Friday, May 8, 2015

የተጨናገፈው፤ የዕልቂት ድግስ (ሚያዚያ 30ን ከስፍራው)

(በደረጀ ሀብተወልድ፤ኢሳት-በማእደ- ኢሳት የቀረበ)

በጎቹ ጨፌው ላይ - በፍቅር ያዜማሉ፣
ተኩሎች አድፍጠው - ይጠባበቃሉ፣
ጩኸት ሊበረክት-ሊፈስ ሲል ዕንባ፣
እረኛው በድንገት-መሀል ጣልቃ ገባ።
አገር በደም ባህር-ሊጠመቅ ተፈርዶ፣
ውሀ ጥምቀት ሆነ-ከላይ ዝናም ወርዶ።

ቅንጅት፤ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ የጠራውን የሚያዚያ 30/1997 ዓ.ም ሰልፍ ለመዘገብ ወደ መስቀል አደባባይ ያመራሁት እኩለ-ቀን ላይ ነው። ከረፋዱ 4 ፡00 ሰ ዐት ጀምሮ ታክሲዎች መደበኛ ሥራቸውን ትተው ሰዎችን በነፃ ወደ መስቀል አደባባይ ማመላለስ በመጀመራቸው፤ሰልፉ ምን መልክ ሊኖረው እንደሚችል መገመቱ ቀላል ነበር።ቀድሜ ወደ ሥፍራው የተንቀሳቀስኩትም፤ ማለፊያ መንገድ ሳይዘጋጋ ወደ አደባባዩ ለመቅረብ እንድችል ነው።እንደወትሮው ሁሉ ዛሬም መቅረፀ-ድምፄንና ካሜራዬን አንግቤያለሁ። የወቅቱ ሀዳር ቀጥሎም የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ማኔጅንግ ኤዲተር የነበረው ዳዊት ከበደ፤ እንዲሁም የሀዳር ምክትል ዋና አዘጋጅ የነበረው ፈለቀ ጥበቡ አብረውኝ አሉ።

የሰው ጎርፍ ከየአቅጣጫው እየተግተለተለ ወደ አንድ ሥፍራ ተከማችቶ እንደ ረጋ ውቅያኖስ ሆነ።ዳርቻው የማይደረስበት ውቅያኖስ።
መለስ፤ ከአንድ ቀን በፊት ያዩትን የኢህአዴግ ሰልፍ በማድነቅ “ማዕበል” ብለው መጥራታቸውን ያስታወሰው ሪፖርተር ጋዜጣ ፤ከቅንጅት ሰልፍ በሁዋላ ባወጣው ርዕሰ-አንቀጽ ” ለማዕበልም፤ ማዕበል አለው” በማለት ነበር ለመለስ ንግግር ምላሽ የሰጣቸው።
የማዕበሎች ሁሉ ማዕበል።
ምኒልክ ጋዜጣ ደግሞ፦”ሱናሚ”ሲል ነው የጠራው።
የሚገርም ቀን።

ሚያዚያ 30/ 97፦ በኢትዮጵያ የሺህ ዓመታት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የታዬ ህልም ሚመስል ትዕይንት።ሚሊዮኖች ነፃነታቸውን በአደባባይ በማወጅ ዲሞክራሲን በጋራ የዘመሩበት ታሪካዊ ቀን።

ሆኖም፤የሰልፉ አስተባባሪዎች ለዕለቱ የተሰናዳውን ፕሮግራም ለማቅረብ ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁ ፈፅሞ ያልተጠበቀ ነገር ሆነ-መብራት ጠፋ። በወቅቱ ተቀርፎ የነበረው የአዲስ አበባ የመብራት ችግር፤ ከረዥም ወራት በሁዋላ የቅንጅት ሰልፍ ፕሮግራም ሊጀመር ደቂቃዎች ሲቀሩት እንደ አዲስ ተቋረጠ።

እንደ ትናንት የኢህአዴግን ሰልፍ በተንቦገቦገ መብራት ያስተናገደው አደባባይ፤ዛሬ ሚሊዮኖች ለወጡበት ሰልፍ ብርሀኑን ነፈገ።
በተደጋጋሚ ወደ መብራት ሀይል ባለሥልጣን ስልክ በመደወል የተደረገው ጥረትም ሳይሳካ ቀረ።
ጥቂት ሰዎች- ዕልፎችን፦“የጀኔሬተሩ ቁልፍ በእኛ እጅ እሰከሆነ ድረስ ብርሀን እንድታዩ አንፈቅድላችሁም” አሏቸው።
በሆነው ነገር ህዝቡ ተቆጣ። ከዳር እስከ ዳር የተቃውሞ ጩኸት ማሰማት ጀመረ።

የህዝቡ ቁጣ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን የሰጉ የቅንጅት አመራሮችም ፤ የእጅ ማይክራፎን ይዘው በሰልፉ መሀል በመዟዟር ‘ከመብራት መቋረጥ ጀምሮ ሆነ ተብለው እየተፈፀሙ ያሉትን ማናቸውንም የሚያበሳጩ ድርጊቶች ህዝቡ በትዕግስት እንዲያልፋቸው’ በአደራ ጭምር ተማፀኑ።
“…እነሱ የፈለጉት በብስጭት ወደ ህገ-ወጥ ድርጊት እንድንገባ ነው።እያመቻቹን ያሉት የሀይል እርምጃ ለመውሰድ ነው።ንቁባቸው! እንኳን መብራት ማጥፋት ሌላም ነገር ቢፈጽሙ ከህጋዊና ሰላማዊ መስመራችን የማንነቃነቅ የዲሞክራሲ ሰልፈኞች መሆናችንን እንድናሳያቸው፤ ደግመን ደጋግመን አደራ እንላለን!!”
ህዝቡ የመሪዎቹን ጥሪ ተቀብሎ የሚሆነውን ነገር በትዕግስት መጠባበቅ ጀመረ።
በላዩ፤አናት የሚበሳው የፀሀይ ቃጠሎ አለ።

ግን…ግን…
ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች የተሰባሰቡበት ዝግጅት ሊጀመር ፤ደቂቃዎች ሢቀሩ ሆነ ተብሎ መብራት እንዲጠፋ የተደረገው ለምን ይሆን? ?

አንዳፍታ ከእኛ ጋር በሰልፉ መሀል እየተሻሻችሁና እየተገፋፋችሁ ወደ መድረኩ እንድንሄድ ላስቸግራችሁ...
በግምት፤ መድረኩን በ20 ሜትር ርቀት እስከከበበው አጥር ድረስ ከመጣችሁ ይበቃችሁዋል።በቃ! ከዚህ በሁዋላ ማለፍ አትችሉም። ከመንግስት ጋዜጠኞች በስተቀር ማንም ወደ መድረኩ እንዲወጣ አልተፈቀደም።እዛው ቆማችሁ በመድረኩ ጀርባ ስላለው ነገር የምነግራችሁን አዳምጡ።

እኔና ጓደኞቼ ከመድረኩ ሆነን የታሪካዊውን ሰልፍ ፎቶ ለማስቀረት ስለፈለግን ወደ ሰባት ከሚደርሱት የኢቲቪ፣የኢትዮጵያ ራዲዮ እና የራዲዮ ፋና ጋዜጠኞች ጋር በመቀላቀል የተከለለውን አጥር አልፈን ወደ ፊት መራመድ ጀመርን።
ከፊት እየመራ ጋዝይጠኞቹን ወደተዘጋጀላቸው ቦታ የሚወስዳቸው ሰውዬ፤ የግል ፕሬስ ጋዜጠኞች ይቀላቀላሉ ብሎ ስላልገመተ ያለምንም ጥያቄ “ተከተሉኝ”እያለ ወደ ፊት ወሰደን። የሰልፍ መስመር እንደያዝን በኢትዮጵያ ዓለማቀፍ የሰላምና የልማት ኢንስቲትዩት ጓሮ በኩል ገባን።

እንዴ!?
ምንድነው የሚታየው ጉድ!?
ዐይኔን ማመን አልቻልኩም።
ሁላችንም በድንጋጤ እርስ በእርስ ተያዬን።

ከመድረኩ ጀርባ ዙሪያውን በአጥር በተከለለና እንደ ምድር ቤት ዝቅ ባለ ቦታ ላይ በስድስት ከባድ መኪናዎች ላይ የሠፈሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች መትረየሶችንና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን ወደ ህዝቡ ደግነው በተጠንቀቅ ይጠባበቃሉ።
አገር ሰላም ብለው መስኩ ላይ በደስታ የሚዘምሩት በጎች እነዚህን ያደፈጡ ነጣቂዎች አላዩዋቸውም።አዎ! እንደኛ ወደ ውስጥ ያልገባ ካልሆነ በስተቀር ማንም ሊያያቸው አይችልም።

በግዮን ሆቴል ጀርባ በኩል የታችኛውን ቤተ-መንግስትና የመስቀል አደባባይን መድረክ የሚያገኛኝ ልዩ መንገድ እንዳለ በዐይኔ ያየሁት የዛን ዕለት ነው።መንግስቱ ሀይለማርያም መስቀል አደባባይ ንግግር ለማድረግ ይመጡ የነበረው በዛ ስውር መንገድ እንደሆነ ይወራል።ነገሩ እንደነ መለስ መንገዱን ጭር በማድረግ አገር ምድሩን ከማሸበር -ይህን ስውር መንገድ መጠቀሙ ይመረጣል ።
ዛሬም በመድረኩ ጀርባ አድፍጠው የሚጠባበቁት ታጣቂዎች ይህን መንገድ ሳይጠቀሙ አልቀሩም ብዬ እገምታለሁ።ያ ካልሆነ፤ ከአንድ ቀን በፊት- ልክ የኢህአዴግ ሰልፍ እንዳበቃ እዛው ቦታ ላይ ሆነው ሌሊቱን ሙሉ ሢጠባበቁ አድረዋል ማለት ነው።
መድረኩ ጫፍ ወጥተን ሥራችንን ጀመርን። የካሜራችንን “ዙም” እያስረዘምንና እያሳጠርን ልዩ ልዩ ትዕይንቶችን ማስቀረቱን ተያያዝነው።
ባንዲራ ተጎናጽፈው ዕልልታ የሚያሰሙ አዛውንቶች፣ በገላቸው ላይ የቅንጅትን አርማ የተነቀሱ ወጣቶች፣”ትናንት ለገንዘብ፤ዛሬ ለነፃነት”እያሉ መፈክር የሚያሰሙ ሴቶች፣ በወላጆቻቸው ትከሻ ላይ ሆነው ሁለት ጣታቸውን የሚያሳዩ ህፃናት፣”ይትባረክ እንደ አብርሐም!”እያሉ የሚዘምሩ የሰንበት ተማሪዎች፣ “አላህ ወአክበር!” የሚሉ መድረሳዎች፣”ኢየሱስ ጌታ ነው!”እያሉ የሚጮኹ ጴንጤዎች…ማን ነበር የቀረው?
እኚህ ሁሉ፤ በፍቅር ተያይዘው፣በአንድ ልብና በአንድ ሀሳብ ሆነው ዲሞክራሲን እያወደሱ ነው።ሥርዓትና ህግን በጠበቀና ሥልጡን በሆነ መንገድ።

“ሟርት በያዕቆብ ላይ አይሠራም!” ነው የሚለው ታላቁ መፅሐፍ?
አዎ! ኢትዮጵያውያን በአንድ አገራዊ አስተሣሰብ እንዳይቆሙ ለዓመታት ሢቀመም የቆየው የዘርና የሀይማኖት ሥራይ፤ውሀ እንደነካው የደብተራ ክታብ ፈስዶ ታዬ።
ዕልፎች፦
“የሀይማኖት ካብ- ብትክቡ፣
የዘር ገመድ -ብትስቡ፣
ደከማችሁ እንጂ- በከንቱ፣
እኛ ያው ነን-እንደ ጥንቱ፣
እኛ አንድ ነን-እንደ ፊቱ”
እያሉ ተቃቅፈው በዕልልታ ሲዘምሩ ተስተዋሉ።

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ካሜራ ፤ ለዜና እንኳ የሚሆን ምስል አላገኘም መሰል፤ ገና ሥራ አልጀመረም።መድረኩ ላይ ካሉት በተጨማሪ ፤ለኢቲቪ ምሽት ዜና የሚሆን ትዕይንት የሚፈልጉ ሌሎች ጋዜጠኞችም በሰልፉ መሀከል ካሜራ ይዘው ተሰማርተዋል።ግን እንደታዘዙት፣እንዳሰቡትና እንደተመኙት ረብሻዎችንና ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ማግኘት አልቻሉም።
አሁን ግን ሰልፉ መካከል ላይ የሚሰማን ለየት ያለ ጩኸት ተከትለው ከተለያየ አቅጣጫ ካሜራቸውን ወደ መካከል ማነጣጠር ጀመሩ።

ከጀርባ ያደፈጡት ተኩላዎችም፤ ከአንገታቸው ቀጥ ብለውና ጆሯቸውን ቀስረው በተጠንቀቅ ሆኑ።
“በለው! በለው! በለው!...”
“እንዳትነኩት! እንዳትነኩት! እንዳትነኩት!”
የሚሉ ጩኸቶች ከወደመሀል እያስተጋቡ ነው።
ምክንያቱ ምን ይሆን?
በግምት ከ16 ዓመት የማይበልጠው ታዳጊ ህፃን የንብን(የኢህአዴግን) ቲ-ሸርት ለብሶ፤ በዛ የሚሊዮኖች ሰልፍ መሀከል መገኘቱ ነው።

እስኪ አስቡት፤ በዛ ማዕበል፣ በዛ ስሜትና ትርምስ መሀከል(የሰልፉ እንብርት ላይ) የንብን ቲሸርት የለበሰ ሰው፤ያውም ታዳጊ ህፃን! ለእርድ እየተነዳ የመጣ ንፁህ በግ!
ልጁ፤ የንብን ቲ-ሸርት ለብሶ እንዴት ቅንጅት ሰልፍ መሀል ሊገኝ እንደቻለ በአስተባባሪዎቹ ለቀረበለት ጥያቄ፤ ሰዎች፤ ቲ-ሸርቱን አልብሰውና ከላይ ጃኬቱን እንዲደርብ አድርገው እስከመሀከል ድረስ ካመጡት በሁዋላ፤”እንዳይሞቅህ” በማለት ጃኬቱን አውልቀው እንደያዙለት መጠፋፋታቸውን በማብራራት፤ ስለ ፖለቲካ ምንም ግንዛቤ የሌለው መሆኑን ይናገራል። ሆኖም፤ “እነዛ ሰዎች ማናቸው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ይቀራል።
በዚህ ጊዜ ነው፦”በለው! በለው! ካልተናገረ በለው!.....” የሚል ድምፅ በዙሪያው ከነበሩ ወጣቶች የተሰማው። ሆኖም፦” እንዳትነኩት!” የሚለው ድምፅ በእጥፍ ብልጫ ነበረው።

”እንደውም፤ እሱን አውልቁለትና የቅንጅትን ቲ-ሸርት አልብሱት” የሚሉ ወጣቶች ተሰሙ። ሀሳባቸው የጭብጨባ ድጋፍ አገኘ። ልጁ ሲጠየቅም ፈቃደኛ ሆነ።ስማቸውን ያልጠቀሳቸው ሰዎች አልብሰው የላኩትን የጽልመት ግርዶሽ አውጥቶ በመወርወር ልቡ የፈቀደውን ለበሰ።ጭብጨባው ቀለጠ።ተንኮለኞች ይገደል ዘንድ ፈረዱበት።እግዚአብሔር ግን “አትሞትም፤ገና በህይወት ትኖራለህ!” አለው።

ተቀጥቅጦ ይገደል ዘንድ የተላከው ታዳጊ፤ከወገኖቹ ጋር ተቃቅፎ መዘመር ቀጠለ።
አዎ! የመጀመሪያው የተንኮል ድር በዚህ ሁኔታ ተበጣጠሰ።ህፃን ልጅ ቲ-ሸርት አልብሶ ሰልፈኛ መሀል ላይ በመጣል፤ በሱ ጉዳት ምናልባትም፦ በሞቱ ለመነገድ የተወጠነው ሴራ ከሸፈ። ቀጥ ብሎ የነበረው የተኩላዎቹ ጆሮ ረገበ።
”በቅንጅት አመራሮች አደገኛ ፕሮፓጋንዳ የተለከፉ ጥቂት ቦዘኔዎች ለምን የንብ ቲሸርት ለበስክ? በማለት የ 13 ዓመት ታዳጊ ወጣትን ደብድበው ገደሉ” ተብሎ ከወዲሁ ለምሽት የተዘጋጀው የኢቲቪ ዜና ውድቅ ሆነ። ህዝቡ “ነቄ ነን” አለ።
አሁን፤ ከቀኑ 8፡30 ሊሆን ነው።እስካሁን የተቋረጠው መብራት አልመጣም። ዕልልታውና ዝማሬው ግን ከጫፍ ጫፍ እያስተጋባ እንደቀጠለ ነው።ልደቱ አያሌው በአንገቱ ላይ የባንዲራ ስካርቭ አድርጎና በሰዎች ትከሻ ላይ ሆኖ ድንገት ብቅ አለ።
“ማንዴላ! ማንዴላ!ማንዴላ!.....” በማለት ህዝቡ በሆታ ተቀበለው።
ህዝቡ ለሰልፉ የተዘጋጀውን የመሪዎቹን ንግግር በመብራት መቋረጥ ምክንያት ለመስማት ባለመቻሉ፤ ብስጭቱ እየጨመረ መምጣቱን የተገነዘበው ልደቱም፤ሰልፈኞቹ በኤሌክትሪክ ሀይል አለመምጣት ሳቢያ ወዳልሆነ እርምጃ እንዳይገቡ ደጋግሞ ተማፀነ።
ሰዐታት ነጎዱ።

9፡00፣ 9፡30፣ 10፡00፣10፡15…..
የመድረኩ ዝግጅት በመብራት አለመኖር ሳቢያ መቅረቱ ተነገረ።ህዝቡ ዳግም ቁጣ ማሰማት ጀመረ።የመብራቱ ነገር፦”አውቆ የኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም”እንደሆነ በደንብ ገባው።”ካሁን አሁን ይመጣል”የሚለው ተስፋው ጨርሶ ተሟጠጠ።
አዲስ አበባ በጩኸትና በፉጨት ተናጠች።በእስጢፋኖስ ቤተ-ክርስቲያን አካባቢ ካሉት ወጣቶች ፦

”ኢህአዴግ ሌባ!
አል-አሙዲ ሌባ!” የሚል ቁጭትና ንዴት የወለደው ጭፈራ ተሰማ።
ሦስት ሚሊየን ህዝቦች ለሦስት ሰዐታት መብራት ሲከለከሉ የሚፈጥረውን ስሜት በሰልፉ የነበራችሁ ታውቁታላችሁ፤ ያልነበራችሁም ትረዱታላችሁ።
ስለዚህም ወጣቶቹ ንዴታቸውን መግለጽ ጀመሩ።አደባባዩ በውጥረት ተሞላ።ሲቪል የለበሱ ሁለት ሰዎች በመገናኛ ሬዲዮ መልዕክት እየተቀበሉ ከመድረኩ ጀርባ ላሉት አጋዚዎች የሆነ ነገር ነገሯቸው።መሳሪያቸውን አንቀጫቀጩ። እጃቸውን ወደ ቃታ በመላክ በከፍተኛ ተጠንቀቅ ሆኑ፡፡እርግጠኛ ነኝ፤ እየጠበቁ ያለው፦”ቀጥል!” የሚለውን ትዕዛዝ ብቻ ነው።
ሁኔታውን እያየን ያለነው ጋዜጠኞች የበለጠ ድንጋጤና ጭንቀት ውስጥ ገብተናል።
በወጣቶቹ የተጀመረው የተቃውሞ ጩኸት ዳር እስከ ዳር መቀጣጠል ጀመረ። ተኩላዎቹ ካደፈጡበት በመነሳት ወደ መድረኩ መውጫ በር ተንቀሳቀሱ።የሰልፉ አስተባባሪዎች መረጃ ደረሳቸው መሰል
፦”እባካችሁ ሰልፈኞች አደራ! ምንም ነገር እንዳታደርጉ! አደራ!አዳራ!...’እያሉ እንደ አዲስ አብዝተው መጮኽ ጀመሩ። ህዝቡ ግን፦” የአገራችንን ብርሀን የሚነፍገን ማነው?” እያለ መጠየቁን ቀጠለ።
“ተከብረሽ የኖርሽው ባባቶቻችን ደም፣
እናት ኢትዮጵያ-የደፈረሽ ይውደም!” የሚል ዝማሬ ተከተለ-በምልዓተ-ሰልፉ።
አስጨናቂ ሰዐት።
“አዲስ አበባ በደም ልትታጠብ ነው” የሚል የባህታዊ ትንቢት የሰማሁት፤ ኢህአዴግ ከተማዋን ለመያዝ በተቃረበበት ጊዜ ነበር።ለነገሩ፤ያኔ በመዲናዋ ውስጥ ሰፍረው ከነበሩት የቀድሞ ሥርዓት ወታደሮች ብዛት አኳያ፤ ” የአዲስ አበባ መሬት በደም ይታጠባል” ብሎ ለመናገር የነቢይነት ቅባት የሚጠይቅ አልነበረም።ለዚህም ነው ከባህታውያኑ ባሻገርም የፖለቲካ ተንታኞችም ፦’ስለ አዲስ አበባ የደም ጎርፍ’ ለመተንተን አፋቸው ያልተሳሰረው።
ትዝ ይለኛል፤ ህዝቡ በየአብያተ-ክርስቲያናቱና በየመስጊዱ በመሄድ ፦”አድህነነ ከመዓቱ ሰውረነ!” እያለ ከጧት እስከ ማታ ወደ ፈጣሪው ሲያለቅስ።
እግዚአብሔር ይመስገን!
በወጀብና በአውሎ ነፋስ መካከል መንገድ ያለው ጌታ ፤ትንቢቱንም፤ትንታኔውንም ሽሮ ከዛ አስጨናቂ ሰዐት ህዝቡን በሰላም አሳለፈው።
ዛሬስ ፤ ከዚህች አስጨናቂ ሰዐት እኚህን በጎች የሚታደጋቸው ማን ነው?ዛሬስ ከደቂቃዎች በሁዋላ በመስቀል አደባባይ ሊፈስ ያለውን የደም ጎርፍ ፤ማን ያቆመው ይሆን?
ማንም!
ተስፋ ቆረጥኩ።
አዎ!ስትዘምር የዋለችው ከተማ ማምሻዋን በዋይታ ልትሞላ ነው።”አኬልዳማ- የደም ምድር..”የሚለው የታምራት ዝማሬ ጆሮየ ላይ ደጋግሞ እያንቃጨለ ነው።
የህዝቡ ጩኸት እጅግ በረታ… አስተባባሪዎቹ ፦”ሰልፉ ስለተጠናቀቀ ወደየቤታችሁ ሂዱ!” ቢሉም ፤ህዝቡ እምቢ አለ። ተኩላዎቹ ፤ ከባለ ሬዲዮ መገናኛዎቹ የመጨረሻውን መልዕክት ተቀበሉ መሰል መሳሪያቸውን እንዳቀባበሉና እጃቸውን ቃታ ላይ እንዳደረጉ ከመኪናቸው በመውረድ ፈጠን ባለ እርምጃ ወደ ግቢው መውጫ በር ሄደው አደፈጡ።አስቀያሚው ትዕይንት ሊጀመር ትቂት ሰከንዶች ቀሩ….አንድ..ሁለ…ት….ሦ…ስ…..
ኦ!
ይህን ማን ያምናል?
በዛ ጠራራ ፀሀይ ዶፍ የቀላቀለ ሀይለኛ ዝናም በድንገት ወረደ።በአስተባባሪዎቹ ተማጽኖ አልነቃነቅ ያለው ሰልፈኛ በራሱ ጊዜ እየተሯሯጠ ተበታተነ።ገሚሱ በየቦታው ሲጠለል፤የተቀረው ዝናሙን ተቋቁሞ ወደ ቤቱ ገሰገሰ።ሰልፉ በዚህ መልክ በሰላም ተጠናቀቀ።
የተወጠነው የዕልቂት ድግስ ተጨናገፈ።
የዛን ቀን ምሽት ፦ “ወጥመድ ተሰበረ-እኛም አመለጥን፤ ለጥርሳቸው ንክሻ ያላደረገን እግዚአብሔር ይመስገን!” የሚለውን የዳዊት መዝሙር ደጋግሜ ማንበቤን አስታውሳለሁ።
በሆነው ነገር የተደነቁት ዶክተር ብርሀኑ ነጋ ከጊዜያት በኋላ ይህን ነገር አስታውሰው፦“ኢትዮጵያን የሚጠብቃት አምላክ አላት የሚባለውን ነገር ያስተዋልኩት ያንጊዜ ነው” ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ።
እኛም ከሞት አመለጥን-የ’ሱም እቅድ አልተሳካ፣
የደበደበን ዶፍ ዝናም- ከሞት ሊያድነን ነው ለካ። (ለበጎ ነው ከሚለው የራሴ ግጥም)

No comments:

Post a Comment