Sunday, March 1, 2015

አድዋ!


ዋ! አድዋ ፤ ያ ሑዳዴ
መድፍን ፈንጅን ፤ በጎራዴ
ባሕር ተሻግሮ ፤ የሐበሻን ምድር
ቅኝ ሊገዛ ፤ ይሄ ደፋር!
አንች አድዋ ፤ የበኩር ልጅ
ላንቺ ውልደት ፤ ስንቱ ሲፈጅ
ተጸንሰሽ ፤ ከውጫሌ
ለደም መሬት ፤ ለአሞሌ
እርግዝናሽ ፤ ዘጠኝ ወሩ
ዓመታትን ፤ ማስቆጠሩ
ክፉውን ቀን ፤ ይዞ አሳሩ
ከብቱ እረግፎ ፤ ባገር ምድሩ
ሰው ሁሉ አልቆ ፤ በችጋሩ
በፋሽስት ሸር ፤ በእኩይ ግብሩ
ከብት የሚፈጅ ፤ ደዌ ረጭቶ
በምን ታርሶ ፣ በምን ለምቶ
የገበሬው ፤ ሀብት ጠፍቶ
አከርካሪው ፤ ተመትቶ
የሚቀመስ ፤ እህል ታጥቶ
ረሀቡ ፤ ሕዝቡን በልቶ
ምኑ ተብሎ ፤ ስንቱን ነግሮ
የግፍ ግፉ ፤ ተዘርዝሮ
ዝም ይሻላል ፤ ምን ተቆጥሮ
በክፉው ቀን ፤ ራብ ደክሞ
ያለቀ ሕዝብ ፤ በአዋጅ ተሞ
በዚያ ድቀት ፤ ተጎድቶ
አፈር ልሶ ፤ ግድ ተነሥቶ
አይቀር ነገር ፤ የሀገር ጥሪ
ነፍሱ የሷ ፤ እሱ አኗሪ
ጉልበት ሆኖት ፤ የሀገር ፍቅሩ
አስቆጥቶት ፤ መደፈሩ
ገሰገሰ ፤ ወደ አድዋ
ጠላት ሊግት ፤ የሞት ጽዋ
አድዋ ላይ ፤ ከግንባሩ
ሊሞሻለቅ ፤ ሲተም ጦሩ
እንደ ሙላት ፤ ደራሹ ጎርፍ
ሲያስገመግም ፤ ጠላት ሊቀስፍ
ከተፍ ሲል ፤ ፊት ለፊቱ
ጥሊያን ራደ ፤ ልብ አጥቶ
ባለ የሌለ ፤ መሣሪያ አጉል
እያስጓራ ፤ ሲከላከል
በመድፍ አረር ፤ በመትረየስ
ግማሽ ሲቀር ፤ ሲሠዋ ነፍስ
ጠጋ ሲባል ፤ ወደ ምሽግ
ሌላ አሳር ፤ ምን ይደረግ?
በስል ችንካር ፤ በውጋቱ
በጠርሙስ ጦር ፤ በስለቱ
ምሽግ ማዶ ፤ በተከለው
አርበኛውን ፤ እንዲያስቀረው
ጠርሙስ አልፎ ፤ የፈንጅ ንጣፍ
ፋኖ የሚፈጅ ፤ በነፍስ ወከፍ
ያ ባዶ እግር ፤ ቢቀረደድ
ቢሸረከት ፤ ቢጎራረድ
ማን ተሰምቶት ፤ ለማን ታውቆ?
በፈንጅውም ፤ ረግፎ አልቆ

ሊነሣ ይሻል ፤ ሞቶም ወድቆ
በወደቀው ፤ ተረማምዶ
ምሽግ ሰብሮ ፤ ጥሶ ንዶ
በጠላት ላይ ፤ ማት አውርዶ
ቆርጦ ሲጥል ፤ አንገት ጎርዶ
በፉከራ ፤ ቀልቶ አጭዶ
ሲፈጅ ሲማርክ ፤ ቆልቶ አሳዶ
ብቻ በሀገር ፤ በሕዝብ ፍቅር
በሚፋጀው ፤ እንደ ገሞር፡፡
አንች የረፋድ ፤ የድል ፀሐይ
የወጣሽው ፤ አድዋ ላይ
ከአባትሽ ፤ ከምኒልክ
ድባቅ መትቶ ፤ ካገባው ልክ
ከጣይቱ ፤ ከእናት ኩሩ
ፋኖዎቹ ፤ እያጋፈሩ
አድዋ ላይ ፤ ከአፈሩ
በቅዱሱ ፤ ጊዮርጊስ ለት
ተራድቶሽ ፤ ተርፈሽ ከሞት
ሰዓቱ ሲደርስ ፤ መወለጃሽ
በጭንቅ ምጥ ፤ የተወለድሽ
በሰው አጥንት ፤ በሰው ልጅ ደም
የታረስሽው ፤ የዓለም ሰላም
የሐበሻ ዘውድ ፤ የድል ማማ
በአጥንት ዕዳ ፤ በደም ጉማ
ምታስከፍይ ፤ ቃል ሲሰማ
ያችን ገልቱ ፤ ከንቱ ሮማ፡፡
አድዋ ቅኔ ፤ አድዋ ዜማ
የምትማርክ ፤ ምትስማማ
ለሰው ልጅ ልብ ፤ ያላት ግርማ
የአውሬን ልብ ፤ ምታደማ
በአፍታ ፍልሚያ ፤ ፈጣን ሽኝት
ወዲያው ብልት ፤ እዚያው ጥጥት
በአርበኛ ወግ ፤ በፋኖ ደንብ
ሳይገመት ፤ ሳይታሰብ፡፡
ነጭ በጥቁር ፤ በግፍ ገኖ
በጨካኝ ክንድ ፤ ይዞ አፍኖ
ጥቁሩ ሲኖር ፤ ተኮንኖ
መገልገያ ፤ ዕቃ ሆኖ
አሜን ወዴት ፤ አለሁ ብሎ
አንገት ሰብሮ ፤ ተገልሎ
በምድሪቱ ፤ በመላ ዓለም
በግፍ ሲኖር ፤ አጥቶ ሰላም
ለነጭ ተድላ ፤ ጥሮ ማስኖ
እሱ እንደሚያንስ ፤ ከልቡ አምኖ
ቅስም ሐሞቱ ፤ ነኩቶ ፈሶ
መራር ሐዘን ፤ ልቡ ውስጥ ነግሦ
ሲኖር ዘወትር ፤ ቀንበር አዝሎ
አድዋ ላይ ፤ የድሉ አውሎ
አሽቀንጥሮ ፤ ሸክሙን ጥሎ
ነጩን እባብ ፤ ላይድን ገሎ
አነሣለት ፤ ከስር ነቅሎ
አስበርግጎ ፤ አስደንብሮ
ፈነቃቅሎ ፤ ጥልቅ ሰርስሮ፡፡
እናም ዓለም ፤ ተገደደ
ውዳቂ ሐሳብ ፤ በግድ ካደ
አዲስ ታሪክ ፤ ተሰነደ
የተጠላው ፤ ተወደደ
ሰው መሆኑን ፤ የአዳም ዘር
ከነጭ ቢጫ ፤ ከቀይ ፍጡር
እንደማያንስ ፤ ምን ቢጠቁር
አረጋግጦ ፤ ቆመ በክብር
እድሜ ለዚያች ፤ የድል ፀሐይ
ለበራችው ፤ አድዋ ላይ
የባርነት ፤ ሰንሰለቱን
በጣጠሰ ፤ እግር ብረቱን
ተቀዳጀ ፤ ነጻነቱን
ቀበረለት ፤ ባርነቱን
የሀገሩ ፤ የመብቱ
ራሱ ሆነ ፤ ባለቤቱ
ዕድሜ ለዚያች ፤ የድል ፀሐይ
ለበራችው ፤ አድዋ ላይ
የምዕት ዓመታት ፤ ጣር ጨለማ
ተወገደ ፤ ድል ተሰማ
ያች ፀሐይ ፤ የድል ጮራ
ደማቅ ጸዳል ፤ የገድል አውራ
የከበረች ፤ ስጦታ ናት
ምንም ነገር ፤ የማይተካት
ከሐበሻ ሕዝብ ፤ ለጥቁር ዘር
ለተገፋው ፤ ለበላ አሳር፡፡

የካቲት 19 2007ዓ.ም.
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

No comments:

Post a Comment