Monday, May 11, 2015

ፀረ ኢትዮጵያ የሆነውን የሕወሓት ቡድን ለማስወገድ ሁላችንም በህብረት እንነሳ!

በቅዱስ ዮሃንስ

ላለፉት 24 አመታት በሕወሓት አምባገነናዊ የጭቆና አገዛዝ ስር የወደቀችው አገራችን ኢትዮጵያ ስላለችበት ጭንቅ እና መከራ፤ ህዝባችን ስለሚኖርበት የምድር ሲኦል ብዙ ብዙ ተብሏል። የሕወሓት መሪዎችና የቡድኑ ፀረ-ኢትዮጵያዊነት አቋም፤ በአገር እና በወገን ላይ የፈፀሙትን በደልና ግፍ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጠንቅቆ ያውቀዋል ብየ በፅኑ አምናለሁ። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚፈልገውንና የሚመኘው ነገር ቢኖር በአገራችን ላይ ሰላም ሰፍኖ፣ የህዝብ መብት ተጠብቆ፣ የዜጎች አንድነትና የአገር ህልውና ተከብሮ፣ በአለም እያዋረደን ካለው የድህነት ችግራችን ተገላግለን ማየት እንደሆነ እሙን ነው።

ይሁን እንጂ በዚህ አስከፊ ክፉ ዘመን፤ ከረሃቡም፣ ከችግሩም፣ ከግድያውና ከእስራቱ በላይ፣ የኢትዮጵያችን ህልውና፣ የአገዛዙን ስልጣን በያዙ ፀረ-ኢትዮጵያ ቡድኖች ምክንያት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ወድቋል፡፡ በተጨማሪም በሕወሃት መሪዎች እብሪትና ማናለብኝነት የጠፋው የህዝብ ህይወት፣ የተዘረፈው የአገር ሃብት፣ የባከነው እውቀት እና ጉልበት በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ይታወቃል።  

በነገራችን ላይ ባለፉት 24 የጨለማ አመታት በአገራችን ለደረሰው ውርደትና ጥፋት የሕወሓት ቡድን የአንበሳውን ድርሻ ይውሰድ እንጂ የተቃዋሚ የፖለቲካ ሰዎች ነን የምንል ሁሉ በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ ለተፈፀመው ጥፋት ተገቢ የሆነውን የየራሳችንን የጥፋት ድርሻ መቀበል ይኖርብናል፡፡ ህዝብም ቢሆን በተለይ አቅሙና ችሎታው የነበረው ሁሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን መረን በመልቀቅ እና መሪዎችን በማቅበጥ ለደረሰው ጥፋት እራሱ ሃላፉነት መቀበል የሚገባው መሆኑን ሳልጠቁም ማለፍ አልፈልግም። በስልጣን ላይ ያለው አስከፊው የሕወሓት አገዛዝ የሚያዋርደን እኛ እስከፈቀድንለት ድረስ እንደሆነ ሁሉ ፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎችም በህዝብ ላይ መቀለድ የሚችሉት ህዝብ እስከፈቀደላቸው ድረስ መሆኑን ልናውቀው ይገባል። የፖለቲካ ድርጅቶች የህዝብን አደራ እንዳይበሉ፣ የህዝብ ቅስም እንዳይሰብሩ፤ በማን አለብኝነት ያሻቸውን እንዳይፈፅሙም ምን ያህሎቻችን ነን ከዳር ቆመን ከማውራት አልፈን በውስጣቸው ገብተን ልንቆጣጠራቸው፤ በህዝብ ስሜት መቀለድ አትችሉም ብለን የሞገትናቸው?
 
ስንቶቻችን ነን ሁሉንም የፖለቲካ ሰዎች በድፍን ከማማትና አይረቡም ከማት አልፈን ከግብዝነት እና ከአድር ባይነት በላይ ተሻግረን  አጥፊዎቹን ፊት ለፊት መናገር ድፍረቱን የተላበስን? ስንቶቻችን ነን ሊደገፉ የማይገባቸውን ድርጅቶችና የፖለቲካ መሪዎች አገራዊና ህዝባዊ ከሆነ ጉዳይ ምክንያት ውጭ በጭፍን በመደገፍ የጥፋት ስራ የሚሰሩበት እድሜያቸውን እየቀጠልንላቸው ያለነው? ለዚህ ደግሞ እያመንን ተከዳን ብቻ እያልን ማማረር ሳይሆን ሁሉም ይህንን የእምነት ክህደት አዙሪት ለመስበር ምን ሰርቻለሁ የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡

ስለዚህ አሁን ሁላችንም የህወሃትን የጥላቻና ንቀት ፖለቲካ በመስበር፤ ለአገዛዙ የአንድ ቀን የስልጣን እድሜ መስጠት የኢትዮጵያውያን ውርደት ማስቀጠል መሆኑን በማወቅ ለራሱ ክብር የሚሰጥ እና በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራው ዜጋ ሁለ በያለበት ኢትዮጵያችንን ከጥፋት ቡድኖች ለመታደግ ሊንሳ ይገባል። ህወሃት የሃገራችንን ውበቷን፣ ክብሯን እና ግርማዋን ከማንም በላይ አዋርዷዋል፡፡ የዜጎቿም መታወቂያ እስር እና ስደት ሆኗል። ደምና አጥንት ቆጥሮ ተደራጅቶ ደምና አጥንት እየቆጠረ ዜጎችን የሚያዋርድ እና የሚያሰቃይ ዘረኛ ቡድን በኢትዮጵያችን ራስ ላይ ተቀምጦ እያየን እስከ መቼ ዝም ብለን በባርነት እንገዛለን። የስልጣን ህልውናውን ለማርዘም እንዲረዳው አስጠያፊ ዘረኝነትንና ጎሰኝነትን በኢትጵያ ላይ የዘረጋውን የህወሃት ዘረኛና ጠባብ ቡድን ከአገራችንና ከህዝባችን ጫንቃ ለማውረድ በያለንበት ተደራጅተን ልንፋለመውይገባል። ኢትዮጵያ የእኔም ሃገር ነች ማለት መጀመር አለብን፡፡ በዘረኝነት በሽታ የናወዙት የህወሃት ሹማምንት አገሪቷን እንደፈለጉ ሲያደርጓት ዕያዩ ዝም ማለት አገር እና ክብርን ከማሳጣት በተጨማሪ ለጥፋቱ ተባባሪ በመሆን ከመጠየቅ አያድንም።

ዛሬ ኢትዮጵያችን ከጥፋት የሚታደጓት ከደም እና ከአጥንት ልቆ ማሰብ የሚችሉ ዜጎቿን ከምንጊዜውም በላይ ትፈልጋለች። አሁንም አገራችን ለፍትህ፣ ለእኩልነት እና ነፃነት ዘብ መቆም የሚችሉ ዜጎቿን አድኑኝ ስትል ትጣራለች። ለሚመጣው ትውልድ ጥቂቶች ብዙሃኑን ተጭነው፤ ብዙሃንም ጥቂቶችን ተሸክመው መከራቸው በዝቶ የሚኖሩበት አገር ትተንላቸው እናልፍ ዘንድ ፈጽሞ አይገባም። በኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሆኑና የዘረኛው ቡድን ግፍና በደል ያንገፈገፋቸውና እያንገፈገፋቸው ያሉ የሰራዊቱ አባላት ከታሪክ ተወቃሽነት ለመዳንና የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት መነሳትና አገር አድኑን የነፃነት ትግል መቀላቀል ያለባቸው ጊዜም ዛሬ ነው። በተጨማሪም ጥቂት ዘረኞችና ዘራፉዎች አገሪቷን እንደፈለጉ ሲቀራመቱ እያየን እኔ ምን አገባኝ የሚባልበት ጊዜ ላይ እንዳልሆንን ሁሉም ዜጋ ሊገነዘብ ይገባል።

ስለዚህም ከአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፤ ከእምነት ማካሄጃ ስፍራዎች እስከ የአገዛዙ መስሪያ ቤቶች፤ ከአርሶ አደሩ መንደር እስከ ምሁራኑ ሰፈር፤ ከአገር ቤት እስከ ውጭ ሃገረት ያለው ዜጋ ሁሉ የሕወሓት አገዛዝን በማስወገድ አገሩንና ህዝቡን ከጥፋት ለመታደግ በያለበት የነፃነት ትግሉን ልንቀላቀል ይገባል ስል ወገናዊ ጥሪየን አቀርባለሁ።

ድል የህዝብ ነው!



No comments:

Post a Comment