በመሃመድ አሊ
በግንቦት 1983 በኢትዮዽያ አቆአጣጠር ሕ.ወ.ሀ.ት መራሹ ጦር የመንግስት ወንበር ከተቆጣጠረ በኋላ ግዜዉ የሚያሥገድደዉንና በምዕራባያዉያንም ተፅእኖ ጭምር አዲሥ ሊባል የሚችል ሕገመንግስት ማርቀቁ ይታወሳል፡፡
በ1985 የፀደቀዉ የኢትዮዽያ ሕገመንግስት ቀድሞ ከነበሩት የደርግና የዘዉዳዊ መንግስት በብዙ መልኩ እንደሚሻል በሃገር ዉስጥም በዉጭ መንግስትም ችሮታ ተለግሶት ነበር፡፡ ሆኖም የበግ ለምድ የለበሰዉ ተኩላ ባሕሪዉ የመንግስት ስልጣንን ላለመልቀቅ ራሱ ያፀደቀዉን ሕገመንግስት በየግዜው እየሸረሸለዉ ይገናል፡፡ ከቶም እየናደዉ ካሉት ሕጎች መካከል የዜጐች የመናገር፣ የመፃፍና የመደራጀት መብት ዛሬ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ተሸርሽፘል፡፡
በ1997 በዜጎች የመደራጅት መብት ተጠቅመዉ ሕብረብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ መብትን በተግባር ለማዋል ተቀናጀተዉ የነበሩ ፓርቲዎች በሐገሪቱ ሕዝብ ንቃተ ሕሊና ማዳበራቸዉ ስልጣን ላይ የተቀመጠዉን የወያኔ መንግስት አስደምብሮት አዉሬያዊ ባሐሪዉ እንዲገነፍል አድርጐታል፡፡በወቅቱ ተከስቶ የነበረዉ አዲስ የዴሞከራሲ ጅምር ሕብረተሰቡ መቅመሱ በሰዉ ልጅ ላይ ድርድር አለመኖሩን አሳይቶ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ነገሮች ሁሉ መገልበጣቸዉ በይፋ መታየት ጀመፘል፡፡
ዛሬ ኢትዮዽያዊ በሐገሩ የዜግነት መብት በነፃነት የመናገር ፣የመፃፍም ሆነ መደራጀቱ በጥርጣሬ እንዲታይና ወህኒ ማደርያዉ እንዲሆን እያስደረገዉ ይገኛል፡፡ ሐገራችን የዜጐች መብት የተጨፈለቀበት በመሆኑ ሰዉ እርስ በርሱ መተማመን እያቃተዉ በጥርጣሬና በመፈራራት እየኖረ ገዢዉ ፓርቲ አንባገነንነቱን ከመቼዉም ግዜ በላይ በማናር አንዱን ከሌላናዉ ጋር በማጋጨት ዜጐች ተግባብተዉ እንዳይኖሩ እያደረገ ይገኛል፡፡በኢትዮዽያ እስር ቤቶች ከጋዜጣና መፅሔት ስራ ጋር የተገናኙ አዘጋጆች፣ ሪፖርተሮች፣ የጋዜጣና መፅሔት ባለቤቶች ስለ ነፃነት በመፃፋቸዉ ብቻ የመከራ ግፋትን እንዲቀምሱ ተደርጋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በ1997 በብዛት ይታዩ የነበሩ ጋዜጣና መፅሔቶች ዛሬ ለዐይን አይታዩም፡፡በከተማዋ በመንግስት የሚደጐሙ ጥቂት የፓርቲ ልሳን የሆኑ ነፃ መሰል ጋዜጦች እንጂ አንድም ነፃ ፕሬስ አይገኝም፡፡ እስከ ቅርብ አመት ስለ ነፃነትና ስለ ዜጐች መብት ሲዘምሩ የነበሩ ጋዜጦች ወይ ከሐገር ተሰደዋል አልያም እጅና እገሮቻቸዉ ተጠፍሮ ወህኒ ገብተዋል፡፡እስር ላይ ከሚገኙ ዜጎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት የዜጐች መብት ላይ ጥያቄ የሚያቀርቡ የነቁና የተማሩ ኢትዮዽያዊያን ናቸዉ፡፡ በመንግሰት ወንበር ላይ ከተቀመጡት ባለሥልጣናት በላይ በኢትዮዽያ እስር ቤቶች ሐገሪታን መምራት የሚችሉ የነቁ ሙሑራን ወህኒ ታጉረዋል፡፡
በኢትዮዽያ በአሁኑ ግዜ በየትኛዉም የዜጎች መብት ላይ በነፃነት ሚናገሩ ዜጎችን ማግኘት አይቻልም፡፡ ከአምስት በላይ ሰዎች አንድ ቦታ ላይ ተሰብስበዉ መነጋገር ካለባቸዉ ለመንግስት ማሳወቅ እንዳለባቸዉ ይፋ ባልሆነ መንገድ እየተገለፀ ይገኛል፡፡ በቅርቡ አንድ ጋደኛዬ በትምህርት ጉዳዮች ላይ ባዘጋጅዉ አጫጭር ዉይይቶች በተደጋጋሚ ከደህንነቶች ማስፍራሪያና ዛቻ ገጥመዉታል፡፡
በሐገራችን ዉስጥ መብት ላይ የሚፅፉ ሰዎች ስልካቸዉ ሊጠለፍ፣የግል ምስጢር ሳጥኖቻቸዉ ሊሰበሩ፣ የፌስቡክና የዌብ ሳይት አድራሻቸዉ መንግስት ባቃቃመዉ INSA በተባለ ድርጅት ሊሰበር ይችላል፡፡ በ24 አመታት የአገዛዝ ዘመን ወያኔ የባለስልጣናትን ኪስ ከማደለብና ንቅዘትን በሰፊዉ ከመዘርጋት ውጭ የሚታዩ ተጨባጭ ለዉጥ ሰዎች ላይ አይታይም፡፡ ሐገሪቱ እያስመዘገበች ነዉ ሚባለዉ እድገት በዜጎች ሕይወት ላይ ለዉጥ አላመጣም፡፡ መብትን የጣሰ እድገት ከቶም ሊኖር አይችልም፡፡
በአጭሩ ኢትዮዽያ ዉስጥ የዜጎች መብት ከላይ የተጠቀሰዉን ይመስላል ፡፡ለአብነት ያክል የታዩትን ነገሮችን ማስተዋል ለቻለ ሰዉ ዜጎች እንዴት ያለ በግፍ ስርዐት ዉስጥ ህይወታቸዉን እየገፉ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህንን ለዉጥ ለማምጣት ሁሉም ሊረባረብና አለምአቀፍ ጫና እንዲኖር ሀያላን መንግስቶች፣ ለዜጎች መብት ዴሞክራሲ መከበር የሚጮሁ ሁላን ኢትዮዽያ ዉስጥ የዜጎችን መብት ለሚደፈጥጥዉ የወያኔ አፋኝ ሥርዐት የብድርና የመሳሰሉትን ድጋፍ እንዲያቆሙና ሥርዐቱ እንዲወገድ ሁላችንም ልንረባረብ ይግባል እያልኩ ፅሁፌን በዚሁ አበቃለዉ፡፡
No comments:
Post a Comment