣ ከዚህ በፊት ያደርግ እንደነበረው ግፍን ከመፈጸም እንደሚቆጠብ ተናገረ። ምን ተፈጠረ ? ምን አዲስ ነገር ሆነ ? ተፈጥሯዊ የሆነ የተለወጠ ነገር የለም። ሌላ የመንግስት ስርዓትም አልተለወጠም። ይህ ሰው ከነበረው ስልጣን አልተነሳም። ምን የተለየ ነገር ተከሰተ ?
ይህ ሰው አንድ ቀን ከአንድ ታላቅ ሰው ጋር ተገናኝ። ይህ ሰው ዘኬዎስ ይባላል። የተገናኘውም ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ነበር።

ዘኬዎስ ለሮማዊያን (ያኔ እስራኤልን ይገዝዙ የነበሩ)ሚሰራ፣ ለነርሱ ግብር የሚቀበል ቀራጭ ነበር። የገዢው ቡድን ( የሮም) አገልጋይ ነበር። አሁን በአገራችን ያለዉን ምሳሌ ከተጠቀምን፣ ይህ ሰው "ወያኔ" ነበር እንደማለት ነው። ትላንት ሕዝብ ሲያስጨንቅ የነበረው "ወያኔው" ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ሲያገኝ ሕይወቱ ተቀየረ።

ስለ ጌታ አስቀድሞ ሰምቶ ሊያየው ይፈልግ ነበር። አጭር ስለነበረና በጣም ከመጠላቱ የተነሳ ከህዝቡ ጋር ቢቀላቀል ሊሰደብ ወይንም ሊደብደብ ስለሚችል፣ ሰው ሳያየው በሩቅ ጌታን ለማየት ፣ ጌታ በሚያልፍበት መንገድ ላይ ካለ ዛፍ ላይ ወጥቶ ጠበቀ። ሰዎች በዚያ ያልፋሉ፤ ግን አላዩትም። እዚያች ዛፍ ስር ሲደርስ፣ ጌታ ቆም አለ። ሰዎች ያላዩትን ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አየው። አዎን "ወያኔዉን"፣ በሕዝብ የተጠላዉን ጌታ አየው።

"ኢየሱስም ወደዚያ ስፍራ በደረሰ ጊዜ፥ አሻቅቦ አየና። ዘኬዎስ ሆይ፥ ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ አለው። ፈጥኖም ወረደ። በደስታም ተቀበለው።" ይላል የሉቃስ ወንጌል ምእራፍ 19 ።ሌሎች ከዚህ በሕዝብ ከተጠላ ፣ ህዝብን ሲያሰጨነቅ፣ ከሚገባው በላይ ግብር እየተቀበለ ድሃን ሲዘርፍ ከነበረ ሰው ጋር መነጋገሩ አስገረማቸው። "ከኃጢአተኛ ሰው ጋር ሊውል ገባ ብለው አንጐራጐሩ" እንደሚል ቃሉ፣ በጌታ ሁኔታ አልተደሰቱም።


ዘኬዎስ ግን ተገረመ። ሰዎች ሲጠሉት፣ ሲሰድቡት እንጂ በአክብሮት ሲቀበሉት አይቶ አያወቅምና። ከሌላው በተለየ ሁኔታ ጌታ አክብሮት ፣ ያዉም ወደ ቤቱ ሲገባ ሲያይ፣ ልቡ ተሸነፈ። ሕይወቱ ተቀየረ። እዚያው መሰረታዊ ዉሳኔዎችን ወሰደ። "ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታን። ጌታ ሆይ፥ ካለኝ ሁሉ እኵሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ከስሼ እንደ ሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ አለው። " እንደሚል ቃሉ።

በአገራችን ግፍና ጭካኔ፣ ሙስና በዝቷል። በጣም ሲበዛ ስልጣናቸውን ተጠቅመው በሌላው ላይ ቀንበር የሚጭኑ ዘኬዎሶች ብዙ ናቸው። ብዙዎች በግፍ ታስረዋል። ብዙዎች በግፍ ይደበደባሉ። ብዙዎች ከቤታቸው በኃይል ይፈነቀላሉ። ፍርድ ቤት የውሸት ነው። ሕግ የለም። ኢሰብአዊነትና ኢፍትሃዊነት ከመረን በላይ ተንሰራፍቷል። የሕዝብ ብሶት ወለደን ያሉት፣ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ብሶትን በሕዝብ ላይ እየጨመሩብት ነው።ኢትዮጵያ ጥቂት የስርዓቱ መሪዎችና ባለሟሎች፣ የከበሩባት ግን አብዛኛው ህዝብ እንባ እያነባባት፣ በፍርሃትና በሰቀቀን እየኖረባት ያለች አገር ሆናለች። አንድ የጀነራል ፎቅ ይሠሩና መቶ የድኃ ቤቶችን ያፈርሳሉ። ግፍና ጭካኔ በዛ !!!!!

ምልክቶች እየታዪ ነው። ሰማዩን ደመና ሸፍኖታል። መዝነቡ አይቀሬ ነው። ሰዎቹ አስተዋይ ከሆኑና የጊዜውን ምልክት ማየት ከቻሉ፣
እግዚአብሄር ከረዳቸው፣ ትላንት ከሕዝብ የተጣሉ ቢሆኑም ፣ ዛሬ ዘኬዎሶች መሆን ይቻላሉ። ለአገዛዙ ባላስልጣናት በእግዚአብሄር ቃል ላይ ተመርኩዤ፣ በኃይልና በስልጣን የማስጠንቀቂያ ምክር አዘል መልእክት አስተላልፋለሁ። “ንስሐ ግቡ። ሕዝቡን ማስጨነቃችሁን አቁሙ። የታሰሩትን ፍቱ። ፍቅርን እና መግባባትን እንዲሁም እርቅን ፈልጉ” እላለሁ።

እምቢ ካሉ፣ ለእግዚአብሄር ቃል ካልታዘዙ፣ የፍቅርን፣ የብሄራዊ መግባባትን የሰላምን በር ከዘጉ፣ ልባቸዉን ፈርኦን እንዳደነደነው ካደነደኑ በርግጥ ሰይፍ ይበላቸዋል። እግዚአብሄር አምላክ የፍትህ አምላክ ነው። ድሃ ሲጠቃ፣ ድሃ ሲጨቆን ማየት የማይወድ አምላክ ነው። እግዚአብሀር ጻድቅ ፈራጅ ነው!!!!! ያኔ ጸባቸው ከአንድዬ ጋር ይሆናል።
እንግዲህ ጆሮ ያለው ይስማ፣ ልብ ያለው ያስተዉል።

No comments:

Post a Comment