የምርጫ ማኒፌስቶም ሀገራችን አሁን ካለችበት የኢህአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሚደረግ ሽግግር ወቅት በሀገራችን ሰማያዊ ፓርቲ በምርጫ ተወዳድሮ ማሸነፍ ቢችል የሚያከናውናቸውን ተግባራት በዝርዝር የሚተነትን ነው፡፡ ይህ የምርጫ ማኒፌስቶ በዋናነት በሦስት ምዕራፍ የተከፈለ ሲሆን የመጀመሪያው የፖለቲካ ሥርዓቱ አደረጃጀት ምን መምሰል እንዳለበት የሚገልፅ ክፍል ነው፡፡ በዚህ ምዕራፍ ሰማያዊ ፓርቲ ባለፉት 24 ዓመታት የህወሀት/ኢህአዴግ መራሹ ሥርዓት በሀገራችን ላይ የፈፀማቸውን የፖሊሲ ሰህተቶች በዝርዝር የሚያስቃኝ ሲሆን፤ በአንፃሩም ፓርቲው በሥልጣን ላይ ቢቀመጥ በዋነኛነት በቋንቋ ላይ የተመሰረተውን የፌደራል ሥርዓት በመቀየር መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥን፣ የሕዝብ አሰፋፈርን፣ ልማትና ሌሎች ማህበራዊ ትስስሮችን መሰረት ያደረገ ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር አማራጩን የሚያሳይበት ሲሆን፤ የመንግሥት አወቃቀሩ፣ የነፃ-ፕሬስ፣ መከላከያ ፖሊስና ደህንነት አደረጃጀቱ እንዲሁም የውጭ ግንኙነት አማራጭ ፓሊሲው በዝርዝር የሚዳሰሱበት ከፍል ነው፡፡
በሁለተኛዉ ምዕራፍ የማህበራዊ ሥርዓቱን በተመለከተ የተዘረዘሩ ነጥቦችን የያዘ ሲሆን ህወሃት /ኢህአዴግ የሀገራችን ሕዝብ ማህበራዊ ዕድገት ላይ ያስከተለውን ሁለንተናዊ ቀውሰ በማስቃኘት፤ በሰማያዊ ፓርቲ የማህበራዊ ጉዳይ መሰረታዊ ፍልስፍና መሰረት ጤነኛና በእውቀት ላይ የተመሠረተ በራሱ የሚተማመን ዜጋን ለመፍጠር ዋነኛ ምሰሶ ተደርጎ በሚቆጠረው ትምህርትና ጤና ላይ ያለውን ፖሊሲ በመዳሰስ፤ አረጋውያንና በተፈጥሮና በአደጋ የአካልና የአዕምሮ ጉዳት የደረሰባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በተመለከተ የፓርቲውን እይታ ይተነትናል፡፡ በተጨማሪም ሃይማኖት፣ ባህል፣ ኪነ-ጥበብ፣ ስፖርት እና ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚገነዘብበት ድርጅታዊ እይታዎች ያስቃኛል፡፡
በመጨረሻም በዚህ ማኒፌስቶ በጥልቀት የተገለፀው የፓርቲውን የኢኮኖሚ አማራጭ የሚያሣየው ምዕራፍ ነው፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የህወሃት/ኢህአዴግ ሥርዓት እከተለዋለሁ የሚለውን ገጠርን ማዕከል ያደረገ ግብርና መር የኢንዱስትሪ ልማት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በማስቀደም ልማት የሀገሪቱ መሠረታዊ ጥያቄ ስለሆነ በሚል ለኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲ ቅንጦት እንደሆነ በመቁጠር ’’ሁሉ ነገራችንን ለልማት’’ በሚል ሰበብ በሀገራችን ኢኮኖሚ ለውጥና ዕድገት ላይ የፈጠረውን ደንቃራ በጥልቀት ይመረምራል፣ ትችቱንም ያቀርባል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰማያዊ ፓርቲ በሕዝብ ተመርጦ የመንግሥትነትን ሥልጣን ቢይዝ፤ በሀገሪቱ ውስጥ ሊያሰፍን የሚሻውን የኢኮኖሚ መርህም ያሳያል፡፡ በዚህም መሠረት ሰማያዊ በሀገራችን ተግባራዊ ለማድረግ ያቀዳቸዉን የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማራጮች በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን በዋነኝነትም የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ በተመለከተ አርሶ አደሩን የመሬቱ ባለቤት የሚሆንበትን መብት ማረጋገጥ፤ እንዲሁም ሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች የትኩረት አቅጣጫ ገበያ መር ሆኖ ዜጎች በፈለጉት ሙያ እና የሥራ መስክ ተሰማርተው፣ ሀብት የማፍራት፣ በሕጋዊ መንገድ የንብረት ባለቤት የሚሆኑበት በተጨማሪም በሀገሪቱ በሁሉምአቅጣጫዎች ተሰማርተው የሚሠሩበትን መብት የሚያረጋግጥ እንዲሆን የሚረዳ የፖሊሲ አማራጩን አስቀምጧል፡፡
ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ
No comments:
Post a Comment